ጢሞቴዎስና አፍሮዲጡ፣ ወደር የማይገኝለት ጥንድ (ፊልጵስዩስ 2፡19-30) 

በሳን በርናዲኖ ካሊፎርኒያ ውስጥ፥ አንድ ጋዜጠኛ ተዘዋዋሪ በሚበዛበት መንገድ አጠገብ ከሚገኝ ቦይ ውስጥ አንዱን ሰው ሕመምተኛ አስመስሉ እንዲተኛ አደረገ። ታዲያ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በአጠገቡ ይለፉ እንጂ፥ አንዳቸውም ቆመው ሊረዱት ይቅርና የሐዘን ፊት እንኳን አላሳዩትም ነበር። 

ከጥቂት ዓመታት በፊት ጋዜጦች አንድ ከዳር እስከዳር የተናኘ ዜና አውጥተው ነበር። ይኸውም አንድ ሰው እያደባ ሴትየዋን ሲቀርባትም ሆነ በመጨረሻም በጩቤ ሲወጋት ሠላሳ ስምንት ተመልካቾች ቢያዩም አንዳቸውም ፖሊስ ለመጥራት ስልክ አለመደወላቸውን የሚገልጽ ነበር። 

እንደዚሁም ሁለት ወጣቶች በዲትሮይት ውስጥ ሲሄዱ በስልክ መደወያ ጎጆ ውስጥ አንዲት ሴት በልብ ድካም በሽታ ስትሰቃይ ያገኙአታል። እነርሱም ቅርብ ወደሆነው ቤት ተሸክመዋት በመሄድ፥ ባለቤቱ በሩን ሲከፍትላቸው እርዳታ ጠየቁ። ያገኙት መልስ ግን «ከበረንዳዬ ላይ ዘወር በሉ – እርሷንም የምታደርሱበት አድርሷት» የሚል ነበር። 

አንድ የከንታኪ ሐኪም በሽተኛውን ለመጠየቅ በመኪና በመጓዝ ላይ እንዳለ አንድ አደጋ ሲደርስ አየ። ቆመና ለተጎዳው ሰው እርዳታ ካደረገለት በኋላ ወደ በሽተኛው ቤት አመራ። ሆኖም ያ የረዳው ሰው ከጥቂት ቀናት በኋላ ክስ አቀረበበት። 

ታዲያ በዛሬው ጊዜ «መልካሙን ሳምራዊ» መሆን ይቻላል? እያንዳንዱስ ሰው ራሱን ለመጠበቅ ሲል ልቡን ማደንደን አለበት ማለት ነው? ምናልባት «መሥዋዕትና አገልግሉት» ጥንታዊ ልማድ ስለሆኑ እኛ ዘመናዊ ሥልጣኔ ብለን ከምንጠራው ጋር ሊስማሙ አይችሉም ይሆናል። እንዳውም እርስ በእርስ መረዳዳት በጳውሎስ ጊዜ እንኳን ያልተለመደ ለመሆኑ አያጠያይቅም። በሮም ያሉ ክርስቲያኖች በፊልጵስዩስ ስላለው ችግር ግድ የላቸውም ነበር። ጳውሎስ ወደ ፊልጵስዩስ ፈቃደኛ ሆኖ የሚሄድለት አንድም ሰው አላገኘም (2፡19-21)። ጊዜው ብዙም አልተለዋወጠም ማለት ነው። 

ጳውሎስ በዚህም አንቀጽ፥ አሁንም ቢሆን ስለ ትሑት አእምሮ እያስረዳን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በማድረግ ለትሑት አእምሮ መግለጫ ሰጥቶናል (2፡1-11)። ከእራሱ ልምምድ በመነሣት የትሑት አእምሮ እንዴት እንደሚሠራ ቀደም ሲል ያሳየን ነው (2፡ 12-18)። አሁን በአገልግሎቱ ጊዜ ከረዱት ሰዎች መሀል ሁለቱን ያስተዋውቀናል፣ ጢሞቴዎስንና አፍሮዲጡን፣ እና ይህንንም ያደረገው ያለ ምክንያት አልነበረም። በእርግጥ አንባቢዎቹ የሚከተለውን ምክንያት እንደሚያቀርቡ ያውቃል፥ «እኛ እንደ ክርስቶስና እንደ ጳውሎስ ይህን መሰሉቹን ምሳሌዎች ለመከተል አይቻለንም። መቼም ኢየሱስም የእግዚአብሔር አንድያ ልጁ ነው ጳውሎስም የተመረጠ ሐዋርያ፥ ትልቅ መንፈሳዊ ልምምድ ያለው ነው! » ሲሉ ምክንያት ይሰጣሉ። ከዚህም የተነሣ ነው ጳውሎስ ሐዋርያ ወይም በጣም የሚያስደንቅ ተአምር የሚሠሩትን ሳይሆን ሁለቱን «ተራ ቅዱሳን» የሚያስተዋውቀን። እንድናውቅ የሚፈልገውም ትሑት አእምሮን ጥቂት የተመረጡ ሰዎች ብቻ የሚታደሉት ስጦታ አለመሆኑን ነው። ይህ ስጦታ ማንኛውም ክርስቲያን ደስታን ያገኝ ዘንድ የሚያስፈልገው ነው። በመሆኑም ዕድሉ ለሁሉም አማኞች ተሰጥቷቸዋል። 

  1. ጢሞቴዎስ (2፡19-24) 

ጳውሎስ በመጀመሪያ የወንጌል አገልግሎት ጉዞው ላይ ጢሞቴዎስን በድንገት አገኘው (ሐዋ. 16፡6 ጀምሮ)፥ ምናልባትም በዚያን ጊዜ ወጣቱ ተለውጦ ሊሆን ይችላል (1ኛ ቆሮ. 4፡17)። በመጀመሪያም ክርስትናን የተቀበሉት የጢሞቴዎስ እናትና አያት ነበሩ (2ኛ ጢሞ. 1፡3-5)። እርሱም በእናቱ የአይሁድ በአባቱም የአሕዛብ ልጅ ነበር፥ ነገር ግን ጳውሎስ ሁልጊዜ በእምነት የራሱ «የተወደደ ልጅ» አድርጎ ይቆጥረዋል (2ኛ ጢሞ. 1፡2)። ወጣቱ ጢሞቴዎስ የጳውሎስ ረዳት መሆን የጀመረው ጳውሎስ ወደ ልስጥራንና ደርቤን ለሁለተኛው ጊዜ በተመለሰበት ወቅት ነው(የሐዋ. 16፡1-4)። በአንድ በኩል፥ ጢሞቴዎስ በኋላ ማርቆስ በመባል የሚታወቀውን ዮሐንስን ተክቷል። ይኸውም ጳውሎስ በዚህ በጉዞው ላይ ማርቆስን ይዞ ለመሄድ ባለመፈለጉ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ማርቆስ ከዚህ ቀደም ሲል ኃላፊነቱን ለመሸከም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው (ሐዋ. 13፡13፤15፡36-41)። 

ከዚህ ከጢሞቴዎስ ልምምድ ውስጥ የምንማረው ትሑት አእምሮ በአንድ አማኝ ሕይወት ውስጥ ከመቅፅበት የሚታይ ወይንም ትኩረት ሳንሰጠው የሚከሰት ነገር አለመሆኑን ነው። ጢሞቴዎስ ለማደግና ለመጎልበት «የክርስቶስን አሳብ» ያዘ። አገልጋይ መሆን የተፈጥሮው አልነበረም። ነገር ግን የጌታን ፈለግ በመከተሉና ከጳውሎስ ጋር በቅርብ በመሥራቱ፥ ጳውሎስ የሚተማመንበትና እግዚአብሔር የሚባርከው ዓይነት አገልጋይ ለመሆን በቃ። የዚህን ወጣት ሰው ባሕርይ ተመልከት።

እርሱ የማገልገል አሳብ ነበረው (2፡19-21) 

መጀመሪያ ነገር፥ ጢሞቴዎስ በተፈጥሮው ለሰዎች ጥንቃቄ የሚያደርግ ስለሚያስፈልጋቸውም ነገር የሚጨነቅ ነበር። እርሱ «ጓደኞቹን በማሸነፍና ሰዎችን በመጫን» አይደሰትም ነበር፤ እርሱ ከልቡ የሚደሰተው በሚያገለግላቸው ሰዎች አካላዊና መንፈሳዊ ደኅንነት ነበር። ጳውሎስ ስለፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ጭንቀት አድሮበት ነበር። በመሆኑም ጭንቀቱን የሚገልጽለትና በዚያም የሚያየውን ሁሉ ሳይደብቅ የሚነግረው አንድ ሰው መላክ ፈልጎ ነበር። በሮም ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ነበሩ (በሮሜ ከተማ ውስጥ ጳውሎስ ለ26ቱ በስማቸው ሰላምታ አቅርቧል)፤ ሆኖም አንዳቸውም ይህንን ጉዞ ለማድረግ ፈቃደኞች አልነበሩም። «ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም» (ፊልጵ. 2፡21)። ከዚህ የምንረዳው ሁላችንም ብንሆን በፊልጵ. 1፡21 ወይም በፊልጵ. 2፡21 ውስጥ መኖራችንን ነው! 

ነገር ግን ጢሞቴዎስ በተፈጥሮው ለሌሎች በጎ ለማድረግ የሚጨነቅ ነበር። ስለዚህ የአገልጋይ አሳብ ያለው ሰው ነበር። በሮም ውስጥ ያሉ አማኞች ግን በራሳቸው ጉዳይ ብቻ የተጠመዱና በውስጣዊ ጭቅጭቃቸው የተያዙ በመሆናቸው (1፡15-16) ለዚህ ዓይነቱ ጠቃሚ ለሆነው የጌታ አገልግሉት ጊዜ አልነበራቸውም። በአሁኑም ጊዜ ቢሆን የቤተ ክርስቲያን ዓቢዩ ችግር አባሎቹ ጊዜያቸውንና ኃይላቸውን አላስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ማዋላቸው ነው። ጢሞቴዎስ አንዱን ወገን የማጠናከር ወይም ሌላውን የመከፋፈል ፍላጎትም ምኞትም አልነበረውም። እርሱ በእግዚአብሔር ሰዎች መንፈሳዊ ሁኔታ ብቻ ደስተኛ ነበር። ይህም በተፈጥሮው የተቀዳጀው ጸጋ ነበር። ሆኖም ይህ ጸጋ እንዴት ነው ሊበለፅግና ለሌሎችም አገልግሎት ሊውል የሚችለው? መልሱን በሚቀጥለው በወጣቱ ሰው ባሕርይ ውስጥ እናገኛለን። 

ሌሎችን ለማገልገል የሠለጠነ ነበረ (2፡22) 

ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ክርስቶስን እንደተቀበለ ወዲያውኑ የ«ቡድኑ» አባል አላደረገውም። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱን ስህተት ላለመፈጸም የሚጠነቀቅ ሰው ነበር። መጀመሪያ ላይ በልስጥራንና ደርቤን ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ተራ አባል በመሆን እንዲያገለግል ትቶት ሄደ። ከዚያም በዚያ ኅብረት በመንፈሳዊ ነገሮች አደገ፥ ጌታንም እንዴት እንደሚያገለግል ተማረ። ጳውሎስ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ወደዚያ አካባቢ ሲመለስ ስለ ወጣቱ ጢሞቴዎስ «ወንድሞች ሲመሰክሩለት» በመስማቱ ደስ አለው (ሐዋ. 16፡2)። ጳውሎስም ከዓመታት በኋላ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት፥ አዲስ የተለወጠ ሰው ለአገልግሎት ብቁ ከመሆኑ በፊት ማደግና መሠልጠን እንደሚያሻው ገልጦለታል (1ኛ ጢሞ. 3፡6-7)። 

አንድ ታዋቂ የምሽት ክበብ ተጫዋች ወደ አንድ መጋቢ በመሄድ መዳኑንና ጌታን ለማገልገል መፈለጉን አስታወቀው «ከዚህ ቀጥዩ ምን ማድረግ ይገባኛል?» በማለትም ጠየቀው። 

«እኔ የማሳስብህ፥ ከአንድ ጥሩ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተገናኝተህ ማደግ እንድትጀምር ነው» ብሉ መጋቢው ከመለሰለት በኋላ፥ ከዚያም «ሚስትህ ክርስቲያን ናት?» ሲል ጠየቀው። 

«አይደለችም» አለ ሙዚቀኛው፥ «ሆኖም በእኔ አማካይነት እንደምትለወጥ ተስፋ አደርጋለሁ» ካለ በኋላ «ግን እኮ እርሷ ለመለወጥ እፈልጋለሁ እስከምትለኝ መጠበቅ የለብኝም! ማለቴ አሁኑኑ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ» አለ። 

«አዎን፤ ስለ ጌታ ለመመስከር መጠበቅ አያስፈልግህም። የቤተ ክርስቲያን አባል በመሆን ተሰጥዖህን ለክርስቶስ ተጠቀምበት» ሲል መከረው። 

«ነገር ግን እኔን አላወቅከኝም» ብሉ ሙዚቀኛው ተቃወመ፥ «እኔ እኮ ሁሉም ሰው የሚያውቀኝ ትልቅ ተጫዋች ነኝ። የራሴ የሆነም ድርጅት መጀመር እፈልጋለሁ የሙዚቃ ሸክላዎችን ማሳተም፥ በብዙ ሕዝብ መሀልም መታየት እፈልጋለሁ»። 

መጋቢው በማስጠንቀቅ፥ «በጣም በርቀትና በፍጥነት ከሄድክ እራስህንና ምስክርነትህን ልትጎዳ ትችላለህ። ሰዎችን መማረክ የሚጀመርበት ቦታ ከቤት ውስጥ ነው። እግዚአብሔር የአገልግሎትን ቦታ የሚከፍትልህ እንደተዘጋጀህ ሲያይ ነው። እስከዚያው ድረስ መጽሓፍ ቅዱስህን አጥና፥ እራስህን ለማሳደግ ዕድል ስጠው» አለው። 

ሰውየው የመጋቢውን ምክር አልተቀበለም። በእርሱ ምትክ ግን የራሱ የሆነ ድርጅት ከፍቶ በራሱ ኃይል ለማደግ ጀመረ። ሆኖም ሥራው «የተሳካለት። ከዓመት ላነሰ ጊዜ ብቻ ነበር። ከባዱን ኃላፊነቱን ለመወጣት በቂ ጥንካሬ ስላልነበረው ምስክርነቱን ብቻ ሳይሆን፥ በማያቋርጥ ጉዞው የተነሣም ከሚስቱና ከቤተሰቡ ጋር እንደ ባዕድ መተያየት ጀመረ። ከዚያም እንግዳ ከሆነ ቡድን ጋር በመግጠሙ ከሕዝባዊ አገልግሎቱ ላይ ተሰወረ፥ በመጨረሻም የተበላሸና የከሰረ ሰው ሆነ። 

መጋቢውም ሰለ ሰውየው ሁኔታ ሲተች «የጠለቀ ሥር በመስደድ ምትክ፥ ቅርንጫፎቹን ለማንሰራፋት የፈለገ ሰው ነበር። ይህን የሚያደርግ ሰው መጨረሻው ውድቀት ይሆናል» አለ። 

ጳውሎስ ይህን መሰሉን ስሕተት በጢሞቴዎስ ላይ አልፈጸመም። ወደታች ሥር እንዲሰድ ጊዜ ሰጥቶት ነበር። ከዚያም ወጣቱን ሰው በወንጌል ሥራ ካስገባው በኋላ አብረው ይሠሩ ነበር። ለጢሞቴዎስ ቃሉን ማስተማር ብቻ ሳይሆን በአገልግሎቱ የሐዋርያውን ፈለግ ይከተል ዘንድ ከጎኑ እንዳይለይ ፈቀደለት (2ኛ ጢሞ. 3፡10-17)። ይህ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ያሠለጠነበት መንገድ ነው። በሥራ ልምምዳቸው ላይ የሚረዳቸውን ሚዛናዊ የሆነ የግሉን ትዕዛዝ ይሰጣል። ከትምህርት ውጪ የተገኘ ልምድ ወደ ተስፋ መቁረጥ ያመራል። እንደዚሁም ትምህርት ከልምምድ ውጭ ሲሆን ወደ መንፈሳዊ ሞት ያመራል። ትምህርትና ልምምድ ሁለቱም ያስፈልጋሉ። 

የአገልጋይ ሽልማት አለው (2፡23) 

ጢሞቴዎስ የ«መሥዋዕትንና የአገልግሎትን» ትርጉም ያውቅ ነበር (2፡17)፤ ሆኖም ግን እግዚአብሔር ለሽልማት ያበቃው በታማኝነቱ ነው። በመጀመሪያ ነገር፣ ጢሞቴዎስ ሌሎችን በመርዳት ደስ ይለዋል። ችግሮችና መከራዎች ቢኖሩም ቅሉ በዚያ መጠን ድሎችና በረከቶችም ነበሩ። ምክንያቱም ጢሞቴዎስ «ጥሩ እና ታማኝ አገልጋይ» ስለነበር በጥቂት ነገሮች ላይም የታመነ ስለ ሆነ እግዚአብሔር “በብዙ ነገሮች” ሾመው፥ ትሑት አእምሮውም በደስታ ተሞላ (ማቴ. 25፡21)። ከታላቁ ሐዋርያ ከጳውሎስ ጋር በማገልገሉ እና በሚያስቸግሩ ሥራዎች ላይ በመርዳቱ ደስ ይለዋል (1ኛ ቆሮ. 4፡17 ጀምሮ፤ በጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ ጢሞቴዎስ ቢያንስ ቢያንስ 24 ጊዜ ተጠቅሷል)። 

ምናልባትም እግዚአብሔር ለጢሞቴዎስ ከሁሉም የበለጠውን ሹመት የሰጠው፥ ታላቁ ሐዋርያ ጳውሎስ ወደ አገሩ በተጠራበት ጊዜ በጳውሎስ ምትክ እንዲሠራ በመምረጡ ነበር (2ኛ ጢሞ. 4፡1-11 ተመልከት)። ጳውሎስም ቢሆን ወደ ፊልጵስዩስ ለመሄድ ይፈልግ እንጂ፥ ዳሩ ግን በምትኩ ጢሞቴዎስን ላከው። ይህ የቱን ያህል ታላቅ ክብር ነው! ጢሞቴዎስ የጳውሎስ ልጅና የጳውሎስ አገልጋይ ብቻ አይደለም ግን የጳውሎስ ምትክ ሆነ። ስሙም በክርስቲያኖች ዘንድ እስከ ዛሬ በከፍተኛ አክብሮት ይነሳል፥ ወጣቱ ጢሞቴዎስ ክርስቶስን በማገልገል ሥራ በተጠመደበት ጊዜ እንኳን ይህን ክብር አገኘዋለሁ ሲል ጨርሶ አልሞም አያውቅም ነበር። 

ትሑት አእምሮ የሰዓት ስብከት፥ የሳምንት ትምህርታዊ ጉባኤ ወይም የዓመት አገልግሎት ውጤት አይደለም። ትሑት አእምሮ በውስጣችን አድጓል የምንለው እንደ ጢሞቴዎስ ከጌታ ተቀብለን ሌሎችን ለማገልገል ፈቃደኞች ስንሆን ነው። 

  1. አፍሮዲጡን (2፡25-30)

ጳውሎስ «ከዕብራውያንም ዕብራዊ» ነበር፤ ጢሞቴዎስ በአንድ በኩሉ አይሁድ በሌላው ደግሞ አሕዛብ ነበር (ሐዋ. 16፡1)። አፍሮዲጡን ግን እኛ እስከምናውቀው ድረስ ሙሉ በሙሉ አሕዛብ ነበር። በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን አባል ሆኖ በጤናውና በኑሮው ላይ አደገኛ ኃላፊነት በመውሰድ ወንጌላዊ ስጦታቸውን ወደ ሮም ለማድረስ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ነበረ (4፡18)። ስሙ «ደስ የሚል» ማለት ነው። እና እርሱም ደስ የሚያሰኝ ክርስቲያን ነው። 

እርሱ ሚዛናዊ ክርስቲያን ነበር (2፡25) 

ጳውሎስ ስለዚህ ሰው ብዙ በመናገር ምትክ «ወንድሜ እና የሥራ ጓደኛዬ፥ ወታደሬ» ብቻ ሲል አልፎታል። እነዚህ ሦስቱም ገለጻዎች ጳውሎስ በዚህ መልእክት መጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ስለወንጌል ከጻፈው ጋር ይዛመዳሉ። 

«ወንድሜ» – «የወንጌል ኅብረት» (1፡5) 

«የሥራ ጓደኛዬ» – «የወንጌል መስፋፋት» (1፡12) 

«ወታደር» – «የወንጌል እምነት» (1፡27) 

አፍሮዲጡን ሚዛናዊ ክርስቲያን ነበር! 

የተሟላ መሆን በክርስትና ሕይወት ውስጥ ጠቃሚ ነው። አንዳንድ ሰዎች «ኅብረትን» ያገንናሉ፤ በዚያው ልክ ደግሞ ወንጌልን ማስፋፋትን ይረሳሉ። አንዳንዶች «የወንጌልን እምነት» በመጠበቅ ተካፋይ ይሆናሉ፥ ግን ከሌሎች አማኞች ጋር ኅብረትን መገንባትን ችላ ይላሉ። አፍሮዲጡን ከእነዚህ በአንዱም ወጥመድ ውስጥ አልገባም። እርሱ የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደሠራው እንደ ነህምያ በአንድ እጁ ጎራዴ በሌላው እጁ ደግሞ ቅጥሩን የሚሠራበትን መሣሪያ የያዘ ነበር (ነህ. 4፡17)። በጎራዴ መገንባት እንደማይቻል ቅጥሩን በሚሠሩበት መሣሪያም መዋጋት አይቻልም። የጌታን ሥራ ለማከናወን ሁለቱም የግዴታ አስፈላጊዎች ናቸው። 

ሸክም ያለው ክርስቲያን ነበር (2፡26-27፥ 30) 

እንደ ጢሞቴዎስ፥ አፍሮዲጡንም ስለሌሎች ያስብ ነበር። በመጀመሪያ ነገር እርሱ ስለ ጳውሎስ ይጨነቅ ነበር። ጳውሎስ በሮም እስር ቤት እንዳለ ፊልጵስዩስ ሆኖ በሰማ ጊዜ፥ ረጅምና አደገኛ ጉዞ ወደ ሮም ለመጓዝና ከጳውሎስ ጎን ለመቆምና ለመርዳት ፈቃደኛ ሆነ። የቤተ ክርስቲያንን የፍቅር ስጦታ ወሰደለት። ይህንንም ያደረገው በሕይወቱ ፈርዶ ነው። 

በዛሬውም ጊዜ ቤተ ክርስቲያናት ሸክማቸው የከበደና ወንጌል የሚያሰራጩትን በችግር ላይ የሚገኙ አገልጋዮችን ለመርዳት የብዙ ወንዶችንና ሴቶችን እርዳታ ይፈልጋሉ። አንድ የወንጌል አገልግሎት መሪ «የእኛ ቤተ ክርስቲያን ችግር በጣም ብዙ ተመልካቾች አሉን ግን በቂ ተሳታፊዎች የሉንም» በማለት ደምድመዋል። አፍሮዲጡን የቤተ ክርስቲያንን ምፅዋት በማዋጣት ብቻ የሚረካ ሰው አልነበረም። የተሰበሰበውን ስጦታ ለማድረስ እራሱን መሥዋዕት እስከማድረግ የደረሰ ሰው ነበር። 

ከዚህ በተጨማሪም ይህ ሰው ለራሱ ቤተ ክርስቲያን የሚቆረቆር ነበር። ሮም ከደረሰ በኋላ ሕመም አድሮበት ሊሞት ምንም አልቀረውም። ይህም ወደ ፊልጵስዩስ መመለሱን አዘገየበት፥ እናም በዚያ ያሉት ሰዎች ለእርሱ ተጨነቁ። አፍሮዲጡን ግን ስለእራሱ አሳብ አልገባውም፥ የበለጠ ያሳሰበው ስለእርሱ በመጨነቅ ላይ የነበሩት በፊልጵስዩስ ያሉት ሰዎች ሁኔታ ነበር። ይህ ሰው የኖረው በፊልጵስዩስ 1፡21 ነው እንጂ በፊልጵስዩስ 2፡21 ውስጥ አይደለም። እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ እርሱም፥ ለሌሎች መጨነቅ ተፈጥሮው ነው። በ2፡26 ውስጥ «በሐዘን ስሜት በመዋጡ» የሚለው ሐረግና በክርስቶስ ላይ በጌተሰማኒ (ማቴ. 26፡37) ያደረው ስሜት ተመሳሳይ ናቸው። እንደ ክርስቶስ፥ አፍሮዲጡን የመሥዋዕትንና የአገልግሉትን (2፡30) ትርጉም ያውቃል። ሁለቱም የትሑት አእምሮ ባለቤቶች ነበሩ። 

የተባረከ ክርስቲያን ነበር (2፡28-30) 

ለአንድም ሰው በረከት ሳያተርፉ ሕይወትን ያህል ነገር ማሳለፍ ምንኛ የሚያሳዝን ነገር ነው! አፍሮዲጡን ለጳውሎስ በረከት ነበር። ጳውሎስ በእስር ቤት ሳለ አፍሮዲጡን ሕመሙ እንኳን ቢያሰቃየውም ከጎኑ አልተለየም። ጳውሎስና እርሱ ያሳለፉት እንዴት ያለ የተባረከ ጊዜ ይሆን! ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አፍሮዲጡን ለቤተ ክርስቲያኑም በረከት ሆኗል። ጳውሎስ ስለ መሥዋዕትነቱ እና ስለ አገልግሎቱ እንዲያከብሩት ቤተ ክርስቲያኑን አስጠነቀቀ። (ክርስቶስ ክብሩን አግኝቷል ግን አገልጋይም ክብር ቢቀበል ምንም ስሕተት የለውም 1ኛ ተሰ. 5፡12-13 አንብብ)። በፊልጵ. 2፡7 («እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም» ) እና 2፡29 («በሙሉ ደስታ ተቀበሉት») በሚለው መካከል የሚቃረን አሳብ የለም። ክርስቶስ በቸርነቱ ራሱን ዝቅ፥ ዝቅ አደረገ፥ እግዚአብሔር ግን ከፍ፥ ከፍ አደረገው። እንደዚሁም አፍሮዲጡን ምንም ሽልማት ሳያስብ ነው ራሱን መሥዋዕት ያደረገው። ሆኖም ጳውሎስ ይህንን ትሕትናውን በመረዳት የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ለእግዚአብሔር ክብር ሲሉ አፍሮዲጡንንም በአክብሮት እንዲመለከቱት አሳሰባቸው። 

እርሱ ለቤተ ክርስቲያኑና ለጳውሎስ በረከት ነበረ፤ እና ዛሬም ደግሞ ለእኛ በረከት ሆነ። የትሑት አእምሮ ባለቤት ለመሆን መሥዋዕትነትንና አገልግሉትን ቢጠይቅም፥ ሆኖም ግን ውጤቱ ደስተኛ ሕይወት ለመሆኑ በአፍሮዲጡን ተረጋገጠ። እርሱ እና ጢሞቴዎስ በአንድነት፥ ራሳችንን ለጌታና ለእርስ በርሳችን እንድናስገዛ በክርስቶስ መንፈስ ያሳስቡናል። ክርስቶስ እኛ የምንከተለው ምሳሌ ነው። ጳውሎስ ለእኛ ኃይልን አሳይቶናል (4፡ 12-19)፤ እና ጢሞቴዎስና አፍሮዲጡን ይህ አሳብ በእውነት እንደሚሠራ ማስረጃ ናቸው። 

አንተስ መንፈስ ቅዱስ በአእምሮህ ውስጥ «የክርስቶስን አስተሳሰብ» እንዲያሠርፅብህ ትፈቅድለታለህ?

ምንጭ፣ ጽሑፍ በ ዋረን ደብልዩ ዌርዝቢ፣ ትርጉም በመስፍን ታዬ፣ እርማት በ ዓብይ ደምሴ

Leave a Reply

%d bloggers like this: