የኦሪት ዘጸአት አስተዋጽኦ እና ዓላማ

፩. የኦሪት ዘጸአት አስተዋጽኦ

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ኦሪት ዘጸአት ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። እዚያ የሚገኘውን አስተዋጽኦ ገልብጥ። በሚቀጥሉት ገጾች የሚገኘውን አስተዋጽኦም አጥና።

በአጠቃላይ የኦሪት ዘጸአት ታሪክ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል፡

  1. እስራኤላውያን በግብፅ ምድር (ዘጸ. 1-12፡36)

በዚህ የመጀመሪያ ክፍል ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ተጠቅሰዋል። በመጀመሪያ የምናየው፥ የሙሴን ታሪክ ሲሆን ስለ ልደቱ፥ በምድረ በዳ ስላሳለፈው ጊዜና እግዚአብሔር እንዴት ለመሪነት እንደመረጠው እንመለከታለን።

በሁለተኛ ደረጃ፥ ስለ አሥሩ መቅሠፍቶች፥ እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ለመፍረድና ሕዝቡን ከባርነት ቀንበር ነፃ ለማውጣት እነዚህን መቅሠፍቶች እንዴት እንደተጠቀመባቸው እንመለከታለን።

በሦስተኛ ደረጃ፥ በፋሲካ በዓል ታሪክ አማካይነት እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከባርነት ቀንበር ነፃ በማውጣት እንዴት እንደመራቸው የሚያሳየውን ታሪክ እንመለከታለን። 

  1. ከግብፅ ወደ ሲና ተራራ የተደረገ ጉዞ (ዘጸ. 12፡37- ምዕ. 18) 

እስራኤላውያን ወደ ሲና ተራራ ለመድረስ ያደረጉት ጉዞ ሦስት ወራት ፈጀባቸው። እግረ መንገዱንም የሚከተሉት ዋና ዋና ድርጊቶች ተፈጸሙ፡-

አንደኛ፥ እግዚአብሔር እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን እንዲሻገሩ አስቻላቸው፥ ፈርዖንና ሠራዊቱን ግን አሰጠማቸው።

ሁለተኛ፥ እስራኤላውያን በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች በእግዚአብሔር ላይ አጉረመረሙ። ስለ መራራው ውኃ አጉረመረሙና ሙሴ፥ በእግዚአብሔር ኃይል ወደ ጣፋጭነት ለወጠው። እግዚአብሔር ለሕዝቡ መናንና ድርጭቶችን ለምግብነት ሰጣቸው። ሕዝቡ እግዚአብሔር ከዓለት ውኃ እስኪሰጣቸው ድረስ አጉረመረሙ።

ሦስተኛ፥ ከአማሌቃውያን ጋር ጦርነት ተካሄደ። እግዚአብሔርም ለእስራኤል ሕዝብ ድልን ሰጠ።

አራተኛ፥ የእስራኤልን ሕዝብ በመምራት ሥራ ሙሴን ይረዱት ዘንድ የሰባ ሽማግሌዎች ምርጫ ተካሄደ። 

  1. በሲና ተራራ የቃል ኪዳኑ መሰጠት (ዘጸ. 19-40)

የእስራኤል ሕዝብ በሲና ተራራ ላይ ለአንድ ዓመት ያህል ቆዩ። ኦሪት ዘጸአትና ዘሌዋውያንም ሕዝቡ በሲና ተራራ ላይ ስለነበሩበት ጊዜ ይናገራሉ። በሲና ተራራ የተደረጉ አራት ዋና ዋና ድርጊቶች በኦሪት ዘጸአት ውስጥ ተገልጸዋል።

አንደኛ፡- እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በጽላት ላይ የጻፋቸውን ዓሠርቱን ትእዛዛት ሰጣቸው።

ሁለተኛ፥ የተቀደሱ ሕዝቦች ይሆኑ ዘንድ መጠበቅ ያለባቸውን የቃል ኪዳን መመዘኛዎች እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ሰጣቸው።

ሦስተኛ፥ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን የሚያመልኩበትን የመገናኛ ድንኳን አሠራር የሚያመላክት ትእዛዝ ተቀበሉ። በተጨማሪ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ካህናትን ለአገልግሎት የመመደብንም ትእዛዝ ሰጣቸው። በሲና ተራራ ላይ እያሉ እነዚህን ትእዛዛት ፈጸሙ።

አራተኛ፥ እስራኤላውያን የጥጃ ምስል ሠርተው በማምለክ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት አደረጉ፤ የማመንዘር ኃጢአትንም ፈጸሙ፤ እግዚአብሔርም በብርቱ ቀጣቸው።

ከዚህ በታች የኦሪት ዘጸአትን ታሪክ በሚገባ ለማስታወስ የሚረዳ ዝርዝር አስተዋጽኦ ቀርቦአል፡-

  1. እግዚአብሔር ሕዝቡን – እስራኤልን ከግብፅ አዳነ (ዘጸ. 1-18)

ሀ. እግዚአብሔር እስራኤልን እንደሚያበዛ የገባውን ቃል ኪዳን ፈጸመ (ዘጸ. 1) 

ለ. እግዚአብሔር ሙሴን ለመሪነት መርጦ አዘጋጀው (ዘጸ. 2-6)፣ 

ሐ. እግዚአብሔር ግብፅን በአሥር መቅሠፍቶች መታ (ዘጸ. 7-11)፤ 

መ. እግዚአብሔር የፋሲካን በዓል ለእስራኤል ሕዝብ ሰጠ (ዘጸ. 12፡1-28)፤ 

ሠ. እስራኤላውያን ከግብፅ ወጡ (ዘጸ. 12፡29-51)፤ 

ረ. በግብፅ የተወለዱት የእስራኤላውያን በኩራት በሙሉ ተቀደሱ (ዘጸ. 13፡ 1-16)፤

ሰ. እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ተሻገሩ (ዘጸ. 13፡17-15፡21)፤ 

ሸ. እስራኤላውያን ወደ ሲና ተራራ ተጓዙ (ዘጸ. 15፡22-18፡27)። 

  1. እግዚአብሔር በሲና ተራራ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ (ዘጸ. 19-24)

ሀ. አይሁድ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘትና ቃል ኪዳን ለመቀበል ተዘጋጁ (ዘጸ. 19)፤ 

ለ. እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ዓሠርቱን ትእዛዛት ሰጣቸው (ዘጸ. 20፡1-17)፤ 

ሐ. እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ስለተቀደሰ አንዋንዋር መመሪያ ሰጣቸው (ዘጸ. 20፡18-23፤ 33)፤ 

መ. እስራኤላውያን በቃል ኪዳኑ ተስማሙ፤ ቃል ኪዳኑም ተረጋገጠ (ዘጸ. 24፡1-8)። 

  1. እግዚአብሔር የሚመለክበትን የመገናኛ ድንኳን አሠራር የሚመለከት ትእዛዝ ሰጠ (ዘጸ. 25-40)

ሀ. የመገናኛውን ድንኳን ለመሥራት ዝግጅት ተደረገ (ዘጸ. 24፡9-31፡18)፤ 

ለ. እስራኤላውያን ጣዖትን በማምለክ ኃጢአት ላይ ወደቁ፤ ተፈረደባቸውም (ዘጸ. 32-34)፤

ሐ. የማደሪያው ድንኳን ተሠራና እግዚአብሔር አደረበት (ሕልውናውን ገለጠበት) (ዘጸ. 35-40)። 

፪. የኦሪት ዘጸአት ዓላማ

ዮፔንታቱክ መጻሕፍት ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትን ይጥላሉ። የኦሪት ዘፍጥረት ተቀዳሚ ተግባር በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የነበሩትን የአይሁድን አጀማመር መግለጥ እንደነበር አይተናል። የኦሪት ዘፍጥረት መጨረሻ የሚያሳየው የእስራኤል ሕዝብ ከተስፋይቱ ምድር ውጭ በግብፅ እንዴት እንደተገኙ ነው። ኦሪት ዘጸአት እስራኤላውያን ወደ ታላቅ ሕዝብነት እንዴት እንዳደጉና ግብፅን ትተው ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከነዓን ለመመለስ እንዴት ጉዞ እንደጀመሩ ያሳየናል። ይህ መጽሐፍ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን እንዴት ትልቅ ሕዝብ እንዳደረጋቸው፥ የተመረጡ ሕዝብ እንደ መሆናቸው መጠንም ከእርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያስረዳውን ቃል ኪዳን እንዴት እንደገባ ይነግረናል።

ኦሪት ዘጸአት አራት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት። እነርሱም :

  1. እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከባርነት እንዴት ነፃ እንዳደረጋቸው መናገር ነው። 

ይህ ታሪክ የመዋጀት ታሪክ ነው። «መዋጀት» የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያስችል ቁልፍ ቃል ነው። «መዋጀት» የሚለው ቃል የሚናገረው ተገቢውን ዋጋ በመክፈል ሰውን ከባርነት ነፃ ስለ ማውጣት ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ በኢየሱስ ደም ከኃጢአት ባርነት ተዋጅተናል (ማር. 10፡45)። በብሉይ ኪዳን ግን የመዋጀትን ግልጥ ሥዕል የምንመለከተው እግዚአብሔር የአይሁድን ሕዝብ ከግብፅ ባርነት ለመዋጀት በሠራው ሥራ ውስጥ ነው (ዘጸ. 6፡6፤ ዘዳ. 15፡15 ተመልከት)።

እስራኤላውያን በትውልዶች ሁሉ እግዚአብሔር በግብፅ ከነበሩበት ባርነት እንዴት ነፃ እንዳወጣቸው ማስታወስ ነበረባቸው። ይህም እግዚአብሔር ከምንም ዓይነት ባርነት ነፃ እንዳወጣቸው ለማመን መሠረት ሆናቸው። በተጨማሪም የሌሎች አሕዛብን አማልክት ሳይከተሉ፥ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት እንዲጠብቁ ረድቶአቸዋል። 

  1. የእስራኤል ሕዝብ ልዩ ወይም የተለዩ እንደሆኑ ለማስታወስ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 19፡3-6 አንብብ። ሀ) እስራኤላውያን በእነዚህ ቁጥሮች የተገለጡት እንዴት ነው? ለ) እነዚህን ቁጥሮች ከ1ኛ ጴጥ. 2፡5-9 ጋር አወዳድር። ቤተ ክርስቲያን ከእስራኤል ጋር የምትመሳሰለው እንዴት ነው? ሐ) የአንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን ጥሪ እንዴት እየፈጸመች ነው?

እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በዚህ ምድር ከሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ለይቶ የተለዩ ቅዱስ ሕዝብ እንዲሆኑ መረጣቸው። ከሌሉች ሕዝቦች ሁሉ የተለዩ ነበሩ። የእግዚአብሔር የግል ገንዘቡ ነበሩ። የእግዚአብሔር ካህናት የሆኑ ሕዝብ ነበሩ። እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን የሕዝቡን ልዩ መሆን አጠናከረው። ከሌላው ሕዝብ ጋር ጨርሶ ባልተገናኘበት መንገድ ከዚህ ሕዝብ ጋር ተገናኘ፡፡ እግዚአብሔር ለነዚህ ሕዝብ፥ በቃል ኪዳኑና በሲና ተራራ በሰጣቸው ትእዛዛት መሠረት በታዛዥነት ከተራመዱና ከኖሩ ብቻ፥ ከዓለም የተለዩ እንደሚሆኑ ሊያሳያቸው ፈልጎ ነበር። ይህ ሲሆን ብቻ ነው የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ሕዝብ ሊሆኑ የሚችሉት (ዘጸ. 19፡5-6)።

በሲና ተራራ ላይ የተፈጸመው ቃል ኪዳን፥ በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ መካከል ሊኖር የሚገባውን ይህን ልዩ ግንኙነት አሳይቷል። እርሱን ብቻ ሊያመልኩ ይገባ ነበር። በእግዚአብሔር ፊት በመታዘዝና በቅድስና ሊኖሩ፥ በቅድስናቸውም እርሱን ሊመስሉ ይገባ ነበር፤ (ዘጸ. 22፡31)። በእርሱ በኩል እግዚአብሔር ለእነርሱ በተለየ መንገድ ኅብረት ያደርግ ነበር። በአእምሮአቸው ውስጥ የሚኖረው ክብሩን ሊያንፀባርቅ በሚችል የደመና ክብር እንጂ፥ በተቀረፀ ምስል ክብር አልነበረም። እግዚአብሔር «እርሱ የሚያድርበትን የመገናኛ ድንኳን» እንዲሠሩ አዘዛቸው (ዘጸ. 40፡33-38 ተመልከት)።

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ቆሮ. 3፡16-17፤ 6፡19 አንብብ። ሀ) በአዲስ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ምንድነው? ለ) በብሉይ ኪዳን ከነበረው ከመገናኛው ድንኳን ዓላማ ጋር እንዴት ይመሳሰላል?

  1. እስራኤላውያን ልዩ የሆኑት በሕዝብነታቸው ታላቅነት ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ምሕረትና ሉዓላዊ ምርጫ መሆኑን እንዲያስቡት ለማድረግ ነው። 

እነርሱ እግዚአብሔርን አልመረጡትም፤ እርሱ መረጣቸው እንጂ። ሆኖም ይህ ልዩ መብት እግዚአብሔር በሲና ተራራ ከእነርሱ ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን ውስጥ ለሚገኙት ቅድመ-ሁኔታዎች እስራኤላውያን ባላቸው መታዘዝ ላይ መመሥረት ነበረበት። እስራኤላውያን ካልታዘዙ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙት አንዳችም በረከት አይኖርም።

  1. ለእስራኤላውያን የእግዚአብሔርን ታላቅነት ለማሳየት ነው። 

ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን ሊረዳቸው እንደማይችል እንደ አንድ ደካማ ምስል አድርገው ያስቡት ነበር። የአብርሃምን፥ የይስሐቅንና የያዕቆብን ታሪክ የሰሙ ቢሆንም እንኳ በግል እግዚአብሔርን አልተዋወቁትም ነበር። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው ግንኙነት መጀመሪያ ታላቅነቱን ለእነርሱ ገለጠላቸው። እግዚአብሔር ታላቅነቱን የገለጠላቸው በተለያዩ መንገዶች ነው። በመጀመሪያ ታላቅነቱንና ኃይሉን የበለጠ ሊገልጥ የሚችለውን የራሱን አዲስ ስም ሰጣቸው። ያ ስም «ጂሆቫ» ወይም «ያህዌ» የሚል ነበር፤ (ዘጸ. 3፡13-15 ተመልከት)። ሁለተኛ፥ በፍጥረታት ሁሉና በምድር ከሁሉም ይበልጥ ገናና በነበረው መሪ ላይ እንኳ 10 መቅሰፍቶችን በመላክ ኃይሉን ገለጠ። ሦስተኛ፥ ቅድስናውንና ኃይሉን በሲና ተራራ በነጎድጓድ በታጀበ ታላቅ ድምፅ ገለጠላቸው (ዘጸ. 19፡15-19 ተመልከት)። አራተኛ፥ እግዚአብሔር ታማኝ መሆኑን ለአብርሃምና ለቀሩት የእስራኤል ሕዝብ አባቶች የገባላቸውን ተስፋ በመፈጸም አሳየ። እግዚአብሔር ለመረጣቸው ሰዎች ሁልጊዜ ታማኝ ነው። የገባውንም የተስፋ ቃል ዘወትር ይጠብቃል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔር ፍላጎት ራሱን ለእኛ መግለጥ ስለሆነ በኦሪት ዘጸአት ያለው ከሁሉም የሚበልጥ ዓላማ ይህ ሳይሆን አይቀርም። እግዚአብሔር አምላካችንን የምናውቅ ሕዝብ መሆን አለብን። በተለይ ጥርጥር በተስፋፋበት በዚህ ዘመን የእግዚአብሔርን ባሕርይ ባወቅንና በተረዳን መጠን በእርግጠኛነትና በእምነት ዋስትና መኖራችን ይቀጥላል። 

የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህ አራት ዓላማዎች ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚንፀባረቁት እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: