አንድ ሰው የመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞውን በመልካም ሁኔታ ጀመረ ማለት ያለማቋረጥ በእምነት ይጓዛል ማለት አይደለም። እግዚአብሔር አይሁዳውያንን ከግብፅ ባርነት በታላቅ ኃይል አወጣቸው። አይሁድ በታላቅ ደስታ ከምርኮኛነት ተላቀቁ፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ መጠራጠር፥ ማጉረምረም ማማረር ጀመሩ። ከዚህም አልፈው ወደ ግብፅ ለመመለስ ከጀሉ። መንፈሳዊ አረማመዳቸው ልክ እንደ እኛው የድልና የሽንፈት ጊዜያትን ያካተተ ነበር። የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ያሳለፉት ሕይወት በመንፈሳዊ ሕይወታችን ተጠንቅቀን እንድንኖር ለሁላችንም ማስጠንቀቂያ ሊሆን ይገባል። ተግባራችን እንደ እነርሱ እንዳይሆንና በአለማመን እንዳንወድቅ፥ ከስሕትታቸው መማር አለብን።
የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ቆሮ. 10፡1-13 አንብብ። ከእስራኤላውያን የምድረ በዳ ኑሮ መማር እንዳለብን ጳውሎስ የሚናገረው ምንድን ነው?
የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 13-18 አንብብ። ሀ) እስራኤላውያን ወደ ሲና ተራራ በሚጓዙበት ጊዜ የሠፈሩባቸውን ቦታዎች ሁሉ ዘርዝር። ለ) በእያንዳንዱ ስፍራ ስለተፈጸመው ነገር አጫጭር ገለጻ አድርግ። ሐ) ከዚህኛው የእስራኤላውያን ጉዞ የምትማራቸው መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። መ) የአንተና የቤተ ክርስቲያንህ ሕይወት ከእስራኤላውያን ጉዞ ጋር የሚመሳሰልበትን ነገር ዘርዝር።
እስራኤላውያን ከግብፅ ወደ ሲና ተራራ ያደረጉት ጉዞ ሦስት ወር ገደማ ፈጀባቸው። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን እንዲህ በሚያስደንቅ ጅማሬ ከግብፅ ባርነት ካወጣቸው በኋላ፥ ፍጹም በሆን እምነትና መታዘዝ ይጓዛሉ ብለን መጠበቃችን አይቀርም። በእስራኤላውያን ሕይወት የተፈጸመው ግን ይህ አልነበረም። ከግብፅ ወደ ሲና ያደረጉት ጉዞ በጣም አስቸጋሪ ነበር። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በእግዚአብሔር ከመታመን ይልቅ እርሱን ወደማማረርና በእርሱም ላይ ወደ ማጉረምረም አዘነበሉ።
የውይይት ጥያቄ፥ እኛ ክርስቲያኖችም ችግር በሚያጋጥመን ጊዜ የምናጉረመርመውና የምናማርረው እንዴት ነው? ለምን?
እስራኤላውያን ወደ ሲና ተራራ በሚጓዙበት ጊዜ ያለፉባቸው ቦታዎች ከዚህ እንደሚከተለው ተተንትነዋል።
1) አብዛኛዎቹ እስራኤላውያን በግብፅ በነበሩበት ጊዜ ከኖሩበት ከራምሴ ተነሥተው ግብፅን ለመልቀቅ ወደ ተዘጋጁበት ወደ ሱኮት ሄዱ (ዘጸ. 12:37-13፡19)። በዚህ ስፍራ ሁለት ዋና ዋና ድርጊቶችን ፈጸሙ። በመጀመሪያ፥ በቂጣ በዓል ምን መደረግ እንዳለበት የወሰኑት በሱኮት ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፥ የእስራኤልን በኵር ሁሉ ለእግዚአብሔር የመቀደስ ተግባር የተከናወነው በሱኮት ነበር (ዘጸ. 13:1-16)።
በኩራትን የመቀደስ ተግባር እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር አሥራትን ከሰጡባቸው መንገዶች አንዱ ነበር። እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ያስጀመረው መመሪያ በአይሁድ ዘንድ ከሰውም ሆነ ከእንስሳ ለእግዚአብሔር አሳልፎ የመስጠት ተግባር ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ ከምርታቸው ወይም ከእንስሶቻቸው መካከል ለእግዚአብሔር መስጠት ያለባቸው የመጀመሪያውን እንጂ የመጨረሻውን አልነበረም።
ስለ በኩር በተሰጠው ትምህርት ውስጥ የተካተቱት ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ። በቅድሚያ በኩር ስለሆኑት ሰዎች የተሰጠ ትምህርት እናገኛለን። ) የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ አንድ ሕዝብ እንደ መሆኑ መጠን በኩር ነበር። ይህም የሚያንፀባርቀው እግዚአብሔር ያዕቆብን ወይም እስራኤልን የተስፋው ልጅ የኪዳን ወራሽ አድርጎ በመምረጥ የበኩሩን ልጅ መብት እንደሰጠው ነው፤ ስለዚህ የያዕቆብ ልጆች የሆኑ እስራኤላውያን ሙሉ እንደ እግዚአብሔር ልዩ ልጅ ተቆጥረው የእርሱ በኩር ሆኑ (ዘጸ. 4፡22)።
2) ነገር ግን የበኩር ትምህርት የእስራኤላውያን የመጀመሪያ ልጆች የሆኑትንም ሁሉ የሚመለከት ነው። እያንዳንዱ በኩር ልጅ የእግዚአብሔር ነበረ። ምክንያቱም እግዚአብሔር የግብፃውያንን በኩር በመቅሠፍት ባጠፋ ጊዜ የእስራኤላውያንን በኩር ትቶ ነበር (ዘጸ. 12፡12-13)፤ ስለዚህ የበኩሩ ልጅ ወላጆች ገንዘብ ከፍለው ልጁን እንዲያስመልሱ ወይም «እንዲዋጁ» እግዚአብሔር ይፈልግ ነበር። ገንዘብ መከፈል ነበረባቸው (ዘኁል. 18፡15-16)።
በእስራኤላውያን በኩሮች ምትክ መላው የሌዊ ነገድ ለእግዚአብሔር ተሰጥቶ ነበር፤ (ዘኁል. 3፡41-5)።
ሁለተኛ፥ የእንስሳትን በኩር እናገኛለን። እንስሳትን በሚመለከት ሁለት ዓይነት ሕግጋት ነበሩ።
ሀ. «ንጹሕ» እንስሳት የሚባሉና ለመሥዋዕትነት የተፈቀዱ እንስሳት ነበሩ። የተባዕት እንስሳ በኩር የእግዚአብሔር ስለሆነ መሥዋዕት ሆኖ በመሠዊያ ላይ ይቀርብና ይሰዋ ነበር። ሥጋውም ለካህናት ይሰጥ ነበር (ዘኍል. 18፡14-19)። 2) ለመሥዋዕት ይቀርቡ ዘንድ ያልተፈቀዱ «ንጹሐን ያልሆኑ» እንስሳትም ነበሩ። ንጹሕ ባልሆነው እንስሳ ምትክ እስራኤላውያን ጠቦት መስጠት ነበረባቸው። ጠቦቱንም በመሠዊያ ላይ አቅርቦ በመሠዋት ለእግዚአብሔር መስጠት ተገቢ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለእግዚአብሔር አሥራት በምንሰጥበት ጊዜ የሁሉን ነገር በኩር ለእግዚአብሔር መስጠት መልካም መመሪያ የሆነው ለምንድን ነው? ለ) በአሁኑ ጊዜ ብዙ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ከመተ ከአሥር እጅ (10%) በታች የሚሰጡት ለምንድን ነው? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች ከገንዘባቸውም ሆነ ከምርታቸው የተረፈውን ለእግዚአብሔር የሚሰጡት ለምንድ ነው? መ) ይህ መመሪያ ዛሬ አሥራትን ስለመክፈል የሚያስተምረን ነገር ምን ይመስልሃል?
የውይይት ጥያቄ፥ ሉቃ. 2፡7፤ ሮሜ 8፡29፤ ቆላ. 1፡15፥ 18 አንብብ። ሀ) በዚህ ስፍራ ለክርስተስ የተሰጠው ማዕረግ ምንድን ነው? ለ) ይህ ማለት ምን ማለት ነው?
ለ. ሕዝቡ ከሱኮት ወደ ኤታም አመሩ (ዘጸ. 13፡20-22)። ከሱኮት ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚወስዱ ሁለት የተለያዩ መንገዶች ነበሩ። አንደኛው በሜዲትራኒያን ባሕር አጠገብ በፍልስጥኤማውያን ምድር ወደ ሰሜን የሚወስደው ሲሆን፥ የተለመደ የንግድ መስመር ነበር። ይህ መንገድ አጭር ስለሆነ፥ እስራኤላውያን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከነዓን ይደርሱ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በዚህ መንገድ አልመራቸውም። ረጅምና አስቸጋሪ በሆነው ወደ ሲና በረሀ በሚወስደው መንገድ መራቸው። እግዚአብሔር ይህን ያደረገው ለምን እንደሆነ አናውቅም። ምናልባት በምድረ በዳው ልምምድና በሲና ተራራ ላይ ባሳለፉት ጊዜ የተመረጡ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን እንዴት መኖር እንዳለባቸው ሊያስተምራችው የፈለገ ይመስላል። የጉዞው አስቸጋሪነት በእግዚአብሔር ላይ እንዲታመኑ ለማስተማር የታቀደ ነበረ።
የውይይት ጥያቄ፥ በእርሱ ላይ ያለህን እምነት ለማነፅ እግዚአብሔር በሕይወትህ የሚከሰቱ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዴት ይጠቀምባቸዋል?
በኤታም በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድ ነገር ተፈጸመ። እግዚአብሔር ቀን በደመና ዓምድ ሌሊት ደግሞ በእሳት ዓምድ በመምራት ከእነርሱ ጋር መኖሩን አሳያቸው። በሚቀጥሉት 40 ዓመታት እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በምድረ በዳ የመራቸው የእርሱን መኖር በሚገልጹት በእነዚህ ሁለት ምልክቶች ነበር። በኋላም የእግዚአብሔር ክብር ደመና የማደሪያውን ድንኳንና ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። አይሁድ ይህን የእግዚአብሔር መኖር ደመና «የሽካይናህ ክብር» ብለው ይጠሩታል።
3) ከኤታም ተነሥተው ወደ ፊሀሒሮት በመምጣት ቀይ ባሕርን ተሻገሩ (ዘጸ. 14፡1-15፡21)። ፊሀሒሮት የት እንደሆነ እርግጠኞች ሳንሆንም፥ በትልቅ የውኃ አካል ጠርዝ ላይ ያለ ስፍራ ነበር። እግዚአብሔር ውኃውን በከፈለላቸው ጊዜ እስራኤላውያን በትክክል የተሻገሩት የትኛውን የውኃ አካል እንደሆነ በማሰብ ምሁራን ብዙ ጊዜ መደነቅ ይዞአቸዋል። ያቋረጡት ባሕር መጠሪያ ስሙ «የሸምበቆ ባሕር» የሚል እንጂ ቀይ ባሕር አልነበረም። ያቋረጡት ያሁኑን ቀይ ባሕር ነው ማለት ትክክል አይመስልም። ብዙ ምሁራን እንደሚሉት እግዚአብሔር በተአምር ለሁለት ክፍሎች ያቋረጡት ውኃ በቀይ ባሕርና በሜዲትራኒያን ባሕር መካከል የነበረ አንድ ትልቅ ውኃማ አካል ነው።
እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የመጀመሪያውን ፈተና በዚህ ስፍራ ሰጣቸው። ከፊት ለፊታቸው ታላቅ ውኃ፥ ከኋላቸው ደግሞ የፈርዖን ሠራዊት ነበር። ከጥቂት ቀናት በፊት 10 መቅሠፍቶችን በግብፅ ላይ በማውረድ ከፈርዖን ብርቱ እጅ ባዳናቸው እግዚአብሔር ላይ ታምነው ይሆን? የለም፤ በእግዚአብሔር አላመኑም ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ውኃውን ለሁለት ከፈለው። እስራኤላውያን በደረቅ ምድር ሲሻገሩ፥ የግብፅ ሠራዊት ግን በውኃው ውስጥ ሰጥሞ ቀረ።
የውይይት ጥያቄ፥ በእግዚአብሔር ጠላቶችም ሆነ በሌሎች ችግሮች ልንሸነፍ የተቃረብን በሚመስለን ጊዜ እግዚአብሔርን ባለማመን ሊኖረን ስለሚችል ዝንባሌ ይህ ምን ያስተምረናል?
4) ከሸምበቆ ባሕር ወደ ማራ (ዘጸ. 15፡22-26)፡- በማራ እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በሌላ ነገር ፈተናቸው። ይህም ፈተና የሚጠጡትን ውኃ እንደሚሰጣቸው በእግዚአብሔር ይታመኑ እንደሆነ ለመለየት የተደረገ ነበር። የነበረው ውኃ መራራ ስለ ነበር ሰው ሊጠጣው አይችልም ነበር፤ ስለዚህ ከግብፅ ባወጣቸው አምላክ ላይ በመደገፍ ወደ እርሱ በመጸለይ ፈንታ፥ በሙሴ ላይ ያጉረመርሙ ጀመር። ሙሴ በእግዚአብሔር የተመረጠ መሪ ስለነበር፥ ያጉረመረሙት በእግዚአብሔርም በሙሴም ላይ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወይም በክልል ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ላይ በምናጉረመርምበት ጊዜ ምን እያደረግን እንደሆነ ምን ያስተምረናል? ለ) በዚህ ረገድ ከእስራኤላውያን ጋር የምንመሳሰለው እንዴት ነው?
እግዚአብሔር በእኛ ላይ በኃላፊነትና በሥልጣን ባስቀመጣቸው ሰዎች ላይ በምናጉረመርምበት ጊዜ የሚሆነው ነገር ተመሳሳይ ነው። ያጉረመረምነው በእነርሱ ላይ ብቻ እንደሆነ ሊመስለን ይችላል፤ ዳሩ ግን የሚመሩት በእግዚአብሔር ተመርጠው ስለሆነ፥ የምናጉረመርመው በእግዚአብሔርም ላይ ጭምር ነው። እግዚአብሔር በጸጋው እንደገና ሙሴን በመጠቀም በተአምር ንጹሕ ውኃን ሰጣቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሕዝቡ በማራ ያሳለፉት ይህ ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ የማጉረምረማቸው ምሳሌ ተደርጎ ይታያል (መዝ. 95፡7-11፤ ዕብ. 3፡7-19)።
5) ከማራ ወደ ኤሊም፥ ከዚያም ወደ ሲን ምድረበዳ መጡ (ዘጸ. 15፡27-16፡36)። ኤሊም ብዙ ውኃ ያለበት ስፍራ ነበር። ከዚያም የሲን በረሀ ተብሎ ወደሚጠራው ምድረ በዳ ሄዱ። አሁን እስራኤላውያን ግብፅን ከለቀቁ ልክ አንድ ወር ስለሆናቸው፥ በጉዞው መሰላቸት ጀምረው ነበር። የሚበሉትን ምግብ አጡ። ስለዚህ እንደገና በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ። ምቹ ነው ብለው ወደጠሩት ወደ ግብፅ ኑሮ መመለስም ተመኙ። ነፃ ሆኖ ከመራብ፥ ባሪያ ሆኖ መጥገብ ይሻለናል የሚሉ ይመስላሉ። አሁንም እግዚአብሔር እንደገና በምሕረቱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሰጣቸው። «የሰማይ እንጀራ»፥ «መናን» ሰጣቸው (ዘጸ. 16፡4)። የድርጭትንም ሥጋ ላከላቸው። «መና» ማለት በዕብራይስጥ «ይህ ምንድን ነው?» ማለት ነው። እንዲህ የተባለበት ምክንያት እግዚአብሔር በመጀመሪያ ለእስራኤላውያን እንደሰጣቸው ምንነቱን ስላላወቁ ነበር። እግዚአብሔር የፈቀደላቸው ለየዕለቱ የሚሆነውን መና እንዲሰበስቡ ብቻ ነበር። እስራኤላውያን ለዕለት እንጀራቸው በእርሱ እንዲታመኑ ማድረጉ ነበር (ማቴ. 6፡11)። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን አንድ ማድጋ ጎሞር ሙሉ መና ወስደው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ባለው ታቦት ሥር እንዲያስቀምጡ አዘዛቸው።
የውይይት ጥያቄ፥ ዮሐ. 6፡32-51 አንብብ። ሀ) እነዚህ ጥቅሶች እውነተኛ «የሕይወት እንጀራ» የሚሉት ማንን ነው? ለ) ይህስ ለአንተ እውነትነቱ እንዴት ነው?
6) ከሲን ምድረ በዳ ወደ ራፍቃ፥ ከራፍቃ ወደ ኤሉስ፥ ከኤሉስም ተጉዘው በራፊዲም ሠፈሩ (ዘኁል. 33፡12-13፤ ዘጸ. 17-18) እስራኤላውያን ወደ ሲና ተራራ የሚወስደውን የደቡብ ጉዞአችውን ቀጠሉ። ወደ ራፊዲም በደረሱ ጊዜም ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ተፈጸሙ።
- ውኃ ስላልነበራቸው እንደገና በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። ዓለቱን በበትሩ እንዲመታ እግዚአብሔር ሙሴን አዘዘው። በመታውም ጊዜ ከዓለቱ ውኃ ወጣ። በመጽሐፍ ቅዱስ ይህ ድርጊት የእግዚአብሔር ሕዝብ እግዚአብሔርን የተፈታተነበት ምሳሌ ሆኖ ቀርቧል። እግዚአብሔር እንደሚሰጣቸው በማመን እርሱን ከመጠበቅ ይልቅ «እግዚአብሔር በመካከላችን ነውን ወይስ አይደለም?» በማለት ፈተኑት (ዘጸ. 17፡7)። እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ ፍላጎታቸውን እንደሚያሟላላቸው ከመተማመን ይልቅ፥ በራሳቸው ጊዜ እግዚአብሔር እንዲያደርግላቸው ግፊት አደረጉ።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም እግዚአብሔርን በተመሳሳይ መንገድ እንዴት ልንፈታተነው እንችላለን? ለ) ይህም በእግዚአብሔር ላይ እምነት ማጣት መሆኑን የሚያሳየን ለምንድን ነው?
- እስራኤላውያን ከአማሌቃውያን ጋር ተዋግተው አሸነፏቸው። እግዚአብሔር በሙሴ የተዘረጉ እጆች ላይ ድል እንዲመሠርት ማድረጉ የሚያስደንቅ ነው። የሙሴ እጆች ወደ እግዚእብሔር ጸሎት በተዘረጉ ጊዜ እስራኤላውያን ያሸንፉ ነበር። እጆቹን ባወረደ ጊዜ ግን አማሌቃውያን ያሸንፉ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ለጸሎት አስፈላጊነት እንዴት ጥሩ መግለጫ ይሆናል?
- ዮቶር፥ የሙሴ አማት የእግዚአብሔርን ሕዝብ በመምራት ሥራ ውስጥ ይረዱት ዘንድ ሽማግሌዎችን ወይም የተለያየ ደረጃ ያላቸውን ሰዎች እንዲሾም ሙሴን መከረው። ሙሴ ሁሉንም ሰው ለመምራት ከሞከረበት ጊዜ ይልቅ፥ ይህን እንዳደረገ የእስራኤል ሕዝብ የበለጠ ስኬታማ በሆነ መንገድ ለመተዳደር ችሏል።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ አሠራር ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው አመራር ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ይህ አሠራር ቤተ ክርስቲያንህ እንዴት እንደሚደረግ ወይም እንደማይደረግ ምሳሌዎችን ስጥ።
7) ከራፊዲም ወደ ሲና ተራራ (ዘጸ. 19)፡- እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ከሦስት ወራት በኋላ ወደ ሲና ተራራ ደረሱ። በዚያ ስፍራም እግዚአብሔር ለእርሱ የተቀደሱ ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ እያዘጋጃቸው ለአንድ ዓመት ቆዩ። የቀሩት የኦሪት ዘጸአት፥ ዘሌዋውያንና ዘኁልቁ ምዕራፍ1-10 ታሪክ የተፈጸምው በብሉይ ኪዳን የኮሬብ ተራራ በተባለው በዚህ በሲና ተራራ ላይ ነው (ዘጸ. 33፡6)።
የውይይት ጥያቄ፥ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ሲና ተራራ ካደረገው ጉዞ ስለ ራሳችን የእምነት ጉዞ የምንማራቸው ጠቃሚ ትምህርቶች ምንድን ናቸው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)