ዘጸአት 19-24

ምናልባት ከእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ከሁሉም ላቅ ያለ ስፍራ ሊሰጠው የሚገባው ሕዝቡ በሲና ተራራ የቆዩበት የአንድ ዓመት ጊዜ ነው። እግዚአብሔር ራሱን በታላቅ ክብር ለሕዝቡ የገለጠው በዚያ ነበር። እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ግንኙነት የሚያደርግበትን የሥነ-ምግባርና የመንፈሳዊ ሕይወት መሠረት የሰጣቸው በዚያ ነበር። በእግዚአብሔር ሕዝብና በዓለም ሕዝብ መካከል የሚገኙ ዋና ዋና ልዩነቶች የተገለጡት በዚያ ነበር። ክርስቲያኖች ለሆንን ሁሉ ከእነዚህ መመሪያዎች አብዛኛዎቹ ዛሬም የሚሠሩ ናቸው። እኛም ለእግዚአብሔር የተለየን ሕዝብ መሆን አለብን። በዙሪያችን ካሉ ሕዝቦች ሁሉ የተለየ ኑሮ መኖር አለብን።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸአት 19፡3-6 አንብብ። ሀ) ስለ እስራኤል ሕዝብና ስለ ዓላማቸው በእነዚህ ጥቅሶች የተጠቀሱ የተለያዩ ነገሮችን ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስለነበረው ግንኙነት ምን ልንማር እንችላለን? ሐ) ለእግዚአብሔር ሊኖራቸው የሚገባው ምላሽ ምን መሆን ነበረበት? መ) እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በሚመለከት የተናገረውን ነገር በአዲስ ኪዳን ስለ ቤተ ክርስቲያን ከተነገረው ጋር አወዳድር። እኛ በዚህ አንፃር ከእስራኤላውያን ጋር የምንመሳሰልባቸው ወይም የምንለያይባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? (1ኛ ጴጥ. 2፡9 ተመልከት)።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 19-24 ተመልከት። ሀ) እግዚአብሔር ተፈጥሮውንና ኃይሉን ለእስራኤል ሕዝብ የገለጠባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝር። ለ) የእግዚአብሔር ቅዱስነትና እርሱ ከሕዝቡ የሚፈልገው ቅድስና በእነዚህ ቁጥሮች የታየው እንዴት ነው? ሐ) ዓሥርቱን ትእዛዛት ዘርዝር። መ) እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ትእዛዛት ለመሰሎቻቸው ያለባቸውን ኃላፊነት የሚያሳዩት እንዴት ነው?

እግዚአብሔር ከሕዝቡ (ከእስራኤል) ጋር በሲና ተራራ ያደረገው ግንኙነት፥ በሁሉም ዕድሜ ያሉ የእግዚአብሔር ሰዎች ከእርሱ ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባ ግንኙነት መሠረት የተጣለበት ነው። በርካታ ሕግጋትና ሃይማኖታዊ ልምምዶች ሊለወጡ ይችላሉ። ዋናው መመሪያ ግን አሁንም ይሠራል። ዘጸአት 19-24 የሲና ተራራ ቃል ኪዳን የተመሠረተበት ነው። በእነዚህ ምዕራፎች በእርሱና በሕዝቡ (በእስራኤል) መካከል ልዩ የሆነው ግንኙነት እንዲቀጥል ከእስራኤል ሕዝብ የሚጠበቁትን የቃል ኪዳኑን ግዴታዎች እግዚአብሔር ገልጧል። በሲና ተራራ ስለተገባው ቃል ኪዳን የሚከተሉትን ነገሮች ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡-

  1. በምንም ቅድመ ሁኔታ ላይ ሳይመሠረት እግዚአብሔር ከአብርሃምና ከዳዊት ጋር ከገባላቸው ሌሎች በርካታ ቃል ኪዳኖች በተቃራኒ በሲና ተራራ የተደረገው ቃል ኪዳን በቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነው። ማለትም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነው በረከትና የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል እንዲፈጸም እስራኤላውያን በቃል ኪዳኑ ውስጥ ለተጠቀሱት ትእዛዛት ታዛዦች መሆን ነበረባቸው። እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዳዊት በሰጣቸው ሌሉች ቃል ኪዳኖች፥ እንዲሁም በአዲሱ ቃል ኪዳን (ኤር. 31፡31) በመታዘዝ ቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር። የተስፋው ፍጻሜ የተመሠረተው ሰው በሚሰጠው ምላሽ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ተስፋ ላይ ብቻ ነበር።
  2. በሲና ተራራ የተሰጠው ቃል ኪዳን በዚያን ጊዜ በነበረው ባሕል ላይ የተመሠረተ ነበር። «የሱዜሪያን-ቫዛል» ቃል ኪዳን ተብሎ ተሰይሟል። እንዲህ ዓይነቱ ቃል ኪዳን በቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነበር። ይኸውም በገዢ ንጉሥና በእርሱ አገዛዝ ሥር ከወደቁት ሌሎች ነገሥታት መካከል ከአንዱ ጋር የሚደረግ ቃል ኪዳን ዓይነት ነበር። በእንደዚህ ዓይነቱ ቃል ኪዳን ገዥው ንጉሥ በሥሩ ባለው ንጉሥ ላይ ፍጹም የሆነ መብትና ሥልጣን እንዳለው ይናገራል። በሥሩ ካለው ንጉሥ ፍጹም ታማኝነትና አገልግሎት ይጠብቃል። ይህ ንጉሥ ታማኝና ታዛዥ ከሆነ ከጠላቶቹ ሁሉ ሊታደገው ገዥው ንጉሥ ቃል ይገባለታል። ልክ እንደዚሁ፥ እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ላይ ፍጹም ንጉሥ ነበር፤ ስለዚህ እስራኤላውያን የሚጠብቁትን ሕግ ሰጣቸው። እነርሱ ለእርሱ ታማኞችና ታዛዦች መሆን ነበረባቸው። ለታማኝነታቸውና ለታዛዥነታቸው እግዚአብሔር ሊባርካቸውና ሊጠብቃቸው ቃል ገባ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ነገር ዛሬ እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ግንኙነት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) እንዴትስ ይለያያል?

  1. በሲና ተራራ የተገባው ቃል ኪዳን በደም መፍሰስ ጸንቶአል (ዘጸ. 24፡3-8 ተመልከት)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ማር. 14፡24 ተመልከት። የአዲስ ኪዳን አጀማመር ከብሉይ ኪዳን አጀማመር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ከዘጸ. 19-24 ባለው ጥናትህ ውስጥ የሚከትሉትን 6 ነገሮች ልብ ማለት ጠቃሚ ነው፡፡

  1. እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ቃል ኪዳንን ከመስጠቱ በፊት ኃይሉንና ታላቅነቱን ገለጠ። ይህ የእግዚአብሔር ኃይልና ቅድስና (መለየት) በተለያዩ ብዙ መንገዶች ይታያል። ማንም ሰው ወደተቀደሰው ተራራ እንዳይቀርብ ወይም እንዳይነካው በሚለው ትእዛዝ ውስጥ ይታያል (ዘጸ. 19፡12-13)። እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው በተሰጠው ጥብቅ ትእዛዝ ውስጥ ትኩረት ተሰጥቶታል፤ (ዘጸ. 19፡10-11)። እግዚአብሔር እጅግ ታላቅ የሆነው ኃይሉን በሚገልጥ ከተራራው ላይ በተገለጠ ነጎድጓድ፥ መብረቅ፥ ከባድ ደመና፥ እጅግ በሚያስተጋባ የቀንደ መለከት ድምፅ፥ የእሳትና የመሬት መንቀጥቀጥ ወዘተ. አሳይቷል (ዘጸ. 19፡ 16-19)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን ከመግባቱ በፊት ክብሩንና ኃይሉን የገለጠላቸው ለምን ይመስልሃል? ለ) እግዚአብሔር ዛሬስ ኃይሉን የሚያሳየው እንዴት ነው? ሐ) ዛሬ የእግዚአብሔርን ኃይልና ታላቅነት መረዳታችን አምልኮአችንን እንዴት ይለውጠዋል? 

በጊዜያችን ካሉት ችግሮች አንዱ፥ ክርስቲያኖች ስለ እግዚአብሔር ኃይልና ቅድስና ያላቸው አመለካከት ዝቅተኛ መሆን ነው። ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን አይፈሩም። የእግዚአብሔርን ኃይልና ክብር ይበልጥ በተረዳን ቁጥር፥ የሚገባውን ያህል ልናመልከውና ልናከብረው እንችላለን። በመከራና በስደት ውስጥ ሳለን እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ ያለውን ኃይልና ሥልጣን ደግሞም የበላይ ተቆጣጣሪነት ስናስታውስ በእግዚአብሔር ላይ ለመታመን ብርታት እናገኛለን። ለእግዚአብሔር ያለን ፍርሃት ሁልጊዜ እርሱ ለእያንዳንዳችን ካለው ጥልቅ ፍቅር ጋር መስተካከል አለበት። ይህ ፍቅር እግዚአብሔር «አባ አባት» (ሮሜ 8:15) ብለን የምንጠራበትን ድፍረት ይሰጠናል። አምልኮአችን ፍቅርና ፍርሃት ደግሞም አክብሮትና ቅርበት የሚታይበት መሆን አለበት።

  1. እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን የማድረጉ ዓላማ እነርሱን ለራሱ የተለየ ርስት፥ የተለየ ሕዝብ፥ የንጉሥ ካህናት መንግሥትና የተቀደሰ ሕዝብ ለማድረግ ነበር (ዘጸ. 19፡5-6)። በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ዓላማ አንድ የተለየን ሕዝብ መምረጥ ነበር። በእስራኤላውያን ማንነት በኩል ምንም የተለየ ነገር አልነበረም። በቁጥር ብዙዎች ወይም ኃያላን የተማሩ ወይም የሠለጠኑ አልነበሩም። የተለዩ ወይም ልዩ ያደረጋቸው እግዚአብሔር በምሕረቱ ስለመረጣቸው ብቻ ነው። ስለዚህ የተለዩ ነበሩ። 

ዛሬ እግዚአብሔር ሰዎችን የሚመርጠው ከተለየ የዘር ሐረግ ስለተገኙ አይደለም። ይልቁንም እርሱ ወንዶችንና ሴቶችን በዓለም ላይ ከሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ የተለየ ዓይነት ሕዝብ ወይም ዘር እንዲሆኑለት ይመርጣል። ያ ሕዝብ ቤተ ክርስቲያን ናት። የዚህ ሕዝብ አካል የመሆን መመዘኛ እንደ ብሉይ ኪዳን ዘመን በሥጋ መወለድ አይደለም። ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኝ መንፈሳዊ ልደት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ እውነታ በተለያዩ ነገዶችና ጎሣዎች መካከል ያለውን እኔ ከሌላው እሻላለሁ የሚለውን አዝማሚያ እንዴት ያስወግደዋል?

እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ የመረጠበት ምክንያት በሁለት ሐረጎች ተገልጾአል። በመጀመሪያ፥ «የንጉሥ ካህናት» እንዲሆኑ ነበር። ካህን መካከለኛ ነው። እግዚአብሔርንና ሰውን ወደ አንድነት በማምጣት ተግባር ውስጥ ለእግዚአብሔር ይሠራል፤ ስለዚህ እስራኤል፡ የካህናት ሕዝብ እንደመሆንዋ መጠን ልትፈጽማቸው የሚገባት ሁለት ተግባራት ነበሩዋት። 1) እግዚአብሔርን ማገልገል ነበረባቸው። 2) አሕዛብን በሙሉ ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ለማድረግ መሣሪያ መሆን ነበረባቸው (ኢሳ. 49፡6)።

ሁለተኛው ሐረግ እስራኤል «ቅዱስ ሕዝብ» መሆን እንዳለባት ይናገራል። ይህም ማለት ሕዝብዋ ከአሕዛብ የተለየ ኑሮ መኖር ነበረባቸው ማለት ነው። ከዘጸአት-ዘዳግም ያሉት አብዛኛዎቹ ትእዛዛት እስራኤል ቅድስት መሆን እንዳለባትና የተቀደሰ ሕይወት መኖር እንደሚጠበቅባት በመግለጥ ይህን እውነት አንፀባርቀዋል።

  1. ከእስራኤል ጋር የተደረገው ቃል ኪዳን የተመሠረተው በዓሥርቱ ትእዛዛት ላይ ነበር። እነርሱም እግዚአብሔር ራሱ የጻፋቸው ስለሆነ (ዘጸ. 20፡22) ዋና ወይም መሠረታዊ የቃል ኪዳን ሕግጋት ነበሩ። እነዚህ ትእዛዛት የመጡት ከሰማይ እንጂ ከሲና ተራራ አልነበረም። የእግዚአብሔርን ዓለም አቀፋዊ ሕግጋት ስለሚያሳዩ፥ በየዘመኑ በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ መጠበቅ አለባቸው።

ዓሥርቱ ትእዛዛት በሁለት ክፍሎች ተከፍለዋል። እነርሱም፡-

  1. አራቱ ትእዛዛት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖረው በሚገባ ግንኙነት ላይ ያተኩራሉ። 

ሀ. «ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።» እስራኤላውያን በዚያን ጊዜ በነበራቸው እውቀት እውነተኛው አምላክ አንድ ብቻ እንደሆነና ሌሉቹ ጣዖታት እንጂ አምላክ እንዳልሆኑ አያውቁም ነበር። እግዚአብሔር ግን የመጀመሪያና ፍጹም የሆነ ታማኝነት ፈለገ። እርሱን ብቻ ማክበርና መፍራት ነበረባቸው። አይሁድ እርሱን ብቻ ማምለክ ተገቢያቸው ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ ለእኛ እንደ «አማልክት» ሊሆኑብን የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ለ. «የተቀረጸ ምስል ለአንተ አታድርግ።» ይህ ትእዛዝ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሌሎች አማልክት ማንኛውንም ዓይነት ቅርፅ ወይም ምስል ማድረግን ይከለክላል። ዛፎችን ማምለክ፥ ወይም እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል እነርሱ በሚያስቡት መንገድ ቅርፁን ወይም ምስሉን ማበጀት አይገባቸውም ነበር። 

ሐ. «የእግዚእብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ።» ለእግዚአብሔር ክብርን የመስጠት አንዱ ክፍል ስሙን ማክበር እንደሆነ ተመልክተናል፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ስም በየጊዜው እንደፈለግን የምንናገረው ወይም የምንጠራው መሆን የለበትም። ይህ ትእዛዝ ብዙ ጊዜ በሁለት መንገድ ይጣሳል፡- በመጀመሪያ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች የእግዚአብሔርን ወይም የኢየሱስን ስም ለእርግማን ዓላማ መጠቀማቸው ነው። በሁለተኛ ደረጃ ክርስቲያኖች የሆኑ ሳይቀሩ፥ ምንም ሳያስቡት ወይም ትርጉም በማይሰጥ መልኩ የእግዚአብሔርን ስም መጠቀማቸው ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ስም ያለአግባብ መጠቀማቸውን እንዴት አየኸው? ለ) ሰዎች የእግዚአብሔርን ወይም የኢየሱስ ክርስቶስን ስም እንዲያከብሩ ለማስተማር ቤተ ክርስቲያንህ ምን እያደረገች ነው?

መ. «የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ።» በብሉይ ኪዳን፥ እግዚአብሔር የሳምንቱን የመጨረሻ ቀን፥ ማለት ቅዳሜን ለእረፍትና ለአምልኮ ለየው። በአዲስ ኪዳን ክርስቶስ ከሞት የተነሣበትን ቀን ለማክበር፥ ክርስቲያኖች የአምልኮን ቀን ወደ እሑድ ለወጡት። ክርስቲያኖች ከዓሥርቱ ትእዛዛት መካከል እንዳለ ቃል በቃል ተቀብለው የማይታዘዙት ብቸኛ ትእዛዝ ይኸኛው ነው (ቆላ. 2፡16-17)፤ ነገር ግን የዚህ ትእዛዝ መንፈስ መጠበቅ አለበት። ለማረፍና እግዚአብሔርን ለማክበር በሳምንት አንድ ቀን ለጌታ መለየት አለብን። በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች ይህ ቀን እሑድ እንዲሆን መርጠዋል። በኦሪት ዘጸአትና ዘሌዋውያን የሚገኙ በርካታ ትእዛዛት አይሁድ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸና እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንዳለባቸው የሚናገሩ ናቸው። እነርሱም ይህንኑ መሠረት አጠናከሩት። 

  1. ስድስቱ ትእዛዛት ሰዎች ከሌሉች ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። የሚቀጥሉት ስድስት ትእዛዛት እርስ በርሳችን፥ በተለይም ደግሞ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል ከሆኑት ሰዎች ጋር ሊኖረን ስለሚገባ ግንኙነት ይናገራሉ።

ሠ. «አባትህንና እናትህን አክብር።» እግዚአብሔር ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ፥ ለወላጆቻቸው እንዲጠነቀቁና፥ እንዲታዘዙ ሕዝቡን አዘዘ። ይህን ካላደረጉ በረከትን እንደማያገኙ ነገራቸው። እግዚአብሔር ለዚህ ትእዛዝ ምንም ቅድመ ሁኔታ አላኖረም። ወላጆቻችንን ማክበር ያለብን ቸርና መልካም ሰዎች ሲሆኑ ብቻ አይደለም። የተማሩ ስለሆኑ ወይም ገንዘብ ስለሚሰጡንም ወዘተ. አይደለም። ሰዎች ወላጆቻቸውን ላለመታዘዝ የሚችሉበት አንድ ወቅት ብቻ አለ። ይኸውም ወላጆቻቸው እግዚአብሔር በግልጥ አታድርግ ያለውን እንዲያደርጉ፥ ወይም አድርግ ያለውን እንዳያደርጉ ሲጠይቁአቸው ብቻ ነው። በዚህ ጊዜ ከወላጆቻቸው ይልቅ ለእግዚአብሔር መታዘዝ አለባቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ በዚህ ዘመን ብዙ ወጣቶች፥ ክርስቲያኖችም ሳይቀሩ ይህንን ትእዛዝ የማይከተሉት እንዴት ነው? 

ረ. «አትግደል።» ይህ ማለት ጨርሶ መግደል የለብንም ማለት አይደለም። እግዚአብሔር ይህንን የእርሱን ትእዛዝ በግድ የለሽነት የሚጥሱትን፥ በተለይ ደግሞ ሆን ብለው የሰዎችን ሕይወት የሚያጠፉትን ሰዎች በሞት እንዲቀጡ ለመንግሥታት መብት ሰጥቶአቸዋል (ሮሜ 13፡4 ተመልከት)። አንዳንዶች እንደሚያስተምሩት ይህ ሕግ ወደ ጦርነት መሄድን ጨርሶ የሚከለክል አይደለም፤ ይልቁንም ሕይወትን በግዴለሽነት ስለማጥፋት የሚናገር እንጂ።

ሲ. «አታመንዝር።» ይህ ትእዛዝ ሁለት ዓይነት ኃጢአቶችን ያጠቃልላል። የመጀመሪያው፥ በባልና ሚስት መካከል በግብረ ሥጋ ግንኙነት ረገድ ታማኝ ያለመሆን ኃጢአት ነው። ባልየውም ሆነ ሚስትየዋ ከሌላ ከማንኛውም ሰዎች ጋር የግብረ ሥጋ ኅብረት እንዲኖራቸው አልተፈቀደላቸውም። ሁለተኛው ደግሞ፥ ያላገቡ ሰዎች የሚፈጽሙት ማንኛውም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ተግባር ነው። እግዚአብሔር እንዳዘዘው ግብረ ሥጋ መፈጸም ያለበት በጋብቻ በተጣመሩ ባልና ሚስት መካከል ብቻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል በርካታ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ኃጢአት የሚከሰተው ለምንድ ነው? ለ) አንዳንድ ሰዎች ማመንዘር ከወንድ ይልቅ ለሴት የከፋ እንደሆነ የሚያስተምሩት ለምንድን ነው? ትክክል ናቸውን? መልስህን አብራራ። ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ «አታመንዝር» የሚለውን ሕግ እንዲያከብሩ ያገቡ የትዳር ጓደኛሞችንም ሆነ ያላገቡትን አባላትዋን እንዴት ማበረታታት ትችላለች?

ሸ. «አትስረቅ።» ይህ ማለት ስሕተት መሆኑን እያወቅህ፥ የራስህ ያልሆነውን ነገር ከሰው ላይ መውሰድ ለራስህ ማድረግ ስህተት ነው። ይህም ገንዘብ ወይም ቁሳቁሳዊ ነገር መሆን ይችላል። ወይም በትምህርት ቤት ከሌላ ሰው ወረቀት ላይ የፈተና መልስ መቅዳት ወይም መኮረጅ ሊሆን ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ ሰዎች (ክርስቲያኖች ሳይቀሩ) የሚሰርቁባቸውን የተለያዩ መንገዶች ግለጽ።

ቀ. «በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።» ይህ ትእዛዝ ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን ያንፀባርቃል። የመጀመሪያው በዳኛ ፊት ወይም ለአንድ ነገር ምስክርነት መስጠት በሚያስፈልግበት ሰዓት አንዳችም ነገር ሳንቀንስና ሳንጨምር እውነቱን በሙሉ እንዳለ የመናገር ኃላፊነት ነው። እውነትን መሸሽግ ወይም እውነትን በከፊል ብቻ መናገር ውሸትና ስሕተት ነው። ሁለተኛ ስላደረግነውና ስላየነው ነገር እውነትን ብቻ የመናገር ኃላፊነት አለብን። ይህ ትእዛዝ ሐሜትንና የመሳሰሉትን ይቃወማል። 

በ. «የባልንጀራህን ቤት አትመኝ …።» መመኘት የብዙ ኃጢአት ምንጭ እንደሆነ ክርስቶስም፥ ጳውሎስም ተናግረዋል (ማቴ. 5፡20፤ ሮሜ 7፡7)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ማቴ. 22፡34-40 ሀ) ኢየሱስ ታላላቅ ያላቸው ሁለቱ ትእዛዛት ምንድን ናቸው? ለ) እነዚህ ሁለት ትእዛዛት ዓሥርቱን ትእዛዛት የሚጠቀልሉበት እንዴት ነው?

በብሉይ ኪዳን ከሚገኙ ሌሎች ሕጎች አብዛኛዎቹ እግዚአብሔርን እናከብር ዘንድ ከሚፈልጋቸው ከሁላቱ ኅብረቶች በአንዱ ላይ ማተኮር አለባቸው። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔርን የሚያከብሩና እርሱንም ስለማምለክ የሚናገሩ ሕጎች አሉ። ለምሳሌ፡- እስራኤላውያን እንዴት ማምለክ እንዳለባቸው (ዘጸ. 20፡22-26) እና ሊጠብቁዋቸው ስለሚገባቸው ሃይማኖታዊ በዓላት (ዘጸ. 23፡14-19) የተነገሩ ሕግጋት አሉ።

ሁለተኛ፡ እስራኤላውያን ከጎረቤቶቻቸው ጋር እንዴት መኖር እንዳለባቸው በግልጽ የሚናገሩ ሕግጋት አሉ። ምናልባት እነዚህን ሕግጋት ሁሉ ዛሬ መጠበቅ አስፈላጊ ባይሆንም እንኳ፥ እነርሱን በሚመለከት እርስ በርስ ሊኖረን ስለሚገባ ግንኙነት የምናወጣቸው በርካታ መመሪያዎች አሉ። አይሁድ አገልጋዮቻቸው የሆኑትን ሌሉች አይሁድ እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የሚናገሩ ሕግጋት ነበሩ (ዘጸ. 21፡2-11)። አንድ ሰው ወይም እንስሳ በሌላ ሰው ወይም እንስሳ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ጉዳት ሲደርስበት ሁኔታውን እንዴት መያዝ እንደሚገባ የሚናገሩ ሕግጋት ነበሩ (ዘጸ. 21፡12-36)። አንድ ሰው ንብረት ሲሰርቅ፥ ወይም ሲያበላሽ ሁኔታውን እንዴት መያዝ እንደሚያስፈልግ የሚናገሩ ሕግጋትም ነበሩ (ዘጸ. 22፡1-15)። በጋብቻ ውስጥ አለመተማመን በሚፈጠርበት ጊዜ ሁኔታውን እንዴት መያዝ እንደሚገባ የሚናገሩ ሕግጋት አሉ። ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር አሳብ ሰዎች ሁሉ በሰላምና በፍትሕ ተባብረው እንዲኖሩ ነበር (ዘጸ. 23፡1-9)። 

  1. እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግጋት ሰዎች ለሚሳተፉባቸው የተለያዩ ግንኙነቶች የሚጠቅሙ ትእዛዛት የሚገኙባቸው ናቸው። ከእነዚህ ሕጎች አብዛኛዎቹ በቀጥታ ተግባራዊ መሆን አለባቸው ማለት አይደለም። ነገር ግን እስራኤላውያን እርስ በርስ እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያሳዩ ምሳሌዎች ነበሩ። የተቀደሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደመሆናቸው መጠን በዚህ በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያሳዩ መመሪያዎች ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው። 

እነዚህን ሕጎች በምናጠናበት ጊዜ፥ ዛሬ ከሕይወታችን ጋር እንዴት እንደምናዛምዳቸው በጣም መጠንቀቅ አለብን። በመጀመሪያ ቋሚና ጊዜያዊ የሆኑ ሕግጋትን ለይተን ማወቅ አለብን፤ (ዘሌዋ. 17፤ ዘዳ. 12፡20-24 የጊዜያዊ ሕጎች ምሳሌዎች ናቸው)። አንድ ሕግ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ መሆኑን ለመለየት በጣም ጥሩው መንገድ፥ በአዲስ ኪዳን እንደ ሕጉ እንደገና ተደግሞ እንደ ሆነና እንዳልሆነ ማየት ነው። በሁለተኛ ደረጃ፥ ደግሞ እግዚአብሔር ሕጉን በሚሰጥበት ጊዜ የነበረውን ዓላማ ወይም ምክንያት ማየት ነው። እነዚህ የተለያዩ ሕጎች በተናጠል በዚህ ዘመን የማይሠሩ ቢሆኑም እንኳ በውስጣቸው ያለው መመሪያ ግን አሁንም ዋጋ ያለው ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 23፡1-9 አንብብ። እነዚህን ሕግጋት በሁለት ከፋፍለህ ተመልከታቸው። ሀ) በመጀመሪያ፥ ዛሬም ልንጠብቃቸው የሚገባን ቋሚ የሆኑ ሕግጋት የትኞቹ ናቸው? ለ) ሁለተኛ፥ ጊዜያዊ የሆኑ በተናጠል ለአንድ ሁኔታ ብቻ የሚጠቅሙ ሕግጋት የትኞቹ ናቸው? ሐ) ከእነዚህ ሕግጋት የምናገኛቸው ዛሬ ለሕይወታችን የሚጠቅሙን መመሪያዎች የትኞቹ ናቸው? መ) ከእነዚህ ሕግጋት መካከል ዛሬ በክርስቲያኖች ላይ ችግር የሚፈጥሩ የትኞቹ ናቸው?

በዘጸ. 24 የእስራኤል ሕዝብ በቃል ኪዳኑ ቅድመ ሁኔታዎች ሁሉ እንዴት እንደተስማሙ ያሳያል። በስምምነታቸውና በፈሰሰው ደም ቃል ኪዳኑን አጸኑት።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ዘጸአት 19-24”

Leave a Reply

%d bloggers like this: