ከዘጸአት 25-40 ባሉት ክፍሎች ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ቀርበዋል። 1) እግዚአብሔርን የማምለኪያ ስፍራ የሆነው የመገናኛው ድንኳን እንዴት መሠራት እንዳለበት የሚናገረው መመሪያ ሰፊውን ክፍል ይዟል። ቀጥሎም የእስራኤል ሕዝብ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ተቀብለው እግዚአብሔር የሚኖርበትን የመገናኛ ድንኳን እንዴት እንደሠሩ ይናገራል። 2) በሁለተኛ ደረጃ የካህናትና የሊቀ ካህኑ አልባሳት እንዴት እንደተሠሩ የሚናገር ክፍል እናገኛለን። 3) ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ የጥጃን ምስል ሠርተው እንዴት እንዳመለኩ የሚናገር ክፍል እናገኛለን።
የውይይት ጥያቄ፥ ዕብ. 8፡1-6፤ 9፡1-14 አንብብ። የዕብራውያን ጸሐፊ የቀድሞውን የመገናኛ ድንኳን ከክርስቶስ ሥራ ጋር በማወዳደር ያቀረበው እንዴት ነው?
የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 25-40 አንብብ። ሀ) በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ ዕቃዎች ዝርዝር። ለ) ለመገናኛው ድንኳን የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ የሰጠው ማን ነበር? ሐ) እግዚአብሔር የመገናኛው ድንኳን እንዲሠራ ያዘዘበትን የተለያዩ ምክንያቶች ዘርዝር። መ) ሙሴ በተራራው ላይ በቆየበት ጊዜ እስራኤላውያን ምን ኃጢአት ሠሩ? ሠ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የሙሴ ታላቅ መንፈሳዊ መሪነት የተገለጠው እንዴት ነው?
፩. የመገናኛው ድንኳን
እስከዚህ ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን በመሠዊያ ላይ ያመልኩ ነበር። የየቤተሰቡ ኃላፊም ለቤተሰቡ እንደ ካህን ያገለግል ነበር። መሠዊያ ሠርቶ፥ በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር የሚሆን እንስሳ ይሠዋ ነበር። በምድሪቱ ውስጥ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ፥ ሌሎች መሠዊያዎችን ይሠራ ነበር። አሁን ግን እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ስለ መረጠና ለሕዝቡ የሚሆን ሕግ ስለ ሰጠ፥ የአምልኮ መንገዳቸውን ለወጠው። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር እርሱን የሚያመልኩበት የመገናኛ ድንኳን እንዲሠሩ አዘዛቸው። ሁለተኛ፥ አምልኮውን ይመሩ ዘንድ ካህናትን ለዚህ ሥራ ለየ። በዚህ በዘጸአት ባለው የተወሰነ ክፍልና በኦሪት ዘሌዋውያን ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለማምለክ እንዴት መቅረብ እንዳለባቸው የተጻፉ ትእዛዛት አሉ።
የእስራኤል ንጉሥ በሆነው በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን ከተደረገና የእግዚአብሔር አገልጋዮችም ካጸኑት በኋላ፥ ሕዝቡ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት የመገናኛ ስፍራ ይሆን ዘንድ የመገናኛ ድንኳንን እንዲሠሩ አዘዘ። የመገናኛው ድንኳን እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን ለሕዝቡ የሚገልጥበትም ስፍራ ነበር። እግዚአብሔር እንዳለው «በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ» (ዘጸ. 25፡8)። የመገናኛው ድንኳን ዛሬ እንዳሉት ቤተ ክርስቲያኖቻችን ቋሚ ሕንጻ አልነበረም። እስራኤላውያን በሚሄዱበት ስፍራ ሁሉ በውስጡ ካሉት ዕቃዎች ጋር ይዘው ለመሄድ እንዲችሉ ተደርጎ የተሠራ ነበር። ቤተ መቅደሱ ቋሚ የማምለኪያ ስፍራ ተደርጎ በሰሎሞን የተሠራው ከ400 ዓመታት በኋላ ነበር።
ስለ መገናኛው ድንኳን የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-
- የመገናኛው ድንኳን አንድ ብቻ ነበር እንጂ እንደ አሕዛብ የማምለኪያ ስፍራ ብዙ አልነበረም። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በመገናኛው ድንኳን ብቻ እንዲያመልኩ አዘዛቸው። ይህም እስራኤላውያንን ከመኮብለልና ሐሰተኞች አማልክትን ከማምለክ ለመጠበቅ ነበር።
- የእስራኤል ሕዝብ የመገናኛውን ድንኳን ለመሥራት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን የመስጠት ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር። የእስራኤል ሕዝብ የመገናኛውን ድንኳን ለመሥራት ምን ያህል ከፍተኛ ጉጉት እንደነበራቸው የምናየው ለመሥሪያ ከሚያስፈልጉ ነገሮች በላይ በመስጠታቸው ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ሙሴ ሕዝቡን ከመስጠት እንዲቆጠቡ ይነግራቸው ነበር (ዘጸ. 36፡2-7)።
- የመገናኛው ድንኳን የሚገኘው በእስራኤላውያን ሠፈር መሐል ነበር። ይህም እግዚአብሔርን ማምለክ በሕይወታቸው ከሁሉ በላይ አስፈላጊ ነገር መሆኑን የሚያሳይ ነበር (ዘኁል. 2፡17)።
- የእግዚአብሔር መገኘት የተቀደሰ መሆኑንና ከኃጢአትም መለየቱን ለማመልከት፥ ከሕዝቡ በሐር መጋረጃ ተለይቶ ነበር።
ለመገናኛው ድንኳን አራት የተለያዩ ክፍሎች ነበሩት። የመጀመሪያው፥ ከመገናኛው ድንኳን ውጭ ያለው ስፍራ ነው። ሰዎች እግዚአብሔርን ስለማምለክ አንዳችም ትኩረት ሳያደርጉ ሊመላለሱና ሊሠሩ የሚችሉበት ስፍራ ነው። ይህም ሕዝቡ የሚኖሩበት ስፍራ ነው። ሕዝቡን ከመገናኛው ድንኳን የሚለየው መጋረጃ ነበር። የመገናኛው ድንኳን እግዚአብሔር የሚያድርበትና እርሱ ሊመለክበት የሚገባ ስፍራ መሆኑ በግልጽ ታውቆ መከበር የሚገባው ነበር።
በሁለተኛ ደረጃ፥ ውጫዊው ክፍል ወይም «አምልኮ የሚፈጽሙ ሰዎች ያሉበት ክፍል» የሚባል ስፍራ ነበር። በዚህ ክልል ለአምልኮ የሚያገልግሉ ሁለት ዋና ዋና ዕቃዎች ነበሩ። እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡
1) የነሐስ መሠዊያ፡- መሠዊያው 2.5 ካሬ ሜትር ስፋትና 1 ሜትር ከፍታ ነበረው። እርሱም መሥዋዕቶች ሁሉ የሚቀርቡበት ትልቅ መሠዊያ ነበር። ማንኛውም ተራ ሰው ወደ እግዚአብሔር በመምጣት አምልኮ ለመፈጸም የሚችልበት ስፍራ ነበር። ከዚህ የበለጠ ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ ግን አይችልም ነበር። ከዚህ የበለጠ በመቅረብና ወደ መገናኛው ድንኳን ውስጥ በመግባት ለማምለክ የሚችሉት ካህናት ብቻ ነበሩ።
2) የነሐስ መታጠቢያ፡- ይህም የተሠራው ከነሐስ ሲሆን፥ በውስጡ ውኃ ይደረግበት ነበር። ካህናት ወደ ቅድስት በመግባት እግዚአብሔርን ከማምላካቸውና ከማገልገላቸው በፊት፥ ንጽሕና ከጎደላቸው ከማናቸውም ነገሮች መንጻታቸውን ለማሳየት፥ እግሮቻቸውን የሚታጠቡት በዚህ ውኃ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፥ ይኸው መንፈሳዊ መንጻት በዚህ ዘመን ላሉ መሪዎች የሚያስፈልገው እንዴት ነው?
በሦስተኛ ደረጃ፥ የሚገኘው ስፍራ ቅድስት ተብሎ የሚጠራው ነው። በዚያ በሰፊው የመገናኛ ድንኳን ክልል ውስጥ አነስተኛ ድንኳን ነበር። ይህ ድንኳን ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፥ ሰፊው ክፍል ቅድስት ይባል ነበር። ቅድስት የተባለው ስፍራ እግዚአብሔር ለማገልገል ኃላፊነት ያለባቸው ካህናት በየዕለቱ አገልግሎታቸውን የሚፈጽሙበት ስፍራ ነበር። ቅድስት በተባለው ስፍራ ሦስት የአምልኮ ዕቃዎች ነበሩ።
1) በስተሰሜን በኩል የኅብስቱ መቀመጫ ወርቃማ ጠረጴዛ ነበር። የተሠራው ከግራር እንጨት ሲሆን በወርቅ ተለብጦ ነበር። በጠረጴዛው ላይ እያንዳንዳቸው አንዳንድ የእስራኤል ነገድ የሚወክሉ እርሾ የሌለባቸው አሥራ ሁለት ቂጣዎች ነበሩ። እነዚህ በየሳምንቱ እየተቀየሩ ካህናቱ ይበሏቸው ነበር።
2) በደቡብ የቅድስት ክፍል ደግሞ የወርቅ መቅረዝ ነበር። መቅረዙ ሰባት ቅርንጫፎች ነበሩት። በየጠዋቱና በየምሽቱ የሚሆነውን ነገር ለማድረግ ካህናቱ ይከታተሉ ነበር። መቅረዞቹም ሌሊቱን በሙሉ ሲበሩ ያድሩ ነበር።
3) በምዕራብ በኩል ቅድስትን ከተከታዩ ክፍል ከሚለየው መጋረጃ አጠገብ፥ ከወርቅ የተሠራ የዕጣን መሠዊያ ነበር። ይህ መሠዊያ ከነሐስ መሠዊያው የሚያንስ ሲሆን፥ 1.2 ካሬ ሜትር ቁመት ነበረው። በዕጣን መሠዊያው ላይ ካህናቱ በየቀኑ ጥዋትና ማታ ዕጣን ያጥኑበት ነበር።
በአራተኛ ደረጃ፥ ቅድስተ ቅዱሳን የሚባል ስፍራ ነበር። ይህ አነስተኛ ክፍል ሲሆን፥ የያዘውም ታቦት ብለን የምንጠራውን አንድ የአምልኮ ዕቃ ብቻ ነበር። ይህ የእግዚአብሔር ዙፋን ስለነበር፥ ከመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች ሁሉ የሚበልጥና የተቀደሰ ነበር። ታቦቱም ከግራር እንጨት የተሠራ ሆኖ በወርቅ የተለበጠ ነበር። ከ1 ሜትር ትንሽ የሚበልጥ ርዝመት ሲኖረው፥ 0.75 ሜትር ቁመትና ጎን ነበረው። ታቦቱ ክዳን ያለው ሳጥን ይመስል ነበር። በክዳኑ ጫፍና ጫፍ ላይ ክንፎቻቸው የሚያንዣብቡ የሚመስሉ ከወርቅ የተሠሩ የሁለት ኪሩቦች ምስል ነበረበት። ከሁለቱ ኪሩቦች ክንፎች በታች ያለው የክዳኑ ክፍል «የሥርየት መክደኛ» በመባል ይታወቅ ነበር። ምክንያቱም በዓመት አንድ ጊዜ እግዚአብሔር የሕዝቡን ኃጢአት ይቅር ይል ዘንድ ደም የሚረጨው በዚህ ስፍራ ላይ ስለነበር ነው። የእግዚአብሔር ክብር የሚያድረውም በሥርየት መክደኛው ላይ ነበር። ይህም ዙፋኑ ነበር። ከቅድስተ ቅዱሳን ንጉሥ ሆኖ እስራኤልን ያስተዳድር ነበር። ይህ የመገናኛው ድንኳን ክፍል እጅግ የተቀደሰ ስፍራ ስለነበር በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ወደ እርሱ የመግባት ሥልጣን ያለው ሊቀ ካህኑ ነበር።
በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ዓሥርቱ ትእዛዛት የተጻፈበት ጽላት (ዘጸ. 25፡21)፥ መና ያለበት ማድጋ (ዘጸ. 16፡32-34) እና ያቆጠቆጠች የአሮን በትር (ዘኁል. 17፡10) ነበሩበት። ኋላም የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበት መጽሐፍ በታቦቱ አጠገብ እንዲቀመጥ ተደረገ (ዘዳ. 31፡26)።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የመገናኛውን ድንኳን በመሥራት ረገድ ከምናየው ከፍተኛ ጥንቃቄና ሰፊ ተግባር ውስጥ የምንማራቸው አንዳንድ መንፈሳዊ መመሪያዎች ምንድን ናቸው? ለ) ከአራቱ ክፍሎች ውስጥ እግዚአብሔርን ስለ ማምለክ የምንማረው ነገር ምንድን ነው?
አንዳንድ ክርስቲያኖች እነዚህ የአምልኮ ዕቃዎች ወደ ክርስቶስ ያመለክታሉ ይላሉ። ለምሳሌ፡-
ሀ) የነሐስ መሠዊያው፥ ክርስቶስ በእኛ ምትክ መሥዋዕት የመሆኑ ምልክት ነው (ሮሜ 5፡8)።
ለ) የነሐስ መታጠቢያው፥ ክርስቶስ ከኃጢአታችን እንደሚያነጻን ያመለክታል (1ኛ ዮሐ. 1፡9)።
ሐ) የኅብስቱ ጠረጴዛ፥ ክርስቶስ የሕይወት እንጀራ መሆኑን ያመለክታል (ዮሐ. 6፡51)።
መ) የወርቅ መቅረዙ፥ ክርስቶስ የዓለም ብርሃን የመሆኑ ምልክት ነው (ዮሐ. 8፡12)።
ሠ) የዕጣን መሠዊያው፥ ክርስቶስ አማላጃችን መሆኑን ያመለክታል (ዕብ. 7፡25)።
ረ) የቃል ኪዳኑ ታቦት ክርስቶስ ንጉሣችን መሆኑን ያመለክታል (ራእ. 19፤ 16)።
ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ለመረዳት «ክርስቶስ በማደሪያው ድንኳን» የሚለውን መጽሐፍ ማጥናት ትችላለህ።
- የመገናኛውን ድንኳን ለመሥራት እግዚአብሔር ሁለት ሰዎችን መርጦ ኃይል አስታጠቃቸው። እነዚህ ሰዎች ባስልኤልና ኤልያብ ይባሉ ነበር፤ (ዘጸ. 31፡1-11)። እግዚአብሔር የስብከትና ወንጌልን የማስተማር ሥራ እንደሚያከብር ሁሉ፥ የእጅ ሙያንም ያከብራል።
ችሎታዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው።
- የመገናኛው ድንኳን ሥራ በተጠናቀቀ ጊዜ፥ እግዚአብሔር የክብር ደመናውን በማውረድ ሥራቸውን ሁሉ እንደተቀበለ አረጋገጠ። ሕዝቡን ሲመራቸው የነበረው ደመና በመገናኛው ድንኳን ላይ ወረደና ሞላው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር ክብር ከመገናኛው ድንኳ በሚነሣበት ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን ለመከተል ይንቀሳቀሱ ነበር (ዘጸ. 40፡34-38)።
የውይይት ጥያቄ፥ ዮሐ. 1፡14ን አንብብ። «በእኛ አደረ» ማለት «በእኛ መካከል የመገናኛው ድንኳን ሆነ» ማለት መሆኑን አስተውል። ሀ) ይህ ጥቅስ፥ በዘጸ. 40 ከተጠቀሰው ታሪክ ጋር የሚነጻጸረው እንዴት ነው? ለ) ይህ ስለ ክርስቶስ ምን ያስተምረናል?
፪. የካህናት አልባሳት
ከዚህ ቀደም፥ ከሙሴ ዘመን በፊት የቤተሰቡ ካህን የቤተሰብ ኃላፊ የሆነው ሰው እንደነበረ ተመልከተናል። ለእግዚአብሔር መሥዋዕትና ለመሠዋት ኃላፊነት የተሸከመው ሰው እርሱ ነበር። አሁን ግን እግዚአብሔር ያንን አሠራር ለወጠው። እርሱን ያገለግለው ዘንድ አንድ የእስራኤል ነገድ ለየ። ያም የተለየ ነገድ የሌዋውያን ነገድ ነበር። በብሉይ ኪዳን ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን እንዲሠሩ የተፈቀደላቸው ሌዋውያን ብቻ ነበሩ። በተጨማሪ የተመረጡ መንፈሳዊ መሪዎች እንዲሆኑ ከሌዋውያን መካከል እግዚአብሔር አንድ ቤተሰብን ለየ። እነርሱም አሮንና ልጆቹ ናቸው። የአሮን ዝርያዎች ካህናት ሆኑ። ለመገናኛው ድንኳን አጠቃላይ አገልግሎት ኃላፊነት የነበራቸው ሌዋውያን ሲሆኑ፥ ካህናቱ ደግሞ እግዚአብሔርን የማምለክ ፕሮግራም ይመሩ ነበር። በብሉይ ኪዳን ዘመን ካህናት ለሚከተሉት ነገሮች ኃላፊነት ነበረባቸው፡-
- ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን በመሠዋትና ለሕዝቡ የኃጢአት ይቅርታን በማስገኘት፥ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል መካከለኛ ሆኖ የማስታረቅን ተግባር መፈጸም ዋና ሥራቸው ነበር (ዘጸ. 28፡29-30፥43)።
- ብዙ ጊዜ ኢሪምና ቱሚም በመጠቀም ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይለዩ ነበር (ዘኁል. 27፡21)።
- ቅዱሳት መጻሕፍትን የመገልበጥና ጠብቆ የማቆየት ኃላፊነት በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል የማስተማር ኃላፊነት ነበረባቸው።
- በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚፈጸሙ ዕለታዊ ተግባራትን ማከናወንና በኃላፊነት መቆጣጠር ነበረባቸው።
የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህ ኃላፊነቶች ዛሬ የቤተ ክርስቲያን መሪዎቻችን ካለባቸው ኃላፊነቶች ጋር የሚመሳሰሉት ወይም የሚለያዩት እንዴት ነው?
ካህናት ምን ዓይነት ሰዎች መሆንና በማደሪያው ድንኳን እንዴት ማገልገል እንዳለባቸው እግዚአብሔር ዝርዝር መመሪያዎችን ስለሰጠ፥ ቆይተን እርሱን እንመለከታለን። እንዲሁም ካህናት እንዴት መሥራት እንዳለባቸው መመሪያዎችን ሰጥቷል።
ካህናት መንፈሳውያን መሪዎች ስለሆኑ፥ ለእግዚአብሔር ራሳቸውን በቅድስና መጠበቅ ነበረባቸው። በእግዚአብሔር ፊት ላላቸው ልዩ ስፍራ መለያና ከመቀደሳቸው አስፈላጊነት አንጻር፥ እግዚአብሔር ልዩ የሆኑ ልብሶችን ሰጣቸው።
- በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት ልብሶች፡- አገልጋዮች እንደ መሆናቸው ካህን መልበስ ያለበት አራት ዓይነት ልብሶች፡-
ሀ. ረጅምና ያልተሰፋ፥ እስከ እግር ድረስ የሚወርድ እጅጌ ያለው ኮት፥
ለ. በሰማያዊ፥ በሐምራዊና በቀይ ጨርቆች የተሠራ የወገብ መታጠቂያ፡
ሐ. በራስ ላይ የሚደፋ ቆብ፥
መ. ከኮት ሥር የሚለበስ በፍታ የሆነ ዝንጉርጉር የውስጥ ልብስ ነበሩ።
- የሊቀ ካህኑ ልብሶች በጣም የተለዩና ከሌሎች ካህናት ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርጉት ነበሩ። እነዚህን ልብሶች የሚለብሰውም በመገናኛው ድንኳን በሚያገለግልበት ጊዜ ብቻ ነበር።
ሀ. ረጅም መጎናጸፊያ፡- ይህ ከአንገት ጀምሮ እስከ ጉልበት በታች ድረስ የሚደርስ ልብስ ነው። መልኩ ሰማያዊ ሲሆን፥ ሮማኖችና የወርቅ ሻኩራዎች (ቃጭሎች) ነበሩበት። ሻኩራ ለሁለት ምክንያት ጠቃሚዎች ነበሩ፡- አንደኛ፥ ሊቀ ካህኑ በመገናኛው ድንኳን በሚያገለግልበት ጊዜ፥ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በመግባት ላይ መሆኑን ማስጠንቀቂያ ነበሩ (ዘጸ. 28፡35)። ሁለተኛ፥ ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ሲገባ፥ እንቅስቃሴ በማሰማት በሕይወት እንዳለና ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር እንዳልቀሠፈው ሕዝቡ እንዲያውቁ ነበር።
ለ. ኤፉድ፡- ከተልባ እግር የተሠራ (በፍታ)፥ ሁለት ጨርቆች የያዘና በሊቀ ካህኑ ትከሻ የሚያርፍ ነበር። መልኩም በወርቅ፥ በሰማያዊ፥ በሐምራዊና በቀይ ግምጃ የተፈተለ ነበር። ለሁለቱ ጫፎች እያንዳንዳቸው ስድስት ስድስት የእስራኤል ነገዶች ስሞች የተጻፉባቸው መረግድ (የከበረ ድንጋይ) ነበረባቸው። ይህም የሚያመለክተው፥ ሊቀ ካህኑ የእስራኤልን ነገዶች እንደሚወክልና በጌታ ፊት ሸክማቸውን እንደሚያቀርብ ነበር።
ሐ. የደረት ኪሱ 25 ካሬ ሳንቲሜትር የሆነ ጠፍጣፋ ነገር፥ በብዙ ኅብረ ቀለም ያሸበረቀ ነው፤ ሁለት ዓላማዎችም ነበሩት። የመጀመሪያ፥ በእያንዳንዳቸው ላይ የእስራኤል ነገዶች ስም የተጻፉባቸው አሥራ ሁለት ዕንቁዎች ተሰፍተውበት ነበር። እነዚህም ድንጋዮች ሊቀ ካህኑ እግዚአብሔር ፊት እንዴት ሕዝቡን እንደሚወክል የሚያሳዩ ነበሩ። በደረቱ (በልቡ) ላይ መሆናቸው፥ በፍቅርና በርኅራኄ አሥራ ሁለቱን የእስራኤል ነገዶች ማገልገል እንዳለበት የሚያሳዩ ሊሆኑ ይችላሉ። በሁለተኛ ደረጃ፡ በደረቱ ላይ ባለው ጠፍጣፋ ነገር ሁለት ኪሶች ነበሩ። በሁለቱ ኪሶች ውስጥ ኡሪምና ቱሚም የሚባሉ ሁለት ልዩ ድንጋዮች ነበሩ። እነዚህ ሁለት ድንጋዮች ምን እንደሆኑ በእርግጥ የምናውቀው ነገር የለም። የስማቸው ትርጉም «ብርሃንና» «ፍጹምነት» የሚል ነው። የምናውቀው ነገር የጌታን ፈቃድ ለመወሰን አገልግሎት ላይ መዋላቸውን ነው (ዘኁል. 27፡21)።
መ. ሊቀ ካህኑ በቅጠል ቅርፅ በወርቅ የተሠራና በግንባር ላይ የሚንጠለጠል ነገርም ያደርግ ነበር። በላዩ ላይ «ቅድስና ለእግዚአብሔር» የሚል ጽሑፍም ነበረበት። ይህም የሚያመልኩት አምላክ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሆነ የሚያስታውስ ነበር፤ ስለዚህ ወደ እርሱ ሊቀርቡ የሚገባቸው በተቀደሰ ሕይወት ነበር። በተጨማሪም ሊቀ ካህኑ ለኃጢአት መሥዋዕትን በማቅረብ፥ ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎችን በእግዚአብሔር ፊት እንዴት የተቀደሱ እንደሚያደርጋቸው የሚያመለክት ነበር።
ካህናቱን ለአምልኮ ሥራ ለመለየት ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ ነበር። ለኃጢአታቸው የሚሆኑ መሥዋዕቶችም ነበሩ። ለተለየ አገልግሎት በእግዚአብሔር መለየታቸውን የሚያሳይ ዘይት የመቀባት ሥርዓትም ነበራቸው። በቀኝ አውራ ጣታቸው ላይ፥ በጆሮአቸውና በትልቁ የእግር ጣታቸው ላይ የደም መረጨት ሥርዓትም ይካሄድ ነበር። ይህም የእግዚአብሔርን ቃል መስማት፥ የጌታን ሥራ መሥራትና፥ በእግዚአብሔር መንገድ መሄድ እንዳለባቸው የሚያሳይ ለመሆኑ አንዳችም ጥርጥር የለውም።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ካህናትን በማንጻትና ለአገልግሎት በማዘጋጀት ይህን ያህል ጥንቃቄ ያደረገው ለምን ይመስልሃል? ለ) ስለ ቤተ ክርስቲያን አመራር ከዚህ የምንማረው ምን ይመስልሃል?
፫. የጥጃ ምስል በማምለክ ሕዝቡ የሠሩት ኃጢአት
ስለ እስራኤል ሕዝብ ታሪክ የሚያስደንቅ ነገር፥ እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር በተገናኘበት ተራራ ጫፍ ላይ እንኳ ቆመው፥ ከእግዚአብሔር ፊታቸውን መልሰው ኃጢአት መሥራታቸው ነበር። ወደ ተራራው በመመልከት የእግዚአብሔርን ሕልውና በደመናው ውስጥ ማየት ይችሉ ነበር። ኃያል የሆነውን እግዚአብሔር በመብረቅ፥ በነጎድጓድና በመሬት መንቀጥቀጥ ውስጥ ካዩና ሲናገራቸው ኃያል ድምፁን ከሰሙ ገና ጥቂት ጊዜ አልፎ ነበር። ይህም ቢሆን እንኳ ሙሴ እስኪመለስ ለ40 ቀናት መቆየት አልቻሉም። ሙሴ ሞቷል ብለው በመገመት እግዚአብሔርን ትተው፥ ጣዖትን ወደ ማምለክ ዞር አሉ። እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር አውጥቶአቸው ነበር፤ ነገር ግን በግብፅ ምድር የነበረው የጣዖት አምልኮ ከልባቸው አልወጣም ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን ትተው ከግብፅ ያወጣን አምላካችን ነው በማለት ከግብፅ አማልክት መካከል አንዱ የሆነውን ጥጃን ያመልኩ ጀመር (ዘጸ. 32፡4)።
እግዚአብሔር ይህንን ባየ ጊዜ የሰጠው ምላሽ ከባድ ነበር። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በሙሉ በማጥፋት በሙሴ በኩል አዲስ ሕዝብን ለማስነሣት ወሰነ። ሙሴ ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዳያጠፋ ለመነ። በዚህ ስፍራ ሙሴ ያለውን ነገር አስተውሉ መመልከት ጠቃሚ ነው (ዘጸ. 32፡11-14)። በመጀመሪያ፥ ለእግዚአብሔር ስምና ክብር የሰጠውን ትኩረት እንመለከታለን። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ካጠፋ፥ የእግዚአብሔርን ኃይል የመሰከሩት ሕዝቦች ይህንን ተግባር በተሳሳተ መንገድ ይተረጉሙታል። የሙሴ ትኩረት እግዚአብሔር የሚገባውን ክብር በመቀበሉ ላይ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር በአብርሃም በይስሐቅና በእስራኤል በኩል ለራሱ ልዩ ሕዝብ እንደሚያስቀር ቃል የገባውን እንዲያስታውስ ይጠይቀዋል። እግዚአብሔር ከእስራኤል ፍርዱን ይመልስ ዘንድ የሙሴን የአስታራቂነት አገልግሎት ተቀበለ።
የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) ከዚህ ታሪክ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ የምንማረው ነገር ምንድን ነው? ለ) ከዚህ ክፍል ስለ ሙሴ ባሕርይ የምንማረውስ ነገር ምንድን ነው?
ነገር ግን ሙሴ የሕዝቡን ኃጢአት በተመለከተ ጊዜ፥ የወሰደውን እርምጃ መመልከት አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር በገዛ እጁ ቀርፆ ዓሥርቱን ትእዛዛት የጻፈበትን የድንጋይ ጽላት በቁጣ ሰባበረው። በሁለተኛ ደረጃ፥ ከወርቅ የተሠራውን የጥጃ ምስል ሰባብሮ ፈጨና በውኃ ተበጥብጦ ሕዝቡ እንዲጠጡት አደረገ። በሦስተኛ ደረጃ፥ ሕዝቡ ውሳኔ እንዲያደርጉ ጥሪ አደረገላቸው። ከጌታ ወገን የሆኑ በእርሱ በኩል እንዲሆኑ አደረገ። ሌዋውያን ወደ እርሱ ሲመጡ፥ የእግዚአብሔር የፍርዱ መሣሪያ እንደሆኑ ገልጾላቸው፥ ወንድሞቻቸው የሆኑትን እስራኤላውያን እንዲገድሉ አዘዘ። ሌዋውያኑም የሙሴን ትእዛዝ በመከተል በዚያን ቀን ብቻ ሦስት ሺህ እስራኤላውያንን ገደሉ።
የውይይት ጥያቄ፥ ) ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም አስቸጋሪ የሆነው ለምን ነበር? ለ) ይህ ነገር ስለ ኃጢአት አስቸጋሪነት (አስጨናቂነት) እና በጽኑ ሊፈረድበት እንደሚገባም ምን ያስተምረናል?
ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ በመሄድ ለሕዝቡ መለመን ጀመረ። እንደገና የሙሴን የአመራር ብቃትና ታላቅነት እንመለከታለን። የተጨነቀው ለእግዚአብሔር፥ ለክቡሩና ለቃል ኪዳኑ ላለው ታማኝነት ብቻ ሳይሆን፥ ለእግዚአብሔር ሕዝብም ነበር። ሙሴ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት የሠሩትን ታላቅ ክፋት አምኖ ተቀበለ። ከዚያም ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን ለመነ። እግዚአብሔር ይቅር ሊላቸው ፈቃደኛ ካልሆነ፥ በሕዝቡ ፈንታ የራሱን የዘላለም ሕይወትን ሊሰጥ ዝግጁ መሆኑን ተናገረ። ከሕይወት መጽሐፍ ስሙን እንዲደመስስ እግዚአብሔርን ለመነ፤ (ዘጸ. 32፡32)።
ሙሴ በመሪነቱ ልዩና ታላቅ እንደነበር የሚያሳዩ ሌሎች ሁለት ታሪኮች አሉ። የመጀመሪያው፥ የመገናኛው ድንኳን ተሠርቶ ከመጠናቀቁ በፊት እንኳ ሙሴ ከሰፈር ውጪ ድንኳን ተክሎ እንደነበር የሚናገረው ታሪክ ነው። ይህ ድንኳን እስራኤላውያን የሚገናኙበት ነበር። ደግሞም ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበት ስፍራ ነበር። ለእግዚአብሔር ቅርብ ከመሆኑ የተነሣ፥ የእግዚአብሔር ክብር ከፊቱ ያንጸባርቅ ነበርና ሕዝቡ ሊያዩት ባለመቻላቸው ሙሴ ፊቱን ይሸፍን ነበር። ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ተገናኝቶ ሲያበቃ ድንኳኑን በሚለቅበት ጊዜ፥ ኢያሱ ግን እዚያው ይቆይ እንደነበር መመልከቱ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ (ዘጸ. 33፡11)።
ሁለተኛው ነገር፥ ሙሴ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያለማቋረጥ መምራት ይችል ዘንድ የእግዚአብሔር መገኘት ሁልጊዜ ያስፈልገው እንደ ነበር መገንዘቡ ነው፤ ስለዚህ እንዳይተወው እግዚአብሔርን ለመነ። ክብሩንም እንዲያሳየው ለምኖታል። እግዚአብሔር በቸርነቱ ለዚህ ልመናው መልስ ሰጠውና በሙሴ ፊት ክብሩን አሳለፈ።
የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 32-33 እንደገና አንብብ። ሀ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ሙሴ እግዚአብሔርን የሚፈራ ታላቅ መሪ መሆኑን የሚያሳዩትን ነገሮች ዘርዝር። ለ) እነዚህን እውነቶች ዛሬ በቤተ ክርስቲያን አመራር ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ልናደርጋቸው እንችላለን?
በኦሪት ዘጸአት ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ትምህርቶች፡-
- እግዚአብሔር፡- የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ዓላማ ለሕዝቡ ያለውን የእግዚአብሔር ባሕርይና ሥራ መግለጥ ነው፤ ስለዚህ በዘጸአት ውስጥ ስለ እግዚአብሔር የምናያቸው በርካታ እውነቶች አሉ።
የውይይት ጥያቄ፥ ዘጸ. 3፡13-15 አንብብ። እግዚአብሔር በሚቃጠለው ቁጥቋጦ ውስጥ ራሱን በገለጸ ጊዜ ለሙሴ የተሰጠው ስም ማን ነበር?
ሀ. ያህዌ የእግዚአብሔር ልዩ ስሙ ነው፡- በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ በእግዚአብሔር የተሰጡ የተለያዩ ስሞችን ተመልክተናል። በጣም በብዛት ያየናቸው ግን ኤሎሄምና አዶናይ የሚሉትን ስሞች ነበር። እንደምታስታውሰው፥ የእግዚአብሔር «ስም» በዕብራውያን ባሕል የእግዚአብሔር ባሕርይ የሚገልጥ ነው። በኦሪት ዘጸአት እግዚአብሔር ሙሴን በተገናኘው ጊዜ ልዩ የሆነ ባሕርይውን ለሙሴ የሚገልጥበትን ያህዌ ያለውን የራሱን አዲስ ስም ስጠው። ይህ ስም «እኔ፥ እኔ ነኝ» የሚል ነበር። በዕብራይስጥ ይህ ሐረግ «ጄሆቫ» ወይም «ያህዌ» የሚል ነው። በኋላ አይሁድ ይህ ስም ከሁሉም በላይ የተቀደሰው የእግዚአብሔር ስም ነበር ብለዋል።
የእግዚአብሔር ስም ጄሆቫ ወይም ያህዌ የተባለው ለምንድን ነው? የዕብራይስጥ ቋንቋ የሚጻፈው ምንም አናባቢ በሌለው ፊደላት ብቻ ነበር። ስለዚህ ይህ ስም በዕብራይስጡ ያለ አናባቢ ሲጻፍ ይሆናል። አይሁድ በምርኮ ወደ ባቢሎን ከተወሰዱና ከምርኮም ከተመለሱ በኋላ ይህን ይህውህ በሚለው የእግዚአብሔር ስም መጠቀም አቆሙ። ምክንያቱም ይህ ስም ለማንበብ በጣም የተቀደሰ ነው ብለው ስላመኑ ነበር። ስለዚህ እንደ ኤሉሂምና አዶናይ ያሉትን ሌሎች ስሞች ወይም ደግሞ «ቅዱሱ» ወይም የመሳሰሉትን ስሞች ብቻ መጠቀም ቀጠሉ። ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አይሁድ የአጻጻፍ ስልታቸውን ለወጡና ሰዎች ዕብራይስጥን ለማንበብ ማስታወስ ይችሉ ዘንድ አናባቢዎችን ማከል ጀመሩ፤ ስለዚህ ወደ ይህውህ ሲደርሱ፥ አዶናይ የሚለውን ስም ያስገኙትን አናባቢዎች እዚህም ላይ አከሉበት። (እነርሱም በላቲን ፊደል አ፡ኦ፡አ የሚሉት ሲሆኑ በሚጻፍበት ጊዜ ያህዌ የሚል ሆነ።) ይህንን ያደረጉበት ዋና ምክንያት ሰዎች ይህውህ ብለው ከማንበብ ይልቅ፥ አዶናይ እንዲሉ ነበር። በ1520 ዓ.ም. አካባቢ ግን ይህ የእግዚአብሔር ስም በትክክል ሥርዓት እንዲይዝ ተደረገና ጄሆቫ (ያህዌ) ተባለ። ይህንን ስም በቀላሉ የምታስታውሰው፥ የይሖዋ ምስክሮች ተብሎ የሚጠራ የሐሰት ትምህርትን የሚከተሉ ክፍል በመኖሩ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ግን እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው የመጀመሪያው ስም መነበብ ያለበት ያህዌ ወይም ጃሄዌ ተብሉ እንጂ ጄሆቫ (ይሖዋ) ተብሎ አይደለም ብለው ያምናሉ።
ይህውህ የሚለው ቃል በዕብራይስጥ «እኔ ነኝ»፥ ወይም «እርሱ ነው»፥ ወይም «እርሱ ይሆናል» የሚል ትርጉም ከሚሰጠው ግሥ ጋር አንድ ዓይነት ነው። ይህም እስራኤላውያን ስለ እርሱ ባሕርይ እንዲያስታውሱ እግዚአብሔር የፈለገው ልዩ ስም ነው። እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ለእነርሱ ለመግለጥ የተጠቀመበት የቃል ኪዳን ስም ነው። ይህ ስም ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ «እኔ ነኝ» እያለ የተናገራቸው ዐረፍተ ነገሮች ሁሉ የተመሠረቱበት ስም ነው። ለምሳሌ፡- «እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ»፤ «እኔ የሕይወት ውኃ ነኝ»፤ «እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ» ወዘተ. እያለ በዮሐንስ ወንጌል የሰጣቸው መግለጫዎች ማለት ነው።
እግዚአብሔር ይህንን ስም በርካታ መንፈሳዊ እውነቶችን ለመግለጥ የተጠቀመበት ይመስላል። በመጀመሪያ፥ ዘላለማዊ የሆነውን የእግዚአብሔርን ባሕርይ በመግለጥ፥ እርሱ መጀመሪያና መጨረሻ እንደሌለው ያሳየናል። እርሱ ምንጊዜም ነበር። እግዚአብሔር ለሙሴ ሊያሳየው የፈለገው ነገር እርሱ ከዓለም መፈጠር መጀመሪያ የነበረው፥ ደግሞም ከእስራኤል ሕዝብ አባቶች ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን ያደረገው አምላክ መሆኑን ነው። በሁለተኛ ደረጃ፥ ደግሞ ይህ ስም እግዚአብሔር ራሱ የሕይወት ኃይል እንዳለውና ስለ ሕያውነቱ በማንም ወይም በምንም ነገር ላይ ያለመደገፉን ያሳያል። በሦስተኛ ደረጃ፥ ደግሞ እግዚአብሔር የማይታወቅ አምላክ እንዳልሆነ፥ የሩቅ አምላክም እንዳልሆነ ይልቁንም ለሚወዱትና በእርሱ ለሚያምኑ ቅርብ መሆኑን ያስተምረናል። አራተኛ፥ ይህ ስም እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ የሆነ፥ ብቃት ያለው በመሆኑ ሕዝቡ በምንም ሁኔታ ውስጥ ይሁኑ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን ያሳያል።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ለሙሴ ይህንን ስም መግለጥ ያስፈለገው ለምን ይመስልሃል? ለ) የዚህን ስም ትርጉም ማወቅ ለእኛ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ሐ) የእግዚአብሔርን ስምና ባሕርይ ማወቅ ዛሬ እኛን እንዴት ያበረታታናል?
ለ. እግዚአብሔር ራሱን ለሰዎች የገለጠባቸው የተለያዩ መንገዶች፡-
በኦሪት ዘጸአት ውስጥ የምናገኘው አንድ አስደናቂ እውቀት እግዚአብሔር ራሱን ለእስራኤል ሕዝብ የገለጠባቸው በርካታ መንገዶች ናቸው። እግዚአብሔር በአንድ መንገድ ብቻ ለመሥራት ራሱን አልወሰነም። ራሱን ለመግለጥ የተጠቀመው በተጻፈ ቃል፥ በፍጥረት፥ በሕልም ወዘተ. ብቻ አይደለም። በታሪክ ውስጥ ራሱን ለሕዝቡ የገለጠባቸው በርካታ የተለያዩ መንገዶች አሉ። ኦሪት ዘጸአትን በምታነብበት ጊዜ እግዚአብሔር ራሱን የገለጠባቸውን የሚከተሉትን መንገዶች አስተውል፡-
- «በጌታ መልአክ» በኩል (ዘጸ. 3፡2፤ 14፡19) ከኦሪት ዘፍጥረት ጥናታችን ውስጥ እንደምታስታውሰው፥ ይህ መልአክ እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራ ልዩ መልአክ ነው። ይህ መልአክ በቤተልሔም ከመወለዱ በፊት የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይሆን አይቀርም።
- በሌሎች መላእክት (ዘጸ. 23፡20፤ 33፡2)
- በተአምራት (ዘጸ. 8፡ 16-19)
- በሚቃጠል ቁጥቋጦ (ዘጸ. 3፡2)
- በእሳት፥ በጢስና፥ በመብረቅ (ዘጸ. 19፡18-20)
- በሚሰማ ድምፅ (ዘጸ. 24፡1)
- በደመና ክብር (ዘጸ. 16፡10)
- በደመናና በእሳት ዓምድ (ዘጸ. 40፡34-38)
- ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት (ዘጸ. 33፡11)
የውይይት ጥያቄ ሀ) ዛሬ እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ የሚገልጥባቸው የተለመዱ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ለእግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን አልፎ አልፎ ባልተለመዱ መንገዶችስ የሚገልጥባቸው የትኞቹ ናቸው?
ሐ. በኦሪት ዘጸአት ውስጥ ስለ እግዚአብሔር የተገለጡ ሰባት እውነቶች፡-
- እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ሁልጊዜ ይጠብቃል፤ ተስፋ የሰጠውን የቃል ኪዳን ግዴታም ይፈጽማል (ዘጸ. 2፡24)።
- እግዚአብሔር በክፉዎች ላይ ይፈርዳል፤ ሕዝቡንም ከመከራቸውና ከችግራቸው ያድናቸዋል (ዘጸ. 12፡27)።
- እግዚአብሔር ከሁሉም ነገር የሚበልጥና የበላይ ነው፤ ነገር ግን ለሚወዳቸው ደግሞ ቅርብ ነው (ዘጸ. 19፡10-15፥ 13-18)።
- እግዚአብሔር ለመረጠው ለራሱ ሕዝብ ጥቅም ሲል አሕዛብን ሁሉ የሚገዛና የሚቆጣጠር ነው (ዘጸ. 15፡4-6፤13-18)።
- እግዚአብሔር ቅዱስ ነው። ቅዱስ የሚለው ስም መሠረታዊ ትርጉም «መለየት» ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቅዱስ የሚለው ቃል ሁለት የተሰወሩ ትርጉሞች አሉት። በመጀመሪያ፥ መለየት ወይም ልዩ ማለት ነው። እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም። ከእግዚአብሔር ጋር የሚወዳደር ወይም እርሱን የሚመስለው ማንም የለም። አቻ፥ አምሳያ የለውም። እጅግ ከፍ ያለና ሕልውና ካላቸው ነገሮች ሁሉ በላይ ነው (ዘጸ. 15፡11፤ 18፡10-12)። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፥ ከኃጢአት የተለየ ማለት ነው። እግዚአብሔር በኃጢአት የተበላሸ አይደለም። በአጠገቡ ኃጢአት እንዲኖር አይፈልግም። ጻድቅ ከሆነው ባሕርይ ጋር የሚቃረን፥ ኃጢአት የሆነ ማንኛውንም ነገር ሊያደርግ ወይም ሊያስብ ጨርሶ አይችልም።
- እግዚአብሔር ለሕዝቡ ጸጋንና ምሕረትን የተሞላ ነው። ቅጣት በሚገባቸው ሰዓት እንኳ በንስሐ ሲመለሱ ይቅር ይላቸዋል። ቅጣት በሚገባቸው ጊዜ እንኳ ለጸሎታቸው መልስን ይሰጣል (ዘጸ. 32፡11-14)።
- እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚያድን አምላክ ነው። እርሱ ከእስራት ይቤዣቸዋል፤ ከባርነት ይታደጋቸዋል፤ እንዲያገለግሉት፥ እንዲያመልኩትና እንዲታዘዙት ነፃ ያወጣቸዋል።
የውይይት ጥያቄ፥ ህ) ስለ እግዚአብሔር እነዚህን እውነቶች ማስታወስ ያለብን ለምንድን ነው? ለ) እነዚህ እውነቶች ዛሬ ለክርስቲያኖች | መጽናኛ የሚሆኑት እንዴት ነው?
- እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚመሩ ልዩ መሪዎችን ይመርጣል። እነዚህ መሪዎች ልዩ የሆኑት በችሎታቸው ሳይሆን እግዚአብሔር ስለመረጣቸው ነው። ሙሴን የእስራኤል ሕዝብ መሪ አድርጎ እግዚአብሔር የመረጠው ገና ከመወለዱ አስቀድሞ ነው። ሆኖም ግን እግዚአብሔር ሙሴን የተጠቀመበት በመንፈሳዊ አንፃር ሕዝቡን ለመምራት ዝግጁ በሆነበት ጊዜ ነው። በኦሪት ዘጸአት ስለ መሪነት የምናያቸውን የሚከተሉትን ነገሮች ልብ በል፡-
ሀ. መሪዎችን የሚመርጥ እግዚአብሔር እንጂ ሰዎች አይደሉም። ምርጫውም የሚሆነው በሰውዬው ግላዊ ፍላጎት አይደለም።
ለ. እግዚአብሔር ምድራዊ የሆነ የኃይልና የአመራር እውቀት አይማርከውም። ይልቁንም መሪነትን የሚመለከት የዚህ ዓለም አስተሳሰብ (ለምሳሌ፡- ትምህርት፥ ሥልጣን፥ ከአባቶች የተወረሰ ማዕረግ እግዚአብሔር ከሚፈልገው ዓይነት አመራር ጋር በተቃራኒ የሚሄዱ ናቸው። ሙሴ በግብፅ ጥበብ ሁሉ ተኮትኩቶ አድጎ ነበር፤ ስለዚህ እስራኤልን የመምራት መብት እንዳለውና በራሱ ብርታት እስራኤልን ለመምራት እንደሚችል አሰበ። ይህ ግን አልሠራም። እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ በአንድ መሪ ከመገልገሉ በፊት፥ አስቀድሞ ያንን ሰው ዝቅ ያደርገዋል። እግዚአብሔር ይህንን የሚያደርገው፥ መሪው በእግዚአብሔር ብርታት እንጂ በራሱ መደገፍ እንደሌለበት እንዲማር ነው። በዚህ መንገድ ሰውዬው ክብር ከመውሰድ ፈንታ፥ እግዚአብሔር ክብሩን ለራሱ ይወስዳል። ሙሴ የእግዚአብሔር መገልገያ ለመሆን ከመዘጋጀቱ አስቀድሞ በምድረ በዳ በበግ እረኝነት ዓመታትን አሳልፏል።
ሐ. እግዚአብሔር ከየትኛውም የመሪ ባሕርይ ይልቅ ትሕትናንና በእርሱ ላይ ያለውን መደገፍ ያከብራል። እግዚአብሔር ሙሴን በራሱ ለመናገርም ሆነ ሕዝቡን ለመምራት እንደማይችል ዋስትና እስኪያጣ ድረስ ትሑት አደረገው።
መ. የእግዚአብሔር ሕዝብ መሪዎች ራሳቸውን ሳይሆን ሕዝቡን ማገልገል ይኖርባቸዋል። ሙሴ መሪነትን የተማረው «በጎችን» በማገልገል ነበር። ከዚያ በኋላ ብቻ ነበር ከእግዚአብሔር የሆኑ መሪዎች የሚመሩት በኃይልና በሥልጣን ሳይሆን በማገልገል ላይ የሚሆነው (ማር. 10፡45 ተመልከት)።
ሠ. ከእግዚአብሔር የሆኑ መሪዎች የሕዝቡን ጥቅም ከራሳቸው ጥቅም ያስቀድማሉ። እስራኤላውያን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ፈለገ፤ ሙሴ ግን እነርሱ ከሚጠፉ ይልቅ ራሱ እንዲጠፋና እነዚያ በሕይወት እንዲኖሩ ማለደ (ዘጸ. 32፡ 12)።
ረ. የእግዚአብሔር መሪዎች ሸክም የሆነባቸው ስለ ራሳቸው ክብርና ደህንነት እምብዛም ሳይጨነቁ ስለ እግዚአብሔር ክብርና ሰለ ስሙ ክብር ነበር። እስራኤላውያን ኃጢአት ባደረጉና እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው በተነሣ ጊዜ፥ ሙሴ ስለ እግዚአብሔር ስም ገዶትና ይህ ስም በአሕዛብ መካከል ሊኖረው ስለሚችለው ምስክርነት ተጨንቆ ጸለየ (ዘጸ. 32፡12)።
ሰ. ከእግዚአብሔር የሆኑ መሪዎች የመሪነትን ሸክም ከሌሎች ጋር ይካፈላሉ። ሙሴ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚመራው እርሱ ብቻ እንዳልሆነ መማር ነበረበት። ኃላፊነቱን በሥራው ሊረዱት ከሚችሉ ሰባ ሽማግሌዎች ጋር መካፈል ነበረበት (ዘጸ. 18)።
ሸ. ከእግዚአብሔር የሆኑ መሪዎች በጸሎትና በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት ይኖራቸዋል። የእግዚአብሔርን ቃል በቅጽበት ይሰማሉ፤ ሙሉ በሙሉም ይታዘዛሉ። በኦሪት ዘጸአት ውስጥ፥ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት ሳይቀር በተደጋጋሚ ይገናኝ እንደነበር እናነባለን። በሙሴና በአመራሩ ውስጥ የምናየው የኃይል ምንጭ ይህ ነበር (ዘጸ. 33፡7)።
እነዚህ ከኦሪት ዘጸአት ውስጥ ስለመሪነት ከምናገኛቸው በርካታ መመሪያዎች ጥቂቶቹ ናቸው። የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሆንክ ኦሪት ዘጸአትን በሙሉ በጥንቃቄ በማንበብ እግዚአብሔር ሙሴን ለመሪነት እንዴት እንዳዘጋጀውና እርሱም የተዋጣለት የእግዚአብሔር ሕዝብ መሪ እንዴት እንደሆነ መመልከት ጠቃሚ ነው።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከላይ የጠቀስናቸው የመሪነት መመሪያዎች ዛሬም ላሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በጣም ጠቃሚ የሆኑት ለምንድን ነው? ለ) ከእነዚህ መመሪያዎች መካከል ብዙ ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን ያልተጠቀሱትና ያልተገለጹት የትኞቹ ናቸው? ለምን? ሐ) ከእነዚህ መመሪያዎች መካከል ብዙ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ሥራ ላይ ያልዋሉትስ የትኞቹ ናቸው? ለምን? መ) ከምታውቃቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መካከል ከሁሉ ይሻላል የምትለውን ሰው አስብ። በአመራሩ ከእነዚህ መመሪያዎች ውስጥ በምን ያህሉ ይጠቀማል?
- የእግዚአብሔር ሕዝብ ባሕርይ፡- በተለይ በኦሪት ዘጸአት ውስጥ ከምናገኘው የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ፥ ዛሬም ያለው የእግዚአብሔር ሕዝብ ባሕሪያዊ ዝንባሌ ምን እንደሆነ ለማየት እንችላለን። የእስራኤልን ሕዝብ እግዚአብሔር ያዳናቸው እጅግ በሚያስደንቅ መንገድ ነበር። የእግዚአብሔርን ኃይል ሲያድናቸው አይተዋል። ከግብፃውያን እጅ በታደጋቸው ጊዜ እግዚአብሔርን በማምለክ ሐሴት አድርገዋል። ለእግዚአብሔር መገናኛ ድንኳን መሥሪያ የሚያስፈልገውን ነገር እንዲሰጡ በጠየቃቸው ጊዜ፥ ሙሴ በቃ አቁሙ እስኪል ድረስ በከፍተኛ ልግሥና ሰጥተዋል (ዘጸ. 35፡20-29፤ 36፡37)፤ ዳሩ ግን ልክ እንደ እኛ እስራኤላውያን ብዙ ጊዜ በኃጢአት ይወድቁ ነበር። በእግዚአብሔርና በመሪዎቹ ላይ ያጉረመርሙና ያማርሩ ነበር (ዘጸ. 16፡2-3)። እምነታቸው በጣም ደካማ ስለነበር፥ ነገሮች በማይስተካከሉበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ፊታቸውን ይመልሱ ወይም እግዚአብሔርን ይጠራጠሩ ነበር። የእግዚአብሔርን ክብር ያዩ ቢሆንም፥ ወደ ኃጢአት ያዘነበሉ ነበሩ። ከእግዚአብሔር ዞር ብለው ጣዖትን ያመልኩና ያመነዝሩ ነበር (ዘጸ. 32)። የተሻለ ሕይወት ይሰጠናል ብለው የሚያስቡት ዓለም ባርነት ቢሆንም እንኳ ያለማቋረጥ ወደዚያ ለመመለስ ይፈልጉ ነበር። ልክ በአብርሃም ውስጥ የኃጢአት ባሕርይ እንደታየ ሁሉ ያው ባሕርይ ወደ ልጆቹ ሁሉ ተላለፈ።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ የኃጢአት ዝንባሌ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የሚታየው እንዴት ነው? ለ) የእግዚአብሔር ሰዎች እንደዚህ የሆኑት ለምን ይመስልሃል? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደመሆናችሁ መጠን አባሎቻችሁ ኃጢአትን ድል አድርገው ይኖሩ ዘንድ ልታደርጉ የምትችሉት ነገር ምንድን ነው?
- በኦሪት ዘጸአት ውስጥ ወደ ክርስቶስ የሚያመለክቱ በርካታ ነገሮች አሉ።
ሀ. ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ከባርነት ነፃ ያወጣ በመሆኑ፥ ከኃጢአት ባርነት ነፃ አውጥቶ የሚመራን የክርስቶስ ምሳሌ ነው (ሮሜ 6፡6፥17-18)።
ለ. የፋሲካ በዓል የእግዚአብሔር ሕዝብ ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡበት በዓል እንደሆነ ሁሉ፥ ክርስቶስም ከኃጢአት ባርነት ነፃ ስላደረገን ፋሲካችን እርሱ ነው። ሞትን እንዳንሞት ደሙን ያፈሰሰልን የፋሲካ በግ ነው (1ኛ ቆሮ. 5፡7)።
ሐ. የሕዝቡን የሥጋዊ ምግብ ፍላጎት ለማርካት እግዚአብሔር በምድረ በዳ መናን እንደሰጣቸው፥ ክርስቶስም የሰዎችን መንፈሳዊ መሻት ሁሉ የሚያሟላ የሕይወት እንጀራ ነው (ዮሐ. 6፡35፥ 48)።
መ. እግዚአብሔር ከዓለት ውስጥ ለሕዝቡ ውኃን እንደሰጠ፥ ኢየሱስ የሕይወት ውኃ ነው። ውኃ የሚሰጥ ዓለት ነው (1ኛ ቆሮ. 10፡2-4)።
ሠ. የመገናኛው ድንኳንና የአምልኮ ሥርዓቱ በርካታ የክርስቶስ ተምሳሌቶችን ያመለክታሉ። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ስለሚገኙ የተለያዩ የክርስቶስ ተምሳሌቶች ዝርዝር ከዛሬው ትምህርት ተመልከት።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)