Site icon

በሲኦል፣ ገሃነም፣ ገነት፣ መንግስተ ሰማይ እና የአብርሃም እቅፍ መካከል ያሉት ልዩነቶች ምንድን ናቸው?

ብዙ ቃላቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንግስተ ሰማይን እና ገሃነምን ለማመልከት ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ እነዚህ ቃሎች ብዙ ጊዜ ግራ የሚያጋቡ ሊሆኑ ቢችሉም ነገር ግን እያንዳንዳቸው ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት አስፈላጊ መረጃዎችን ይሰጣሉ ፡፡

ገነት፣ በአዲስ ኪዳን ሦስት የተለያዩ ቦታዎች ውስጥ አማኞች ከሞት በኋላ ከጌታ ጋር አብረው እንደሚኖሩበት ስፍራ ተደርጎ ተጠቅሷል፡፡ በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ በሉቃስ 23፡43 ውስጥ በመስቀል ላይ ሳለ ንስሃ ለገባው ሰው በዛው ቀን ከእርሱ ጋር በገነት እንደሚሆን በተናገረው አረፍተ ነገር ውስጥ ተገልጿል፡፡ በ 2ኛ ቆሮንቶስ 12፡3 ውስጥ ጳውሎስ፣ በራዕይ 2፡7 ውስጥ ደግሞ ዮሐንስ ይህንኑ ቃል ተጠቅመው እናነባለን፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ እንደምንረዳው ገነት እና መንግስተ ሰማይ በተለዋዋጭነት ጥቅም ላይ ውለዋል። ያም ሆኖ ግን ገነት የሚለው ቃል፣ ቅዱሳን በትንሣኤ አዲስ አካልን እስከሚለብሱ ድረስ ነፍሳቸው በጊዜያዊነት የሚቆይበትን ሥፍራ የሚያመለክት ይመስላል፡፡ 

የአብርሃም እቅፍ ተጠቅሶ የምናየው በአዲስ ኪዳን ውስጥ በአንድ ስፍራ ላይ ሲሆን እርሱም በሉቃስ 16፡19-31 ውስጥ ነው፡፡ አልዓዛር የሚባል አንድ ድሃ ሰው ከሞተ በኋላ ወደ አብርሃም እቅፍ ተወሰደ። ባለጸጋው ደግሞ ከሞቱ በኋላ ስቃይ ወደሚቀበልበት ሥፍራ ተወሰደ፡፡ ይህ ንፅፅር ድሃው ሰው ወደ ሰማይ እንደተወሰደ ያሳያል፡፡ በተጨማሪም፣ አላዛር በአብርሃም እቅፍ ውስጥ መሆኑ ከእግዚአብሔር ጋር እንደነበር በግልጽ ያሳያል፡፡ ምክንያቱም አብርሃም የእግዚአብሔር ወዳጅ በመባል ይታወቅ ነበርና፡፡ የአብርሃም እቅፍ በታልሙድ ውስጥ ከመንግስተ ሰማይ ጋር በአቻ ትርጉም ቀርቧል፡፡ (ታልሙድ፡- የአይሁድን የፍትሐ ብሔርና የሃይማኖት ሕግን የያዘ መጽሐፍ ስብስብ ነው፡፡)

ሲኦል በብሉይ ኪዳን ውስጥ ሙታን ያሉበትን ስፍራ ወይም መቃብር ለመግለጽ የሚያገለግል የዕብራይስጥ ቃል ነው። አንዳንድ ጊዜም የፍርድ ቦታን ያመለክታል። ነፍሱ ከሥጋው የተለየች ማንኛውም ሰው ራሱን ወደሚያውቅበትና በሌላ ሕይወት ህያው ሆኖ ወደሚኖርበት ስፍራ ይጓዛል፡፡ የዚህ ስፍራ አጠቃላይ ስሙ ሲኦል ሲሆን “መቃብር” ወይም “የሙታን ግዛት” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ ሲኦል (የሙታን መንደር) በሁለት ስፍራዎች ይከፈላል፡፡ አንደኛው እንደአላዛር ያሉ ጻድቃን ደስታንና ተድላን የሚቀበሉበት ገነት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ እንደባለጠጋው ሰው ያሉ ሃጥአን መከራ የሚቀበሉበት ገሃነም ነው፡፡  

ገሃነም የግሪክ ቃል ሲሆን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥቅም ላይ ሲውል የሚቃጠል የቆሻሻ ክምር የሆነውን እና ከኢየሩሳሌም ወጣ ብሎ የሚገኘውን የሄኖም ሸለቆን የሚያመለክት ቃል ሊሆን ይችላል፡፡ ቃሉ ከሙታን ጋር በተያያዘ ሲቀርብ ደግሞ፣ ከትንሳኤ በኋላ የሚኖረውን የፍርድ ቦታ ያመለክታል፡፡ ገሃነም እና የእሳት ባሕር ተመሳሳይ ሃሳብን የሚገልጹ ሁለት ቃላት ናቸው (ማቴ. 10:28 ፤ ማር 9፡43 ፣ ራዕ 19፡20 ፣ 20፡14)፡፡ የእሣት ባሕር፣ በመጨረሻው ዘመን የሰይጣን እና የማያምኑ ሰዎች የመጨረሻው የመቆያ ስፍራ ሆኖ በራዕይ 19፡20፣ 20፡10፣ 20፡14-15 ላይ ተጠቅሷል፡፡ ምንም እንኳን በአሁኑ ሰአት የሰይጣን እና የማያምኑ ሰዎች መኖሪያ ባይሆንም በመጨረሻው ዘመን ግን ሰይጣንንና ተከታዮቹ ለዘላለም የሚኖሩበት የስቃይ ስፍራ ይሆናል፡፡

መንግሥተ-ሰማያት፣ በራዕይ መጽሐፍ መገባደጃ ውስጥ ከአማኞች የመጨረሻው ዘላለማዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ተገልጿል፡፡ እግዚአብሔር ከኃጢያት እና ከመከራ ነፃ በሆነ ህያውነት ለዘላለም ህዝቡ ከእርሱ ጋር የሚኖሩበትን አዲስ ሰማይን፣ አዲስ ምድር እና አዲስ ሰማያዊ ከተማን ይፈጥራል (ራዕይ 21-22)።

Exit mobile version