በሕይወታችን የምናደርገው ምርጫ ለሚያጋጥመን በጎም ይሁን ክፉ ነገር ሁሉ ወሳኝ ሚና አለው። በኢየሱስ ማመንን በመረጥን ጊዜ፥ የወደፊት ሁኔታችን ሁሉ ይለወጣል። ኢያሱና ካሌብ በእግዚአብሖር ለመታመንና ከነዓናውያንን ለመውጋት ሲወስኑ፥ ከዚያ ትውልድ መካከል ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚገቡ ብቸኛዎቹ ሰዎች እነርሱ መሆናቸውን አላወቁም ነበር። የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ላለመከተል በምንወስንበት ጊዜ፥ ለጊዜው የቱንም ያህል ትንሽ ቢመስለንም፥ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ የሚታይ መጥፎ ውጤት ሊኖረው ይችላል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መልካም ምርጫዎቻችን ለሕይወታችን በጎ ውጤት እንዴት እንደሚያመጡ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ ለ) ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛችን እርሱ ይቅር ሊለን ቢችልም እንኳ ውጤታቸው በሕይወታችን ዘመን ሁሉ ሊከተሉን ለሚችሉ ነገሮች ምሳሌዎችን ጥቀስ።
ሳኦል ለእግዚአብሔር ሙሉ ለሙሉ ለመታዘዝ ባለመወሰኑ መንግሥቱ ከእርሱ እንዲወሰድ አደረገ (1ኛ ሳሙ.15፡2-3፡ 13-30)። ዳዊት ዝሙት በፈጸመና ከወዳጆቹ አንዱን ባስገደለ ጊዜ ቀሪው የሕይወት ዘመኑ በሙሉ በዚህ እንደሚነካ፥ በመንግሥቱና በቤተሰቡም ሰላም እንደሚጠፋ አላወቀም ነበር (2ኛ ሳሙ.12፡1-14 ተመልከቱ)። እግዚአብሔር ይቅር ካለው በኋላ እንኳ የኃጢአቱ ውጤቶች ዳዊትን ይከተሉት ነበር። አንዲት ልጃገረድ ካላገባችው ወንድ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ኃጢአት ፈጽማ በምትናዘዝበት ጊዜ እግዚአብሔር ይቅር ይላታል፤ ነገር ግን ክብረ ንጽሕናዋን የማጣት ኃፍረቷን፥ ምናልባትም የማርገዝንና ሌላ ለማግባት ያለመቻልዋን፥ ወይም በኤድስ የመያዝን ኃፍረት ሊያስወግድላት አይችልም።
ወደ ከነዓን ጉዞ ከሚጀምሩበት ካለፈው አንድ ዓመት እንሥቶ እግዚአብሔር ኃይሉንና በጸጋ የተሞላ ቸርነቱን ለአይሁድ ሲገልጥ ቆይቶአል፤ ነገር ግን በቃዴስ በርኔ እንዲታመኑበትና ወደ ከነዓን ምድር በእምነት እንዲገቡ እግዚአብሔር ሲጠይቃቸው እስራኤላውያን እምቢ አሉ። በዚህ ውሳኔአቸው ምክንያት አይሁድ በሚከተሉት 38 ዓመታት በምድረ በዳ ተንከራተቱ። ከ20 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆኑት በግምት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በሙሉ አለቁ። ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ በጭራሽ ያልገመቱትን ፍርድ አስከተለባቸው። ስሕተታቸውን ለማረም እንኳ ቢሞክሩ ጨርሶ የማይቻል ሆነባቸው። የኦሪት ዘኁልቁ ክፍል የሆነው የዚህ ክፍል ታሪክ እግዚአብሔር ከግብፅ ባርነት በጸጋው ነፃ ያወጣቸው የእስራኤላውያን አለመታዘዝና ያስከትለው ውጤት ታሪክ ነው።
የውይይት ጥያቄ፦ ዘኁልቁ 13-21 አንብብ ሀ) ሰላዮችን ወደ ከነዓን የመላኩ ዓላማ ምን ነበር? ለ) ) የአሥሩንና የሁለቱን ሰላዮች የተለያዩ ምላሾች አወዳድር። 2) ስለ ምድሪቱ የነበራቸው መረዳት አንድ የሆነው እንዴት ነው? 3) ስለ እግዚአብሔር የነበራቸው መረዳት የተለያየው እንዴት ነው? 4. ከዚህ የምንማረው ነገር ምንድን ነው?ሐ) ከኦሪት ዘኁልቁ ይህን ክፍል አለፍ አለፍ እያልክ ተመልከት፡፡ እስራኤላውያን የሄዱባቸውን ስፍራዎችና በየደረሱባቸው ስፍራዎች የተፈጸሙትን ነገሮች ዝርዝር። መ) የሙሴን ኃጢአት ግለጥ። እግዚአብሔር ክፉኛ የፈረደበትና የቀጣው ለምን ይመስልሃል? ሠ) እስራኤላውያን የከነዓንን ምድር መውጋት በጀመሩ ጊዜ ያሸነፏቸውን ሕዝቦች ዘርዝር፡፡
12ቱ ሰላዮች (ዘኁ.13-14)
እስራኤላውያን የከነዓንን ምድር ካዩ ከ400 ዓመታት በላይ ሆኖአል። አሁን የከነዓን ደቡባዊ ጫፍ በሆነው በቃዴስ በርኔ ሰፍረዋል። ይህም እግዚአብሔር ሊሰጣቸው ያለች ምድር ምን ያህል መልካምና ፍሬያማ እንደሆነች ለማየት እንጂ፥ የጠላቶቻቸውን ብርታት ለማየት አላስቻላቸውም። 12ቱ ሰዎች ወደ ከነዓን ምድር በመሄድ ለ40 ቀናት ምድሪቱን ሲሰልሉ ቆይተው የየራሳቸውን ዘገባ ይዘው ተመለሱ።
አሥሩ ሰላዮች በመጀመሪያ ዘገባቸውን አቀረቡ። ምድሪቱ ምን ያህል ፍሬያማ እንደሆነች ተናገሩ፡፡ እንዲያውም ምድሪቱ ከምታፈራቸው ነገሮች ለናሙና የሚሆን ነገርም አምጥተው ነበር። ዘገባቸው ግን በጠላቶቻቸው ብዛትና ታላቅነት ላይ የሚያተኩር ሆነ! ስለዚህ ወደ ከነዓን እንዳይሄዱ ሕዝቡን ተስፋ አስቆረጡአቸው። ካሌብና ኢያሱ የተባሉት ሁለት ሰላዮችም ተመሳሳይ ዘገባ አቀረቡ። ስላዩአቸው ታላላቅ ነገሮች ተናገሩ፤ ነገር ግን ጠላቶቻቸው ምንም ያህል በቁጥር የበዙና ታላላቅ ቢሆኑም፥ በጠላቶቻቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ፥ ሊያጠፋቸው በሚችለው በእግዚአብሔር ኃይል ላይ አተኮሩ።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአሥሩና በሁለቱ ሰላዮች መካከል የነበረው የአመለካከት ልዩነት ለሕዝቡ በሰጡት ምክር ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ምንድን ነው? ለ) ዛሬ ጠላቶቻችንንም ሆነ ችግሮቻችንን ስለ መጋፈጥ ከዚህ ነገር ምን እንማራለን?
የሚያሳዝነው ሕዝቡ 2ቱን ሳይሆን 10ሩን ሰላዮች ተከተሉ። ዓይኖቻቸውን ከጠላቶቻቸው ሁሉ በላይ ከሆነው ከእግዚአብሔር ላይ አነሡና በችግራቸውና በራሳቸው ላይ አደረጉ። ሌሊቱን በሙሉ ሲያጉረመርሙ አድረው፥ ጠዋት የባርነት ምድር ወደሆነችው ወደ ግብፅ ለመመለስ ወሰኑ። እግዚአብሔር በቁጣው እስራኤላውያንን በሙሉ እንዳያጠፋቸው የሚከለክለው የሙሴ የማማለድ አገልግሎት ነበር። ሆኖም እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ፍርድን አመጣባቸው። የሚከተሉትን ነገሮች ልብ በል፡-
- እግዚአብሔር አሥሩን ሰላዮች ወዲያውኑ ገደላቸው።
- ከ20 ዓመት በላይ የሆኑ ማለትም የእግዚአብሔርን ክብር ያዩና የተአምራቱ ምስክሮች የሆኑ ሰዎች በሙሉ የተስፋይቱን ምድር ሳይወርሱ በምድረ በዳ ማለቅ ነበረባቸው።
iii. እስራኤላውያን በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት ተንከራተቱ። ሰላዮቹ ለአንድ ዓመት ሙሉ በየቀኑ በከነዓን ነበሩ። በኋላ ግን ከከነዓን ውጭ ሞቱ።
- ከዚያ ትውልድ መካከል ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ካሌብና ኢያሱ ብቻ ነበሩ።
እስራኤላውያን ካለማመን ኃጢአታቸው ንስሐ ለመግባት ቢሞክሩም እንኳ እግዚአብሔር ከተናገረው ፍርድ ወደ ኋላ አላለም። ያለ እግዚአብሔርና ያለ ታቦቱ ሕልውና እስራኤላውያን በራሳቸው ኃይል ከጠላቶቻቸው ጋር ለመዋጋት ሞከሩ፤ ነገር ግን የተረፋቸው ሽንፈት ነበር።
የውይይት ጥያቄ፡- ይህ ጠላቶቻችንን በራሳችን ኃይል ለመዋጋት ብንሞክር፥ ስለሚደርስብን ነገር ምን ያስተምረናል?
(ማስታወሻ፡- ሕዝቡ 40 ዓመታት በምድረ በዳ ነበሩ ስንል፥ ከግብፅ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ያሳለፉትን አንድ ዓመት ከሁለት ወር ጨምሮ ነው)
38 ዓመታት በምድረ በዳ በተንከራተቱ ጊዜ የተፈጸሙ ነገሮች (ዘኁ.15-19)
ዘኁ. 15-19 በእነዚህ 38 ዓመታት የምድረ በዳ ኑሮ ስለነበሩት ሁኔታዎችና ስለተፈጸሙት ሁኔታዎች አንዳንድ ነገሮችን ይነግረናል። ቢሆንም በከነዓን በስተደቡብ ባለው ምድረ በዳ በመንከራተት ሰላሳለፉት ጊዜ የምናውቀው ነገር በጣም ጥቂት ነው። ቆይታ ያደረጉባቸውን አብዛኛዎቹን ስፍራዎች አናውቃቸውም። የምናውቀው ነገር ቢኖር፥ ከፍተኛ ኃዘን የነበረባቸው ዓመታት መሆናቸውን ነው። ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ሞቱ። በእነዚህ ምዕራፎች የሚከተሉት ነገሮች ተተንትነዋል፡
- ሕዝቡ ከነዓን በደረሱ ጊዜ ምን ዓይነት መሥዋዕት ማቅረብ እንዳለባቸው እግዚአብሔር ለሙሴ ነገረው፤ (15፡1-31)።
- የሰንበት ዕረፍት ትእዛዝን እያወቀ የጣሰ ሰው በድንጋይ ተደብድቦ እንዲገደል ታዘዘ፤ (15፡32-36)።
ይህ ቀላል ስሕተት አይደለም፤ ይልቁንም በእግዚአብሔር ላይ የተፈጸመ ግልጥ ዓመፅ ይመስላል። በእግዚአብሔርና በትእዛዛቱ ላይ ሆን ተብሎ ለሚሠራ ዓመፅ ይቅርታ የለም፤ ስለዚህ ሕጉን የተላለፈው ሰው በድንጋይ ተውግሮ እንዲገደል ይደረግ ነበር።
- ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ያስታውሱ ዘንድ በልብሶቻቸው ዘርፍ ላይ ቋጥረው እንዲያስሩት እግዚአብሔር ሙሴን አዘዘው (15፡37-40)።
እግዚአብሔር ሕዝቡ ትእዛዛቱን በቀላሉ ለማስታወስ እንዲችሉ ለማድረግ ሞክሯል፤ ስለዚህ ቀኑን ሙሉ በማስታወስ ይታዘዙት ዘንድ ውጫዊ የሆኑ ምልክቶችን እንዲያበጁ ነገራቸው። ሌሎች ማስታወሻዎችን (ዘዳ.6፡4-9 ተመልከት)
- የተለያዩ የእስራኤል መሪዎች በሙሴና በአሮን ሥልጣን ላይ ዓምፀዋል (ዘኁ.6-17)።
የዓመፁ መሪዎች ቆሬ፥ ዳታን፥ አቤሮንና ኦን ሳይሆኑ አይቀሩም፤ ሆኖም በሙሴና በአሮን ሥልጣን ላይ ያመፁ ሌሎች 250 ዋና ዋና የእስራኤል መሪዎች ነበሩ። የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመምራት ሙሴና አሮን የነበራቸውን ሥልጣን ተፈታተኑ። ሙሴ የፖለቲካ መሪ ሲሆን፡ አሮን ሊቀ ካህን ወይም ሃይማኖታዊ መሪ ነበር። ሙሴና አሮን እርሱ የመረጣቸው መሪዎች እንደሆኑ እግዚአብሔር ለሁሉም ሰው አሳየ፡፡
ሀ. የዓመፁ መሪ የነበሩት፥ ቆሬ፥ ዳታን፥ አቤሮንና ኦን ከነቤተሰቦቻቸው ከእስራኤል ሕዝብ ተለዩና መሬት ተከፍታ እነርሱና ቤተሰቦቻቸውን፥ እንዲሁም ንብረቶቻቸውን በሙሉ ዋጠች።
ለ. ቆሬ ሌዋዊ ነበር፤ ስለዚህ የእርሱ ዓመፅ በተለይ አሮን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በነበረው ስፍራ ላይ ነበር! ስለዚህ እግዚአብሔር እርሱንና የተከተሉትን ሰዎች በሙሉ (በአጠቃላይ 250 ነበሩ) ጥናዎችን ወስደው እሳት እንዲያደርጉባቸውና ዕጣን እንዲጨምሩባቸው በመገናኛው ድንኳንም በእግዚአብሔር ፊት እንዲያቀርቡት አዘዘ። ይህንንም በሚያደርጉበት ጊዜ ከመገናኛው ድንኳን የወጣች እሳት ቆሬን፥ ዳታንን አቤሮንንና ኦንን የተከተሉትን 250 ሰዎች በላች። የዕጣን ማቅረቢያቸው በእሳት ተበልቶ ጠፍጣፋ ሆነና እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንደመረጠ እነርሱም ትክክለኛዎቹ የእስራኤል ሕዝብ መሪዎች እንደሆኑ ቋሚ መታሰቢያ ሆኖ ቀረ።
ሐ. እነዚህ ዓመፀኛ መሪዎች ከሞቱ በኋላ፥ ሕዝቡ መሪዎቻችንን ገደልክብን ብለው በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። እግዚአብሔርም ተቆጣና ከመካከላቸው 14700 ሰዎችን ገደለ። አሮን፥ የመሠዊያውን ጥና እሳትን በማድረግና እጣን በመጨመር ለሕዝቡ ባይማልድ ኖሮ፥ የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ይጠፉ ነበር። ብዙ ክርስቲያኖች ዕጣንን በጥና ላይ ማጠን የጸሎት ምልክት ነው ይላሉ። አሮንና ሙሴ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል አማላጅ ሆነው ሕዝቡን አዳኑ።
መ. ሊቀ ካህኑ አሮን ብቻ እንደሆነ እግዚአብሐር በሕዝቡ ሁሉ ፊት አረጋገጠ። እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሙሴ በእያንዳንዳቸው ላይ የአንድ ነገድ ስም የተጻፈባቸውን አሥራ ሁለት በትሮች ወሰደ። በአንድ ሌሊትም የአሮን በትር አቆጥቁጣ፥ ቅጠሎች አውጥታና ፍሬ አፍርታ አደረች። ሊቀ ካህን የመሆኑ መብት ቋሚ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የአሮን በትር በቅድስተ ቅዱሳን በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ተቀመጠች።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ ያሉ ሰዎች፥ በስፍራው የተቀመጡት በእግዚአብሔር ምርጫ ስለሆነ ሊከበሩ እንደሚገባ ማወቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ለ) ይህ ታሪክ መሪዎች በእግዚአብሔር ፊት ስለ ሕዝቡ መማለድ ስላላቸው ሥልጣንና ሚና የሚያስተምረን ነገር ምንድን ነው?
- ሕዝቡ ለካህናት ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔርን አምልኮ መምራት ይችሉ ዘንድ መሥዋዕት እንዴት እንደሚሠዉና በእግዚአብሔር ፊት ንጽሕናቸውን እንዴት እንደሚጠብቁ የተሰጡ ትእዛዛት (ዘኁ.18)።
- የቀይ ጊደር መሥዋዕትና የሚያነጻ ውኃ ሥርዓት (ዘኁ.19)
ኃጢአት ምን ያህል ኃይለኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እግዚአብሔር ሌላ ግልጥ የሆነ ምልክትን ሰጠ፡- በመጀመሪያ፥ ቀይ ጊደር ከእስራኤላውያን ሰፈር ውጭ ተመስዳ ትታረድና ሙሉ በሙሉ ትቃጠላለች። ከዚያም አመዷ ተወስዶ ከውኃ ጋር ይቀላቀላል። ይህ ውኃ የሞተን ሰው በድን በመንካት የረከሰውን ሰው የሚነጻበትን ሥርዓት የሚያመለክት ነበር። ውኃ ራሱ
አያነጻም ነበር፤ ዳሩ ግን ውስጣዊ መንጻት አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት እግዚአብሔር የሰጠው ውጫዊ ምልክት ነበር።
- ሙሴ ከዓለት ውስጥ ውኃ በማውጣት በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት በመሥራቱ ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከነዓን እንዳይገባ ተከለከለ (ዘኁ.20፡1-13)።
ዘኁ. 20 እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ በወጡ በ40ኛው ዓመት የተፈጸመ ይመስላል። ይህም ማለት የመጀመሪያዎቹ የእስራኤል ትውልድ በሙሉ ስለሞቱ፥ ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተዘጋጅተው ነበር ማለት ነው። እስራኤላውያን ወደ ቃዴስ በርኔ በመመለስ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተዘጋጅተው ነበር። በዚህ ስፍራ ሁለት ዋና ዋና ነገሮች ተፈጸሙ፡-
ሀ. የሙሴ እኅት ማርያም ሞተች።
ለ. ሙሴ ለእግዚአብሔር ሳይታዘዝ ቀረ። እስራኤላውያን (አዲሱ ትውልድ) ልክ እንደ አባቶቻቸው በእግዚአብሔር መታመንን ገና አልተማሩም ነበር። የሚጠጣ ውኃ ስላልነበራቸው፥ በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረሙ። ከ40 ዓመታት በፊት እግዚአብሔር ሙሴ ዓለቱን በመምታት ለሕዝቡ ውኃ እንዲያወጣ አድርጎ ነበር (ዘጸ.17፡5-6)፤ አሁን ግን እግዚአብሔር ሙሴን ለዓለቱ ተናገር ውኃም ይወጣል አለው። ሙሴ ባለመታዘዝና በቁጣ ዓለቱን ሁለት ጊዜ መታው፤ ከዓለቱ ውኃ ወጣና ሕዝቡን አረካ፤ ነገር ግን ሙሴ በዚህ መልክ ኃጢአት በመሥራቱ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ተከለከለ።
የሙሴ ኃጢአት ምን ነበር? እግዚአብሔር ሙሴን በዚህ ዓይነት ከባድ ቅጣት ለምን ቀጣው? የሙሴ ዋና ስሕተት አለመታዘዝ ብቻ አልነበረም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ከመደገፍ ለእርሱ ያለውን ታዛዥነት ከመግለጥ ፈንታ በንግግሩ ኃይሉን እንደራሱ ኃይል አድርጎ አቀረበ። «በውኑ ከዚህ ድንጋይ ውኃ እናወጣላችኋለን?» በማለት ትአምራቱን የሠራው እግዚአብሔር ሳይሆን እርሱና አሮን እንደሆኑ አድርጎ አቀረበ። ለእግዚአብሔር ብቻ ሊሰጥ የሚገባውን ክብር ለራሳቸው ወሰዱ። እንዲሁም ሙሴ በእግዚአብሔር ላይ እምነት እንደጎደለው የሚያሳይ ነገር አደረገ፤ ምክንያቱም ዓለቱን ሳይመታው፥ በመናገር ብቻ ውኃ ሊወጣ ይችላል ብሎ በእግዚአብሔር አልታመነም።
ይህ ታሪክ አስፈላጊ የሆነ መንፈሳዊ መመሪያን ያስተምረናል። ለእግዚአብሔር የሚሆነውን ከብር ለራስ ማድረግ እጅግ በጣም ክፉ ነገር ነው። በምንዘምርበት፣ በምንሰብክበት፣ በምንመሰክርበትና ሰዎች በሚድኑበት ጊዜ ማንኛውም ኃይል ከእኛ የሚመጣ አይደለም፤ ስለዚህ ከክብሩ የትኛውንም ክፍል መውሰድ አይገባንም፤ ነገር ግን በእኛ ውስጥ ለሚሠራው ለእግዚአብሔር ብቻ ክብር ልንሰጥ ይገባናል። በተጨማሪም፥ እግዚአብሔር አንድን ሰው ወደ ሥልጣን ወይም ወደ መሪነት ኃላፊነት ሲያመጣው፥ ከተራው ምእመን ይልቅ በሥራው ወደሚጠየቅበት ወደ ከፍተኛ ደረጃ የመጣ መሆኑን እንረዳለን፤ ምክንያቱም አንድ መሪ እግዚአብሔርን ባያከብርና ኃጢአትን ቢሠራ፥ ሌሎች በርካታ ሰዎች ኃጢአትን እንዲሠሩ ምክንያት ይሆናል።
የውይይት ጥያቄ. ሀ) እግዚአብሔር በሙሴ ላይ ከባድ ፍርድ ያስተላለፈው ለምን ይመስልሃል? ለ) ከዚህ ነገር ስለ መንፈሳዊ
መሪነት ምን እንማራለን?
- እስራኤላውያን ወደ ከነዓን ባደረጉት ጉዞ ኤዶማውያን አገራቸውን አቋርጠው እንዳያልፉ ከለከሉዋቸው (ዘኁ.20፡14-21)
ስለዚህ እስራኤላውያን በኤዶም ምድር ዙሪያ አድርገው ወደ ሞዓብ ምድር ረጅም መንገድ በመሄድ ወደ ከነዓን መጓዝ ነበረባቸው።
- ሊቀ ካህኑ አሮን በሖር ተራራ ሞተ (ዘኁ.22-29)
የሊቀ ካህንነት መብቱም ወደ ልጁ ወደ አልዓዛር ተላለፈ።
- ዓራድ ከተባለው ንጉሥ ጋር የተደረገ ጦርነት (ዘኅ. 21፡1-3)
እስራኤላውያን በ40 ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያ ጦርነት ያደረጉት ከከነዓን በስተደቡብ ከምትገኝ ዓራድ ከተባለች ከተማ ንጉሥ ጋር ነበር። የዓራድ ንጉሥ በድንገት አደጋ ጥሎ ያለ አንዳች ማስጠንቀቂያ የገጠማቸው ይመስላል። በውጤቱ እስራኤላውያን ተበቀሉዋቸውና እነርሱንና ከተሞቻቸውን በሙሉ አጠፉ። «ፈጽመው ደመሰሱ» የሚለው ቃል የዕብራይስጥ ትርጉም፥ አንድን ነገር ወይም ሰው ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ከመስጠት ጋር የተያያዘ ነው። አንዳንድ ጊዜ ይህ ቃል ከ «ተለዩ» ወይም ከ «ተቀደሱ» በኋላ ለእግዚአብሔር ስለሚሠዉት እንስሳ ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል ነው። ይህ ቃል በጦርነት ዓውድ ስንጠቀምበት በዚያ ከተማ ውስጥ ያሉ እንስሳትንና ሰዎችን በሙሉ ስለማጥፋት ይናገራል። በዚያ ከተማ ያሉ እንስሳትና ሰዎች ሁሉ ለእግዚአብሔር እንደሆኑ ያህል ነው። እንስሳት ለእርሱ በብዛት የመሠዋታቸውን ያህል፥ ሰዎችም የእግዚአብሔር ፍርድና ጥፋት ዒላማ ሆኑ።
- በእስራኤል ሕዝብ ላይ ለፍርድ የተላኩት መርዘኛ እባቦች (ዘኁ.21፡4-9)
ኤዶማውያን የእስራኤል ሕዝብ በምድራቸው እንዲያልፉ ስላልፈቀዱላቸው፥ ወደ ሰሜን ከመጓዛቸው በፊት ወደ ደቡብ ረጅም ጉዞን ማድረግ ነበረባቸው። ምናልባት ይህ ነገር ከጠየቀው ረጅም ጉዞ የተነሣ፥ ሕዝቡ በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ ማጉረምረም ጀመሩ። የእግዚአብሔርን መና አንበላም በማለታቸው፥ ለእነርሱ ባሳየው ቸርነት ጸጋውን እምቢ ማለታቸው ነበረ። ስለዚህ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ፈረደባቸው። መርዛማ እባቦችን ልኮ ብዙ እስራኤላውያን ተነድፈው እንዲሞቱ አደረገ።
ሕዝቡ ኃጢአታቸውን በተናዘዙ ጊዜ፥ የነሐስ እባብ እንዲሠራ እግዚአብሔር ሙሴን አዘዘው። ሕዝቡ ወደ ነሐሱ እባብ በእምነት በተመለከቱ ጊዜ ይፈወሱ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዮሐ.3፡14-15 ተመልከት። ይህ ታሪክ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ተምሳሌት የሆነው እንዴት ነው? ለ) እስራኤላውያን የዳኑበትና እኛም ድነት (ደኅንነት)ን የምናገኝበት መንገድ ተመሳሳይ የሆነው እንዴት ነው?
የነሐሱ እባብ ታሪክ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆነ። ወደ ተሰቀለው የነሐስ እባብ በእምነት የተመለከቱ ሁሉ በሥጋቸው ፈውስ እንዳገኙ ሁሉ፥ ወደ ተሰቀለው ክርስቶስ በእምነት የሚመለከቱም መንፈሳዊ ፈውስን ያገኛሉ። እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ግን ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን የነሐስ እባቡን ማምለክ መጀመራቸው ነው (2ኛ ነገ.18፡4 ተመልከት)። ሰይጣን ሁልጊዜ ለሕይወታችን መልካም የሆነን ነገር ይወስድና ወደ ማሰናከያ ዓለትነት ይቀይረዋል።
- ወደ ሞዓብ ሜዳዎች የተደረገ ጉዞ (ዘኁ.21፡10-35)
ሕዝቡ ከምድረ በዳ ተነሥተው ወደ ሰሜን በመጓዝ፥ በሞአብ ምድር ላይ ሰፈሩ። ሊሰፍሩ ወደሚችሉበት ወደ እስራኤላውያን በአሞን ምድር ለማለፍ ፈቃድ በጠየቁ ጊዜ የአሞን ንጉሥ ሊወጋቸው ሞከረ። እስራኤላውያን ግን አሸነፉትና የአሞንን ምድር ወሰዱ። የባሳን ንጉሥ ዐግ ደግሞ እስራኤላውያንን ሊወጋ ሞከረ፤ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ተሸነፈ። እነዚህ ስፍራዎች የምናሴና የጋድ ነገዶች የወረሷቸው ስፍራዎች ናቸው።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)