የውይይት ጥያቄ፥ ዘዳግም 30፡15-18 አንብብ። ሀ) በሰው ፊት የቀረቡ ሁለቱ ምርጫዎች ምንድን ናቸው? ለ) የእነዚህ ምርጫዎች ውጤት በተናጠል ምንድን ነው? ) እነዚህ የምንሰብከው ወንጌል ክፍል የሆኑት እንዴት ነው?
ብዙ ጊዜ ከርስቲያኖች ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት ለሚያጋጥማቸው ችግር በአንድ ነገር ላይ ወይም በሌላ ሰው ላይ ያላክካሉ። አንዳንድ ጊዜ በሰይጣን ያመካኛሉ። ሌሎቹ ደግሞ እግዚአብሔርን ይወቅሳሉ። ሰይጣንም ሆነ እግዚአብሔር በምንወስነው ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ቢችሉም፥ የመጨረሻ ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት መውሰድ ያለብን እኛ ነን። ሰይጣን ከፈቃዳችን ውጭ ኃጢአት እንድንሠራ ሊያስገድደን አይችልም። በሌላም በኩል እግዚአብሐር፥ አንድን መልካም ነገር እንድናደርግ ፈቃዳችንን ጥሶ አያስገድደንም። በመጨረሻ እግዚአብሔር ምርጫውን ለእኛ ሰጥቷል። ሕይወትን ወይም ሞትን፥ በረከትን ወይም መርገምን መምረጥ እንችላለን። ሙሴ ከመሞቱ በፊት እስራኤላውያን ማድረግ ስላለባቸው ትክክለኛ ምርጫ ሊያስታውሳቸው ፈለገ። በእግዚአብሔር የሚሸለሙት ወይም የሚቀጡት ባደረጉት ምርጫ መሠረት እንደሆነ ሊያሳያቸው ወደደ።
እንደ ወንጌል ሁሉ ቃል ኪዳንም ተስፋ የተሰጠበትን በረከትና የቅጣት ማስጠንቀቂያዎችን ይዟል። ወንጌል «የምሥራች» ነው። ከኃጢአታቸው ያድናቸው ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑት ሁሉ የድነት (ደኅንነት) ተስፋ ይዞአል። እንዲሁም ወንጌል «ክፉ ወሬ» ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሰጠውን ድነት (ደኅንነት) እንቢ ላሉ ዘላለማዊ ፍርድን ያውጃልና። የወንጌል መልእክተኞች እንደመሆናችን፥ መናገር ያለብን ሰው በማመኑ ምክንያት ስለሚያገኘው በረከት (ቃል ስለ ተገባለት በረከት) ብቻ ሳይሆን፥ ለማያምኑትም ሁሉ ስለተደረገውና ስለሚጠብቃቸው ዘላለማዊ ፍርድም ጭምር ነው። ወንጌል ለሰዎች ሞት ወይም ሕይወት፥ በረከት ወይም የሞት ፍርድ እርግማን ይዞ ይቀርባል። ሰዎች ወንጌልን የበለጠ እንዲወዱት ብለን ርግማኑን ወይም የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት መደበቅ የለብንም። ሙሴ ከመሞቱ በፊት በፊታቸው ያለውን ምርጫ ለሕዝቡ በጥንቃቄ አሳያቸው።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በወንጌል መልእክት ውስጥ የተጠቃለሉትን የበረከት ዓይነቶች ዘርዝር። ለ) በወንጌል መልእክት ውስጥ የተጠቃለሉትን የርግማን ዓይነቶች ወይም ፍርዶች ዘርዝር። ለ) ላልዳኑት ሰዎች ምርጫቸውን ያስተካክሉ ዘንድ ሁለቱንም ነገሮች ማሳየት የሚጠቅመው ለምንድን ነው? መ) ዛሬ ወንጌልን ለአንድ ሰው አካፍል። በመልእክትህ ውስጥ ሁለቱንም ማለትም የወንጌልን በረከትና ርግማንንም አቅርብ።
የውይይት ጥያቄ፥ ዘዳግ። 27-34 አንብብ። ሀ) ሕዝቡ ባለመታዘዛቸው ምክንያት የሚመጡባቸውን የርግማን ዓይነቶች ዘርዝር? ) ሕዝቡ በመታዘዛቸው ምክንያት የሚያገኙአቸውን የበረከት ዓይነቶች ዘርዝር። ሐ) ኢያሱ አዲሱ መሪ መሆኑን እግዚአብሔር ለሕዝቡ እንዴት አሳያቸው? መ) ከኦሪት ዘዳግም ለራስህ ሕይወትም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙና ሊዛመዱ የሚችሉ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ዘርዝር።
እያንዳንዱ ትውልድ ለእግዚአብሔር መሰጠትና ቃል ኪዳኑን ማደስ አለበት። ከ40 ዓመታት በፊት፥ የመጀመሪያው የእስራኤል ትውልድ በሲና ወይም በኮሬብ ተራራ ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘት፥ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል። አሁን ደግሞ ሕዝቡ ወደ ከነዓን ከመግባታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ሙሴ አዲሱ ትውልድ ቃል ኪዳኑን እንዲያረጋግጥ ሲያደርግ እንመለከታለን። እግዚአብሔር ደግሞ በሲና ተራራ የሰጠውን ሕግ ሲደግም እንመለከታለን። ከዚያም ወደ ከነዓን ምድር በሚገቡበት ጊዜ ቃል ኪዳኑን እንዴት እንደሚያጸኑ መመሪያ ሲተውላቸው እንመለከታለን። ሙሴ ሕጉን እንዴት በጽላት ላይ መጻፍ እንዳለባቸውና እንዴት በመታሰቢያነት እንደሚያቆሙት እስራኤላውያንን አዘዛቸው። ከዚያም በጌባል ተራራ ሕጉን እንዲያነብቡና በመታዘዝ የሚገኙትን በረከተችና ባለመታዘዝ የሚመጡትን ርግማኖች እንዲደግሙአቸው አዘዘ።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሙሴ ይህንን ትእዛዝ ለአይሁድ የሰጠው ለምንድነው ብለህ ታስባለህ? ለ) ቀጣዩን ትውልድ በወንጌል ውስጥ ስለሚገኙት በረከቶችና ርግማኖች እንዴት ማስተማር እንዳለብን ይህ ምን ያስተምረናል?
አብዛኛዎቹ በረከቶች፥ በተለይም ደግሞ ርግማኖች የተሰጡት በትንቢት መልክ ነው። የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ በማጥናት ወደ ፊት እየገፋን ስንሄድ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ የነገራቸው በረከቶችና መርገሞች በኃላ እንደ ተፈጸሙ እንመለከታለን። መታዘዝ ሲኖር፥ በረከትም ነበር። ዳሩ ግን እስራኤላውያን ብዙውን ጊዜ ባለ መታዘዝ ተመላልሰዋል። ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ በኦሪት ዘዳግም ውስጥ የተጠቀሱትን ርግማኖች ለቃል ኪዳኑ ባለመታዘዛቸው ምክንያት በእነርሱ ላይ መፈጸማቸውን የሚናገር ታሪክ ነው ለማለት እንችላለን። የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ የተመዘገበባቸውን መጻሕፍት ስታጠና በእስራኤል ላይ የተፈጸመውን ቅጣት በኦሪት ዘዳግም አስቀድሞ ከተነገረው ጋር ማወዳደር በጣም እንደሚጠቅም አስታውስ።
የውይይት ጥያቄ፣ አንዳንዶቹ ርግማኖች በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ እንዴት እንደተፈጸሙ መግለጫ ስጥ።
ኦሪት ዘዳግም የሚያበቃው በሙሴ ሞት ታሪክ ነው። እግዚአብሔር አስቀድሞቶ ኢያሱን እንደ ተከታይ መሪ አድርጎ እንዲቀባው ለሙሴ ነግሮት ነበር። ከዚያም ሙሴ ወደ ናባ ተራራ ሄደ። እግዚአብሔር በዮርዳኖስ ወንዝ ዙሪያ ያለውን የተስፋይቱን ምድር አሳየው። ከዚያም ሙሴ ሞተ። ትውልዶችን ሁሉ ያየን እንደሆነ በእስራኤላውያን ዓይን እንደ ሙሴ ያለ ታላቅ መሪ አልነበረም። ሙሴ በዚህ ስፍራ እንደ «እግዚአብሔር አገልጋይ» እንደ ነቢይና «እንደ» ተአምራት አድራጊ ሆኖ ቀርቧል። እግዚአብሔር ሕግን የሰጠው በእርሱ በኩል ስለሆነ፥ አይሁድ ሙሴን ሕግ ሰጪ አድርገው ይመለከቱታል።
የውይይት ጥያቄ፥ ከሙሴ ሕይወት ስለ ቤተ ክርስቲያን የውስጥ አመራር ምን ለመማር እንችላለን?
በኦሪት ዘዳግም ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ትምህርቶችን ተመልክተናል፤ ለምሣሌ፡-
- ሰው ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ጋር ላለው ኅብረት መሠረቱ «ፍቅር» በሚለው ቃል ውስጥ ይገኛል። ፍቅር የሚለው ቃል በኦሪት ዘዳግም ውስጥ 22 ጊዜ ተጠቅሷል። አንድ ሰው እግዚአብሔርን በፍጹም ኃይሉ ከወደደና ባልንጀራውን ከወደደ የቃል ኪዳን ሕግ የሚጠይቀውን ነገር ሁሉ ተሟላ ማለት ነው። በኦሪት ዘዳግም የእግዚአብሔር ሰዎች ከሁሉም ነገር በላይ በፍጹም ኃይላቸው እግዚአብሔርን እንዲወዱ ተጠርተዋል።
- በኦሪት ዘዳግም ውስጥ የሚገኘው በጣም አስፈላጊ የሆነ ሁለተኛ ዋና ርዕስ «መታዘዝ» ነው። በመጽሐፉ ውስጥ 10 ጊዜ ተጠቅሷል። መታዘዝ የፍቅር ውጤት (ፍሬ) ነው። አንድን ሰው ካልታዘዝነው እንወደዋለን ማለት አንችልም። እንዲሁም ከልብ ሳንታዘዘው እግዚአብሔርን እንወደዋለን ማለት አንችልም። ደግሞም እርስ በርስ የምንጎዳዳበትን ነገር እያደረግን እንዋደዳለን ማለት አንችልም።
- ኦሪት ዘዳግም፥ የ«ሕግጋት» መጽሐፍ ነው። ብዙ ጊዜ ሕግን የጸጋ ተቃራኒ አድርገን እንመለከታለን። አይሁድ ግን የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን የሚያዩት የእግዚአብሔር የጸጋ ምልክት እንደሆነ አድርገው ነው፤ ምክንያቱም እነርሱ የሚኖሩት እግዚአብሔርን እንዴት እንደሚያመልኩትና እርሱን ደስ የሚያሰኙበትንም መንገድ በማያውቁ አሕዛብ መካከል ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በጸጋው እንዴት እንደሚያመልኩና እንዴት መኖር እንዳለባቸው ለመግለጽ ለአይሁድ ሕግጋትን ሰጣቸው። ለአይሁድ ሕግ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። ከብርና ከወርቅ የሚሻል ከማርም ይልቅ የሚጣፍጥ ነው [መዝ. (119)፡10፤ (119)፡72]። እግዚአብሔር ለእስራኤል የነበረውን ፍቅር ራሱን በመግለጥና ሕግን በመስጠት አሳየ። ሕጉ በእነርሱ ዘንድ እንደ ሸክም የታየበት ጊዜ ጨርሶ አልነበረም።
እግዚአብሔር ሕግን በመስጠት ረገድ የነበረው ዓላማ ሰዎች እንዲሁም ዝም ብለው ሥርዓቶችን እንዲታዘዙ ብቻ አልነበረም። ይልቁንም፥ ሰዎች ለእርሱ ያላቸውን ፍቅር የሚያረጋገጥባቸው መንገዶች ነበሩ። ሰው በእግዚአብሔር ፊት በእውነተኛ የቅድስና ሕይወት እንዲኖር የሚመሩ ነበሩ። እግዚአብሔርን ደስ በማሰኘት እርስ በርስ በፍቅርና በሰላም እንዲኖሩ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ነበሩ።
በአዲስ ኪዳን ጳውሎስ ሕግን አልተቃወመም፤ የተቃወመው አይሁድ ደኅንነታቸውን በሕግ ለማግኘት የነበራቸውን የተሳሳተ እምነት ነበር። ጳውሎስ እንዳለው «ሕጉ ቅዱስ ነው ትእዛዚቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት» (ሮሜ 7፡12)። የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ስሕተት አልነበሩም፤ በተሳሳተ መንገድ ድነት (ደኅንነት) ለማግኘት የሕግጋት አጠቃቀማቸው ግን ስሕተት ነበር።
ብዙ ክርስቲያኖች ዛሬ አይሁድ የሠሩትን ስሕተት ይደግማሉ። የዳኑት ሕግን በመጠበቅ ይመስላቸዋል፤ ደግሞም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኙት በቂ ሕግጋትን በመጠበቅ እንደሆነ ይገምታሉ። ይህ አስተሳሰብ ስሕተት ነው። ይህ በክርስቶስ ወዳለ ነጻነት ሳይሆን፥ ወደ ባርነት የሚመራ ሐሰተኛ ወንጌል ነው። ለሕግ በመታዘዛችን ለእግዚአብሔር ፍቅር እንዳለን እንገልጻለን።
የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች የዳኑት አንዳንድ ድርጊቶችን በመፈጸም እንደሆነ ይመስላቸዋል። እስቲ ምሳሌዎችን ስጥ። ለ) ሕግጋትን ወደሚጎዳ ነገር እንዴት ልንለውጣቸው እንችላለን?
- ሙሴ በኦሪት ዘዳግም ያተኮረበት ሌላ ነገር፡- አምልኮ በአንድ በተቀደሰ ቦታ በውስጠኛ ክፍል ብቻ መደረግ እንዳለበት ነው። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ብዙ አማልክት እንደሌሉና በአንድ በተወሰነ ስፍራ ማለትም በመገናኛው ድንኳ የራሱን ሕልውና የገለጠ አንድ አምላክ ብቻ መኖሩን ገልጦላቸዋል፤ ስለዚህ ያንን እውነተኛ አምላክ በአንድ ስፍራ ብቻ ሊያመልኩ ይገባ ነበር። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የነበሩ አይሁዶች የአሕዛብን ልምምድ በመከተል በርካታ የተለያዩ አማልክትን በተለያየ ቦታ ለማምለክ ሊፈተኑ እንደሚችሉ ያውቅ ነበር። የሚያሳዝነው ግን አይሁድ ይህንን የማስጠንቀቂያ ትእዛዝ ሳይከተሉ ስለቀሩ የጣዖት አምልኮ ለአይሁድ የሁልጊዜ ችግር ሆኖ ቀርቷል።
የውይይት ጥያቄ፥ ዮሐ. 4፡21-24 አንብብ። ጌታ ኢየሱስ ለእውነተኛ አምልኮ መሠረቱ ምንድን ነው አለ በአንድ በተወሰነ ስፍራ ካማምለክ ጋር ያለውስ ግንኙነት ምንድን ነው?
- ሰው ሊታዘዝ ወይም ላይታዘዝ እግዚአብሔር ነጻ ምርጫ ሰጥቶታል። እግዚአብሔር ማንንም አስገድዶ እንዲታዘዝ ወይም እንዳይታዘዝ አያደርግም። ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ስለሆነ፥ የመምረጥ ነጻነት አለው፤ ነገር ግን ምርጫው የሚያስከትለውን ውጤት መከላከል አይችልም። የምርጫውን ውጤት የሚወስነው እግዚአብሔር ራሱ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ብንመርጥ ሕይወት ሊሰጠን ቃል ገብቶልናል፤ ተገቢውንም ሽልማት ይሰጠናል። አለመታዘዝን ከመረጥን ደግሞ እግዚአብሔር ይቀጣናል። ሰዎች ወይም መንግሥታት እግዚአብሔርን ላለመታዘዝ ሲመርጡ በራሳቸው ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ያመጣሉ። ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ መመሪያዎች አንዱ ነው።
- እግዚአብሔር የታሪክ አምላክ ነው። ይህ እውነተኛ ታሪክ በትምህርት ቤት እንደተማርነው ዓይነት አይደለም፤ የድርጊቶች ቅደም ተከተል ብቻ አይደለም። ኦሪት ዘዳግም የሚያስተምረን እግዚአብሔር ታሪክን የሚቆጣጠርና የሚወስን መሆኑን ነው። ታሪክ፥ እግዚአብሔር ዓላማውን በዓለም ላይ ለመፈጸም እንዴት እየሠራ እንዳለ የሚናገር ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ታሪክን እንዴት እንደተቆጣጠረና ተጽዕኖ እንዳደረገበት እንመለከታለን። እግዚአብሔር በዙሪያችን ያለውን ነገር እንዴት እንደሚቆጣጠር ባይገልጽልንም እንኳ ድርጊቶችን በሙሉ እስካሁን ድረስ እየተቆጣጠረ እንደሆነ እርግጠኞች ለመሆን እንችላለ፤ ዓላማውንም ተግባራዊ በማድረግ እየፈጸመ ነው።
የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህን እውነቶች ልናውቃቸውና ልናስታውሳቸው የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ኦሪት ዘዳግም ከአዲስ ኪዳንና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለው ዝምድና፡-
- ፔንታቱክ ብለን ከምንጠራቸው ከመጀመሪያዎቹ አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት አዲስ ኪዳን ብዙ ጊዜ የሚጠቅሰው ከኦሪት ዘዳግም ነው። ጌታ ኢየሱስ በምድረ በዳ በተፈተነ ጊዜ፥ የሰይጣንን ፈተና ለማሸነፍ ከኦሪት ዘዳግም ውስጥ ጠቅሷል፤ (ማቴ. 4፡4፥7፥10 ተመልከት)። ይህን መጽሐፍ ብዙ ባንጠቀምበትም፥ በአይሁድና በቀደምት ክርስቲያኖች አምልኮ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የነበረውና ጠቃሚ ሚና የተጫወተ መጽሐፍ ነው።
- በኦሪት ዘዳግም ውስጥ ስለ ክርስቶስ የተነገረ ድብቅ ትንቢት ነበር፤ (ዘዳግ. 18፡15-18 ተመልከት)። ይህ ጥቅስ የሚናገረው፥ እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ በተለያዩ ዘመናት ውስጥ የተለያዩ ነቢያትን እንደሚያስነሣ ቢሆንም፣ እግዚአብሔር የእርሱን መልእክት ለእስራኤል ሕዝብ የሚናገር አንድ ልዩ ነቢይ እንደሚያስነሣ የተነገረም ትንቢት ነው። በአዲስ ኪዳን የነበሩ አይሁድ ይህንን ነቢይ ሲጠብቁ ነበር (ዮሐ. 1፡21፣ 25፣ 45፤ የሐዋ 7፡37 ተመልከት)። ነገር ግን መሢሑና ነቢዩ አንድ ሰው እንደሚሆን አልተገነዘቡም ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መሢሑም ስለ ነቢዩም የተነገረውን ትንቢት ፈጸመው።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)