ኢያሱ 1-12

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሽንፈት የሚደርስባቸው ለምንድን ነው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ያለማቋረጥ በኃጢአት የሚወድቁትና ጨርሶ ድል የማያገኙ የሚመስሉት ለምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ይህን ይመስልሃልን? ግለጥ።

እግዚአብሔር ለሕዝቡ ድልን ለመስጠት ቃል ገብቷል። ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ሲጽፍ፦ «በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን» ብሉአል (ሮሜ 8፡37)። በተጨማሪ 1ኛ ቆሮ. 15፡57፤ 1ኛ ዮሐ. 2፡13፤ 4፡4 ተመልከት። ይህ ድል ግን እንዲሁ በቀላሉ የሚገኝ ነገር አይደለም። ለዚህ ድል ዝግጅት ማድረግ ያሻናል። እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል። ድል የሚገኘው ከእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን ጥረት እንዳልሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። በኃጢአት ላይ የድል ነሺነት ሕይወት በመኖር፥ የተቀደስን ልንሆን ያስፈልጋል። ለእግዚአብሔር ታዛዦች መሆን አለብን። የመጽሐፈ ኢያሱ የመጀመሪያ ክፍል እስራኤላውያን ከነዓንን ድል አድርገው በወረሱት ልምምድ በኩል እነዚህን አስፈላጊ መንፈሳዊ እውነቶችን ይገልጣል።

የውይይት ጥያቄ. ኢያሱ 1-12 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ኢያሱን ለመሪነት ያዘጋጀው እንዴት ነው? ለ) እግዚአብሔር በጠላቶች ላይ ስላዘጋጀው የድል መንገድ ሁለቱ ሰላዮች የተማሩት ነገር ምን ነበር? ሐ) ቀይ ባሕርን መሻገር ለእስራኤላውያን የሚያሳየው ነገር ምንድን ነው? (ኢያ. 3፡10-13)። መ) ለመታሰቢያ ይሆን ዘንድ በዮርዳኖስ ምዕራባዊ ክፍል እስራኤላውያን የገነቡት ነገር ምን ነበር? ለምን? ) በጌልጌላ ምን ተደረገ? ረ) ኢያሱ የተገናኘው የእግዚአብሔር ሠራዊት አዛዥ ማን ነበር? ለ) በኢያሪኮ ላይ እግዚአብሔር ለአይሁዳውያን ድልን የሰጠው እንዴት ነበር? ) እስራኤላውያን ጋይን ያላሸነፉት ለምንድን ነው? ቀ) እስራኤላውያን በኢባል ተራራ ምን አደረጉ? በ) አይሁድ እንዳያጠፏቸው የገባዖን ሰዎች ያደረጉት ምን ነበር? ተ) በእስራኤላውያን የተደመሰሱትን የተለያዩ ሕዝቦች ዘርዝር።

እስራኤላውያን ዮርዳኖስን በመሻገር ወደ ከነዓን ገቡ፤ (ኢያሱ 1-5)።

እስራኤላውያን በዮርዳኖስ ወንዝ ምሥራቃዊ ክፍል ሰፍረው ነበር። ከ40 ዓመታት በፊት የቀይ ባሕርን እንዲሻገሩ የረዳቸው እዚአብሔር፥ ከሙሴ ሞት በኋላ ደግሞ የዮርዳኖስን ወንዝ እንዲሻገሩ አዘጋጃቸው።

ሀ. በመጀመሪያ ግን እግዚአብሔር የእስራኤል ሕዝብ መሪ እንደ መሆኑ ኢያሱን ወደ ፊት ለሚጠብቀው አዲስ ኃላፊነት ለማዘጋጀት ፈለገ (ኢያሱ 1)። ስለዚህም እግዚአብሔር ለኢያሱ አንዳንድ ትእዛዛትን ሲሰጠው እንመለከታለን፡- 1) ከሙሴ ጋር እንደነበረ ከኢያሱም ጋር እንደሚሆንና በጠላቶቹ ሁሉ ላይ ድልን እንደሚሰጠው ቃል ገባለት። 2) እግዚአብሔር ለኢያሱ እንዲበረታና እንዲጠነክር፥ እምነቱንም በእርሱ ላይ እንዲያደርግ ነገረው። 3) እግዚአብሔር ኢያሱን ከቃል ኪዳኑ ወይም በሙሴ በኩል ከሰጠው ሕግጋት እንዳይለይ አስጠነቀቀው። ይልቁንም እነዚህን ሕግጋት በሕይወቱ በመኖር ሊያሳይና በልቡ ሊሰውር ይገባው ነበር። እግዚአብሔር ለኢያሱ እንዲከናወንለት የሚያደርገው እርሱን ካወቀና ቃሉን ከታዘዘ ብቻ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህን ሦስት ነገሮች በዚህ ዘመን ያሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ማስታወስ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

ለ. እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ በመጀመሪያ ወደምትገኘዋ ከተማ ወደ ኢያሪኮ ኢያሱ ሁለት ሰላዮችን ላከ (ኢያሱ 2)። እነዚህ ሁለት ሰላዮች ረዓብን አገኙአት። ረዓብም በከነዓናውያን ልብ እግዚአብሔር ፍርሃትን እንዳደረገና እያንዳንዱ ሰው እግዚአብሔር ከአይሁድ ጋር ስለሆን በእነርሱ መሸነፋችን የማይቀር ነው የሚል ግምት እንዳደረበት ነገረቻቸው። ረዓብ ምን ዓይነት ሴት እንደነበረች ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ሴተኛ አዳሪ የነበረች ሴት ትመስላለች፤ (ኢያ. 2፡1)። ነገር ግን ይህ ስለማንነቷ የሚገልጠው ቃል የሆቴል ቤት ዓይነት መኝታ ክፍሉችንም የምታከራይ ሴት እንደሆነችም ሊያመለክት ይችላል። ሁለቱ ሰላዮችም ወደ እርሷ ቤት የገቡት ለዚህ ሊሆን ስለሚችል፥ በዚህ መልኩ ልንተረጉመው እንችላለን። ረዓብ ሰላዮቹን በመሸሸግ በእግዚአብሔር ላይ ያላትን እምነት ስለገለጠች፥ እርሱ አከበራት። በአዲስ ኪዳን የእምነት ምሳሌ ሆና ቀርባለች (ዕብ. 11፡31፤ ያዕ. 5፡25)። በኋላም ከይሁዳ ነገድ የሆነ ሰው ስላገባች፥ መሢሑ ክርስቶስ የመጣበት ዘር አካል ሆናለች፤ (ማቴ. 1፡5)። የዳነችው በእምነትና በመታዘዝ ቀይ ፈትልን በመስኮቷ በኩል ስላንጠለጠለች ነው። ብዙዎች ይህ እኛን ያዳነ የክርስቶስ ደም ምሳሌ ነው ይላሉ።

ሐ. እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ (ኢያሱ 3)።

እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ በተሻገሩ ጊዜ እጅግ ሞልቶ እንደ ነበረ እናነባለን። ለመሻገርም የማያስችል ነበር። እግዚአብሔር ግን ተአምር ሠራ። ምናልባት በሚንሸራተት ጭቃ ወይም በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት [መዝ. (114)፡3-4] በስተሰሜን 25 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝና እስራኤላውያን በተሻገሩት አዳም በሚባል ከተማ ውኃው ተገድቦ ይሆናል። በምንም መንገድ ይሁን፥ እግዚአብሔር ምንም ነገር ይጠቀም፥ ተአምር ነበር። 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የዮርዳኖስን ወንዝ በየብስ ተሻገሩ። ይህ ተአምር ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች ነበሩት። የመጀመሪያው፥ ሙሴ ሕዝቡን ቀይ ባሕርን እንዳሻገራቸው ሁሉ፥ ኢያሱም እውነተኛ መሪ መሆኑን ለማሳየት ነበር። ሁለተኛ፥ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንደሆነና በጠላቶቻቸው ላይ ድልን እንደሰጣቸው የሚያሳይ ነበር።

መ. እስራኤላውያን በዮርዳኖስ ምዕራባዊ ክፍል መታሰቢያን አቆሙ (ኢያሱ 4)። ኢያሱ በመጽሐፉ ውስጥ እስራኤላውያን ከእነርሱ በኋላ ለሚመጣ ትውልድ ቋሚ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር በዚህ ዘመን ለእነርሱ ያደረገላቸውን እንዲያውቁ፥ በርካታ ጊዜያት መታሰቢያ ያቀሙ ነበር። ለእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አንድ አንድ ድንጋይ የቆመለትና በአጠቃላይ 12 ድንጋዮች በመታሰቢያነት የቆሙት እግዚአብሔር የዮርዳኖስን ወንዝ እንዲሻገሩ እስራኤላውያንን እንዴት እንደረዳቸው በመታሰቢያነት ለማሳየት ነበር።

ሠ. በጌልገላ የአይሁድ መገረዝ (ኢያሱ 5)። አይሁድ 40 ዓመታት እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ ኖረዋል። ወንዶች ልጆቻቸውን አልገረዙም ነበር። ግዝረት አይሁድ በቃል ኪዳኑ ውስጥ ለመኖራቸው ውጫዊ ምልክት ነበር፤ በተጨማሪ ራሳቸውን ከኃጢአት የመለየታቸው ምልክት ነበር። በግብፅ ሊኖሩ የነበረባቸው የኃጢአት ነውር አልለቀቃቸውም ነበር፤ (ኢያሱ 5፡9)። ስለዚህ እግዚአብሔር አይሁድ ምድሪቱን እንዲወርሱ ከማድረጉ በፊት በመንፈሳዊ ሁኔታ ሊያዘጋጃቸው ያስፈልግ ነበር። በግዝረት የሕመም ስሜት ውስጥ ማለፋቸው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የማክበራቸውን አስፈላጊነት የሚያሳስብ ነበር። በዚያ ቀን በምድረ በዳ ለ40 ዓመታት የተመገቡት መና አበቃና የከነዓንን ምድር ፍሬ መብላት ጀመሩ። በዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ለመጀመሪያ ጊዜ አይሁድ በሰፈሩበት በጌልገላ የተፈጸመ አንድ ሌላ በጣም አስፈላጊ ነገር ነበር። ጌልጌላ የእስራኤል ሕዝብ ጊዘያዊ ዋና ማዕከል ሆነች። በዚህ ስፍራ ኢያሱ «የእግዚአብሔር ሠራዊት አዛዥ» የሆነውን ተገናኘው። መዋጋት ከመጀመሩ በፊት፥ የእስራኤልን ጦር የሚመራው እርሱ እንጂ ኢያሱ እንዳልሆን እግዚአብሔር ሊያስታውሰው ፈለገ። በመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ «የሠራዊት ጌታ» በመባል ይታወቃል። ብዙ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ «የሠራዊት ጌታ» የተባለው እግዚአብሔር የእስራኤል ማለት የሕዝቡ ሠራዊት እውነተኛ መሪ ነበር። ኢያሱ በእርሱ ትእዛዝ ሥር ነበር። ብዙ ሰዎች የጌታ ጦር አዛዥ የነበረው ይህ አለቃ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለው ያስባሉ።

የውይይት ጥያቄ ሀ) ለኢያሱ ይህንን እውነት የመረዳት አስፈላጊነቱ ምን ነበር? ለ) ዛሬ ይህንን እውነት ከሕይወታችን ጋር እንዴት ልናዛምደው እንችላለን?

ረ. እስራኤላውያን ኢያሪኮን ያለ ውጊያ ያዙ (ኢያሱ 6)። እስራኤላውያንን የገጠመቻቸው የመጀመሪያዋ ከተማ ጠንካራዋ ኢያሪኮ ነበረች። ዙሪያዋን በትልቅ ግንብ የታጠረች፥ በምሽት የሚዘጋ ትልቅ መዝጊያ የነበራት ስለሆነ፥ እርስዋን ማጥቃት ፈጽሞ አስቸጋሪ ነበር። ይህችን ከተማ ያለ አንዳች ጦርነት እንዲይዙዋት በማድረግ ድልን የሚሰጥ እግዚአብሔር እንጂ እነርሱ እንዳይደሉ አሳየ። እስራኤላውያን በኢያሪኮ ግንብ ዙሪያ በእምነት ስለዞሩ ቅጥሩ በሰባተኛው ቀን ወደቀ። በከነዓን ምድር በመጀመሪያ ልትጠፋ ያለችው ከተማ ኢያሪኮ ስትሆን በርሷም ውስጥ ያሉት ነገሮችን በሙሉ እንዲያጠፉ ወይም ለእርሱ ጥቅም ብቻ እንዲያውሉ እግዚአብሔር አዘዘ። ከጦርነቱ ምርኮ የሚገኝ ማንኛውም ነገር ቢሆን ለግል ጥቅም እንዳይውል ተከለከለ። በተጨማሪ ኢያሱ ይህችን ከተማ እንደገና ለመገንባት የሚሞክር ሰው ሁሉ በልጆቹ ሞት መከራ ያገኘው ዘንድ ከተማይቱን ረገመ (በ1ኛ ነገሥት 16፡34 የዚህን ጥቅስ ፍጻሜ እናገኛለን)።

ሰ. እስራኤላውያን በኃጢአታቸው ምክንያት በጋይ ተሸነፉ (ኢያሱ 7-8)። እግዚአብሔር በጋይ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ትምህርቶችን ለእስራኤላውያን ማስተማር ነበረበት። በመጀመሪያ፥ ድል ለማግኘት መደገፍ ያለባቸው በእግዚአብሔር እንጂ በራሳቸው ኃይል እንዳልነበረ ነው። እስራኤላውያን ትንሿን የጋይ ከተማ ያለ እግዚአብሔር ርዳታ በራሳቸው ኃይል እንደሚያሸንፉ ገመቱ፤ ነገር ግን ተሸነፉ። ሁለተኛው ነገር ደግሞ፥ እግዚአብሔር ለእነርሱ የሚሠራውን ሥራ በመካከላቸው እንዳይሠራ የሚከለክለው ኃጢአት እንደሆነ ማሳየት ነበረበት። አካን እግዚአብሔርን ስላልታዘዘና ከኢያሪኮ ከተማረከው ነገር ለራሱ የሚሆነውን ስላስቀረ እስራኤላውያን እንዲሸነፉ አደረገ። እስራኤላውያን በተሠራው ኃጢአት ከፈረዱና ከመካከላቸው ካስወገዱ በኋላ ብቻ እግዚአብሔር በጋይ ምድር ላይ ድልን ሰጣቸው። እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ያለውን ጥላቻ ለመግለጥና የእግዚአብሔርን ማኅበረሰብ ኃጢአት እንዴት ችግር ላይ ሊጥለው እንደሚችል ለማሳየት፥ ይህ ታሪክ፥ እግዚአብሔር አካንና ቤተሰቡ ሁሉ እንዲገደሉ መስማማቱን ያሳየናል። በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል የሚፈጸም ኃጢአት በዚያ ሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚሆን ግላዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በአጠቃላይ የሚመለከት ነው። በአክአብና በቤተሰቡ በተቃጠለ አካል ላይ የተከመረው ድንጋይ ኃጢአት እንዴት ሰዎችን እንደሚጎዳ የሚያሳይ የመታሰቢያ ሐውልት ሆኖ የሚያገለግል ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ድል ለማድረግ ባለን ችሎታ ላይ ኃጢአት ስለሚያመጣው ችግር ምን መማር እንችላለን? ለ) ስለ እግዚአብሔር ባሕርይና ኃጢአትን በከባድ ሁኔታ እንዴት እንደሚመለከተው ከዚህ ታሪክ ምን መማር እንችላለን? ሐ) ብዙ ጊዜ ኃጢአትን እንደ ቀላል ነገር የምንመለከተው እንዴት ነው? መ) በኃጢአት ላይ ስላለን አመለካከት ይህ ምን ይላል? ሠ) ኃጢአትን በቀላል ሁኔታ መመልከት በአጭር ጊዜ ውስጥ በቤተ ክርስቲያን እንዲስፋፋ የሚያደርገው እንዴት ነው?

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጋይን ካሸነፉ በኋላ ወደ ሴኬም ተጓዙ። ሴኬም የሚገኘው በጌባል ተራራ ግርጌ ነበር። በጌባልና በገሪዛን ተራራ ላይ በእግዚአብሔርና በእስራኤላውያን መካከል የተደረገው ቃል ኪዳን ታደሰ። በጌባል ተራራ ላይ የእግዚአብሔርን ሕግ ቢጠብቁ ስለሚያገኙት በረከት ከፊሎቹ እስራኤላውያን አነበቡ። የቀሩት ደግሞ በገሪዛን ተራራ ላይ ሆነው የእግዚአብሔርን ሕግ ባይጠብቁ ስለሚገጥሟቸው ርግማኖች የተጻፉትን አነበቡ። ከዚያም በአንድነት ቃል ኪዳናቸውን አደሱ።

ሸ. የገባዖን ሰዎች እስራኤላውያንን አታለሉ (ኢያሱ 9)። ከትላልቅና ከተገነቡ ከተሞች ብዙ ኪሎ ሜትር ሳያርቁ የሚገኙት የገባዖን ሰዎች በኢያሪኮና በጋይ የነበረቱን ከነዓናውያንን በማሸነፍ ሙሉ በሙሉ እንዴት እንዳጠፏቸው ሰሙ። ስለዚህ ከሩቅ ቦታ የመጡና ከእስራኤላውያን ጋር ለመተባበር የፈለጉ በመምሰል ሊያታልሏቸው ወሰኑ። አይሁድም በጉዳዩ እግዚአብሔርን ሳይጠይቁ ከሰዎቹ ጋር ስምምነት አደረጉ። እግዚአብሔር ከከነዓናውያን ጋር ምንም ዓይነት ስምምነት እንዳያደርጉ አግዶአቸው ነበር፤ (ዘጸ. 34፡ 12፥ 15)። ስለዚህ ጉዳይ ንጉሣቸው የሆነውን እግዚአብሔርን ስላልጠየቁ ተታለሉ። ለገባዖን ሰዎች ቃላቸውን ሰጥተው ስለ ነበር ምንም ነገር ያደርጉባቸው ዘንድ እግዚአብሔር አልፈቀድም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደምናየው እግዚአብሔር ሕዝቡ የገቡትን ቃል እንዲጠብቁ ከፍተኛ ትኩረት ያደርግ ነበር (ዘሌ. 19፡12-13)፤ ነገር ግን የገባኦንን ሰዎች ባሪያዎች አደረጉአቸው። 

ቀ. ከደቡብ ከነዓን ነገሥታት ጋር የተደረገ ጦርነት (ኢያሱ 10)። የደቡብ ከነዓን ነገሥታት የገባዖን ሰዎች ከእስራኤላውያን ጋር መተባበራቸውን በሰሙ ጊዜ ገባዖንን ወጉ። እስራኤላውያንም ከገባዖን ሰዎች ጋር ባደረጉት ስምምነት የተነሣ የገባኦንን ሰዎች በዚህ ጦርነት መርዳት ግዴታቸው ነበር፤ ስለዚህ እስራኤላውያን አምስቱን የከነዓን ነገሥታት ወግተው አሸነፏቸው። እግዚአብሔር አሁንም ለእስራኤል ሲል ተአምር አደረገ። የእነዚህን አምስት ነገሥታት ሠራዊት ፈጽመው ይመቱ ዘንድ ፀሐይን እንድትቆም አደረገ። የእስራኤል ጦር ከገደላቸው ይልቅ እግዚአብሔር ከሰማይ በላከው፥ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት ቁጥር ይበልጥ ነበር። ከዚህ በኋላ ኢያሱ ወደፊት በመገስገስ በደቡብ ከነዓን የሚገኙትን ሌሎች ዋና ዋና ከተሞች አሸነፈ። 

** እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን መዋጋቱን የሚገልጸውን የዚህን ምዕራፍ ትኩረት አስተውል (ኢያ. 10፡14፥ 42)። ጠላቶቻቸውን እንዲያሸንፉ ያደረጋቸው የራሳቸው ብርታት ሳይሆን ስለ እነርሱ ሲል የተዋጋው የእግዚአብሔር ኃይል ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ በሕይወታችን ለሚያጋጥመን ለማንኛውም ድል ይህ ነገር እውን የሆነው እንዴት ነው?

በ) የሰሜን መንግሥታት ተሸነፉ (ኢያሱ 11)። እስራኤላውያን በኢያሱ መሪነት በመካከለኛይቱ ከነዓን የሚገኙትን ዋና ዋና ነገሥታት (ኢያሪኮና ጋይ) እና እንደዚሁም የደቡብ ከነዓን ነገሥታትን ካሸነፉ በኋላ ወደ ሰሜን ከነዓን ከተሞች ዘመቱ (ኢያሱ. 11፡18)። ይህ ጦርነት ረጅም ጊዜ የወሰደ ቢሆንም (ኢያሱ 11፡18)፥ ሆኖም በሰሜኑም የሚገኙት ዋና ዋና ከተሞች በሙሉ ተሸነፉና እስራኤላውያን ተቆጣጠሩአቸው። 

አሁን እያንዳንዱ ነገድ በምድሪቱ የቀሩትን ከነዓናውያን የማጥፋት ኃላፊነት ነበረበት። ነገር ግን ለእግዚአብሔር በመታዘዝ እንደማጥፋት ከቀሩት ከነዓናውያን ጋር በሰላም መኖርን መረጡ። በዚህም ምክንያት ወደ ፊት እንደምናየው፥ ከነዓናውያን ኃጢአትን ለእስራኤል ሕዝብ በማስለመድና እነርሱን ወደ ኃጢአት በመምራት የእግዚአብሔር ቁጣ በእስራኤላውያን ላይ እንዲመጣ አደረጉ።

ተ) በእስራኤል የተሸነፉ የ31 ነገሥታት ዝርዝር (ኢያሱ 12)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በእግዚአብሔር ጠላቶች ላይ ድል ለመቀዳጀት የሚጠቅሙትን መመሪያዎች ከእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ዘርዝር። ለ) ድል አድራጊ ክርስቲያን እንድትሆን እነዚህን መሠረታዊ የሥነ ምግባር ሕግጋት ከሕይወትህ ጋር እንዴት እንደምታዛምድ ግለጽ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: