እውን ገሃነም አለ?

ገሃነም የግሪክ ቃል ሲሆን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥቅም ላይ ሲውል የሚቃጠል የቆሻሻ ክምር የሆነውን እና ከኢየሩሳሌም ወጣ ብሎ የሚገኘውን የሄኖም ሸለቆን የሚያመለክት ቃል ሊሆን ይችላል፡፡ ቃሉ ከሙታን ጋር በተያያዘ ሲቀርብ ደግሞ፣ ከትንሳኤ በኋላ የሚኖረውን የፍርድ ቦታ ያመለክታል፡፡ ገሃነም እና የእሳት ባሕር ተመሳሳይ ሃሳብን የሚገልጹ ሁለት ቃላት ናቸው (ማቴ. 10፡28፤ ማር 9፡43፣  ራዕ 19፡20፣ 20፡14)፡፡ የእሣት ባሕር፣ በመጨረሻው ዘመን የሰይጣን እና የማያምኑ ሰዎች የመጨረሻው የመቆያ ስፍራ ሆኖ በራዕይ 19፡20፣ 20፡10፣ 20፡14-15 ላይ ተጠቅሷል፡፡ ምንም እንኳን በአሁኑ ሰአት የሰይጣን እና የማያምኑ ሰዎች መኖሪያ ባይሆንም በመጨረሻው ዘመን ግን ሰይጣንንና ተከታዮቹ ለዘላለም የሚኖሩበት የስቃይ ስፍራ ይሆናል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ልክ ስለ መንግስተ ሰማይ አማናዊነት (እውነተኛነት) እንደሚያወራው ሁሉ ስለ ገሃነም አማናዊነትም ያወራል (ራዕይ 20፡14-15፣ 21፡1-2)። እንዳውም፣ ኢየሱስ ሰለ መንግስተ ሰማይ ተስፋ ለማስተማር ከወሰደው ጊዜ በላይ ሰዎችን ስለ ገሃነም አስከፊነት ለማስጠንቀቅ የወሰደው ጊዜ ይበልጣል፡፡ ልክ መንግስተ ሰማይ አማናዊ፣ ዘላለማዊ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ ሁሉ ገሃነምም አማናዊ፣ ዘላለማዊ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንግስተ ሰማያትም ሆነ ስለ ገሃነም ግልጽ ትምህርት ቢያስቀምጥም፣ ሰዎች የመንግስተ ሰማይን እውነታ በመቀበል የገሃነምን እውነታ ሲክዱ መመልከት ያልተለመደ ነገር አይደለም። በከፊል፣ ይህ አስተሳሰብ ከምኞት የሚመነጭ ነው፡፡ ከሞት በኋላ ስላለው “መልካም ነገር” ማሰብ፣ ከሞት በኋላ ስላለው “ጥፋት” እንደማሰብ ማራኪ ሊሆን አይችልም፡፡ ለዚህም ነው በቀላል የማይቆጠሩ ሰዎች ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ሲያስቡ የገሃነምን ሃሳብ ከጭንቅላታቸው ማስወገድ የሚፈልጉት፡፡  

ከምኞት በተጨማሪ የገሃነም መኖርን ላለመቀበል ስለ ገሃነም ምንነት የሚነሱ የተሳሳቱ ግምቶችን እንደምክንያትነት ማስቀመጥም የተለመደ ነው፡፡ ገሃነም ብዙውን ጊዜ ሲመሰል የሚታየው በሚቃጠል ጠፍ ስፍራ፣ በፍርስራሾች እና በሙታን መናፍስቶች በተሞላ የፈራረሰ ከተማ፣ በመንፍሳዊ እስር ቤት፣ ወዘተ ነው፡፡ ይህ አይነቱ እና መሰል አገለላለጾች መጽሐፍ ቅዱስ ስለገሃነም ከሚያወራው ጋር የሚስማሙ አይደሉም፡፡ 

አዲስ ኪዳን ገሃነምን መጨረሻ እንደሌለው ጥልቅ ጉድጓድ (ራዕይ 20፡3)፣ የእሳት ባሕር (ራዕይ 20፡14)፣ ጨለማ (ማቴዎስ 25፡30)፣ ሞት (ራዕይ 2፡11)፣ ዘላለማዊ ጥፋት (2 ተሰሎንቄ 1፡9)፣  ዘላለማዊ ሥቃይ (ራዕይ 20፡10)፣ ለቅሶ እና ጥርስ ማፋጫ ስፍራ (ማቴዎስ 25፡30)፣ እና የተለያየ መጠን ያለው ቅጣት የሚሰጥበት ስፍራ (ማቴዎስ 11፡20-24፣ ሉቃስ 12፡47-48 ፤ ራዕይ 20፡12-13) አድርጎ አቅርቧል፡፡ 

ስለ ገሃነም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተወሰኑ ገለጻዎች ተሰጠው እናያለን፡፡ ሆኖም ይህ ገለጻ በርካታ ሰዎች በሚያስቡት መልክ የቀረበ አይደለም፡፡ እስቲ ከዚህ በታች የቀረቡትን ተጨማሪ ጥቅሶች ለአብነት ይመልከቱ፡-

ኢሳይያስ 66፡24 ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትምና፥ እሳታቸውም አይጠፋምና፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ።

ማቴዎስ 13፡41-42 ፣ የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።

ማቴዎስ 18፡8፣ 9 እጅህ ወይም እግርህ ብታሰናክልህ፥ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንካሳ ወይም ጉንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል። ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።

ማቴዎስ 25፡41 በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል፦ እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ።

ማርቆስ 9፡44 እጅህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት ወደ ገሃነም ወደማይጠፋ እሳት ከመሄድ ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻላል።

የሉቃስ ወንጌል 16፡19-31 በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። እርሱም እየጮኸ፦ አብርሃም አባት ሆይ፥ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ።

ራዕይ 14፡11 የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል፥ ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት የሚቀበል ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።

ራዕይ 20፡12፣ 15 ፣ ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ።..በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።

ራዕይ 21፡8 ፣ ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው።

እንደምናውቀው ገሃነም በመጀመሪያ የተፈጠረው መንፈሳውያን ለሆኑት ለሰይጣን እና መላእክቱ እንጂ ለሰዎች አይደለም (ማቴዎስ 25፡41)። በገሃነም መኖር በእሳት ውስጥ ከማቃጠል ጋር ተነጻጽሯል (ማርቆስ 9፡43፣ 9፡48፣ ማቴዎስ 18፡9፣ ሉቃስ 16፡24)፡፡ እንዲሁም፣ በጨለማ ውስጥ ከመኖር (ማቴዎስ 22፡13) በከከባድ ሀዘን ውስጥ ከመኖር (ማቴዎስ 8፡12) እና በስቃይ ከመኖር ጋርም ተነጻጽሯል  (ማርቆስ 9፡44)።

በአጭሩ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በገሃነም ውስጥ መኖር ምን “ሊመስል” እንደሚችል እንጂ ገሃነም ምን እንደሆነ ወይም እንዴት እንደሚሰራ በግልጽ አይነግረንም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግልፅ ያደረገው ነገር ቢኖር፣ ገሃነም አማናዊ (እውነተኛ)፣ ዘላለማዊ፣ የስቃይ ስፍራ እና ወደ እዚህ ስፍራ ላለመሄድ ማድረግ ያለብንን ሁሉ ማድረግ እንዳለብን ነው (ማቴዎስ 5፡29-30)።

ከዚህ የጥፋት ስፍራ ለመዳን የሚሹ ከሆነ ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ በመጫን ጽሁፉን ያንብቡ፡-  

ከዘላለም ሞት ፍርድ ለመዳን ምን ማድረግ አለብኝ?

1 thought on “እውን ገሃነም አለ?”

Leave a Reply

%d bloggers like this: