መለያየት በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ (1ኛ ቆሮ. 1:4-17)

1ኛ ቆሮንቶስ 1:4-17ን በጥንቃቄ በመመልከት የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ። 

ጥያቄ 1. ጳውሎስ «ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ እንደጸና» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 2. በቁጥር 9 ላይ ሐዋርያው ክርስቲያኖች ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ እንዲሆኑ ይነገራቸዋል፤ ያ ነገር ምንድነው?

ጥያቄ 3. ጳውሎስ፣ “ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ ” (ቁጥር 10) ሲል ሰዎች ሁሉ ተመሳሳይ ሃሳብ እንዲይዙ መፈለጉን ያሳያል?

ጥያቄ 4. በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመለያየት መነሻ የሆናቸው ነገር ምን ነበር? (ቁጥር 12ን ተመልከት።) 

ጥያቄ 5. በውኃ ጥምቀትና በወንጌል መስበክ መካከል ያለውን ልዩነት በማጤን በአጭሩ መግለጫ ስጥ። 

ጥያቄ 6. ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ዘርዝር። ለ) በእነዚህ ችግሮች ላይ ማተኮር ተስፋ መቁረጥን ወይም ፍራቻን እንዴት ሊያስከትል እንደሚችል ግለጽ። ሐ) እግዚአብሔር በግለሰቦችና አብያተ ክርስቲያናት ሕይወት በመሥራት ስሙን ሊያስከብር በመቻሉ ላይ ብናተኩር አመለካከታችን እንዴት ይቀየራል?

ምንም እንኳ የቆሮንቶስ ምእመናን በድካማቸው ሐዋርያውን ቢያደክሙትም በመጀመሪያ የሰበከላቸው ወንጌል በእነርሱ ዘንድ ሥር ሰዶ መገኘቱ እግዚአብሔርን ስለ እነርሱ እንዲያመሰግን ረድቶታል፤ «ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ እንደጸና» ይላልና። ይህ ጽናትም በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ተመስክሮአል፤ «በነገር ሁሉ በቃልም በእርሱ ባለጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋል»፡፡ 

በክርስቶስ ጸንተው እስከቆዩ ድረስ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እየበዛላቸው እንጂ እያነሰባቸው አይሄድም፤ «የጌታችንን መምጣት ስትጠባበቁ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም»፡፡ የጌታን መምጣት መጠባበቅ ማለትም በክርስትና ሕይወት ታማኝ ሆኖ መኖር ማለት ነው። ይህ በክርስትና ሕይወት ታማኝ ሆኖ መኖር ራሱ በጸጋው የሚሰጠን እንጂ በራሳችን ጥረት የምናሳየው አይደደም፤ «እርሱም ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል»፡፡ በሚገጥሙን ነገሮች ሁሌ ታማኝ ሆነን ስንገኝ በነገር ሁሉ እግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ እንደሚረዳን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። 

ይህ ጽናት የሚመጣው:- 1ኛ. አገልጋዮች በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ተገልጋዮችን ሲረዱ፤ 2ኛ. ተገልጋዮች የተነገራቸውን ጉድለት በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ሲያርሙ ነው። ይህንንም አገልገሉት ሐዋርያው በ1:10-13 ባለው ውስጥ ያቀርብላቸዋል። እንግዲህ አንደ ተስፋ ቃሉ መሠረት እስከፍጻሜ ጸንተው ለመቆየት ይህን የማይገባ መከፋፈላቸውን ማረም ይኖርባቸዋል። 

ሐዋርያው «ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝምና ወንጌልን ልሰብክ እንጂ » ሲል ጥምቀትና ወንጌል የተለያዩ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ጥምቀት ምልክት ብቻ እንጂ የማዳን ኃይል የለውም፡፡ ወንጌል ግን ፍጹም የማዳን ኃይል ነው፤ (ሮሜ 1:16 እና 17 ተመልከት)፡፡ ስለዚህ ጥምቀት ያድናል ብለው የሚያምኑ በዚህ ሐዋርያዊ ቃል ሃሳባቸውን ማረም ይገባቸዋል። 

በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መለያየትን የፈጠረው ክርስቲያኖቹ ዓይናቸውን ከክርስቶስ ላይ አንሥተው በሰው ወይም ሰው ሰራሽ በሆኑ ሥጋውያን ሥርዓቶች መደገፍ ስለጀመሩ ነው። ይህም በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በአገልጋዮቻቸው ላይ መደገፍና እንዲሁም በወንጌል ቃል ሳይሆን በጥምቀት መመካታቸው ነው። 

የጳውሎስ ምኞት የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በአንድ መንፈስና በአንድ ልብ እንድትዋሃድ ነበር። እነርሱ ግን እውነተኛ ደህንነት በሚገኝበት በመስቀሉና በኢየሱስ ላይ ዓይናቸውን ከማድረግ ፋንታ በሰዎች ላይ ነበር የታመኑት። በተጨማሪም አንዳንዶች የአይሁድ ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆነው የኬፋ (ለጴጥሮስ የተሰጠ ሌላ ስም) ተከታይ ነኝ እያሉ ፥ ሌሎች ደግሞ የአሕዛብ ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆነው የጳውሎስ ተከታይ ነኝ እያሉ፣ በመጨረሻም ዳግሞ ሌሎች ጳውሎስ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን መሥርቶ ከሄደ በኋላ እዚያ ድረስ መጥቶ የሰበከውና ያስተማረው የአጵሎስ ተከታይ ነን በማለት እርስ በርሳቸው ተከፋፍለው ነበር። (የሐዋ. 18፡24-19:1 ተመልከት)፡፡ ከዚህም በላይ አንዳንዶች ከትዕቢት የተነሣ የእኛ ከሌሎች ይሻላል በማለት ራሳቸውን «እውነተኛቹ የክርስቶስ ተከታዮች» በማለት ሰይመዋል። 

አማኞች በሙሉ እምነታቸው የተመሠረተው በኢየሱስ ክርስቶስና በመስቀሉ ላይ ነው። ደህንነታቸውንም የሚያገኙት ለኃጢአታቸው በሞተው በክርስቶስ በማመን ነው። ያኔ ምንም መከፋፈል በሌለበት በክርስቶስ ቤተሰብ ውስጥ ይጠመቃሉ፡፡ ስለዚህም መከፋፈልና መደባደብ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምንም ቦታ አይኖረውም። ምንም እንኳ የተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት በተለያየ ሃሳብ ቢመሩም፥ እምነታችን በዚህ ላይ አይደለም፡፡ እምነታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እስከሆነና የእርሱን ቃል በታዛዥነት እስከጠበቅን ድረስ የተለያየ ሃሳብም ቢኖረን እንኳን አብረን ልናመልክ እንችላለን።

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d bloggers like this: