መንፈሳዊ ጉልምስና ( 1ኛ ቆሮ. 3:1-23) 

1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 3 ስላ መንፈሳዊ ጉልምስና በሰፊው ያስተምራል። በመንፈስ የመዳን ዋናው ምልክት ክርስቲያን ሕይወቱን ለእግዚአብሔር አገልግሎት መስጠቱ ነው። በቁጥር 9 ላይ «ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና» ይላል። ክርስቲያን እግዚአብሔርን ለማገልገል ታጥቆ ሲነሣ ከእርሱ ጋር አብሮት የሚሠራው እግዚአብሔር እንደሆነ ተረድቶ በእምነት መሠማራት አለበት፡፡ እኛም የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆናችንን ብቻ ሳይሆን በአገልግሎታችን ተባባሪ ሆኖ ኃይል የሚሰጠን እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡

1ኛ ቆሮንቶስ 3ን አንብብ። 

ጥያቄ 1. ከቁጥር 1-4 ያለውን ክፍል በጥንቃቄ ተመልክተህ በሥጋዊነትና በዓለማዊነት መካከል ያለውን መወራረስ (ተመሳሳይ ባሕሪይ) አስረዳ።

ጥያቄ 2. ከቁጥር 5-9 ባለው ክፍል ውስጥ ሁለት ሠራተኛች ተጠቅሰዋል፤ እነማን ናቸው? 

ጥያቄ 3. ቁጥር 10-15ን በመመልከት «የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጕዳበታል፤ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት አንደ ሚድን ይሆናል» የሚለውን በራስህ አማርኛ በአጭሩ ገልጸህ አስረዳ። 

ጥያቄ 4. ቁጥር 15ንና 1ኛ ቆሮንቶስ 6:9ና 10ን አስተያይተህ በሁለቱ መካከል ያለውን ተቃራኒ የሚመስል ሃሳብ አስታርቅ፡፡

መንፈሳዊ ጉልምስና የሚከተሉትን ያሳያል 

1ኛ. ሥጋዊነትን ያስወግዳል ( 1-4) 

2ኛ. አገልግሎት ምን እንደሆነ ይገነዘባል፤ ( 5-9) 

3ኛ. የአገልግሎቱን ድካም በእግዚአብሔር ሚዛን ላይ ያስቀምጣል፤ ( 10-17) 

4ኛ. በሰው ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥበብ ያገለገላል፤ ( 18-23) 

ከላይ ከ1-4 የተዘረዘሩትን ነጥቦች በየተራ እንመልከታቸው፡፡

1ኛ . መንፈሳዊ ጉልምስና ሥጋዊነትን ያስወግዳል ( 1-4) 

በመሠረቱ ሕፃንነት በራሱ አስነቃፊ አይደለም፤ ነገር ግን ሰው በሕፃንነት ሲሰነብት የጤንነት አለመሆኑ ግልጽ ነው። በመንፈሳዊ ደረጃ ነገሩ የከፋ ነው። በመንፈሳዊ ሕይወቱ የማያድግ ክርስቲያን ባለበት አይቆምም፤ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ወደ ሥጋዊነት እያዘነበለ ይመጣል፡፡ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጽኑ ምግብ በመመገቢያቸው ወቅት ወተት መጋት ነበረባቸው። ይህ ሕፃንነት ግን ኃጢአትንም አስከተለ፤ «ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን?» (ቁጥር 2ና 3)፡፡ 

በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በኩል ሥጋዊነታቸው የተገለጠው እርስ በርስ ባለመስማማት ነበር፤ በእኛስ በኩል ሥጋዊነታችን በምን ይገለጣል? አለመጎልመስ እስካለ ድረስ ሥጋዊነትም አብሮ እንዳለ መገንዘብ አለብን። ግን የሥጋዊነት መግለጫ ሊለያይ ይችላል። መለያየትና መከራከር አለመቀራረብ፥ ለመንፈሳዊ ነገር ቅድሚያ አለመስጠት፥ ገድየለሽነት የመሳሰሉት የሥጋዊነት መግለጫዎች ናቸው፡፡ 

ጥያቄ 5. ሀ/ በሕይወትህ መንፈሳዊ ጎልማሳ ነህ? መሆንህን ወይስ አለመሆንህን በምን አወቅህ? ለ/ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ሰዎች መንፈሳዊ ሕፃናት ናቸውን? አለመጎልምሣቸውን በምን ያሳያሉ? 

2ኛ. መንፈሳዊ ጉልምስና አገልገሎት ምን እንደሆነ ይገነዘባል፤ (5-9) 

ሥጋውያን ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ከመለያየታቸውም በላይ በአገልጋዮች መካከልም የመለያየት ምክንያት ይሆናሉ፤ (ለምሳሌ ያህል ማርቆስ በጳውሎስና በባርናባስ መካከል መለያየትን ፈጠረ፤ የሐዋ.15:36-41)። ይህንም የሚያደርጉት የአገልግሉት ነገር ገና ስላልገባቸው ነው፤ (ቁጥር 6-8)፡፡ 

ሰው የእግዚአብሔር መሆኑን ከተገዘበ «የእከሌ ተከታይ ነኝ» ከሚለው የሕፃን ጭቅጭቅ ውስጥ አይገባም። የእግዚአብሔር ከሆነ አገልጋዮቹ በሙሉ የርሱ ናቸው እንጂ አንዱ ወይም ሁለቱ ብቻ አይደሉም። 

የእግዚአብሔር ሀብት መሆናችሁን የተገነዘባችሁ ስንቶች ናችሁ? የእግዚአብሔር ከሆናችሁ በሕይወታችሁ እግዚአብሔርን ለማስቀደም ምን ያህል ጥረት ይታይባችኋል? ለምትወስኑት ውሣኔ «ይህ እግዚአብሔርን በበለጠ እንዳገለግል ይረዳኛል» ብላችሁ ከራሳችሁ ጋር ትነጋገራላችሁ ወይ? ወይስ ጭራሽ የእግዚአብሔር ነገር ከውሣኔአችሁ ውስጥ አይገባም? ለአንዳንድ ክርስቲያን ነን ባዮች በእግዚአብሔር ማመን እንደ ጌጥ ትርፍ ነገር እንጂ የሕይወታቸው መነሻና መድረሻ አይደለም። “የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ” የሚለው ቃል በሕይወታቸው ውስጥ ቦታ ያለው አይመስልም። አንግዲያስ አንድ ሰው ይህን ካልተገነዘበ የመንፈሳዊ አገልግሎት ትርጉሙ በፍጹም ገና አልገባውም። ይህም ከሆነ መንፈሳዊ ሕፃንነቱ ሥር ከመስደዱ የተነሣ አስተሳሰቡ ዓለማዊ ነው። 

በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ እግዚአብሔር ለተለያየ ሥራ የተለያዩ መሪዎችን ይጠቀማል። እንደ ጳውሎስ ያሉ ወንጌላውያን ወንጌልን ለሌሎች ያዳርሳሉ፤ እንደ አጵሎስ መጋቢና መምህራን የሚሆኑ ደግሞ ያመኑትን በእምነታቸው እንዲያድጉ ይረዱአቸዋል። ሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለበለጠ ዓላማና ግብ በሕብረት መሥራት ይገባቸዋል። ይህም ግብ የቤተ ክርስቲያንን ዕድገት በየጊዜው በመገምገም የእግዚአብሔር ሕዝብ በእምነቱ ሲያድግ ማየት ነው፤ (ኤፌ.4:11-13)። ሁላችንም ብንሆን የምናገለግለው መንፈሳዊ እድገት ሊሰጠን የሚችለውን አንዱን ኢየሱስ ክርስቶስን በመሆኑ በልባችን ከእኛ ጋር ከሚያገለገሉት ከሌሎቹ የበለበ ክብር የመፈለግ ምኞት ሊኖረን አይገባም። 

ጥያቄ 6. ሀ/ በተለያየ መልክ በመሪነት በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚያገለግሉትን ሰዎች ስም ዝርዝር ጻፍ። እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያንህ ያለውን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ አብረው በሕብረት የሚሠሩት አንዴት ነው? ለ/ አንዳንዴ ሰይጣን በመካከላቸው የምቀኝነትን ሃሳብ በማምጣት የእግዚአብሔርን ሥራ የሚያደናቅፍባቸውን መንገዶች ገልፅ። 

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አገልግሎታችንን ከአገልጋዮች ወይም ከሽማግሌዎች አንፃር ሳይሆን ከእግዚአብሔር አንፃር ካላየነው አገልጋዮችን እንደ ጣዖት ተደግፈናቸዋል ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በጌታ የሚታመን አያፍርም” ይላል። ስለዚህ ከጌታ በስተቀር በሌላ የሚተማመን እንደሚያፍር ግልጽ ነው። 

3ኛ. መንፈሳዊ ጉልምስና የአገልግሉቱን ድካም በእግዚአብሔር ሚዛን ላይ ያስቀጣል፤ ( 10-17) 

ሰውን የሚያይ፥ መንፈሳዊ አገልግሎቱን በሰው መሠዊያ (ገበታ) ላይ የሚያስቀምጥ የእግዚአብሔርን ሚዛን አያይም። እርምጃው ሁሉ ሰውን ለማስደሰትና ሰው በእርሱ እንዲደሰት ነው። ይህ ሳይሳካ ሲቀር ይሰባበራል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እኔ የእከሌ ነኝ በማለት በመከራከር ላይ ሳሉ ለራሳቸውና ለአገልጋዮቻቸው የተዘረጋውን የእግዚአብሔርን ሚዛን ረሱ። የአገልጋዮችን ሕይወትና ድካም መዛኝ እግዚአብሔር እንደሆነ ጳውሎስ ያስረዳል። 

ሆኖም ይህን ሲል አገልጋይ በኃጢአት ሲመላለስ አይገሠጽ ማለቱ አይለም። ኃጢአትን መገሠጽ እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል (1ኛ ቆር. 5፡1-2 እና 11-13)። በዚህ ክፍል ውስጥ የሚናገረው ስለ አገልገሎት ድካም መዛኙ እግዚአብሔር መሆኑን ለማስረዳት ብቻ ነው። ስንቶች ነን «በመጨረሻ ግዜ እግዚአብሔር ሥራዬን ገልጦ የሚመዝንበት ጊዜ ስለሚመጣ አሁን ሰውን ሳልመለከት እግዚአብሔርን በትጋት ላገልግል የምንል?» ደግሞም ሰው ይህን ካላለ አግዚአብሔርን ማገልገል አይችልም። 

በዚህ ነገር ሰው ካልተጠነቀቀ በሰው ተሰናክሎ የእግዚአብሔርን ቤት ወደ ማፍረስ ይደርሳል (16ና 17)። ያ ከሆነ ያገልግሉት ሽልማት ብቻ የማጣት ነገር ሳይሆን (14ና 15) ጠቅላላ ሕይወቱ በእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ ይወድቃል። ስለዚህ ሰውን ሳይመለከቱ ማገልገል በድካም እንዳንዝል ከማድረጉም በላይ በእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ እንዳንወድቅ ይረዳናል። 

ጥያቄ 7. እኛ ስለ እግዚአብሔር ሚዛን ብናስብ ኖሮ የእኛ ወይም የሌሎች አገልግሎት እንዴት ነበር የሚለወጠው? 

እግዚአብሔርን ማገልገሉ ብቻ በቂ አይደለም፤ እንዴት እንደምናገለግለው ማጤኑም ተገቢ ነው። የምንሠራው ሥራ ከንጹሕ ልብ የመነጨ መሆን ይገባዋል። ሥራው የእግዚአብሔር ቤት በሆነው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዘላቂ የሆነ ለውጥን ማስገኘት አለበት። በእግዚአብሔር የፍርድ እሳት ውስጥ ለእርሱ ክብር ያልሆነ ወይም ከንጹሕ ልብ ሆነን ያልሠራነው ነገር ሁሉ (እንደ እንጨት፥ ሣርና አገዳ) ምንም ጥቅም እንዳሌለው ይታያል። ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ልጆች ብንሆንና ብንድንም ለሠራነው ሥራ ምንም ሽልማት አይኖረንም። በትክክልኛ ንጹሕ መንፈስ ተነሣሥተን ለእግዚአብሔር ክብርና ቤተ ክርስቲያን ጥሩ የሆነ ሥራ ከሠራን ሥራችን ዘላቂ (እንደ ብር፥ ወርቅና የከበረ ድንጋይ) ይሆናል። በተጨማሪም ከእግዚአብሔር ሽልማት እናገኛለን። በእግዚአብሔር ሚዛን ሲለካ ሥራችን የሚያሸልም እንዲሆን እስቲ ሁላችንም ሥራችንንና ልቦናችንን እንመርምር። 

1ኛቆሮ. 3፡15፣ የአማኞች ሥራ እንዴት እንደሚፈተን ነው የሚናገረው። እግዚአብሔር ስለ ኃጢአታቸው እንደገና በአማኞች ላይ እንደማይፈርድባቸው ቃል ገብቷል። ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ለአማኞች ቅጣቱን ከፍሎላቸዋል (ዮሐ.5፡24)። እውነተኛ አማኝ የእግዚአብሔርን ሥራ ሳይሠራ ወደ መንግሥተ ሰማይ ሊገባ ይችላል፤ ቢሆንም ይህ ሰው አሁንም የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል ነው። 1ኛቆሮ.6፡9-10 ግን የሚናገረው የእግዚአብሔርን የዘላለም ሕይወት ስጦታ ስላልተቀበሉና ዝም ብለው በኃጢአት ኑሮ ውስጥ ያለማቋረጥ ስለሚኖሩ ሰዎች ነው። 

4ኛ መንፈሳዊ ጉልምስና በሰው ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥበብ እንድናገለግል ይረዳናል፤ (18-25) 

አንዳንድ ጊዜ በሰው ፊት ተወዳጅ ሆኖ ለመቅረብ ሰው ብዙ ዓለማዊ ጥበብ ይጠቀማል። ግን ይህ በእግዚአብሔር ፊት ምንም ዋጋ የለውም። “ጌታ የጥበበኞችን አሳብ ከንቱ እንደሆነ ያውቃል”። ሰውን ማታለል ይቻላል፤ እግዚአብሔር ግን ስለማይታለል በእግዚአብሔር ቤት የዓለምን ጥበብ ማስወገድ አለብን። 

ሕይወታችንን በጥንቃቄ እንጠብቅ። በእግዚአብሔር እንደምንመዘን ሳንዘነጋ በሕይወታችን እግዚአብሔርን ከማገልገል አንቦዝን። ሕይወታችን ለራስ መደሰቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ማክበሪያ ነውና በሕይወታችን እግዚአብሔርን እናክብር። «የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ የእግዚአብሔር ሕንጻ ናቹሁ… የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ… ናችሁ»።

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d bloggers like this: