የ1ኛ ቆሮንቶስ መግቢያ 

1ኛ ቆሮንቶስ የተጻፈው በሐዋርያው ጳውሎስ ነው! ( 1ኛ ቀር.1፡1)። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረችው ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከተማ ለአሥራ ስምንት ወር በተቀመጠበት ጊዜ ነበር፤ (የሐዋ.18፡1-11) አንብብ። በዚህ በቆሮንቶስ ከተማ የተለያዩ የሕዝብ ዘሮች ይኖሩ ነበር። በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ እንዲሁ የተቀላቀሉ ወገኖች ይገኙ ነበር፤ ለምሳሌ አህዛብና አይሁዶች ነበሩ። ይህን ዓይነት የዘር ልዩነት በዘመናችን በየቤተ ክርስቲያኑ እናገኛለን። ይህንን የዘር ልዩነት በዚያን ጊዜ የመከፋፈል ዝንባሌ እንደፈጠረ አሁንም ያው ችግር ሊነሣ ይችላልና መፍትሔውን በጥንቃቄ ከቃሉ እንመልከት። 

የቆሮንቶስ ሰዎች በንግድ በጣም የተራመዱ ስለነበሩ ሀብታሞች ነበሩ። ደግሞም የቆሮንቶስ ከተማ ሰዎች በኃጢአት በጣም የከፋ ከመሆናቸው የተነሣ «እንደ ቆሮንቶስ ሰው ኑር» የተሰኘ ምሳሌያዊ አነጋገርን አትርፈው ነበር፡፡ በዚህ ሕዝብ መካከል እግዚአብሔር ለራሱ ወገንን መረጠ፤ ( 1ኛቆሮ.6፡9-11)። የኃጢአት ብዛት እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑን ከመትከል አላገደውም!! 

ጳውሎስ ይህን ጸብዳቤ ለመጻፍ የተነሣሣበት ሁለት ምክንያቶች ነበሩት፡

1ኛ / ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ደስ የማይል ሪፖርት ሰምቶ ስለነበር፤ (1:11፤ 5:1) ተመልከት። 

2ኛ / የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ጳውሎስን የተለያዩ ጥያቄዎች ጠይቀውት ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለመስጠት በበር፤  (7:1 ተመልከት)። 

ስለ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ከሰማቸው ሪፖርቶች ውስጥ አምስቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ መከፋፈል ነበር (3፡1-4)። 
  2. ከአባሎቹ ውስጥ አንዱ በክፉ ዝሙት ይኖር ነበር፤ (5:1)። 
  3. በአማኞች መካከል በፍርድ ቤት መካሰስ ነበር፤ ( 6፡6-8)። 
  4. በክርስቲያን ነፃነት እያሳበቡ የሚፈጸሙ ስሕተቶች ነበሩ፤ (10:23-33)። 
  5. በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ብዙ ከሥነ ሥርዓት ውጭ የሆኑ ድርጊቶች ነበሩ። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የጌታ እራት አፈጻፀም ሥርዓት ነበር፤ (11:27-30)። 

የቆሮንቶስ ሰዎች ለጠየቁት ጥያቄዎች ሐዋርያው መልስ የሰጠባቸው ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው። 

  1. ስለ ጋብቻ ጥያቄዎች፤ (ምዕራፍ 7)። 
  2. ለጣዖት ስለተሠዋ ሥጋ (10:14-22)። 
  3. በጉባኤ ውስጥ ስለ ሴቶች መከናነብ (11፡1-16)። 
  4. ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች (ከምዕራፍ 12-14)። 
  5. ስለ ሙታን ትንሣኤ፤ (ምዕራፍ 15)። 

ለእነዚህ ጥያቄዎች በሚሰጣቸው መልሶች በዚያን ጊዜ ስለነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ጠባዮች ብዙ ነገሮችን እንረዳለን። በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን በሚገጥሟት ችግሮችና በዚያን ጊዜ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን በገጠሟት ችግሮች መካከል ብዙ መመሳሰል ስላለ ይህ መጽሐፍ ለእኛም አብያተ ክርስቲያናት በቃሚ የሆኑ መመሪያዎችን ይሰጣል። በሚከተሉት ትምህርቶች ውስጥ እዚህን ነጥቦች በዝርዝር እንመለከታቸዋለን። 

ጥያቄ 1. የሐዋ. 18፡1-11ን በጥንቃቄ በመመልከት የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን አመሠራረትን ተርክ። 

ጥያቄ 2. ይህን ደብዳቤ ለመጻፍ ያነሣሡት ሁለት ምክንያቶች ነበሩ፤ ለእያንዳንዱ ምክንያት የተሰጡትን ጥቅሶች በመመልከት ምክንያቶቹን ጥቀስ፡፡

ጥያቄ 3. በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉ ችግሮች በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ከነበሩት ችግሮች ጋር እንዴት ይመሳሰላሉ?

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d bloggers like this: