ሰላምታ (1ኛቆሮ.1:1-3) 

ሐዋርያው ጳውሎስ ደብዳቤ ለመጻፍ የተነሣሣው ችግሮች መነሣታቸው አስገድደውት ቢሆንም ደብዳቤውን ሲጀምር ችግርን በመጥቀስ ሳይሆን የችግራችን ሁሉ መፍትሔ የሆነውን የእግዚአብሔርን ጸጋ በመተረክ ነው። ይህን ለግል ክርስቲያን ኑሮአችንም ሆነ ለአገልገሎታችን መመሪያ ማድረግ አለብን። ችግር ሲያጋጥመን ማተኮር ያለብን ለችግራችን መፍትሄ በሆነው በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ እንጂ በችግራችን ትልቅነት ላይ መሆን የለበትም። ይህንን ክፍል ስናጠና የሐዋርያውን ምሳሌ እንከተል! 

1ኛ ቆሮንቶስ 1:1-3ን አንብብና ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ስጥ። 

ጥያቀ 1. «ሐዋርያ» ማለት ምን ማለት ነው? (የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመመልከት መልስህን አዘጋጅ፤ በተጨማሪም ኮሜንታሪ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ለመመልከት ሞክር፤ (ሉቃስ 6፡12-16፣ የሐዋ.1፡21-22፤ 1ኛቆሮ. 9፡1-2 ገላ.1፡1-2)። 

ጥያቄ 2. «በቆሮንቶስ ላለች ቤተ ክርስቲያን» ሲል የሚያመላክተው ወደ ሕንፃው ነው ወይስ ወደ ሕዝቡ? (ለመልስህ እንዲረዱህ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፤ ሮሜ 16፡5፤ ፊልሞና 2)፡፡

ጥያቄ 3. በቆሮንቶስ የነበሩ ክርስቲያኖች ብዙ መንፈሳዊ ድካሞች ሲገኙባቸው እንዴት ጳውሎስ «ቅዱሳን» ወይም «በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት» ይላቸዋል? (ለመልስህ ሃሳብ ከ1ኛ ቆሮ. 6፡9-11 ላይ ተመልከት)። 

ሐዋርያው ጳውሎስ መልእክቱን ሲከፍት ሐዋርያነቱን በመናገር ይከፍታል። ይህም ገና ሲጀምር ደብዳቤው የግል ሳይሆን በሐዋርያነት ደረጃ የጻፈላቸው መሆኑን ያስረዳቸዋል። የሐዋርያን መመሪያ አለመቀበል የአንድ ተራ ሰውን መመሪያ አለመቀበል አይደለም። የሐዋርያ ቃል የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል፣ የእግዚአብሔር ቃል ነበርና! ( 1ኛቆሮ.14:37)። አንድ ሰው ሐዋርያ ሊባል የሚችለው በኢየሱስ ለሐዋርያነት ሲመረጥና ከሞት የተነሣውን ኢየሱስን በዓይኑ ካየ ነው። ኢየሱስ ካረገ በኋላ ሐዋርያት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነበሩ። 

«በቆሮንቶስ ያለች የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን» ሲል በጳውሎስና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች መካከል እግዚአብሔር ያለ መሆኑን ያስገነዝባል። የእግዚአብሔር መሆናቸው በ3፡9 ላይና በ3:16 ላይ በሰፊው ተገልጿል። እነዚህን ጥቅሶች ተመልከታቸው፡፡ቤተ ክርስቲያን በእጅ የተሠራ ሕንፃ ሳይሆን እግዚአብሔር ያዳናቸውና ከኃጢአት ያነፃቸው የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑ ሕዝቦችን ያመለክታል። 

«በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት» ክርስቲያን ማለት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የታጠበና የተቀደሰ ነው። በ1ኛ ጴጥ.1:1 እና 2 ላይ በክርስቶስ ደምና በመንፈስ ቅዱስ የተቀድስን መሆናችንን ያስረዳል፡፡በኤፌሶን 5:25-27 ላይ ደግሞ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስና በቃሉ የተቀደሰ እንደሆነ ተጽፏል። 

ጥያቄ 4. ክርስቶስን እንደ ግል መድኃኒት አድርገህ ተቀብለህ የተቀደስከው መቼ ነበረ? በየዕለቱስ ቅድስናህን የምታሳየው እንዴት ነው? 

ክርስቲያን ገና ዕለት በዕለት ከሚሠራቸው ኃጢአቶች ነፃ ያልሆነ ሲሆን እንዴት ቅዱስ ሊባል ይችላል? መልሱ ይህ ቅድስና በእግዚአብሔር ፊት ያለውን አቋማችንን የሚገልጽ እንጂ በራሳችን ሙሉ ቅድስናን ያልተቀዳጀን መሆናችንን አይክድም፡፡ የቆሮንቶስ ክርስቲያና፥ በዕለት ኑሮአቸው ብዙ መንፈሳዊ ጉድለቶች ሲታዩባቸው በእግዚአብሔር ፊት ግን ፍጹም ቅዱሳን ነበሩ፤ (6፡11ን በጥንቃቄ ተመልከት)። 

«የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየሥፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር» ይህ ዐረፍተ ነገር ሁለት ሐሳቦችን በአንድ ጊዜ ያሳስበናል፡-

1ኛ . ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ የተስፋፋች እንጂ በአንድ ቦታ ብቻ የምትገኝ አለመሆንዋን ሲያስረዳ፤ 

2ኛ . እውነተኛ ምእመናን ደግሞ በየሥፍራው እርስ በርስ የሚሰበሰቡ መሆናቸውን ያስረዳል። 

«ጸጋና ሰላም» በዘመኑ ይሰጥ የነበረ የሰላምታ ቃል ሲሆን ጳውሎስ ሐሳቡን ወደ ክርስቲያን ለውጦ «ጸጋና ሰላምን ከእግዚአብሔር የሚሰጡ በረከቶች መሆናቸውን ያስተምራል።

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d bloggers like this: