አገልግሉት በሰው ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጥበብ መሆን አለበት (1ኛ ቆሮ. 2:1-16) 

እግዚአብሔር በጠቢባን ሳይሆን በደካሞች ይጠቀማል ሲባል ያገኘነውን እውቀት እግዚአብሔር አገልገሎት ላይ አናውለው ማለት አይደለም፤ ወይም ደግሞ ለእግዚአብሔር አገልገሎት በቂ ዝገጅትና ትጋት አናሳይ ማለት አይደለም። ግን ሁሉንም ካደረግን በኋላ መንፈስ ቅዱስ ካልተጠቀምበት የእኛ ጥረት ብቻውን ከንቱ መሆኑን መገንዘብ ማለት ነው። 

1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 2ን አንብብ። 

ጥያቄ 1. የሐዋርያው ስብከት «መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበር» ሲል ምን ማለቱ ነው? ይህ ሊሆን የቻለው ጳውሎስ ማንን ስለሰበከ ነው? 

ጥያቄ 2. በቁጥር 7 ላይ ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ «በምሥጢር እንናገራለን» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 3. አማኞች ስውር የሆነውን የእግዚአብሔርን ጥበብ እንዴት ሊያውቁት ቻሉ? 

ሐዋርያው ወንጌልን በቃልና በጥበብ ብልጫ አልሰበከም፤ ይህም ማለት ወንጌልን ለቆሮንቶስ ሰዎች በሰበከ ጊዜ የቆሮንቶስ ሰዎች በሚያደንቁት በግሪኮች ፍልስፍናና የንግግር ዘይቤ (ርሂቶሪክ) በመጠቀም አልነበረም። ነገር ግን አዋቂ ነን የሚሉ በሚንቁት በክርስቶስ ወንጌል ተመክቶ ነበር፡፡ በዚያም አላፈረም፤ የእግዚአብሔር የማዳን ኃይል በወንጌል በኩል ተገልጿልና፤ 

(ሮሜ 1:16ና 17)። 

ይህን ነጥብ በደንብ ልንገነዘበው ይገባናል። በማያምኑ ሰዎች ፊት የክርስትናን እምነት ተቀባይነት ለማስገኘት ብለን ወንጌልን በተለያየ የሳይንስና የፍልስፍና ቅመም ብናጅለው እናበላሸዋለን። ለዓለማውያን አንዲዋጥላቸው እናደርግ ይሆናል፤ ግን ወንጌልን ሳይሆን የሰውን ጥበብ የእምነታቸው መሠረት አደረግን ማለት ነው። ጳውሎስም የፈራው ይህንኑ በር፤ (ቁጥር 4 እና 5) 

ጥያቄ 4. አንዳንድ ሰዎች ወንጌልን ለውጠው በሰው ጥበብ ሲሰብኩ ያየህበት ጊዜ አለ? ካየህ ወንጌሉን የለወጡት እንዴት ነበር? 

«በበሰሉት መካከል ጥበብን እንናገራለን» (ቁጥር 6)። የበሰሉት ማለቱ በመንፈስ ቅዱስ አስተማሪነት የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር የተረዱትን ማለቱ ነው። የእግዚአብሔር ጥልቅ ነገር የመስቀሉ ቃል ነው። ያልበሰሉት ሥጋውያን ወይም ዓለማውያን ይህንን ነገር ሊገነዘቡት አይችሉም። «ያልበሰሉት» የተባሉት በመንፈስ ያላደጉት ክርስቲያኖች ሳይሆኑ ፍጹም ወንጌልን ያልተቀበሉትን ዓለማውያን ናቸው፡፡ ይህ ለመሆኑ ማስረጃው ቁጥር 14-16 ነው። 

ወንጌል «እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር» ይገልጣል፤ (ቁጥር 7)። በምስጢር መገለጥ ማለትም ሰው በሚሰጠው መመራመር የተገኘ ሳይሆን እግዚአብሔር የገልጠው ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ እውቀት የሳይንስ እውቀት አይደለም፤ ምክንያቱም ለተመራመረና ላጠና ሁሉ የሳይንስ ጥበብ ክፍት ነው፤ ይህ ግን ክፍትነቱ እግዚአብሔር ለገለጠላቸው ብቻ ነው፡፡ 

ይህ የወንጌል ምስጢር ከጊዜ በኋላ የታሰበ ትኩስ ነገር አይደለም፤ አስቀድዋ ከዘመናት በፊት በእግዚአብሔር ታስቦ ነበር። ደግሞም ይህ በእግዚአብሔር ብቻ እንጂ ከሰዎች በማንም አእምሮ ውስጥ ያደረ አልነበረም! (ቁጥር 9)። 

እኛ ማለት አማኞች ይህን ምስጢር አንዲት ልናውቀው ቻልን? “ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው” (ቁጥር 10)። ይህም ለእኛ የተሰጠበት ምክንያት በእኛ ውስጥ ሊያሰጠን የሚችል ነገር ተገኝቶብን ሳይሆን “እንዲያው” ነው የተሰጠን፤ (ቁጥር 12)። ስለዚህ ወንጌልን የምናምነውም የምናስተምረውም በመንፈስ ቅዱስ ረዳትነት ብቻ መሆኑን መገንዘብ አለብን። በወንጌል ላይ የሰውን ጥበብ በማንኛውም ደረጃ ላይ ከጨመርንበት እንበርዘዋለን። 

ነገር ግን ለእኛ የእግዚአብሔር ጥበብ የተገለጸልን እንዴት ነው? የተገለጸው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው። በቃሉ ውስጥ የተገለጸውን የእግዚአብሔርን ጥበብ መንፈስ ቅዱስ ይወስድና ለእኛ እንደሚገባን አድርጎ በምንገኝበት ሁኔታ ውስጥ ተግባራዊነቱን ይገልጽልናል። ትምህርታችንና አመለካከታችን በይበልጥ በእግዚአብሔር ቃል ላይ በተደገፈ ቁጥር መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ቃሉን እንደ ጥበብ በእኛና በሌሎች ሕይወት ውስጥ እንድንጠቀምበት ያደርገናል። 

ጥያቄ 5. ላልዳኑት ግልፅ ያልሆነውን ነገር መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል በመጠቀም እንዴት አድርጎ ነው ግልፅ ያደረገልህ? 

እኛ እንዲህ የምናደንቀው ወንጌል ለማያምኑት ምኝነት የሆነበት ምክንያት ምስጢሩ ሳይገባቸው ስለቀረ ነው፤ (ቁጥር 14-15)። ወንጌል ቀርቶ በወንጌል የሚያምኑት ራሳቸው ለማያምን ሰው አስተሳሰባቸው አይገባቸውም፤ ስለዚህ የማያምኑት አማኞችን በከንቱ ሲቃወሟቸውና በድንቁርና ተመርኩዘው እምነታቸውንና ለሕይወታቸው ከንቱ ስያሜና ስድብ ሲሰጡ ይታያሉ። ክርስቶስን የማያውቅ የአማኝንም አስተሳሰብ ሊያውቀው አይችልም (ቁጥር 16)።

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d bloggers like this: