ክርስቲያን በዓለም ውስጥ እንጂ ከዓለም አይደለም (1ኛ ቆሮ. 5:1-13)። 

ምንም እንኳ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ጸጋ ከዓለም ርኩሰት የዳነ ቢሆንም በዓለም እስካለ ድረስ አልፎ አልፎ ዓለማዊ ጸባይ ማሳየቱ አይቀርም። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የዓለማዊ ፀባይ የሆነ የዝሙት ሥራ በመካከላቸው ተነሥቶ ነበር። ነገር ግን ክርስቲያን በኃጢአት ሥር ስለማይኖር በንስሐ ከውድቀቱ ተመልሶ ይነሣል። ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል ግን ደግሞ ሰባት ጊዜ ይነሣል! በዚህ ተስፋ እንጽናና። 

1ኛ ቆሮንቶስ 5ን አንብብ። 

ጥያቄ 15. ከቁጥር 1 እስከ 2 ባለው ክፍል ውስጥ «ታብያችኋል ይልቅስ እንድታዝኑ አይገባችሁምን?» ሲል ከጠቀሰው የዝሙት ሥራ ጋር ትዕቢታቸው ምን ግንኙነት አለው? 

ጥያቄ 16. ከቁጥር 3 እስከ 5 ያለውን ክፍል ከማቴ.18፡15-20 ጋበማወዳደር መግለጫ ጻፍ። 

ጥያቄ 17. ከቁጥር 6-8 ላይ ስለ እርሾ የተናገረውን አብራራ። 

ጥያቁ 18. ከቁጥር 9-13ን በጥንቃቄ በማጥናት የሚከተለውን ጥያቄ መልስ። ክርስቲያን ከዓለማውያን ራሱን መለየት የለበትም፤ ግን ክርስቲያን ነኝ እያለ በኃጢአት ውስጥ ከሚኖር ሰው መለየት አለበት። ለምን? መልስህ ያለው ይሁን። 

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመካከላቸው ታላቅ ኃጢአት ሲካሄድ እንደማዘንና እርምጃ እንደመውሰድ በዓለማዊ ጥበብ እየተመኩ ተቀምጠዋል። በመካከላቸው የነበረውም በደል እንኳን በምእመናን መካከል ቀርቶ በማያምኑት መካከል እንኳ ተቀባይነት የለውም። ከአባሎቹ አንዱ ከእንጀራ እናቱ ጋር በሥጋ ፍትወት ይኖር ነበር። ስለዚህ በደል ብዙም ዝርዝር አይሰጥም። ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ ዝም ማለቷ በጣም ደካማ መሆኗን ያስረዳል። 

«ይህን የሠራ ከመካከላችሁ ይወገድ»። ሐዋርያው ቤተ ክርስቲያኒቱ ማድረግ የሚገባትን በገልጽና በአጭሩ ይናገራል። እንዴት ከመካከላቸው እንደሚያስወግዱት መመሪያ ይሰጣል፡፡

ምእመናን በአንድነት በክርስቶስ ስምና ሥልጣን ተሰብስበው ይህን በደለኛ ከመካከላቸው ማስወገድ አለባቸው። በዚህ ስብሰባቸው ላይ ጌታ ኢየሱስ በሥልጣኑና በኃይሉ ከመካከላቸው ይገኛል። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያኑ ውሣኔ የሰዎች ውሣኔ ሳይሆን የክርስቶስ ውሣኔ ነው! (ማቴ.18፡15-20)፡፡ 

በማቴ.18፡15-20 ላይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ አንድ ሰው ያልተናዘዘው ኃጢአት ካለው ምን ዓይነት እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባን ያሳየናል። በመጀመሪያ፡- ክርስቲያን የሆነ አንድ ሰው ኃጢአተኛውን ሰውዬ መውቀስ ይገባዋል። ሁለተኛ፡- ሰውዬው መናዘዝ ካልፈለገ ግን በሁለት ወይም በሦስት የክርስቲያን ምስክሮች ፊት ይወስደዋል። ሦስተኛ:- አሁንም ሰውዬው አልናዘዝም ብሎ ከወሰነ፥ ለቤተ ክርስቲያን ይነገራትና ኃጢአተኛው ሰውዬ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለው ሕብረት እንዲቋረጥ ይደረጋል። ጳውሎስ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የሚያሳስበው ይህንን የመጨረሻ እርምጃ እንዲወስዱ ነበር። 

ጥያቄ 19. አንደዚህ ዓይነት እርምጃ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ተወስዶ ያውቃል? እንዴት ተፈጸመ? በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ሦስቱም ደረጃዎች ተፈጸሙ? 

በቁጥር 5 ላይ ሐዋርያው ትርጉሙን ለመረዳት የሚያስቸግር ቃል ይናገራል፤ «ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው»። ምን ማለቱ ነው? ከቤተ ክርስቲያን ጉያ መውጣት ከክርስቶስ ቤት ተባሮ ሰይጣን በነገሠበት በዚህ ዓለም ውስጥ መጣል ነው፤ ቆላስያስ 1:13፤ 1ኛ ዮሐ.5፡19 ተመልከት። «ለሥጋው ጥፋት» የሚለውም በቤተ ክርስቲያን መወገዝና ክርስቶስን ማስቀየም የሥጋ መቅሰፍት ሊያስከትል መቻሉን ማስታወሱ ነው፤ ( 1ኛ ቆር.11:30፤ የሐዋ.13:8-11)። እንግዲህ የጳውሎስ ዓላማ አጥፊው በጌታ እጅ ከተገሠጸ አዝኖ ንስሐ ይገባና ነፍሱ ትድናለች ማለቱ ነው እንጂ ያለንስሐ ወደ ዓለም በመጣሉና በዓለም መከራ በመቀበሉ ብቻ ነፍሱ ትድናለች ማለቱ አይደለም፡፡ 

ቁጥር 6 ላይ እንደገና ስለ ትዕቢታቸው ይናገራል። በውጭ በትዕቢት ሲራመዱ በውስጣቸው ግን ኃጢአት እንደ እርሾ እየበላቸው ነው። እርሾ በመጽሐፍ ቅዱስ የኃጢአት ምሳሌ ነው፤ (ማቴ. 13:33፤ ገላ.5፡9)። 

ከቁጥር 7-8 ከብሉይ ኪዳን የእርሾን ምሳሌ ያቀርባል። በአይሁዶች የፋሲካ በዓል ቂጣ እንጂ እርሾ ያለበት ነገር አይበላም። ይህም የግብፅን ባርነት ትተው በነፃነት እንዳሉ አዲስ ሕይወታቸውን የሚያስረዳ ነው። 

አሁንም ክርስቲያኖች የዓለምን መጥፎ ሥራዎች ማስወገድ አለባቸው። «ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷልና ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም»። ክርስቲያን በክርስቶስ ሞት ከኃጢአት ባርነት ነፃ የወጣ ስለሆነ እንደገና ወደ ባርነት ለኃጢአት ሥራ ራሱን መሸጥ የለበትም፤ (ሮሜ 6፡12-14)። 

ከቁጥር 9-13 ባለው ክፍል ውስጥ ከዚህ በፊት የጻፈላቸውን መልእክት በደንብ እንዳልተረዱና አሁን እንደገና ሊያስረዳቸው እንደሚሞክር እንገነዘባለን። የትምህርቱ ዋና ፍሬ ነገር በቁጥር 12ና 13 ላይ ይገኛል። “በውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ አትፈርዱምን? በውጭ ባሉቱ ግን አግዚአብሔር ይፈርዳል። ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት”። ክርስቲያን በዓለም እንጂ ከዓለም አይደል፤ (ዮሐ.17:15 እና 16)። ስለዚህ በጣዖት አምልኮአቸው እስካልተጠላለፈ ድረስ ክርስቲያን ከዓለም ሰዎች ጋር አብሮ መኖር አለበት። ነገር ግን ክርስቲያን ነኝ እያለ በእግዚአብሔር መንገድ የማይመላለስ ከሆነ እንደዚህ ካለው ጋር እንኳን ለአባልነት በቤተ ክርስቲያን መቀበል ቀርቶ በጉርብትና እንኳ መወዳጃት ክልክል ነው። አንድ አማኝ ከቤተ ክርስቲያን በቅጣት ከአባልነት ከተወገዘ በኋላ ከእርሱ ጋር አባሎች በውጭ መወዳጀት የላባቸውም። እንዲህ ካደረጉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተግሣጽ በማክሸፍ ይበርዙታል። በቤተ ክርስቲያን የእርሱን መመገድ ደግፈው ዞር ብለው ግን በውጭ ጓደኝነታቸውን ቢቀጥሉ ወላዋይና መንታ ምላስ ያላቸው ቀላማጆች መሆናቸው ነው። የተገሰጸውም ሰው የተገሣጹን ትልቅነት ባለመረዳት ንስሐ እንዳይገባ እንቅፋት ይሆኑበታል። ስለዚህ ይህን የሐዋርያውን ቃል በጥንቃቄ እንገንዘብ፡

ጥያቄ 20. ክርስቲያን ነኝ እያለ ግን በኃጢአት ውስጥ ለሚኖረው ሰው ሕብረታችንን ማቋረጣችንን የምንገልጸው እንዴት ነው? በምሳሌ ግለጽ።

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d