የሐዋርያ መብት ( 1ኛ ቆሮ.9:1-14) 

ጥያቄ 15. በቁጥር 1 ላይ «እኔ ነፃ አይደለሁምን?» ሲል ስለምን ዓይነት ነፃነት ነው የሚያወራው? 

ጥያቄ 16. በቁጥር 1 እና 2 በጥያቄ መልክ የሚያቀርባቸው የሐዋርያነቱ ማረጋገጫዎች ምን ምን ናቸው? 

ጥያቄ 17. በቁጥር 5 የጌታ ወንድሞች የሚላቸው እነማን ናቸው? (ማር.6፡3) 

ጥያቂቄ 18. በቁጥር 9 ላይ «እግዚአብሔር ስለ በሬዎች ይገደዋልን?» የሚለውን ከማቴ.6፡26 ጋር በማስተያየት አስታራቂ ሃሳብ ጻፍ። 

ጥያቄ 19. ሐዋርያው በመብቱ ቢጠቀም ኖሮ የክርስቶስን ወንጌል ሊከለክል እንደሚችል በቁጥር 12 ላይ ይናገራል፤ ይህ መብት ምን ነበር? አንዴትስ ወንጌልን ይከለክል ነበር? 

ስለ ክርስቲያን ነጻነት በምዕራፍ 8 ይናገር ነበር፡፡ ያንኑ ነጥብ ቀጥሎ በምዕራፍ 9 ያብራራዋል። ሌሎች ነፃነታቸውን በፍቅር ለወንድሞች ጥቅም መሰዋት አለባቸው ብሎ ካስተማረ በኋላ የሚያስተምረውን በሥራ ላይ የሚያውል አስተማሪ መሆኑን ያረጋግጥላቸዋል። 

ቁጥር 1-3፡- በምዕራፍ 8 ላይ ጳውሎስ ምንም እንኳን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ቢሆንም በእውቀቱ ላይ ሳይሆን በፍቅር ላይ ተመሥርቶ እንደሚኖር ያሳየናል። በመጀመሪያ እርሱ ራሱ ነፃ የሆነ ሰው እንደሆነ ለቆሮንቶስ ሰዎች ያሳያቸዋል፡፡ ከፈለገ ሚስት የማግባትም ሆነ ለሐዋርያዊነት ሥራው ደመወዝ የመቀበል ነፃነት ነበረው። ነገር ግን ለወንጌል እንቅፋት ሳይፈጥር የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ሲል ነው ይህን ነፃነቱን ወደ ኋላ የተወው። በመጀመሪያ ግን ጳውሎስ አንዳንድ ጥያቀቄዎችን በመጠየቅ ሐዋርያነቱን አሳውቆ ነበር። 1ኛ/ «ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አላየሁትምን?» ጌታን ያላየ ሐዋርያ መሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ሐዋርያነት በቤተ ክርስቲያን ሳይሆን በቀጥታ በክርስቶስ የሚሰጥ ሥልጣን ስለሆነ ነው፤ (ገላ.1፡1 እና የሐዋ.9፡10-18)። 2ኛ/ ይህ ሐዋርያነቱን እንዲሁ በአፍ ወሪ ሳይሆን በሥራ የተመሰከረለት ነበር። ይህም ራሳቸው የቆሮንቶስ ሰዎች በጳውሎስ አገልግሎት ወደ እምነት መምጣታቸው የጳውሎስን ሐዋርያነት ያረጋግጣሉ። 

ቁጥር 4-7:- በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ሐዋርያ ስለሆነ የሐዋርያነት መብት እንዳለው ይናገራል። «ልንበላና ልንጠጣ መብት የለንምን?» ይህ መብላትና መጠጣት በምዕራፍ 8 ላይ ያለው ዓይነት መብላትና መጠጣት ሳይሆን፥ ከታች ዝቅ ብሎ እንደዘረዘረው ደመወዝ ወይም አበል ማለቱ ነው። 

አንደነጴጥሮስ ያሉት ሐዋርያትና የጌታ ወንድሞች ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ሚስቶቻቸውን ይዘው ለወንጌል ሥራ የመዞር መብታቸውን ተጠቅመውበት ነበር። ባርናባስና ጳውሎስ ግን ምንም እንኳ ይህ መብት እንዳላቸው ቢገነዘቡም በመብታቸው አልተጠቀሙም። ራሳቸው በትርፍ ጊዜያቸው በሚሠሩት ነበር ይተዳደሩ የነበረው። ሥራን ትቶ ወንጌልን ብቻ መስበክ ለእነርሱም የተሰጠ መብት ነበር፤ ግን አልተጠቀሙበትም። 

ከሕብረተሰቡ ልማድ ምሳሌዎችን በማቅረብ ነገሩን ያረጋገጥላቸዋል። እነዚህም የገበሬና የወታደር ምሳሌዎች ናቸው። ስለዚህ በወንጌል ሥራም የተሰማሩ ከወንጌል መተዳደሪያ መቀበል መብታቸው ነው። በወንጌል የሚገለገሉ ለአገልጋዮቻቸው ደምወዝ ሊከፍሏቸው የተገባ ነው። 

«የጌታ ወንድሞች» የሚለው ማሪያም ከዮሴፍ የወለደቻቸው የጌታችን የሥጋ ወንድሞች ናቸው። ማርያም ከጌታችን በኋላ አልወለደችም የሚሉ ማስረጃ ይዘው ሳይሆን የሥጋ ግብር ርኩስ ነው ብለው ስለሚገምቱ ማርያምን ለማክበር አስበው ነው። ግን ይህ አስተሳሰብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጋጫል። በምዕራፍ 7 ላይ ስንመለከት ሐዋርያው በአንድም ቦታ ከሚስት ጋር መተኛት ርኩስ ነው አላለም። አለማግባት ከማግባት ይሻላል ያለውም ለአገልግሎት አመቺ ከመሆኑ አንጻር ነው እንጂ ከሚስት ጋር መተኛት ርኩስ ስለሆነ አልነበረም። እንዲያውም በዕብራውያን 13፡4 ላይ ጋብቻ ክቡርና ንጹሕ እንደሆነ ይናገራል። እንዲሁም እግዚአብሔር የፈጠረው ስለሆነ በምስጋና መቀበል አለብን እንጂ ርኩስ ነው ማለት እግዚአብሔርን መሳደብ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ጋብቻን ማርከስ የአጋንንት ትምህርት መሆኑንም ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ኛ ጢሞ.4:1-3 ላይ አስተምሮአል። 

ከቁጥር 8-12:- የወንጌል አገልጋዮች በሚገለገሉት ምእመናን ሊረዱ ይገባቸዋል የሚለውን ሃሳብ በሰው ባህል ላይ ያም በገበሬና በወታደር ወግ ላይ ብቻ አልመሠረተም። ከመጽሐፍ ቅዱስም ማስረጃ ያቀርባል። “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” ብሎ ሙሴ እንዳዘዘና ይህ ስለሰዎች እንደሚናገር ያስረዳል፤ (ዘዳ.25፡4)። 

“እግዚአብሔር ስለ በሬዎች ይገደዋልን? ይህን የሚለው ፈጽሞ ስለእኛ አይደለምን?” ይህ አነጋገር እግዚአብሔር ለበሬዎች አያስብም ማለት ሳይሆን አነጋገሩ እንዲህ ነው፡፡ “እግዚአብሔር ለበሪዎች አስቦ ይህን ዓይነት ሕግ ካወጣ እኛም ሰዎች ከእንስሳት ስለምንበልጥ እንገዲያስ ሕጉ ከበሬዎች ይልቅ እኛን በበለጠ ይመለከተናል።» ይህን ከማቴዎስ 6፡25-30 ጋር አስተያይ። 

ገበሬ የዘራውን ዓይነት ዋጋ መቀበል ከቻለ የወንጌል አገልጋዮች መንፈሳዊ ነገር ዘርተው ሥጋዊ ደመወዝ መቀበላቸው እንደትልቅ ነገር ሊገመት አይገባውም። ይኸውም ሲያንሳቸው ነውና እግዚአብሔር በመንፈሳዊ ክብር በሚመጣውም ዓለም ያከብራቸዋል። 

ቁጥር 13 እና 14:- ይህን መብቱን ሐዋርያው አልተጠቀመበትም። ስለዚህ የቆሮንቶስም ክርስቲያኖች ለወንድማቸው ሲሉ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ የመብላት መብታቸውን መልቀቅ አለባቸው። ሐዋርያው የእርሱን መብት የለቀቀው «የክርስቶስ ወንጌል እንዳይከለከል» ስለሆነ እነርሱም ክርስቶስ ለሞተለት ወንድም ሲሉ መብታቸውን መልቀቅ መማር አለባቸው። ይህ የሚያስታብየው የእውቀትና የመብት እርምጃ ሳይሆን የፍቅር እርምጃ ነው። 

በአምልኮት አገልግሎት የተሰማሩ ከቤተ መቅደስና ከመሠዊያው ለመካፈል መብት ያላቸው መሆኑን እንኳን ብሉይ ኪዳንን የሚያውቁ ቀርቶ በአህዛብ ወግ እንኳ የተጠበቀ ነበር። ይህንንም የቆሮንቶስ ሰዎች ጣዖት አምላኪዎች ስለነበሩ ያውቁታል። በአረመኔነታቸው ያከብሩት የነበረው አሁን ለክርስቶስ አገልጋዮች ሊነፈጋቸው አይገባም። 

«የክርስቶስን ወንጌል እንዳንከለክል በሁሉ እንታገሣለን እንጂ በዚህ መብት አልተጠቀምንም።» ይህን ሲል ከቤተ ክርስቲያን ደመወዝ ቢቀበል ኖሮ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በእምነታቸው ደካሞች ከመሆናቸው የተነሣ «ጳውሎስ ወንጌልን የሚሰብከው ለደመወዙ ሲል ነው» በሚለው በተቃዋሚዎች ነቀፋ ይሰናከሉ ነበር። ስለዚህ የተቃዋሚዎችን አፍ ለማዘጋትና በዚህም የወንጌልን እንቅፋት ለማስወገድ ሐዋርያው በመብቱ አልተጠቀመም ነበር። ይህን በሁሉም ቦታ አላደረገም፤ ለምሳሌ ከፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች እርዳታ ይቀበል ነበር። ስለዚህ ጉዳይ የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ፤ 2ኛ ቆሮ.11:7-12። 

ጥያቄ 20. ይህንን መብት በቤተ ክርስቲያንህ የሚጠቀሙበት እነማን ናቸው? የማይጠቀሙበትስ እነማን ናቸው? ለወንጌል ብለን መብታችንን ሳንጠቀምበት የምንሠራው ነገር ምንድነው?

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d bloggers like this: