የምእመናን የእርስ በርስ መካሰስ (1ኛ ቆሮ 6፡1-11) 

ጥያቄ 21. በቁጥር 1 ላይ “በቅዱሳን ፊት መፋረድ” ሲል ቅዱሳን የሚላቸው እነማንን ነው? አመፀኛችስ ያላቸው እነማን ናቸው? 

ጥያቄ 22. ከቁጥር 1-8 ውስጥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የፈጸሟቸው ስንት ስሕተቶች ተዘርዝረዋል? ምን ምን ናቸው? 

ጥያቄ 23. ከቁጥር 9-11 ያለው ከቁጥር 1-8 ካለው ጋር የሃሳብ ዝምድናውን አስረዳ። 

ቁጥር 1:- በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አማኝ ከአማኝ ጋር ይካሰስ ነበር። በተካሰሱ ጊዜ ለዳኝነት አማኞች ዘንድ ሳይሆን እማያምኑት ዘንጽ ይሄዱ ነበር። ይህ እንኳን በክርስቲያን መካከል ቀርቶ በአይሁድ ባሕል እንኳ ተቀባይነት አልነበረውም። ጳውሎስ ይህ በክርስቲያኖች መካከል መደረገ እንደሌለበት ያስተምራል። በዚህ ክፍል ውስጥ አማኞችን ቅዱሳን ሲላቸው የማያምኑትን ደግሞ አመጸኞች ይላቸዋል። አምጸኝነታቸው ለእግዚአብሔር ሕግና በወንጌል በኩል ለቀረበው ለአግዚአብሔር ምሕረት ባለመታዘዛቸው ነው። 

ከቁጥር 2–3:- አማኞች በፍርድ ቀን ከክርስቶስ ጋር በመተባበር በዓለም ላይ ይፈርዳሉ፤ (ዳንኤል 7:22፤ ማቴ.19፡28)። እንግዲያስ በአሁኑ ጊዜ በሚነሡ ክሶች ላይ መፍረድ ይችላሉ። ስለ ትዳር ጉዳይ ቀርቶ “በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ” እግዚአብሔር ወስኗል። በመላእክት ላይ መፍረድ ማለትም በመላእክት ላይ መሠልጠን ማለት ነው፡፡ ወይም በመላእክት ላይ ሥልጣን መያዝ ማለት ነው። ይህም ሊሆን የሚችለው አማኝ ከክርስቶስ ጋር ስለሚነግሥ ክርስቶስም በመላእክት ላይ ስለነገሠ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ሙሽራ እንደመሆኗ መጠን ይህን ሥልጣን ከክርስቶስ ጋር ትካፈላለች፤ (ሮሜ 8፡17፤ አፌ.1:22)። 

ከቁጥር 4-5፡- ቁጥር 4ን አንዳንድ የግሪክ ቋንቋ ሊቃውንት እንዲህ ብለው ይተረጉማሉ፤ «እንግዲህ ስለትዳር ጉዳይ የፍርድ ቤት ቢያስፈልጋችሁ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ አስቀምጡ።» እንዲህ ከተወሰደ ትርጉሙ ምንም እንኳ ላዳኝነት የሚበቁ አማኞች በመካከላችሁ ባይገኙም ዓለማውያን ፊት ሄዶ ከመፋረድ በቤተ ክርስቲያን ዝቅተኛው አማኝ የተሻለ ፍርድ ይሰጣልና እርሱን ሹሙት” ማለት ይሆናል። ነገር ግን ይህ አተረጓጎም ትክክለኛ አይደለም። ትክክለኛው ትርጉም የአማርኛው ትርጉም ስለሆነ በዚያው እንረጋለን። ጳውሎስ ጥያቄ ነው ያቀረበው፤ «በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁን?»፡፡ ማለት ዓለማውያን በቤተ ክርስቲያን የተናቁና የአማኝን ሕይወት በደንብ የማያውቁ ሰዎች ስለሆኑ በአማኝ ላይ በፍርድ እንዲቀመጡ አማኝ እነርሱ ዘንድ መሄድ የለበትም። በቁጥር 5 ላይ በትዳር ጉዳይ የሚፈርዱ አማኞች የማይጠፋ መሆኑን አጠራጣሪ እንዳልሆነ ያረጋገጣል። 

ጥያቄ 24. በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ በሁለት ክርስቲያኖች መካከል ክርክር ቢነሣ የሚታረቁት በምን መንገድ ነው? 

ከቁጥር 6-8፡- በዚህ ክፍል ሐዋርያው በመሠረቱ የመካሰስ ነገር በመካከላቸው መነሣት እንደሌለበት ይናገራል። ይህ በመሆኑ በክስ እንኳ ቢረቱ እንደተሸነፉ ያስረዳቸዋል። አማኝ ከክርስቲያን ወንድሙ ጋር በሰላም መኖር አለበት። ቢካሰስ ድካም መሆኑን መገንዘብ አለበት። ግን በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክስ የተነሣው ወንድም ወንድሙን ስለሚያታልል በር። ይህ መሆን አልነበረበትም፡፡ ስለዚህ በዚህ በመካሰስ ጉዳይ የፈጸሟቸው ስሕተቶች እነዚህ ናቸው፡-

1ኛ/ አማኞች እርስ በርስ መፋቀርና መደጋገፍ ሲገባቸው በውስጣቸው ክስ መኖሩ። 

2ኛ/ ክሱም ስለተበደሉ ሳይሆን ወንድሞችን በማታለል ነበር። 

3ኛ/ ይህንም ክስ በአማኞች ፊት ሳይሆን በማያምኑ ፊት ያቀርቡ ነበር። 

ከቁጥር 9-11:- አማኞች ክሳቸውን በማያምኑ ፊት ያቀረቡት በአማኝና በማያምን መካከል ምን ያህል ትልቅ ልዩነት እንዳለ ባለመረዳት ሊሆን ስለሚችል፥ ያለውን ልዩነት በዝርዝር ያስረዳቸዋል። «አመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። አመፀኝነታቸው በሁለት መንገድ ነው። 1ኛ/ የእግዚአብሔርን ሕግ በሕይወታቸው አይጠብቁም። 2ኛ/ እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል የቀረበላቸውን ደኅንነት አይቀበሉም። ስለዚህ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ሕጉንም እንዴት እንዳፈረሱ በዝርዝር ጽፎአል፤ (ቁጥር 9 እና 10)። በቁጥር 11 ላይ የክርስቲያንን መለወጥ ያስተምራል። «ከእናንተም አንዳንዶች እንደዚህ ነበራችሁ»። አሁን ግን፡-

1ኛ. ታጥባችኋል፤ ክርስቲያን ከኃጢአቱ እድፍ በክርስቶስ ደምና በመንፈስ ቅዱስ ታጥቧል። ጥምቀት የዚህ የመታጠብ የውጭ ምሳሌ ሆኖ ቀርቧል። ኃጢአት እድፍ ወይም እርኩስ ነው፤ ስለዚህ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የሚኖረው ከእድፋ ሲታጠብ ብቻ ነው። ይህም በሥራ ሳይሆን እንዲያው በነፃ በክርስቶስ በማመናችን ብቻ ይሰጠናል። 

2ኛ. ተቀድሳችኋል መቀደስ ሁለት ደረጃ አለው። የመጀመሪያው ደረጃ አማኝ ክርስቶስን የተቀበለ ዕለት በእግዚአብሔር መንፈስ ታጥቦ የእግዚአብሔር ዕቃ ይሆናል። ቅዱስ ዕቃ ነው፤ (3፡16 እና 17)። ይህ የሚደጋገም ሳይሆን በአማኝ ሕይወት አንድ ጊዜ ስለተፈጸመ አማኝ ቅዱስ ይባላል፤ (1:2፤ 6፡1)። ሌላው የቅድስና ደረጃ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጊዜ አማኝ ከኃጢአት ነፃ ይሆናል። አሁን አማኝ ከኃጢአቱ ንጹሕ ላለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስም ሕይወቱም ይመሰክራሉ፤ (1ኛ ዮሐ.1:8-10)። ነገር ግን ተቀድሳችኋል ማለቱ የሁለተኛውን ዓይነት ቅድስና ሳይሆን የአንደኛውን ዓይነት ቅድስና ማለቱ ነው። 

3ኛ. ጸድቃችኋል፤ ይህ የፍርድ ቤት ቋንቋ ነው። አማኝ በእግዚአብሔር ፍርጽ ዙፋን ፊት ቀርቦ ክሱ ተሰርዞለት የክርስቶስን ጽድቅ በመጎናጸፍ «ጻድቅ» ተብሎ ተፈርዶለታል። ስለዚህ ስለ ኃጢአቱ ወደፊት በፍጹም አይጠየቅም። ይህ ወንጌል የሚሰጠን የምሥራች ነው። ይህን የምሥራች በእምነት የተቀበለ ሁሉ የዚህ ጽድቅ ወራሽ ሆኖአል፡፡ እንግዲህ አማኝ ይህን መሰል ሲሆን የማያምን ደግም የረከሰና በእግዚአብሔር ፍርድ ሥር ያለ ስለሆነ እንዴት አማኝ ለዳኝነት ጉዳይ ወደማያምን ዘንድ ይሂድ?

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d bloggers like this: