የአማኘ አካልና ዝሙት (1ኛ ቆሮ. 6፡12-20) 

ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ሙሴ «አትስረቅ» ፥ «አትገደል» ፥ «አትመኘ» ፥ «አታመንዝር» በማለት ሕግን ብቻ አይደረድርም። ነገር ግን ክርስቲያን ከኃጢአት ለምን መራቅ እንዳለበት በማስረዳት ኃጢአትን ይከለክላል። ስለ ዝሙት ሰፊ ትምህርት በመስጠት ክርስቲያን ከዝሙት መሪቅ ብቻ ሳይሆን ክርስቲያን ለምን ከዝሙት መራቅ እንዳለበት ያስረዳል። 

1ኛ ቆሮንቶስ 6፡12-20ን በጥንቃቄ በመመልከት የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ። 

ጥያቄ 1. በቁጥር 12 ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን አይጠቅምም» የሚለውን ሃሳብ አብራራ። 

ጥያቄ 2. በቁጥር 12 «ሁሉ ተፈቅዶልኛል በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም» የሚለውን አብራራ። 

ጥያቄ 3. በቁጥር 13 እና 14 ላይ መብል ለሆድ ከሆነ ሥጋ ለዝሙት አለምሆኑን ጳውሎስ እንዴት ያረጋግጣል? 

ጥያቄ 4. ከቁጥር 15 እስከ ቁጥር 17 ሁለት ዓይነት “አንድነቶች” ተጠቅሰዋል፤ ምን ምን ናቸው? 

ጥያቄ 5. በዚህ ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ዝሙትን በተለያዩ ምክንያቶች ይከለክላል፤ እነዚህን ምክንያቶች ዘርዘር፤ (ቁጥር 15-20) 

ከቁጥር 12-14:- የቆሮንቶስን ምእመናን ጳውሎስ ስለክርስቲያን ነፃነት «ሁሉ ተፈቅዶልኛል» በማለት ሳያስተምራቸው አይቀርም። እነርሱ ግን ይህን ትምህርት አጣመሙ። ሁሉ ከተፈቀደ እንገዲያስ ዝሙትም መከልከል የለበትም ማለት ሳይጀምሩ አይቀሩም። ስለዚህ ጳውሎስ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን አይጠቅምም” የሚለውን ሃሳብ መጨመር ነበረበት። በተጨማሪም ሰው በክርስቶስ ያለው ነፃነቱ የጽድቅና የቅድስና አገልጋይ እንዲያደርገው ነው እንጂ የኃጢአት ባሪያ በመሆን ራሱን ለዝሙትና ለመሳሰሉት ኃጢአቶች እንዲሸጥ አይደለም፤ (ሮሜ 6፡13-14)፡፡ 

ምንም እንኳን በአንዳንድ ነገሮች ላይ ነፃነት እንዳለን ብናውቅም እነዚህን ሁለት ጥያቄዎች መጠየቅ ይገባናል። አንደኛ፡- ይህ የማደርገው ነገር ለሥጋዬ፥ ለመንፈሳዊ ሕይወቴ፥ ለምስክርነቴ፥ ወዘተ የሚጠቅም ነው ወይ? መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃወም ማንኛውንም ነገር መተው ይገባናል። ሁለተኛ፡- ይህ ነገር እኔን እየገዛኝ ወይም እየሠለጠነብኝ ነው? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። እኛ የክርስቶስ አገልጋዮች እንጂ የሌላ ነገር ተገዢ መሆን አይገባንም። ኃጢአት ሊቆጣጠረን አይገባም። ጥሩ ነው ብለን የምንለው እንደ ምግብ ያለ ነገር እንኳን ሃሳባችንንና ፍላጎታችንን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የለበትም። 

ጥያቄ 6. የትኞቹ መጥፎ ወይም መልካም ነገሮች ናቸው፥ ሰውን በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው ለራሱና ለወንጌል እንቅፋት የሚሆኑት? 

በቆሮንቶስ ሕዝብ መካከል መብል ለሆድ ነው ሆድም ለመብል ነው» የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ሳይኖር አይቀርም። የቆሮንቶስ አማኞች ይህን ምሳሌ በመመርኮዝ ሥጋ ለዝሙት ነው ዝሙትም ለሥጋ ነው» ሳይሉ አይቀሩም። ይህንን አስተሳሰባቸውን ሐዋርያው ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደላም» ብሉ ይቃወማል፡፡ አሁን ክርስቲያን ስለሆኑ ሥጋ ለዝሙት መሆኑ ቀርቶ ለጌታ ሆኖአል። ስለዚህ አሁን ክርስቲያን በሥጋው እግዚአብሔርን ማክበር አለበት፡፡ የክርስቲያን ሥጋ ለትንሣኤ ክብር ስለታጨ ሥጋችን በክብር ላይ መዋል አለበት። አግዚአብሔር ጌታን ከሞት አንዳሥነሣው ሁሉ የእኛንም ሥጋ ከመቃብር ያነሳል። 

ከቁጥር 15-17:- ዝሙት እግዚአብሔር ለጋብቻ የመሠረውን ባልተፈቀጸ መንገድ በሥራ ላይ ያውላል፡፡ አንድ ወንድ ከሴት ጋር በሥጋ ፍትወት ሲገናኝ ከእርሷ ጋር አንድ አካል ይሆናል። ይህ ዓይነት ኅብረት የተፈቀደው ለጋብቻ ብቻ ነው። እግዚአብሔር የመጀምሪያውን ጋብቻ ሲመሠርት «ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ» ብሏልና ሚስት ካልሆነች ሴት ጋር በሥጋ መገናኘት ይህን አንድነት በተከለከለ ሁኔታ መመሥረት ነው። ስለዚህ ሐዋርያው «ከዝሙት ሽሹ» ይላል። ክርስቲያን ከክርስቶስ ጋር መንፈሳዊ ኅብረት መሥርቷል። ከጌታ ጋር አንድ መንፈስ ሆኖአል። እንዲህ ከሆነ በዝሙት መሠማራት በእግዚአብሔር የተከለከለ ነው፡፡

ቁጥር 18፡- የዝሙት ኃጢአት ከሌሎቹ ኃጢአቶቹ ሁሉ ኃጢአተኛውን በቀጥታ ይጎዳዋል። ምክንያቱም አካሉን ከጌታ ወስዶ «ከጋለሞታ ጋር› ስለሚያስተባብር ነው። ስለዚህ ሰው የዝሙትን ኃጢአት በጥብቅ ማስወገድ አለበት። ከጋብቻ ውጭ የሚፈጸም የሥጋ ግንኙነት ሁልጊዜ ዝሙት ነውና ዝሙትን በሁሉም መንገድ ክርስቲያን ማስወገድ አለበት። 

ከቁጥር 19-20፡- ክርስቲያን ከዝሙት እንዲርቅ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ይሰጠዋል፤ የክርስቲያን አካል የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነው። እያንዳንዱ እውነተኛ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስን የተቀበለ ስለሆነ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሆኖአል። ስለዚህ ትምህርት በተጨማሪ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከቱ፤ (1ኛ ቆሮ.3፡16ና 17፤ ሮሜ 8፡9 እና 15፤ ኤፌ.4:30፤ ቲቶ 3፡4-7)። 

ከአሥርቱ ትእዛዛት አንዱ «አታመንዝር» የሚለው ነው። አሁን በአዲስ ኪዳን ትእዛዙ መሻር ቀርቶ የትእዛዙ ጥብቅነት በአምስት ምክንያቶች ላይ ተመሥርቷል። እነዚህ አምስት ምክንያቶች እንደሚከተሉት ናቸው፤ 

1ኛ. የክርስቲያን አካል ከጌታ ጋር ስለተባበረ ሥጋውን በዝሙት ሥራ ማርከስ የለበትም፤ (ቁጥር 13 እና 15)። 

2ኛ. የክርስቲያን ሥጋ ለክብር (ለትንሣኤ) ስለታጨ በረከሰ ሥራ ላይ መዋል የለበትም፤ (ቁጥር 14)። 

3ኛ. በዝሙት መሠማራት አካልን ከአመንዝራ ጋር ስለሚያስተባብር የዝሙት ሥራ መወገድ አለበት። 

4ኛ. ከሌሎች ኃጢአቶች ሁሉ የዝሙት ሥራ ስለሚጎዳ ሰው ከዝሙት መሸሽ አለበት። 

5ኛ. ሥጋችን የመንፈስ ቅዱስ ቤት ስለሆነ በሥጋችን እግዚአብሔርን ማክበር አለብን፤ ዝሙት እግዚአብሔርን ያስቀይመዋል እንጂ አያክብረውም፤ (19-20)። ዕብ.13፡4 ጋብቻ ክቡር፥ አመንዝራነት ግን በእግዚአብሔር የተከለከለ መሆኑን ያስተምራል። ስለዚህ ጋብቻ ከመመሥረቱ በፊትም ሆነ በኋላ ከጋብቻ ውጭ የሥጋ ፍትወት መወገድ አለበት። 

ጥያቄ 7. ሀ/ በቤተ ክርስቲያን የዝሙት ሥራ እንደዚህ በጣም የበዛው ለምንድነው? ለ/ ከጋብቻ በፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነትን እንዳይለማመዱ ወጣቶቻችንን እንዴት አድርገን ነው በተሻለ መንገድ ልናስተምር የምንችለው?

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d bloggers like this: