( 1ኛ ቆሮንቶስ 1:18-31ን) አንብብ።
ጥያቄ 1. የመስቀሉ ቃል ሞኝነት ነው ሲል እንዴት የእግዚአብሔር ነገር ሞኝነት ሊሆን እንደቻለ አስረዳ።
ጥያቄ 2. እግዚአብሔር ራሱ የሰውን አእምሮ የፈጠረ ሲሆን ለምን የሰውን ጥበብ መልሶ ይቃወማል?
ጥያቄ 3. ለአይሁድና ለግሪኮች ለእያንዳንዳቸው የወንጌሉ ቃል እንዴት መሰናክል ሊሆን ቻለ?
ጥያቄ 4. እግዚአብሔር የዓለምን ጥበብ ለመቃወም ሁለት እርምጃዎችን ወሰደ፤ እነዚህ እርምጃዎች ምንና ምን ናቸው? (ለዚህ ጥያቄ መልስ በተለይ ቁጥር 18ና 26ን ተመልከት)።
የመስቀሉ ቃል ሞኝነት የሆነው በራሱ በእውነትም ሞኝነት ሆኖ ሳይሆን በዓለማውያን ዘንድ ሞኝነት ሆኖ ተቀጠረ ማለት ነው። አናጺዎች የጣሉት ጽንጋይ የማዕዘን ራስ ሆነ ከሚለው ቃል ጋራ አብሮ የሚሄጽ ቃል ነው፡፡ «ለሚጠፉት ሞኝነት ነው ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው»፡፡ ዓለማመን የእግዚአብሔርን የማዳን ኃይል ወደ ሞኝነት ቀየረባቸው። ግን ይህ የናቁት «ሞኝ» ነገር አንድ ቀን በፍርድ ያፋጥጣቸዋል፤ (የሐዋ.17:30-31፤ ሮሜ 2:16፤ ራዕይ 6፡16 እና 17)።
እግዚአብሔር የሰውን ጥበብ ቢፈጥርም ሰው እግዚአብሔር የሰጠውን ጥበብ አዙሮ እግዚአብሔርን መዋጊያ ስላደረገው እግዚአብሔር የሰውን ጥበብ ከንቱ እንዲሆን አድርጓል። ይህም የሆነው ዓለም ሞኝ በምትለውና በምትንቀው በመስቀል ቃል የደህንነትን መንገድ በማቅረብ ነው። ስለዚህ የዓለም መርማሪም ሆነ ተራ ያልተማረው ራሱን ከንቱ አድርጎ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አለበት፤ (ቁጥር 21)።
እግዚአብሔር የዓለምን ጥበብ በሁለት መንገድ ከንቱ አደረገ፤ ሞኝነት በተባለው በመስቀል በኩል ደህንነትን ማዘጋጀቱና የዓለምን ተራ ሰዎች የመንግሥቱ ወራሾች አድርጎ መምረጡ ነው። የዓለም ተራ ነገር የተመረጠበት ምክንያት ያ ተራው ነገር እውነትም ከከበረው ነገር ተመራጭ ሆና ስለተገኘ ሳይሆን በራሱ የሚመካበት ስለሌለውና ባዶነቱን በቶሎ ስለሚገነዘብ ብቻ ነው፡፡ «የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ» የተባለው ቃል የሰው ሁሉ መመሪያ መሆን ይገባዋል፤ ነገር ግን የዓለም አዋቂዎች በጥበባቸው እየተመኩ በመስቀሉ ቃል ይሰናከላሉ፤ (ቁጥር 25-31 ተመልከት)። ስለዚህ መስቀሉ ጥበበኞችን በትዕቢታቸው ስላጠመዳቸው ሞኝነት መሆኑ ቀርቶ ሰው በጥበቡ ሊደርስበት የማይችል ረቂቅ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው፤ (ቁጥር 24)፡፡ ይህን ሀሳብ ሐዋርያው በአግቦ አነጋገር ሲገልጽ እንዲህ ይላል፤ «ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና»፡፡ ይህ ማለት ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት የበለጠ ጥበብን ያሳያል።
የእግዚአብሔር ጥበብ የተገለጸው የእግዚአብሔር ጥበብ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የእግዚአብሔር ጥበብና ኃይል የተገለጸው በኢየሱስ ምጽዓትና ሞት ነው። ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም ምድር ላይ መጥቶ የኖረው በታላቅ ኃይልና ክብር አልነበረም። እንዲያውም አንደ አገልጋይ ሆኖ ነበር የመጣው። የመጣውም ለኃጢአታችን ሲል ለመሞትና በዚህም ሞቱ የደህንነትን መንገድ እንዲከፍትልን ነበር። ላልዳኑት ይህ የደህንነት መንገድ ሞኝነት ነው። አይሁዳውያን ይጠብቁ የነበረው ከጠላቶቻቸው እጅ ነፃ የሚያወጣቸውን ታላቅና ድል አድራጊ ንጉሥ ነበር። እንደማንኛውም ተራ ነፍሰ ገዳይ የሚሰቀል መሢህ አልነበረም የሚጠብቁት። አሕዛቦችም፥ በተለይ ግሪኮች ታላቁን የእግዚአብሔር የደህንነት ዓላማ ሊረዱ አልቻሉም። ነገር ግን የድል ምልክት የሆነው መስቀል በእግዚአብሔር ዓላማ ውስጥ ዋነኛውን ሥፍራ ይዟል፡፡ በዚህ መስቀል አማካኝነት፡-
ሀ. ሰይጣን ተሸንፏል።
ለ. በቅዱሱ እግዚአብሔርና በኃጢአተኛው ሰው መካከል የእርቅ መንገድ ተከፍቷል።
ሐ. እንደ እግዚአብሔር ልጆች የቅድስናና የጽድቅ ኑሮ እንድንኖር ኃይሉ ተሰጥቶናል።
የእግዚአብሔር ዓላማና ጥበብ ከሰው የተለየ መሆኑን የምናረጋግጠው፥ እግዚአብሔር በዓለም የተናቀውን ነገር ወደ ራሱ አምጥቶ ለክብሩ ሲጠቀምበት በማየታችን ነው፡፡
ጥያቄ 5. ሀ/ ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን የእግዚአብሔርን ጥበብ የመናቅን ጉዳይ ለሰዎች በምትመሰክርበት ጊዜ በምን መልኩ ነው ያየኸው? ለ/ እግዚአብሔር በዓለም ዓይን የተናቀውን ሰው መርጦ በታላቅ ኃይል ለእርሱ አገልግሎት ሲያዘጋጃው ያየኽው ሰው ካለ እንዴት አድርጎ ይህንን ሰው ተጠቀመበት?
(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)