ዳግመኛ ለማግባት የሚፈቀደው መቼ ነው? (1ኛ ቆሮ. 7:36-40)

ጥያቄ 1. ዳግመኛ ለማግባት የሚፈቀደው መቼ ነው? (ቁጥር 39ና 40፤ 1ኛ ቆሮ.1:15፤ ማቴ.5፡32) 

ቁጥር 36 የተለያየ ትርጉም የተሰጠው ከባድ ጥቅስ ነው። በዚህ ላይ ባደረገሁት ጥናት መሠረት የሚመስለኝን ትርጉም አቅርቤአለሁ፤ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ አጥጋቢ የሆነ ትርጉም አላገኘሁም። 

አሁን ያለውን የአማርኛውን ትርጉም ቃል በቃል ከግሪኩ ከተተረጎመው ጋር እናስተያየው። ከግሪኩ ቃል በቃል ሲተረጕም እንዲህ ይላል፡- ነገር ግን ሰው የእርሱ ስለሆነችው ድንግል የማይገባውን እንዳደረገ ቢያስብ፥ ድንግሊቱም በዕድሜ እየገፋች ብትሄድ፥ እንዲሁም ለማድረግ ግዴታ ቢኖርበት፥ የሚወደውን የድርግ፤ ኃጢአትን አይሠራም ይጋቡ። 

እንግዲህ በዚህ መሠረት ሁለት አተረጓጕሞች ይገኛሉ፤ አንደኛው የተጠቀሰው ሰው የድንግሊቱ አባት ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ የተጠቀሰው ሰው የድንግሊቱ እጮኛ ነው። አባቷ ነው የሚሉ ይጋቡ የሚለው ገሥ መተርጉም ያለበት «ያጋባቸው» ብሎ ነው ይላሉ። 

የሁለተኛውን አተረጓጉም የሚደግፉ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፤ ምንም እንኳ ግሡ ያጋባቸው የሚል ትርጉም ቢኖረውም በዚህ ጥቅስ ላይ ተስማሚው አተረጓጎም ይጋቡ የሚለው ነው ይላሉ። በተጨማሪም በነጠላ ቁጥር ሆኖ ያጋባቸው ሳይሆን በብዙ ቁጥር የተነገረ ስለሆነ «ይጋቡ» ተብሎ መተርጎም አለበት፤ ያም እጮኛሞቹን ነው የሚያመለክተው ይላሉ። 

የመጀመሪያው አተረጓጎም ይመረጣል፤ የሚከተሉትም ምክንያቶች ይህንኑ ያረጋግጣሉ። 

1ኛ/ ለወጣቶቹ በእጮኝነት መዋዋል በዚያን ጊዜ ባህላቸው አይፈቅድም፤ ነገር ግን አባት ድንግል ሴት ልጁን በጋብቻ መስጠት የተለመደ ነበር። ስለዚህ የጥቅሱ ሃሳብ ይህ ነው፤ አንድ አባት ሴት ልጁን ለጋብቻ ባለመስጠቱ የማይገባውን እንዳደረገ ቢመስለው ያጋባት»፡፡ 

2ኛ/ በግሪክ ቋንቋ «የእርሱ የሆነችው ድንግሊት» የሚለው አነጋገር ለእጮኛ አይውልም፤ ለአባት ግን ይውላል። 

3ኛ/ እጮኛ ብትሆን ኖሮ እጮኛዋ ላለማግባት ከወሰነ ለምን እንደ በደል ይቆጠራል? የማይገባስ ለምን ይሆናል? አላገባም ብሎ ከተዋት አሁን የርሱ አይደለችም። አባት ከሆነ ግን ጋብቻን ከከለከላት «ይህችን ልጅ በደልኳት» ብሉ ትክክለኛ ነገር ማድረግ አለማድረጉ ሊያጠራጥረው ይችላል። 

ስለዚህ የጥቅሱ ጠቅላላ አነጋገር ይህ ነው፤ አንድ አባት ወጣት ልጃገረድ ልጅ ኖራው እንዳታገባ አስጠብቋት የማግቢያ ወቅቷ ሲተላልፍባት አይቶ የማይገባውን ያዳረገ ቢመስለውና እንዲያጋባት ገድ ቢሆንበት ለጋብቻ ቢሰጣት ኃጢአት አያደርግም፤ የቀረበላት እጮኛና እርሷ ይጋቡ። 

ቁጥር 37:- አሁንም የግሪኩን ቃል በቃል መተርጎም አለብን፤ የአማርኛ ትርጉማችን በቂ አይደለም፡፡ ግን በራሱ ልብ ጸንቶ የቆመ፥ ግዴታ ከሌለበትና፥ በራሱ የመወሰን መብት ካለው፥ የራሱም የሆነችውን ድንግል በድንግልና ለመጠበቅ በራሱ ልብ ወስኖ ከሆነ መልካም አደረገ። 

እንግዲህ የጥቅሱ ሃሳብ፥ ይህ አባት ልጃገረድ ልጁን በድንግልና እንድትኖር በራሱ ሳይጠራጠር የወሰነና ይህን ለመወሰን መብት ካለው (የሰው ተገዥ ባሪያ ካልሆነ ወይም አንድ ዓይነት ግዳጅ ከሌለበት ማለት ውል መሳይ ነገር ባያስገድደው) መልካም አጸረገ። 

ቁጥር 38፡- ይህ ቁጥር ቃል በቃል ከግሪኩ ሲተረጕም ይህን ይመስላል፤ እንዲሁም ድንግሊቱን በጋብቻ የሰጠ መልካም አደረገ፤ በጋብቻ ያልሰጣትም የተሻለ አደረገ። 

ቁጥር 39 እና 40፡- ሰው ዳግመኛ ማግባት የተፈቀደላት ሚስቱ ከሞተች ነው። የጳውሎስ ምክር ግን ያው ከላይ በተዘረዘረው ምክንያት ሳታገባ ብትኖር የተሻለ መሆኑን ይናገራል። 

በ1ኛ ቆሮ.7:15 ላይ ደግሞ የማታምነው ከተለየች፣ አማኙ በጋብቻው ያልታሰረ መሆኑን ስለገለጠ እንግዲያስ ዳግመኛ ለማግባትም ተፈቅዷል ማለት ነው። ባሏን ትታ እንደሄደችው አማኝ (ቁጥር 10ና 11) በጋብቻው ስላልታሰረ ሳያገባ እንዲኖር ገዴታ የለበትም፤ «ወንድም ቢሆን ወይም እህት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም»። ስለዚህ የማታምን ሚስቱ ጥላው ከሄደች ዳግመኛ የማግባት መብት ስላለው ይህ ዳግመኛ ለማግባት ሁለተኛው የተፈቀደ መንገድ ነው፡፡ ይህ መደረግ ያለበት የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች አይተውት አማኙ በደለኛ አለመሆኑን ቤተ ክርስቲያን ስትመሰክር ብቻ እንጂ በግል መደረግ ያለበትም። እንደዚህ ከሆነ አማኝ ሚስቱን በግፍ ሊበድላት እንደሚችል መጠራጠር የለብንም። 

ጋብቻ ፈርሶ ሌላ ማግባት የሚፈቀድበት ሌላ አንድ ተጨማሪ ምክንያት አለ፤ ያም ዝሙት ነው። ማቴ.5፡32 እና 19፡9። ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ማግባት ስለተከለከለ፣ እንግዲያስ በዝሙት ምክንያት ሚስትን ፈትቶ ሌላ ማግባት ተፈቅዷል ማለት ነው። በዚህ መንገድ ሰው በግሉ ሳይሆን ነገሩ በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ተጠንቶ መረጋገጥ አለበት። ሚስቴ አመንዝራለች ወይም ባሌ አመንዝሮአል በማለት ጋብቻን በግል ማፍረስ ከጌታ ሥርዓት ውጭ መሆን ስለሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ዝሙት መፈጸሙ እንኳ ቢረጋገጥም በንስሐና በይቅርታ ጋብቻ እንዲጸና ለማድረግ ከፍቺው በፊት ጥብቅ ሙከራ መደረግ አለበት። 

ጥያቄ 2. ያንተ ቤተ ክርስቲያን ስለ ፍቺና ስለ ጋብቻ የምታስተምረው ምንድን ነው? እንዴት ነው ከዚህ ትርጓሜ ጋር የሚመሳሰለው? የሚለያየውስ አንዴት ነው?

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d bloggers like this: