ማሳሰቢያ!
በዚህ የተሰጠውን ዝርዝር ጥናት ከመመልከትህ በፊት ቃሉን በራስህ በመመርመር ለቀረቡልህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሞክር።
ጥያቄ 15. በቁጥር 20 ላይ “እያንዳንዱ በተጠራበት መጠራት እንደዚሁ ይኑር» ሲል ሐዋርያው ምን ማለቱ ነው?
ጥያቄ 16. ባሪያዎች በባርነታቸው እንዳይጨነቁበት ባሉበት ሁኔታ እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ መክሮአቸው ሲያበቃ በቁጥር 23 ላይ «የሰው ባሪያዎች አትሁኑ» ማለቱ ምን ማለቱ ነው?
በዚህ ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ስለ ጋብቻ ተወት አድርጎ ስል አጠቃለይ የክርስቲያን ኑር ይናገራል። በቁጥር 17 ላይ እያንዳንዱ ክርስቲያን ጌታን ሲቀበል በነበረው ኑሮ መቀጠል እንጂ ክርስቶስን ከተቀበለ በኋላ ኑሮውን ለመቀየር ክርስትና አያስገድደውም። መቀየር ያለበት የኃጢአት ኑሮን እንጂ የሥራ ስምሪትን መቀየር ግዴታ አይደለም። በማንኛውም ሥራ ብንሠማራ በዚያ ጌታን ማገልገል እንችላለን።
በሚከተሉት ጥቅሶች ውስጥ ሰው ይሰማራባቸው የነበሩትን አንዳንድ የሥራ መስኮች ምሳሌ ይሰጣል፡፡ እነርሱም ባርነትና ጌትነት ናቸው፤ (20-24)። «ባርያ ሆነህ ተጠርተህ እንደሆነ አይገድህም»። ይህም ማለት ባርነት የክርስቶስ አገልጋይ ከመሆን አይከለክልም ማለት ነው። ሆኖም ባርነትን የተመረጠ ኑሮ አድርገህ ተቀበለው ማለቱ አይደለም። ሰው በነጻነት ለመኖር መንገድ ካገኘ ነጻነቱን ይጕናጸፍ፤ ነገር ግን ነጻነት መጐናጸፍ ባይችል ነጻ እስከሚሆን ድረስ በባርነቱ የክርስቶስ አገልጋይ መሆን ይችላል።
እንዲህ በባርነቱ በክርስቶስ የማይደገፍ ሆኖ ነጻነት ስለሌለው ሁልጊዜ ተስፋ ቢስ በመሆን ቢኖር ለሰው ባሪያ መሆኑ የእግዚአብሔር ባሪያ ከመሆን ከልክሎታል ማለት ነው። ይህ ከሆነ የአግዚአብሔር ባሪያ መሆኑ ቀርቶ የሰው ባሪያ ሆነ ማለት ነው፤ «ባሪያ ሆኖ በጌታ የተጠራ የጌታ ነጻ ነውና፤» (ቁጥር 22)።
ችግር ሰውን እግዚአብሔርን ከማገልገል ሊከለክለው አይችልም። ምንም እንኳ ሰው ክፉ በሆነ ባርነት ቢያዝም በዚያ ውስጥ እንኳ በመንፈስ ነጻ የወጣ ነውና አገልግሎቱን ለእግዚአብሔር ሊያደርገው ይቻላል።
ይህ የሐዋርያው ትምህርት «መጽሐፍ ቅዱስ ባርነትን ይደግፍፋል» ለሚለው ጥራዝ ነጠቅ የነቀፋ አስተያየት መነሾ ሆኖአል። ነገር ግን እዚህ ላይ ሐዋርያው ነጻነትን አይቃወም «አርነት ልትወጣ ቢቻልህ ግን አርነትን ተቀበል፤» (ቁጥር 21)።
ሐዋርያው እዚህ ላይ ክርስቲያን በጭቆና ውስጥ ሳለ እንዴት ጭቆናን መቋቋም እንደሚችል መንፈሳዊ መምሪያ መስጠቱ ነው። በተጨማሪም ስለመገረዝና ስለአለመገረዝ ይናገራል፤ “ማንም ተገርዞ ሳለ ተጠርቶ እንደሆነ ወደ አለመገረዝ አይመለስ” (ቁጥር 18)። በሰው ልቦና ውስጥ ሁልጊዜ መጓጓት አለ። እግዚአብሔር በሰጠው ረክቶ በአእምሮ ሰላም እንደመቀመጥና እግዚአብሔርን አንደማገልገል ሁልጊዜ የሌለውን ነገር ወይም ያልሆነውን እያሰበ በማጉረምረም መኖር ለክርስቲያን አይገባውም። «እያንዳንዱ በተጠራበት እንዲሁ ሆኖ በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር፤» (ቁጥር 24)። እንደዚህ ሆኖ በመንፈስ ነጻ ሆኖ በምስጋና ለመኖር ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ነጻነት ተሰጥቶታልና በሆነው ባልሆነው እያማረረ መበሳጨት የለበትም። ነገር ግን ክርስቲያን በተሰጠው የኑር ጥሪ በእግዚአብሔር ፊት በምስጋናና በድል መኖር አለበት።
ጥያቄ 17. ይህን ምክር በትምህርታቸው፥ በዘራቸው፥ በኑሮ ደረጃቸው፥ ወዘተ ለማይደሰቱ ሰዎች እንዴት አድርገን ነው እንዲገባቸው ማድረግ የምንችለው?
(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)