1ኛ ቆሮ. 7:25–35

መግቢያ 

ሐዋርያው በዚህ ክፍል ውስጥ አለማግባት ለምን ከማገባት እንደሚሻል ሁለት ምክንያቶችን በመስጠት ያስተምራል። እነዚህ ምክንያቶች:- 1ኛ/ በአሁኑ ዘመን ስደት ስላለ በጋብቻ ውስጥ ያሉ በስደት ጊዜ ውስጥ ካላገቡት የበለጠ ስደቱ ይከብዳቸዋል፤ (ቁጥር 28)። 2ኛ/ ጌታን በአንድ ልብ ለማገልገል አለማግባት ከማግባት ይሻል! (ቁጥር 32-33)። ሆኖም ግን አለማግባት ራስን የመግዛት ጸጋ ለተሰጣቸው ብቻ እንጂ ለሁሉ አይሆንም። ይህ ጸጋ ያልተሰጣቸው ባያገቡ ሐዋርያው እንዳላው በስሜት ወደ መቃጠል ይወድቃሉ። እንደዚያ እንዳይሆን ካለማግባት ማገባት ይሻላል፤ (7:1-2)። 

ጥያቀ 18. በቁጥር 25 ላይ «የጌታ ትእዛዝ የለኝም» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 19. በቁጥር 28 ላይ «እንዲህ በሚያደርጉ ላይ በሥጋቸው መከራ ይበዛባቸዋል» ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ አብራራ።

ጥያቄ 20. አለማግባት ከማግባት የተሻለ መሆኑን በሁለት ምክንያቶች ይደግፋል፤ እነዚህን ምክንያቶች ጥቀስ፤ (ቁጥር 29-35)። 

ቁጥር 25 «ስለደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም» እንደበፊተኛው (ቁጥር 10 እና 11 ጌታ ያስተማረው በወንጌል እንደተጠቀሰው የለኝም ማለቱ ነው እንጂ መንፈስ ቅዱስ ይህንን እንዲናገር አልመራውም ማለት አይደለም። እንዲያውም በቁጥር 40 ላይ ይህን ሲያስተምር የእግዚአብሔር መንፈስ እየመራው እንደሆነ ይናገራል። 

«ምክር እመክራለሁ»፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የሚያስተምራቸው እንደ ትእዛዝ ሳይሆኑ በምርጫ የሚደረጉ ምክሮች ናቸው። ሰው የሚወስደውን የእርምጃውን ውጤት አውቆ ባለው ነፃነት እንዲወስን ሐዋርያው ስለደናግል ጋብቻ ምክር ይሰጣል። የማግባትንም ያለማገባትን ውጤት በየመሥመሩ በማስቀመጥ ውሣኔው የምእመኑ እንደሆነ ያስተምራል። በተጨማሪ ይህ ትምህርት ምእምንን «ምነው ባላገባሁ ኖሮ» ወይም ያላገባው «ምነው ባገባሁ» እያለ ያለበትን ሁኔታ እንዳያማርር ይመክራል፤ (ቁጥር 27)። 

ማግባት ወይም አለማግባት የግል ምርጫ ጉዳይ ወይም ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደሰጠው በነፃነት የሚወሰድ እርምጃ ነው እንጂ የኃጢአትና የጽድቅ ጉዳይ አይደለም። ማግባትዎ አለማግባትም ተፈቅዷል (ቁጥር 28)። እንዲያውም ጋብቻን መከልከል የዲያብሎስ ትምህርት እንደሆነ ሐዋርያው በሌላ ቦታ ያወግዛል፤ ( 1ኛጢሞ.4:1 እና 2)። 

ጥያቄ 21. ለምንድነው አንዳንድ የክርስቲያን ሃይማኖት ቡድኖች መሪዎቻቸው (ቄሶቹ) እንዲያገቡ የማይፈቅዱላቸው? ጠይቃቸውና ምክንያታቸውን ገልጽ፡፡

ከቁጥር 29-31:- በእዚህ ጥቅሶች ውስጥ ያለው ምክር በቁጥር 27 ካለው ምክር ጋር ይስማማል። ሰው በማግባቱ «ምነው ባላገባሁ ናሮ» ወይም ባለማግባቱ «ምነው ባገባሁ» ብሉ መጸጸትና የልብ ሰላም ማጣት የለበትም። ምክንያቱም ጋብቻ የዚህ ዓለም ኑሮ ጉዳይ ብቻ ስለሆነ አንድ ቀን እንዳልነበር የሚሆንበት ወቅት ይመጣል። ጋብቻ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የአሁኑ ሥርዓት የሚሻርበት ወቅት ስለሚመጣ ክርስቲያን ባለው ተደስቶ በምስጋናና ራስን በመግዛት መኖር አለበት። ከዚህ ሃሳብ ጋር የዮሐንስ ራእይ 21:4ን ተመልከት። 

ነገር ግን በጊዜው ችግር ምክንያት አለማግባት ይቀላል በማለት ሐዋርያው የራሱን ምክር ከርህራሄ አንፃር ይሰጣል፤ (ቁጥር 25 እና 32-35)፡፡ ሰው ካገባ ለራሱ ማሰብ ቀርቶ ለሚስቱና ለልጆቹ መጨነቅ ይጀምራል። ይህም በችግር ላይ ችግር ያስከትላል። ስለዚህ መላ ልቡን በጌታ አገልግሎት ላይ ማሰማራት ያስቸግረዋል። እንግዲያስ ሰው ከጋብቻ የሚቆጠበው ለራሱ ምቾትን ፍለጋ ሳይሆን ባልተከፋፈለ አእምሮ ጌታን ማገልገል እንዲችል መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ሐዋርያው የራሱን ሕይወት ምሳሌ በማድረግ ሰው ባለማግባት ምን ያህል ለጌታ ሥራ በነፃነት እንደሚሰማራ ይናገራል። ስለዚህ ክማግባት ይልቅ አለማግባትን ይመርጣል። 

ጥያቄ 22. ያላገባ ሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲኖር ብዙ ሰዎች እንዲያገባ ሊያስገድዱ የሚሞክሩት ከምን የተነሣ ነው? ይህ ትክክል ነው? 

አሁንም ደግመን መገንዘብ ያለብን፡- 1ኛ / ጋብቻ ኃጢአት የለበትም። 2ኛ / አለማግባት የግል ጥቅምን ፍለጋ መሆን የለበትም፤ ለጌታ ሕይወትን የመሠዋት ጉዳይ ነው እንጂ፤ ማቴ. 19፡12ን እንመልከት። «ስለመንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ።» ይህም ማለት ራሳቸውን አንደ ስልብ ቆጥረው በነጠላ ኑሮ ጌታን የሚያገልግሉ ማለት ነው። «ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባሏን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባላች፤» (ቁጥር 34)። 

ነገር ግን ይህን የመሥዋዕትነት ኑሮ መቀበል የሚችሉ ራስን መግዛት የተሰጣቸው ብቻ ናቸው እንጂ ሁሉም አይደሉም። ስለዚህ ሐዋርያው “በጠምዳችሁ ብዬ አይደለም” ይላል። «የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች» ወይም «አተርፍ ባይ አጉዳይ» እንዳንሆን መጠንቀቅና በአቅማችን ማደር ይኖርብናል።

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d