1ኛ ቆሮንቶስ 9፡ 15-18 

ጥያቄ 1. በቁጥር 15 ላይ «እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልድፍም» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 2. በቁጥር 15 ላይ «ትምክሕት» የሚለው ምኑን ነው? 

ጥያቄ 3. በቁጥር 17 መሠረት ሐዋርያው ወንጌልን ይሰብክ የነበረው በፈቃድ ነበር ወይስ ያለፈቃድ? 

ጥያቄ 4. በቁጥር 18 ላይ ወንጌልን የመስበክ ደምወዙ ምንድነው ይላል? 

ቁጥር 15:- ከላይ ከዘረዘራቸው መብቶች በአንዱም እንኳ ያልተጠቀመ እንደሆነ ይመሰክራል፡፡ በዚህ ጊዜ በአእምሮው የመጣበት ምናልባት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች «ይህን ሁሉ አሁን የሚናገረው ደመወዝ ፈልጎ ነው ይሉኝ ይሆናል፤» የሚለው ግምት ነበር። ይህም እንዳልሆነ በከባድ አነጋገር ያረጋግጥላቸዋል። «ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርገብኝ ሞት ይሻለኛልና።» 

ትምክህቱ ወንጌልን በነፃ መስበኩ ነው። ግን አሁን ሃሳቡን ቀይሮ ደመወዝ መቀበል ቢጀምር ያ ትምክህቱ ይቀራል። ትምክህቱ የትዕቢት ሳይሆን ደመወዝ በመቀበል ሊመጣ የነበረውን የወንጌልን እንቅፋት በማስወገዱ ነበር። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሐዋርያውን የማይወዱ ሐሰተኛና ደምወዝ ወዳድ አስተማሪዎች ተነሥተው ነበርና የሐዋርያው አቋም ለእውነት በጣም አስፈላጊ ነበር። እነዚህም ሐሰተኛ አስተማሪዎች እርሱም ደመወዝን ተቀብሎ ከእርሱ እኩል በመሆን እንዳያሳጣቸው ይፈልጉ ነበር፤ (2ኛ ቆሮ. 11:12)። 

ጥያቄ 5. በአንዳንድ ቤተ ክርስቲያን ለደመወዝ ብቻ ብለው የሚያገለገሉ መሪዎች አሉ? ይህ ዓይነት ሃሳብ እንዴት ለወንጌልና ለቤተ ክርስቲያን እንቅፋት ሊሆን ይችላል? 

ቁጥር 16፡- «ወንጌልን ብሰብክ እንኳ» የሚለው አነጋገር እንደዚሁ ብሰብክም እንኳ ያንኑ የታዘዝሁትን ፈጸምሁ እንጂ ትርፍ ሥራ የሠራሁ ይመስል ልኮራ አይገባኝም ማለቱ ነው፤ (ሉቃ.17:10)። ወንጌልን መስበክ ግዴታው ስለሆነም ወንጌልን ባይሰብክ “ወዮለት!” ወንጌላዊ ጥሪውን በቀላሉ ሊመለከተው አይገባም። 

ጥያቄ 6. ይህን ዓይነት ገዴታ በእኛ ላይ አለ? እንዴት? 

ቁጥር 17:- «በፈቃዴ ባደርገው» ማለቱ ክርስቶስ በግድ ባያዘው ኖሮ እርሱ ራሱ በገዛ ምርጫው ቢሰማራ ኖሮ ደመወዝ ይገባው ነበር። ይህ ደመወዝ የሚለው አነጋገር ወንጌላውያን ከወንጌል ሥራ መተዳዳሪያ (ደመወዝ) ይቀበሉ ካለው ሃሳብ የተለየ ነው። ይኸኛው እግዚአብሔርን ለደመወዙ ባለዕዳ ማድረግ ነው፤ (ሮሜ 4:4)። ማንም ሥጋ ለባሽ እግዚአብሔርን ባለዕዳ ማድረግ አይችልም። ወንጌልን የሰበከው “የመጋቢነት አደራ” ስለተሰጠው ነበርና ባሪያ እንጂ በእግዚአብሔር ፊት ባለመብት አይደለም። መጋቢ የሚለው ቃል የባርነትን አደራ ያመልክታል፤ በ1ኛ ቆሮ.4: 1 ላይ የተወያየንበትን ተመልከት። 

ቁጥር 18፡- እንግዲህ ሐዋርያው ምንም እንኳ በእግዚአብሔር ፊት ባሪያ ቢሆንም ቤተክርስቲያን ለሥራው ደመወዝ ልትሰጠው መብት እንዳለው በፊት አረጋግጧል። እንግዲህ ይህን ደምወዝ አለመቀበል ሙሉ ትምክህት በሰው ፊት ስለሚሰጠው ይህን ትምክህት አንደደምወዙ ቆጥሮታል። 

ጥያቄ 7. ጥሩ ዓይነት ትምክህትና መጥፎ ዓይነት ትምክህት በምን ይለያል? እኛ በምን ላይ በጥሩ ሁኔታ ልንመካ እንችላለን? 

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d bloggers like this: