ጥያቄ 8. ቁጥር 19 ላይ ጳውሎስ እንደሚለው ሌሎች የሌላቸው ምን ዓይነት ነፃነት ነበረው?
ጥያቄ 9. በቁጥር 20 ላይ ከሕግ በታች ሳልሆን ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች ሆንኩ ሲል ምን ማለቱ ነው?
ጥያቄ 10. ሕግ እንደሌላቸው ሆንሁ ሲል ሕግ አፍራሽ ሆነ ማለት ነው? አብራራ።
ቁጥር 19፡- ሐዋርያው ጳውሎስ ለጥቂቶች ብቻ ይሰጥ የነበረው የሮማዊ ዜግነት የነበረውና ለማንም ተገዥ ሳይሆን በነፃነት የቆመ ሰው ነበር፤ (የሐዋ. 22:25-29)። ነገር ግን ነጻነቱን አንቆ ሳይሆን በፈቃደኝነት ለሌሎች አገልግሎት አዋለው፤ ለሌሎችም ጥቅም የራሱን መብት ሰረዘ፡፡ ስለ ሦስት ዓይነት ሰዎች ይጠቅሳል። ለእነዚህም ሰዎች ጥቅም ሲል ማድረግ የሚችለውን ነገር እንደተወና ለእነርሱ አገልጋይ እንደሆነ ይናገራል።
ቁጥር 20፡- 1. «አይሁድን እጠቅም ዘንድ እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ»። ጳውሎስ አይሁድን በሚያገለገልበት ወቅት፥ አይሁዳውያንን እንዳያሰናክል በፈቃደኝነት ራሱን ለአይሁድ ወግ አስገዛ፤ (የሐዋ.21: 17-26፤ 16፡ 1-3)። ከሕግ በታች ማለቱ እንግዲህ ይህን የሥነ ሥርዓትና የባህሉን ጉዳይ እንጂ ለደህንነት በሥራ ለመጽደቅ ሕግን ጠበቅሁ ማለቱ አይደልም፤ (ገላ.2:3-5፤ የሐዋ.15፡19-29)። በሌላ አነጋገር አይሁዶች በጳውሎስ ድርጊት መጥፎ ስሜት እንዳይሰማቸው በብሉይ ኪዳን የተፈቀደውን ሥጋ ብቻ ይበላ ነበር፤ ቅዳሜ ላይ የአምልኮ ጊዜ ነበረው፤ ወዘተ። ምንም እንኳን እነዚህን ሕግጋት የመጠበቅ ግዴታ ባይኖርበትም፥ ይህንን ያደርግ የነበረው የእምነትን መንገድ ለአይሁዳውያን ለማቅለል ሲል በር።
- ሕግ የሌላቸው ወይም በአይሁድ ባህል ሥርና በኦሪት ሕግ ሥር ለማይኖሩ ራሱን ከእነርሱ በማግለል አላንገዋለላቸውም፤ (2፡13-16)። በሌላ አነጋገር ምንም እንኳን አይሁዳዊም ቢሆን የረከሰ ነው ተብሎ ሊምደብ የሚችለውን የአሕዛብን ምግብ እንኳን ከመብላት አልተቆጠበም። ደህንነት የሚገኘው የአይሁዳውያንን ልማዶች በመከተል ነው እንዳይሉ አንዳንድ የአሕዛቦችንም ልማዶች ለመቀበል ፈቃደኛ ነበር። በዚህ መልኩ ስናየው ደግሞ የሙሴን ሕግ የማይጠብቅ ሰው ይመስላል። ነገር ግን ለአይሁዳውያን በብሉይ ኪዳን የተሰጡትን ብዙዎቹን ሕግጋት ያለመጠበቅ ነፃነት ቢኖረውም ሙሉ በሙሉ ከአሕዛቦች ጋር ተመሳስሎ ሊኖር አይችልም፤ ምክንያቱም በክርስቶስ ሕግ ሥር መኖር አለበትና ነው። የወንጌል እምነት ዘረኝነትን ከሥሩ ነቅለን እንድናስወገድ ያስተምረናል፤ (ገላ.3:26-29)።
ጥያቄ 11. በብሉይ ኪዳን ከነበሩት ሕግጋት ውስጥ በክርስቶስ ሕግም ውስጥ የሚጠቃለሉት የትኛቹ ናቸው?
- ሦስተኛ ለደካሞች ጳውሎስ ደካማ ሆኖ ነበር የሚቀርበው። ጳውሎስ እዚህ ደካሞች ብሎ የሚናገረው ከህሊናቸው የተነሣ ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ የማይበሉትን ነው። ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነቱን ሥጋ መብላት እንደሚችል ቢያውቅም፥ ነፃነቱ ቢኖረውም፥ ይህንን ነፃነቱን ውስን ያደረገበት ምክንያት የእነርሱን መንፈሳዊ ዕድገት ላለማደናቀፍ ሲል ነበር። ሐዋርያው በጠቅላላ ሕይወቱን ለራሱ ጥቅም ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም እንደሠዋ እናያለን። ይህም ፍቅር የራሱ የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር ነው። እኛም በዚሁ ፍቅር እንመራ፤ (ፊል.2:5-8)።
ጥያቄ 12. የጳውሎስን ምሳሌነት በመከተል፡- አንድ ሰው ልክ «እንደ ኦርቶዶክስ» መስሎ ወንጌል ያልተረዳን ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይን እንዴት ወደ ወደ ወንጌል እውነት ማምጣት ይችላል? ወይም እንደ እስላም ሆና ሙስሊሞችን እንዴት ወደ ወንጌል እውነት ማምጣት ይችላል? ይህን ስናዳርግ አኗኗራችንንና ልማዳችንን የምንቀይረው እንዴት ነው? ይህንን ሲያደርግ ያየከው ወንጌላዊ ወይም ክርስቲያን አለ? ይህንንስ ነገር ማድረግ አለባቸው?
(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)
በዚህ ድረ ገጽ ውስጥ በአዘጋጁ የተጻፉ እና የተተረጎሙ እንዲሁም በተለያዩ አገልጋዮች የተዘጋጁ የድነት ትምሕርቶች፣ የደቀ መዝሙር ትምሕርቶች፣ የአዲስ ኪዳን እና ብሉይ ኪዳን ማጥኛዎችን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ጽሑፎችን ያገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከኤስ አይ ኤም ጋር በመተባበር የተዘጋጀ በአንድሮይድ ስልክ ላይ የሚጫን በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ መተግበሪያ (Amharic Bible Commentary App) ያገኛሉ፡፡ የወንጌል በድረ-ገጽ አገልግሎት ዌብ ሣይት (https://ethiopiansite.com/) የፊት ገጽ ግርጌ ላይ በመሄድ፣ በስተቀኝ ባልው ክፍት ሣጥን ውስጥ የኢ-ሜይል አድራሻዎን በመጻፍና “ድረ-ገጹን ይከታተሉ” የሚለውን ቁልፍ በመጫን የዌብ ሣይቱ ተከታይ (follower) እንዲሆኑ ተጋብዘዋል፡፡ ይህን ሲያደርጉ በዌብ ሣይቱ ላይ አዳዲስ ጽሑፎች ሲጫኑ፣ በኢ-ሜይል አድራሻዎ የማስታወሻ መልእክት (notification) የሚያገኙ ይሆናል፡፡