1ኛ ቆሮ. 9፡24-27

ጥያቄ 13. በወንጌል የሚሮጡ ከሌሎች ሩዋጮች በሁለት ነገሮች ተለይተዋል፤ እነዚህ ነገሮች ምንና ምን ናቸው? 

ጥያቄ 14. በቁጥር 27 ላይ «የተጣልሁ እንዳልሆን» የሚለውና «ሥጋውን መጎሰም» ምን ማለት ነው? 

ሐዋርያው በወንጌል ሥራ የሚያደርገውን መሥዋዕትና ትግል በዘመኑ ከነበሩ ስፖርተኛች ጋር ያስተያየዋል፡፡ ከእነዚህ ሩዋጮች የሚወስዳቸው ምሳሌዎች ድል ለማድረግ የሚያደርጉትን ራስን የመግዛት መሥዋዕት ነው። ግን ምሳሌው በማመሳሰል ሳይሆን ብዙው በማነጻጸር (በሚቃረን) ነው የተነገረው። 

ቁጥር 24፡- በስፖርት ዓለም ሐዋርያው እንደሚያውቀው ለውድድር የቀረቡት ሁሉ ይሮጣሉ፤ የሚያሸንፈውና ሽልማቱን የሚቀበለው ግን አንዱ ብቻ ነው። በወንጌል ሩጫ ግን ሁሉም በሚገባ ከሮጡ ሁሉም የማይጠፋውን ዘውድ ይቀበላሉ። 

እንዲሁም በቁጥር 25 ላይ እነርሱ የሚቀበሉት አክሊል የሚጠፋ አክሊል ነበር። በታሪክ እንደምናውቀው ለስፖርተኛ ሽልማቱ ከዘንባባ የተገመዳ አክሊል ነበር። በቶሎ የሚረግፍና የሚጠወልግ ነው። በእውነት ለሚጠፋ አክሊል እንደዚያ ይታገሉ ነበር። ለክርስቲያን ግን በታማኝነት ካገለገለ ሽልማቱ የማይጠፋ የክብር አክሊል ነው። ስለዚህ ሐዋርያው የሚነግራቸው ራስን መሠዋትና ነፃነትን ለዳካሞች አገልግሎት መስጠት ዋጋ እንዳለው ነው። 

ቁጥር 26 ላይ «ያለ አሳብ እንደሚሮጥ» ማለቱ ያለ ሥጋት ማለቱ አይደለም፤ ግን ያለ ዓላማ ዝም ብሎ በደመነፍሱ የሚሮጥ አይደለም ማለቱ ነው። ለሚሠራው ሥራ በደንብ ያሰበበት ዓላማ አለው። 

«ነፋስን እንደሚጕስም» እንደማያሸንፍ ወይም በመጨረሻ በድል እንደማይቆም ሆኖ እየተጠራጠረ አይደለም የሚሮጠው። ነገር ግን በእርግጥ እንደሚያሸንፍ በእርግጠኝነት ይታገላል፤ (2ኛ ጢሞ.4፡6-8)። ጳውሎስ የሯጭን ምሳሌ ከሰጠ በኋላ በትግል ውስጥ ስለሚኖረው ነገር ያስረዳናል። የሚታገለው ሰው ዝም ብሎ ነፋስን እንደሚጎስም ሰው አልነበረም። ነገር ግን ጊዜውን ወስዶ፥ ኃይሉንና አስተሳሰቡን ተጠቅሞ ነው የድሉን አክሊል ለማግኘት የሚጣጣረው። 

በዚህም ነጥብ ከግሪክ ሩዋጮች የተለየን ነን። እነርሱ ሲሮጡ ሁሉም ሳይሆኑ አንዱ ብቻ ነው አክሊሉን የሚቀበለው። ስለዚህ በታማኝነት ቢሮጡም አንዱ ከበለጣቸው ሩጫቸው ዋጋ ቢስ ይሆናል። እኛ ግን እስከፍዳሜ በታማኝነት ከሮጥን ሁላችንም የሕይወት አክሊልን እንቀበላለን። 

ቁጥር 27፡- «ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን» ማለቱ በወንጌል አገልግሎት ተሰልፎ ራሱን መግዛት አቅቶት ለተነገረው ሽልማት የማይበቃ ሆኖ እንዳይገኘ ማለቱ ነው። 

መጣል ማለትም ሁለት ትርጉም ሊኖረው ይችላል። 

1ኛ/ ሊኖረኝ የሚገባኝን ሽልማት እንዳላጣ፤ ( 1ኛቆሮ.3፡ 11-15)። 

2ኛ/ ራሴን ባለመግዛት በኃጢአት ኑሮ ኖሬ በመጨረሻ በእግዚአብሔር ፍርድ ላይ እንዳልወድቅ ማለት ነው። 

2ኛው ትርጉም ይመረጣል። ምክንያቱም ሐዋርያው የሚናገረው ሕይወትን ለአግዚአብሔር ክብር ስለማዋል ወይም ሕይወትን ለራስና ለሥጋ ምቾት ስለማዋል ነው። አንድ ሰው ክርስቲያን ነኝ እያለ የክርስቲያን ኑሮ ባይኖር እምነቱ ከንቱና የማያድን እምነት እንደሆነ መድሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል፤ (ያዕ.2፡18-26)። እንዲሁም በማቴ.24፡13 «እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል» ይላል። 

እርግጥ ነው ሰው አንድ ጊዜ ከዳነ እስከ ፍዳሜ በእግዚአብሔር እንደሚጠበቅ መድሐፍ ቅዱስ ያስተምራል፤ (ፊል.1፡6፤ 1ኛ ተሰ.5፡23 እና 24)። ግን ይህ ተስፋ ያለው ሰው በታማኝ ሕይወቱ ተስፋውን ያረጋግጣል። ለዚህ ነው ሐዋርያው «ታገኙ ዘንድ ሩጡ» ያለው። የሮጠም ያልሮጠም በአንድነት የዘላለምን ክብር አይቀበሉም። ብዙዎች በውጭ የሚቆለፍባቸው ስላሉ «የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ» (ዕብ.10፡23 እና 24 2ኛ ጴጥ.1፡2-11 )። 

ሐዋርያው «ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ» ሲል የወንጌልን ስብከት ማለቱ ነው። የወንጌልም ስብከት ተስፋው የዘላለም ሕይወት ስለሆነ ሌሎች አግኝተውት እርሱ ሊያጣው የሚችለው ያው በወንጌል የተሰጠው ተስፋ ነው። የቃሉ ትርጉም ይህ ለመሆኑ ምዕራፍ 10 ስናጠና በተጨማሪ ይረጋግጣል። 

ጳውሎስ ሥጋዩን እየጎሰምሁ ብሎ ይናገራል። ይህን ሲል ልምጭ ይዞ ራሱን ይገርፋል ማለት አይደለም። ነገር ግን በነገር ሁሉ ሥጋውን አስተሳሰቡንና መንፈሱን ለጥሩ ነገር ያስገዛል ማለት ነው። ይህንንም የሚያደርገው ሁሉ ነገር በእርሱ ቁጥጥር ሥር ሆኖ ወንጌልን በሙሉ ኃይሉ ለማሰራጨት ሲል ነው። 

ጥያቄ 15. አንድ ክርስቲያን ወንጌልን በደንብ እንዳያስፋፋና ዘላለማዊውን የድል አክሊል እንዳያገኘ የሚያሳንፉ አንዳንድ ነገሮች ምንድናቸው?

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

2 thoughts on “1ኛ ቆሮ. 9፡24-27”

  1. ይህንን የመሰለ ተቃሚና ለሕይወታችን መድሐኒት የሆኔውን እንዲሁም ከሁም በላይ የሆነውን የከበረውን የእግዚአብሔር ቃል ስላካፈላችሁኝ ከልብ አመሰግናችሃለሁ ክብሩን ሁሉ እግዚአብሔር ጠቅልሎ ይውሰድ አሜኝ በርቱ በዚህ ብቻ እንዳታቆሙ ዘወትር ያገኛችሁን መረጃ አካፍሉን፡፡
    Best Regards
    Mulatu Eticha Guma
    Ministry of Agriculture, Natural Resource Management Directorate (NRMD) Watershed Case Team.
    Senior Land Use and Planning Expert GIZ SDR project Technical focal person at MoA.
    Telephone: 0116463080
    Mobile : 0921925018/0942429436
    E-mail: mulatueticha@gmail.com

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading