1ኛቆሮ. 10፡23-11፡1

ጥያቄ 7. በቁጥር 23 እና በ6፡12 መካከል ያለውን መመሳሰል ወይም መለያየት አስረዳ። 

ጥያቄ 8. በቁጥር 28 ላይ «ከሕሊና የተነሣ» ማለቱ ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 9. በቁጥር 33 ላይ ማሰናከል የሌለብን ስንት ወገኖች አሉ? 

ቁጥር 23 እና 24፡- በዚህ ቁጥር ላይ ያለው አነጋገር ከምዕራፍ 6፡12 ጋር ይመሳሰላል። በዚያ “ሁሉ ተፈቅዷል ሁሉ ግን አይጠቅምም” በማለት የክርስቲያንን ነፃነት በራስ ጥቅም ሲያጥር፥ በዚህ ጥቅስ ላይ ደግሞ “ሁሉ ተፈቅዷል ሁሉ ግን አያንጽም» በማለት የክርስቲያንን ነጻነት በወንድም ጥቅም ያጥራል፡፡ በዚያኛው ክፍል ክርስቲያን ለምንም ነገር መገዛት ስለሌለበት በዝሙት ቀንበር ሥር መዋል እንደሌለበት ሲያስተምር በዚህ ክፍል ደግሞ ክርስቲያን የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የወንድሙንም ጥቅም ማየት እንዳለበት ይነግረናል። 

ከቁጥር 25-28፡- የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጣዖት ምክንያት ከባድ ችግር እንደገጠማቸው ተመልክተናል። ያን ችግር ለመቋቋም እንዲችሉ አሁን መመሪያ ይሰጣቸዋል። በመጀመሪያ፡- ይህ በእግዚአብሔር ስም ነው ወይ የተሠዋው ብሎ ሳይጠይቅ አማኙ ከሥጋ ቤት የፈለገውን ነገር መግዛት ይችል ነበር። ሁለተኛ፡- ከማያምኑ ቤት ክርስቲያን ተጋብዞ ቢሄድ የቀረበለትን ይበላል እንጂ “ይህ ለጣዖት ተሠውቶ ነበር ወይ?” እያለ መመራመር አያስፈልገውም። እስካላወቀ ድረስ ለጣዖትም የተሠዋ ቢሆን መብላቱ አያረክሰውም። ሦስተኛ፡- ነገር ግን “ይህ ሥጋ ለጣዖት ተሠውቶ ነበር” ተብሎ ቢነገረው መብላት የለበትም። ይህም “ከሕሊና የተነሣነው”። የደካማ ክርስቲያን ወንድሙን ሕሊና ማለቱ ነው። እንግዲህ እርሱ በእውቀት ጎልምሶ የጣዖቱ ምግብ ሕሊናውን ባያረክሰውም የደካማ ወንድሙ ሕሊና ይረክስበታልና ከመብላት መጠበቅ አለበት። 

ለጣዖት የተሠዋ መሆኑን ባያውቅና ቢበላ የማይረክስበት ምክንያት ምግቡ በራሱ ከእግዚአብሔር የመጣ ስለሆነ ነው፤ “ምድርና በእርስዋ የሞላት ሁሉ የእግዚአብሔር ነውና”። ለጣዖት የተሠዋ ርኩስ የሆነበት ምክንያት ሰው በወሰደበት አርምጃ ነውና ያ እርምጃ እስካልታወቀ ድረስ ምግቡ እርኩስ አይሆንም። 

ቁጥር 29፡- «አርነቴ በሌላ ሰው ሕሊና የሚፈረድ እረ ስለ ምንድነው?» ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ አንድ ኃይል ያለው የሚመስለው ክርስቲያን ጠንካራው ክርስቲያን ሲበላ ካየ «ይሄ ክርስቲያን ሆኖ እንዴት ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ይበላል?» ብሎ በልቡ (በሕሊናው) ይፈርድበታል። በዚህም ሕሊናው በሌላ ሰው ሕሊና ፍርድ ላይ ወደቀ ማለት ነው። ስለዚህ ሐዋርያው ራስን በሌላ ሰው ሕሊና ፍርድ ሥር ያለ አግባብ ማስቀመጥ ጥሩ አለመሆኑን ይናገራል። 

ቁጥር 30፡- ሰው እግዚአብሔር የሰጠውን በረከት ሲጠቀምበት የሌሎችን “ስድብ” መጋበዘ የለበትም። በጸጋ የተሰጠንን በምስጋና ተቀብልን ከመብላታችን በፊት «ይህ እከሌን ያሰናክል ይሆን ወይ?» ብለን ማመዛዘን አለብን። 

ጥያቄ 10. በዛሬ ዘመን ክርስቲያኖች ስለነፃነት የተለያየ ሃሳብ አላቸው። ልዩነቱ በምን ዓይነት ነገሮች ላይ ነው? ብርቱ 

ክርስቲያን የትኛው ነው? ደካማውስ የትኛው ነው? 

በቁጥር 31-33፡- ላይ ሐዋርያው ነገሩን ወደ አጠቃላይ ነጥብ አምጥቶ የምንሠራውን ሁሉ ከሌሎች ጥቅም አንፃር በማመዛዘን እንጂ የራሳችንን ጥቅም ብቻ በማሰዳድ ለሰው ማሰናከያ እንዳንሆን መጠንቀቅ እንዳለብን ያስተምረናል። ጳውሎስ ሦስት ዋና ዋና ክፍፍሎችን ኣንደምሳሌ ተጠቅሟል። በመጀምሪያ፡- በሙሴ ሕግ ሥር የሚኖሩትን አይሁዳውያን፥ ሁለተኛ፡- በሙሴ ሕግ ሥር የማይኖሩትን ግሪኮች ወይም አሕዛቦች፥ ሦስተኛ፡- የአማኞች ማህበር የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን። ያለንን ነፃነት እንጠቀምበት ወይም አንጠቀምበት ብለን መወሰን ያለብን ከላይ በተጠቀሱት ምድቦች ወይም በሌሎች ምድቦች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በመገምገም ነው። ይህንንም በማድረገ ፍቅር እንዲገዛን አናደርጋለን። ይህንንም ለማድረግ የረሱን ምሳሌ ያስታውሳቸዋል፤ (9፡10-23)። ከሁሉም በላይ ሕይወታችንንና አረማመዳችንን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ አድርገን እርሱን ሊያስከብርና ሊያስደስት በሚችል መንገድ ለመሥራት መጣር አለብን፤ አበላላችንና አጠጣጣችንንም ቢሆን ለእርሱ ክብር እንዲውል ማድረግ አለብን። 

11፡1፡- ይህ ሌሎችን ለመጥቀም የመኖር እርምጃ ሐዋርያው በግሉ ያወጣው ሕግ ሳይሆን የጌታችን የራሱ አርአያ ነው፤ (ማር.10፡ 45)። ስለዚህ ክርስቲያን እንዲሁ አንደሐዋርያው የሌሎችን ጥቅም በማስቀደም እንደ ጌታ መሆን አለበት። በዚህ ስለክርስቲያን ነጻነት በምዕራፍ 8 የጀመረውን ትምህርት ይደመድማል። 

ጥያቄ 11. ሌሎች ክርስቲያኖች የማያደርጉትን፥ ነገር ግን እኔ በእግዚአብሔር ፊት ነጻ ነኝ ላደርገው እችላለሁ ብለህ የምታደርገው ነገር ምንድነው? ለእነርሱስ ስትል መብትህን የተውከው እንዴት ነው?

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d bloggers like this: