ጥያቄ 1. በቁጥር 14 ላይ ከጣዖት ሽሹ ያለው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጣዖት አምልኮ ችግር ነበረባቸው? ለመልስህ ማስረጃ ስጥ።
ጥያቄ 2. በቁጥር 16ና 17 ላይ ስለምን ገበታ ነው የሚናገረው?
ጥያቄ 3. በጣዖት ገበታ የመሳተፍ በደል ምንድነው?
ቁጥር 14፡- የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “ጣዖት ከንቱ ነው” በሚለው እውቀታቸው እየተመኩ በጣዖት ገበታ የመሳተፍ ዝንባሌ ነበራቸው፡፡ በዚያው አስታከው ደካሞች በልባቸው ጣዖትን ወደማምለክ ይሳባሉ። ይህን ለማስወገድ ጥብቅ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፤ ያም ከጣዖት መሸሸ።
ቁጥር 15፡- የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በአዋቂነታቸው ስለሚኮሩ ያንን የሚኮሩበትን እንዲጠቀሙበት ይመክራቸዋል። ከዚህ ጋር 2ኛ ቆሮ. 11፡19ን አስተያይ።
ቁጥር 16 እና 17፡- በዚህ ክፍል ሐዋርያው ስለ ጌታ እራት (ቅዱስ ቁርባን ) ጥልቅ ትምህርት ይሰጣል። ምንም እንኳ ሐተታ ባይበዛም የሚናገራቸው ቃላት በጣም ጥልቅ ትርጉም ያላቸው ናቸው። በቁጥር 16 ላይ ለቅዱስ ቁርባን የሚቀርበውን ጽዋና ሕብስት እንደምንባርክው ይናገራል። መባረክ ማለት ተራ የሆነውን ጽዋና ሕብስት ለዚህ ለተቀደሰ ተግባር በጸሎት ለእግዚአብሔር መስጠት ማለት ነው። ከዚህ ጋር 1ኛ ጢሞ. 4፡5ን ስናስተያይ “ሁሉም ምግባችን በጸሎት የተባረከ ነው” እንል ይሆናል። አዎ ሁለቱም ያው በጸሎት ይባረካሉ፤ ነገር ግን ይህ ሕብስትና ጽዋ የሚባረኩት ለተራ ማዕድ ሳይሆን ለተለየ ዓላማ ነው።
ይህ ጽዋና ሕብስት ከክርስቶስ ደምና ሥጋ ጋር ሕብረት እንዳለው ይናገራል። ይህ ሕብረት እንዳለ አያከራክርም፤ ግን ምን ዓይነት ሕብረት ነው ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ መልሶች ስለሚሰጡ በዚህ መልስ ላይ ብዙ ክርክር አለ። በክርስትና ዓለም ውስጥ ሦስት ዓይነት መልሶች ይሰጣሉ፤ እዚህንም በየተራ እንመልከታቸው።
1ኛ. በሥጋ ሕብረት፡- ይህ ትምህርት ሕብስቱና ወይኑ በጸሎት ፍጹም የክርስቶስ ሥጋ ፍጹም የክርስቶስ ደም ሆኖ ይቀየራል ይላል። ይህ ትምህርት ከመድሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የሌለው ነው። ሕብስቱና ወይኑ ፍጹም የክርስቶስ አካል ሆነው ከተቀየሩ የምንቆርሰው እንግዲህ ምሳሌው ሳይሆን እርሱ ራሱ ነው፤ ይህም ከሆነ በየጊዜው በመቆረስ በተደጋጋሚ ይሠዋል ማለት ነው። ክርስቶስ አንድ ጊዜ ብቻ በመሠዋት ሕዝቡን ስለቀደሰ ደጋግሞ አይሠዋም፤ (ዕብ.9፡25 እና 26)። ስለዚህ ይህ ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ነው ማለት አለብን።
ጥያቄ 4. እንደዚህ ዓይነት እምነት ያላቸው በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ? ካላወቅህ የካቶሊክ ወይም የኦርቶዶክስ አማኞችን ስለ ቅዱስ ቁርባን ያላቸውን እምነት ጠይቅ።
2ኛ. የመታሰቢያ ሕብረት፡- በሚቀርበው ሕብስትና ወይን እንዲሁም በክርስቶስ ሥጋና ደም መካከል ምንም ግንኙነት የለም። ግንኙነቱ ምሳሌያዊ የሆነ የመታሰቢያ ሥርዓት ብቻ ነው። ይህ ግን የመጀመሪያውን ስሕተት ለማስወገድ ከመጠን በላይ የሸሸ ይመስላል። ዝምድናው የመታሰቢያ ቢሆን ኖሮ እንዴት ሐዋርያው ጽዋውና ሕብስቱ ከክርስቶስ ጋር ሕብረት አላቸው ይላል?
3ኛ. መንፈሳዊ ሕብረት፡- በሕብስቱ፣ በጽዋውና በክርስቶስ መካከል መንፈሳዊ ሕብረት አለ። ይህም ሕብረት ከሕብስቱ-ጽዋው የሚካፈሉት ከክርስቶስ እንደሚካፈሉ ያመለክታል። ይህም ሕብረት መንፈሳዊ ስለሆነ የምንካፈለውም በእምነት እንጂ በሥጋ አይደለም። አፋችን ሕብስቱን ሲበላ መንፈሳችን ደግሞ ክርስቶስን በእምነት ይመገባል። በዚህ ሕብስትና ጽዋ አማካይነት በእምነት ክርስቶስ በመንፈሳዊ ዓይናቻችን ፊት ይቀርባል፤ በእምነት እንድንቀበለውም ይጋብዘናል። ይህ እንደዚህ ያለው ከክርስቶስ ጋር ሕብረት አማኛችንም ያስተባብራል። በቁጥር 17 ላይ የሚናገረው ይህንኑ ነው። በቅዱስ ቁርባን በኩል አንድነትን ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር እንመሠርታለን።
ጥያቄ 5. ስለ ቅዱስ ቁርባን ቤተ ክርስቲያንህ ከሦስቱ ሃሳቦች የትኛውን ነው የምትደግፈው? ለምን?
ቁጥር 18፡- ይህን ሕብረት ከብሉይ ኪዳን መሥዋዕት ጋር በማመሳሰል ያስተምራል። ሆኖም ስለ መሥዋዕት ከብሉይ ኪዳን የጠቀሰው ቅዱስ ቁርባንም መሥዋዕት ነው ብሎ ለማስተማር እንዳልሆነ ማስተዋል አለብን። የማይሆንበትም በአዲስ ኪዳን ክርስቶስ አንድ ጊዜ ብቻ ስለተሠዋ ሌላ መሥዋዕት በምሳሌም መልክ እንኳ ቢሆን አይቀርብም፤ (ዕብ.9፡25 እና 26)። ሐዋርያው የብሉይ ኪዳንን መሥዋዕት የጠቀሰው ከመሥዋዕቱ የሚበሉ ከመሠውያው ጋር ሕብረት አላቸው ለማለት ብቻ ነው። ይህም የሆነው በመሠውያውና በመሥዋዕቱ መካከል ሕብረት ስላለ ነው። እንዲሁም በክርስቶስና በቅዱስ ቁርባን መካከል ሕብረት ስላለ ከቅዱስ ቁርባን የሚሳተፉም ከክርስቶስ ጋር ሕብረት አላቸው።
ቁጥር 19 እና 20፡- በዚህ ክፍል ሐዋርያው ወደ መሠረታዊ ነጥቡ ይመለሳል። ጣዖት ከንቱ ነው ማለት ለጣዖት የሚሠዋም እንዲሁ ከንቱ ነው ማለት አይደለም። ሰው ለጣዖት የተሠዋውን በሚበላበት ወቅት ከጣዖት ጋር ዝምድናን ይፈጥራል። ይህም ዝምድና ከከንቱ ነገር ጋር ሳይሆን ከአጋንንት ጋር ነው። አሕዛብ በጣዖት አምልኮኣቸው የሚሠውት ለአጋንንት ነውና። ስለዚህ ክርስቲያን ለጣዖት የተሰዋን በመመገብ ከአጋንንት ጋር ሕብረት ሊመሠርት አይገባውም። ክርስቲያን ከጣዖት መሽሽ አለበት።
ቁጥር 21 እና 22፡- ሰው የጌታ ከሆነ ከአጋንንት ጽዋ ፈጽሞ መራቅ አለበት። በምንም ምክንያት “ጣዖት ከንቱ ነው” በሚለው እውቀቱ እየተመካ ከሰይጣን ጋር ማህበረተኝነትን ሊፈጥር አይገባውም። ይህንንም ማድረግ እግዚአብሔርን በባዕድ አምልኮ ማስቀናትና ራስን በታላቅ ፍርድ ላይ መጣል ነው። ስለዚህም አደጋ ሐዋርያው በዚሁ ምዕራፍ ከ1-13 ባለው ክፍል ውስጥ አስተምሮአል።
ጥያቄ 6. በእኛ ዘመን ከሰይጣን ጋር ሕብረት እንዳናሳይ መሽሽ የሚገባን ነገሮች አሉ? ምን ምንድናቸው? ምክንያቱን አብራራ።
(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)