1ኛ ቆሮ. 11፡17-26

ጥያቄ 17. በቁጥር 18 ላይ መለያየት በመካከላቸው እንደነበር ሐዋርያው ይናገራል፤ ያ መለያየት ምን ዓይነት ነበር? 

ጥያቄ 18. በቁጥር 19 ላይ ወገኖች ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 19. በቁጥር 20 ላይ “የምትበሉት የጌታ እራት አይደለም” ካለ በኋላ ከቁጥር 23-26 መምሪያ ይሰጣል፤ በሁለቱ መካከል ያለውን ዝምድና አስረዳ። 

ቁጥር 17፡- ጉባኤያቸው ደስ የማይልና የማይገቡ ነገሮች የሚካሄዱበት እንደሆነ ይናገራል። ይህ ሥነ ሥርዓት መጉደል በሴቶች በኩል ብቻ ሳይሆን በቅዱስ ቁርባን ሥርዓት እንደሆነ እናያለን። ይህን ትእዛዝ ሊሰጥ ሲል የሚከተለውን ስለቅዱስ ቁርባን ምምሪያ ማለቱ ነው። 

ቁጥር 18፡- መለያየት በመካከላቸው እንደነበር ሰምቷል፡፡ ይህ መለያየት በመሪዎች የተነሳ ተፈጥሮ እንደነበርም ከዚህ በፊት በምዕራፍ አንድ ተመልክተናል። ያሁኑ ግን በቅዱስ ቁርባን የተነሳ ነው። የሰማውን ወሬ አምኖታል። 

ቁጥር 19፡- መለያየት በሚፈጠርበት ጊዜ አንድ ስህተት ተፈጥሮ ስለሆነ ብዙዉን ጊዜ መለያየቱ ያን ስህተት በፈጠሩትና ያን ስህተት በተቃወሙት መካከል ስለሚሆን አንዱ ወገን ሲመሰገን አጥፊው ወገን ደገዋ ሲነቀፍ ይገኛል። እንዲሁም በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መለያየት ውስጥ የተፈጸመው ይኸው ነበር «የተፈተኑ አንዲገለጡ» ማለት በትግል ውስጥ እንደወርቅ ተፈትነው ፈተናውን ያለፉ እንዲገለጡ ማለት ነው። 

ከቁጥር 20-22፡- በዚህ ክፍል በቆርንቶስ ቤተ ክርስቲያን ይፈጸም የነበረውን ስህተት ያብራራል፡፡ በጉባኤያቸው ጊዜ የጌታ እራት ብለው የሚያካሂዱት መልኩን ቀይሮ የጌታ እራት መሆኑ ቀርቶ ሌላ ነገር ሆኖአል፤ «አብራችሁ ስትሰበሰቡ የምትበሉት የጌታ እራት አይደለም»። ይህም የሆነበት ሀብታምና ድሃ የሚለያዩበት ገበታ ነበር። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የጌታን እራት ታክብር የነበረው በህብስትና በወይን ብቻ አልነበረም። በአንድነት ሆነው ምግባቸውን የሚመገቡበትና እርስ በርሳቸውም የሚተሳሰቡበት ጊዜ ነበር። እንደሚመስለውም የራሳቸውን ምግብ እያመጡ በአንድነት ይበሉ ነበር፡፡ ሀብታሞቹ ብዙ ምግብ ሲያመጡ ድሆቹ ግን ጥቂት ያመጡ ነበር። ሀብታሙ ያመጣውን ለድሃው ወንድሙ ሳያካፍል ለብቻው ይበላ ስለነበር አርሱ ይጠገባል፤ እንዲያውም ይሰክራል፤ ድሃው ግን ተርቦ ይቀራል። ይህ እርምጃ የእግዚአብሔርን ማኅበር የመናቅ እርምጃ መሆኑን ሐዋርያው ያስረዳቸዋል። ያለው ከሌለው ጋር አብሮ በመካፈል የነበረውን የሀብታምና የድሃ ልዩነት በቅዱስ ቁርባን ገበታ እንኳ እንደማስወገድ፥ የቅዱስ ቁርባን ጊዜ ድሃው በድኅነቱ የሚጋለጥበት ወቅት ሆነ። የጌታን እራት እንደ ድገሥ ቀን ከማየት ፋንታ ሁሉም በየቤቱ እየበላ ቢመጣ ይሻል ነበር። 

ከቁጥር 25-26፡- በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ይካሄድ የነበረውን ነቅፎ ትክክለኛውን ሥነ ሥርዓት ይተካላቸዋል፡፡ ቅዱስ ቁርባን የተመሠረተው በራሱ በጌታችን ሲሆን ወቅቱም አልፎ የተሰጠበት ምሽት ነበር። ይህ በዚህ ሐዘን በሞላበት ወቅት የተመሠረተውን ገበታ ክርስቲያኖች በመፈቃቀርና ጌታ የደረሰበትን ግፍ በማስታወስ ሊፈጽሙት ሲገባ እነርሱ ራሳቸው ግፍ የመፈጸሚያና ድሆችን የማንገዋለያ ወቅት አደረጉት፤ በዚህ ምክንያት የጌታን እራት በተገቢው መንገድ በንጹህ ልቦና አላከበሩትም። 

«ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው።» አንዳንዶች በዚህ አነጋገር ላይ ተመርኩዘው በቅዱስ ቁርባን ጊዜ የሚቀርበውን ሕብስት “ፍጹም የጌታ ሥጋ ነው” ብለው ብዙ የተሳሳተ የባዕድ አምልኮት አስተሳሰብ በቅዱስ ቁርባን ሥነ ሥርዓት ውስጥ አሹልከው አስገብተዋል። ጌታ ግን ይህ ሥጋዩን የሚያመለክተው የሥጋዩ ምሳሌ ነው ማለቱ ነው። ካለበለዚያ የእነዚህን ሰዎች ስሕተት ከተቀበልን ጌታን በየጊዜው እየደጋገምን ሥጋውን እንቆርሳለን ማለት ነው። ይህ ከሆነ ጌታ ሁልጊዜ በመደጋገም ይሠዋል ማለት ነው። ግን ይህ አንዳልሆነ ከዚህ በፊት በተሰጠው ትምህርት አይተናል፤ (ዕብ.9፡25 እና 26)። 

«ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት» ይህን ቃል ከ10፡16 ጋር አስተያይተን መተርጐም አለብን። ዓላማው ለመታሰቢያ ይሁን እንጂ የመታሰቢያው አራት ከጌታ ጋር ሕብረት ያለው ነው። ይህን ከጌታ ጋር ሕብረት ያለውን ሥርዓት ለጌታ መታሰቢያ እንድናደርገው ታዘናል። ይህ ሥነ ሥርዓት ጌታንና ሥቃዩን ያስታውሰናል። 

«በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው»፡፡ ጌታ መጥቶ አዲስ ኪዳን መሠረተ፤ (ኤር.31፡31-34፤ ዕብ.8፡8-31)። በፊተኛው ቃል ኪዳን አልጸኑም፤ (ዘፀአት ምዕራፍ 24)። አሁን በአዲሱ ኪዳን በክርስቶስ ሞት በኩል የኃጢአት ይቅርታና የመንፈስ ቅዱስ መሰጠት ስላለ የቃል ኪዳኑ ተቀባዮች በቃል ኪዳኑ እንዲጸኑ ተደርገዋል። በዚህ ሥርዓት አማካይነት ክርስቲያኖች የጌታን ሞት ያውጃሉ። 

ጥያቄ 20. ለጌታ እራት ሳንዘጋጅ መጥተን፥ ለጌታ ክብር በማይሰጥ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው በእንዴት ዓይነት ሁኔታ ነው?  ልናከብረውስ የምንችለው በእንዴት ዓይነት ሁኔታ ነው? 

የጌታን እራት እንደ ድግስ ቀን ከማየት ፈንታ ሁሉም በየቤቱ እየበላ ቢመጣ ይሻል ነበር። በዚህ ምክንያት የጌታን እራት በተገቢው መንገድ በንጹህ ልቦና ስላላከበሩት የጌታን እራት አክብረዋል ብለን ልንል አንችልም።

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d bloggers like this: