ጥያቄ 12. በቁጥር 2 ላይ ወግ ሲል ምን ማለቱ ነው?
ጥያቄ 13. እግዚአብሔር የክርስቶስ ራስ ነው ያለውን፣ የክርስቶስን አምላክነት በማሰብ ማብራሪያ ስጥ።
ጥያቄ 14. ቁጥር 5 ላይ ሴት በጉባኤ እንደምትተነብይና እንደትጸልይ ሲናገር ይህን ክፍል ከ1ኛ ቆሮ. 14፡34 እና 35 ጋር እንዴት እናስታርቀዋለን? በተጨማሪም 1ኛ ጢሞ.2፡11-12ን ተመልከት።
ጥያቄ 15. የሴት መከናነብ ወይም ረዥም ፀጉርዋ የምን ምልክት ነው?
ጥያቄ 16. ወንድ የሴት ራስ ነው የሚለውን ከገላ.3፡28 ጋር በማወዳደር አስታራቂ ሃሳብ ጻፍ።
በቁጥር 2 ላይ ወግ የሚለው አነጋገር ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠ የሐዋርያት ትምህርት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ እኛ አንደለን ቤተ ክርስቲያን የሃዋርያት ትምህርት በድሑፍ ውሎ ገና አልተሰጣትም ነበር። በቃል ይዛመት ስለነበር ወግ ተሳለ። አሁን ግን የሐዋርያት ትምህርት በድሑፍ ውሎ በመድሐፍ ቅዱስ ስለቀረበልን በቃል በሚተላላፍ ወግ አንገዛም፤ በድሑፍ ላይ በዋለው በሐዋርያት ትምህርት እንጂ።
የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር ነው ሲል ክርስቶስ በሰውነቱ የባሪያን መልክ ይዞ ስለመጣ በሰውነቱ የአብ ዝቅተኛ ሆነ። ወንድ ሴትት ራስ ነው ሲል አብ የክርስቶስ ራስ እንደሆነ በዚያው መንገድ ወንድም የሴት ራስ ነው ማለት አይደለም። ሦስት ደረጃዎች ተሰይመዋል፤ ግን ሦስቱም የተለያየ ትርጉም አላቸው፡፡ ምንም እንኳ ወንድ የሴት ራስ ይሁን እንጂ ወንድና ሴት በእግዚአብሔር ፊት እኩል ናቸው፤ (ቁጥር 12፤ ገላ.3፡28)። ስለዚህ ይህ ራስነት በተወሰነ መንገድ የአገልግሎት ወይም የአስተዳዳር ቅደም ተከተል ብቻ ነው።
እንዲሁም ክርስቶስ የአብ ዘቅተኛ ነው በሚለው ደረጃ አይደለም ወንድ የክርስቶስ ዝቅተኛ የሆነው። ክርስቶስ በአንድ በኩል የአብ እኩያ ነው፤ ወንድ ግን በምንም ዓይነት የክርስቶስ እኩያ አይሆንም። ስለዚህ እነዚህን ቅደም ተከተሉኝ በየአኳያቸው መመልከት አለብን እንጂ ማደባለቅ የለብንም።
የአዘጋጁ ማስታወሻ
ስለ የበላይነት በሚናገርበት ጊዜ፥ ጳውሎስ የሚናገረው ስለ ሥልጣን ነው እንጂ እኩልነታቸውን በተመለከተ አይደለም። ጳውሎስ ሦስት ግንኙነቶችን በዝርዝር ይድፋል።
አንደኛ፡- የእግዚአብሔር አብንና የእግዚአብሔር ወልድን ግንኙነት በተመለከተ ነው። ምንም እንኳን ሁለቱም እኩል እግዚአብሔር ቢሆኑም ወልድ ራሱን በአብ ሥልጣን ሥር አስገዝቷል። (ለምሳሌ፡ ዮሐ.5፡19-44)። እዚህ ላይ ያልተጠቀሰው ሌላ ነገር ደግሞ፥ እግዚአብሔር ወልድ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለው ግንኙነት ነው፤ እርሱም የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፡፡ (ለምሳሌ፡- ኤፌ 1፡22-23፤ 4፡15-16)።
ሁለተኛ፡- እግዚአብሔር በሰው ላይ ሙሉ ሥልጣን አለው። ምንም እንኳን እግዚአብሔር ወልድና ሰው በማንነታቸው የተለያዩ ቢሆኑም ሰው ለእግዚአብሔር ወልድ ሁለንተናውን አስገዝቶ ታማኝነቱን መግለድ ይኖርበታል።
ሦስተኛ፡- በወንድና በሴት መካከል ያለው ግንኙነት ነው። በፍጥረታቸው ወንድና ሴት ለእግዚአብሔር እኩል ናቸው። በእግዚአብሔር ፍጥረት ውስጥ ግን በቤቱ ላይ ያለው ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው ለወንዱ ነው።
አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህንን እንደሥልጣን ሳይሆን እንደ ክብር ነው የሚመለከቱት። ኢየሱስ እግዚአብሔርን እንዳከበረው ሁሉ፥ ሰው ኢየሱስን ማክበር አለበት፤ ሴቲቱም ባልዋን ማክበር አለባት ይላሉ።
ከሁለቱ አመለካከቶች ውስጥ የትኛውንም የምንደግፍ ቢህን ጳውሎስ የሚለው ባልየው ይህንን ሥልጣኑን በመጠቀም ሴትየዋ ላይ ችግር አይፍጠር ነው። እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሥልጣን በፍቅር፥ በትዕግሥትና በሩኅሩኅነት ሊታገዝ የሚገባው ሥልጣን ምሳሌ ነው። በኢየሱስና በእግዚአብሔር አብ መካከል ያለውን ግንኙነት፥ በሰውና በኢየሱስ መካከል ያለውን ግንኙነት እንደ ምሳሌ በማቅረብ ነው ወንድ ያለውን ሥልጣን በግልጽ የሚያሳየን። እዚህ ላይ የምንመለከተው አንድ ጌታ በባሪያው ላይ ያለውን ዓይነት ሥልጣን አይደለም። መከናነብ የሴት ከወንድ ሥር የመሆን ምልክት ነው። ይህን ለወንድ ተገዥነትዋን በመከናነብ ወይም ፀጉሯን በትከሻዋ ላይ እንዲንዘረፈፍ በማድረግ መግለጥ ነበረባት።
የአዘጋጁ ማስታወሻ
በጳውሎስ ዘመን እንደ ባሕል ሆኖ አንድ ሴት ባልዋ በአርሷ ላይ ያለውን ሥልጣን እንደምታምንበትና እንደምትቀበለው ታሳይ የነበረው በመከናነብና ፀጉሯን በማሳደግ ነበር ብለው ብዙ ክርስቲያኖች ይገምታሉ። ፀጉርን ሳይከናነቡ ማምለክ ይታይ የነበረው እንደአመጽና እንደ መጥፎ የአስተዳደገ ደረጃ ነበር። ሴተኛ አዳሪዎች ብዙውን ጊዜ ፀጉራቸውን ይላጩት ነበር። ሴቲቱ አመፃን ካስነሣች እንደ ሴተኛ አዳሪ ደረጃዋን እንዳሳነሰች ይቆጠራል ብሎ ነው እዚህ ላይ ጳውሎስ የሚያስጠነቅቀው። ስለዚህም ለእኛ ዛሬ ዋነኛው ትምህርት ራስን መከናነብ ወይም ፀጉርን ማስረዘም ሳይሆን ባሕሏን በማይቃረን ሁኔታ ሁለንተናዋን ለባልዋ መስጠቷንና እርሱን ማክበሯን ማረጋገጡ ነው ዋና ነገር ይላሉ። (ለምሳሌ፡- በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ በመንገድ ላይ ሰትዬዋ ከባልየው በስተኋላ ነው የምትሄዳው። )
በቁጥር 5 ላይ በጉባኤ የምትጸልይና የምትተነብይ ሴት እንዳለች አስመስሉ እንዲያው ለሃሳብ መንደርደሪያ ያህል ብቻ ይጠቅሳል። ይህን አነጋገሩን ይዘን “ሴት በጉባኤ መጸለይና መተንበይ ትችላለች” ማለት አንችልም። ምክንያቱም በምዕራፍ 11 ቁጥር 34 እና 35 ላይ ሴት በጉባኤ መካከል ዝም እንድትል ያዛል።
በዚህ ክፍል የተናገረው በ1ኛ ቆሮ. 14፡34 እና 35 እንዲሁ በ1ኛ ጢሞ.2፡11-14 ባሉት መተርጎም አለበት፡፡ በዚህ ክፍል ራሷን ሳትሸፍን የምትጸልይ ወይም የምትተነብይ ሲል ትተንብይ ወይም ትጸልይ ማለቱ አይደለም፤ ምክንያቱም ይህን እንዳታደርግ ክላይ በተጠቀሱት የመድሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከልክሏታል። የሴቶች በጉባኤ መናገር በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥነ ሥርዓት አሳጥቶ ስለነበር ሐዋርያው ያን ተግሣድ በዚህ በቁጥር 5 ላይ ሳይሆን በ 14፡34 እና 35 ላይ ያስረዳል።
ይህ ትምህርት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አጥቷል፤ ይህ የሆነበት ምክንያት የሐዋርያው ቃል ግልጽነት ጎድሉት ሳይሆን ሰዎች በራሳቸው ሃሳብ ላይ ተመርኩዘው የእግዚአብሔርን ቃል መቀበል ስለተሳናቸው ነው። ነገር ግን እንዲህ የሐዋርያውን ትምህርት አለመቀበል ሐዋርያውን አንዳስቆጣው በ14፡34-38 ላይ እናነባለን። እንግዲህ የሴቶች አስተማሪዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሰለፉ ከሐዋርያው ትምህርት እንዳፈነገጡ መገንዘብና ይህን ስሕተት ማረም አለብን። ይህ እግዚአብሔር የሰጠን መመሪያ ነው እንጂ አንዳንዶች እንዳጣመሙት ወንዶች በሴቶች ላይ የሰነዘሩት ጭቆና አይደለም። እግዚአብሔር የከለከላትን ለሴት ይሰጥ ማለት በሰው ጥበብ ሴትን የሚያክብር እርምጃ ይመስላል፤ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ግን ሴትን የሚያዋርድ እንደሆነ ይናገራል። የሴት ክብር በእግዚአብሔር ቃል ላይ ማመጽ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ቃል ተገዥ መሆን ነው።
ይህንንም በሐዋርያው ዘመን በነበረው ባህል ራሷን በመከናነብ ታሳይ ነበር፤ ምልክቱ ያ ነበርና። አሁን ግን በባህላችን መከናነብ የዚያ ምልክት ስላልሆነ ከመከናነብ ነፃ ናት፤ ግን ከወንድ ሥልጣን ሥር መሆንና በቤተ ክርስቲያን ጉባኤ መካከል ጸጥ ማለት በፈጣሪ የተሰጠ ሥርዓት ነው እንጂ የባህል ጉዳይ አይደለም። ይህንንም በትህትና መቀበል የሴት ክብር ነው፤ ማመጽ ግን ውርዳቷ ነው፤ (ቁጥር 5 የመጨረሻውን ዐረፍተ ነገር ተመልከት )።
የአዘጋጁ ማስታወሻ
የዚህ መጽሐፍ ፀሐፊ ምንም እንኳ ራስን የመከናነቡ ነገር በጳውሎስ ዘመን የነበረ ልማድ ቢሆንም ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጭራሽ መናገር እንደሌለባቸው ያምናል። ያም ሆነ ይህ ብዙ መድሐፍ ቅዱስን የሚከተሉ ክርስቲያኖች ይህንን ክፍል በሚከተሉት ዓይነት አተረጓጕዋች ይተረጉሙታል።
የተወሰኑ ነሮችን ካሟሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሴቶች በጉባዔ መካከል የመጸለይና የመተንበይ (የእግዚአብሔርን ቃል በሕዝብ ፊት የመናገር) አገልግሎት ሊኖራቸው ይችላል ብለው ያስባሉ። ለጳውሎስ የሚያሟሉት ራሳቸውን መከናነቡ ነበር። ለምን ራሳቸውን መከናነቡ ዋና ነገር ሆነ? ምንም እንኳ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሴቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ ራሳቸውን መከናነብ አለባቸው ብለው ቢያምኑም ብዙዎች ግን ይህ አክብሮትን ለማሳየት በጳውሎስ ዘመን ይደረግ የነበረ ባሕላዊ ልማድ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ (ለምሳሌ በሙስሊሞች ዘንድ ይህ የተለመደ ነው፡፡) በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኘውን ጽሑፍ በተመለከተ ሁለት የተለያዩ አስተሳሰቦች ተሠንዝረዋል።
ሀ. አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደሚሉት ከሆነ በመድሐፍ ቅዱስ ሊናገረው የፈለገው አንድ ሴት በሽማገሌዎችና በባልዋ ሥልጣን ሥር መሆን እንደሚገባት ነው። እነዚህ ሰዎች አንዲት ሴት ባሕላዊ በሆነ መንገድ በቤተ ክርስቲያን መሪዎችና በባልዋ ሥልጣን ሥር መሆኗን ካሳየች ዛሬ በቤተ ክርስቲያን መፀለይና ትንቢት መናገር እንደምትችል ይናገራሉ። ምንም እንኳን አንዳንዶች ራሷን ምከናነቧን እንደ ትልቅ ነገር ቢያዩትም፥ ሌሎች ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሥልጣን ሥር ራስዋን ማስገዛትዋን ማየት እንደሚገባን ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህንን ክፍል ሲተረጉሙ፡- «አንዲት ሴት እንድትጸልይ ወይም እንድትናገር በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከተፈቀዳላት ልታደርገው ትችላለች፤ ምክንያቱም በሽማገሌዎቹ ሥልጣን ሥር ሆና ስለምታደርገው ነው። ይህንን ስታዳርግም የሸማገሌዎቹን ሥልጣን ለመቀናቀን ብላ አይደለም» ይላሉ።
ለ. ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ ትኩረት የተሰጠው አንድ ሴት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በምትናገርበት ጊዜ ስለሚኖራት ጨዋነት (ሥነ ሥርዓት ) ነው ይላሉ። እነዚህ ሰዎች አንዲት ሴት ጨዋነቷን ሳትጠብቅ ለሌሎች መዘበቻ እስካልሆነች ድረስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መናገር ትችላለች ብለው ያምናሉ። ራስ የመከናነቡ ነገር በጳውሎስ ዘመን ብዙ ሰዎች የሚያደርጉት ነገር ስለነበር አንዲት ሴት ያንን ሳታደርገ በሕዝብ ፊት ለመናገር መውጣቷ ጨዋነቷን እንዳልጠበቀች ያሳያል። እነዚህ ሰዎች ጳውሎስ «አንዲት ሴት ራሷን ከተከናነበች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጸለይ ወይም ትንቢት መናገር ትችላለች» ነው የሚለው ብለው ያምናሉ። ስለዚህ እነዚዚህ ክርስቲያናኖች ዛሬም ቢሆን በዚህ ክፍል መሠረት አንዲት ሴት በጨዎነት ከለበሰች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሕዝብ ፊት ቆማ መጸለይም ሆነ ትንቢት መናገር ትችላለች ይላሉ፡፡
የትኛውንም አመለካከት ብንመርጥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሴቶች ብዙ ኃላፊነትን ይዘው መሥራታቸውን መዘንጋት የለብንም። ለምሳሌ፡- ሁለት ነቢይ የነበሩ ሴት ልጆች ስለበሩት ፊሊጶስ ስለሚባል ሰው እናነባለን። በሌላ ቦታ ደግሞ እግዚአብሔር ጵርስቅላ የምትባልን ሴት በመጠቀም አጵሎስን እንዳስተማረው እናያለን። ግልጽ ያልሆኑ የመድሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በማየት የሴቶችን አገልግሎት ውስን እንዳናደርገው መጠንቀቅ አለብን። ምንም እንኳን ሰቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲሰብኩ ባይፈቀድላቸውም ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ግን የእግዚአብሔርን ቃል ማስተማር ይችላሉ።
በቁጥር 6 ላይ ሴት ለወንድ ታዛዥ ለመሆንዋ ምልክት ባታዳርግ ራስዋን እንደተላጨች ይቆጠራል ማለቱ ነው። ይህን እንደ አማራጭ ማቅረቡ ሳይሆን ያለመከናነብን ውጤት ማስረዳቱ ነው።
በቁጥር 10 ላይ ስለ መላእክት ማለቱ ቅዱሳን ለአምልኮት ሲሰበሰቡ መላእክትም ተመልካች ሆነው ይቀርባሉና ሴት ክብርዋን ጠብቃ መገኘት አለባት ማለቱ ነው፡፡ “በራስዋ ሥልጣን ሊኖራት ይገባል” ሲል አዲስ ሃሳብ መስጠቱ አይደለም፤ ግን ሴት የወንድ ተገዥ ሆና ትቅረብ ማለቱ ነው። በራስዋ ላይ ሲል በጭንቅላቷ ላይ ማለቱ ነው። ከወንድ ሥልጣን ሥር መሆንዋን የሚያመላክተውን የሪስ ሽፋን አድርጋ ትቅረብ።
ይህን የሴትን ለወንድ ተገዥነት በተፈጥሮ ሴት ከወንድ ታንሳለች ወደ ማለት ትርጉም እንዳይወሰድ ሐዋርያው ሴትና ወንድ በእግዚአብሔር ፊት እኩል እንደሆኑና አንዱ ያለ ሌላው እንደማይሆን ይናገራል፤ (ቁጥር 12)። ከዚህም ጋር ገላ.3፡28 ይስማማል።
(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)