1ኛ ቆሮ. 12፡ 1-11

በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጉባኤያቸው ብዙ ስሕተቶች ነበሩ። እስከአሁን እንኳ ሁለት ስሕተቶችን ሐዋርያው እንዳረመላቸው አይተናል፤ እነርሱም ስለ ሴቶችና ስለቅዱስ ቁርባን ነበሩ። አሁን በዚህ ምዕራፍ ስለመንፈሳዊ ሥጦታዎች ይፈጽሙ የነበሩትን ስሕተቶች ያርምላቸዋል። ይህ የመንፈሳዊ ሥጦታ ጉዳይ በዘመናችንም አከራካሪ ሆኖ ስለመጣ የሐዋርያውን መምሪያ በጥንቃቄ በመመልከት የእኛንም ስሕተት በቃሉ መሠረት ማረም ይኖርብናል። 

ጥያቄ 6. የመንፈሳዊ ሥጦታዎች ዋና ዓላማ ምንድነው? 

ጥያቄ 7. ከቁጥር 8-10 ውስጥ ስንት መንፈሳዊ ሥጦታዎች ተዘርዝረዋል? 

ጥያቄ 8. እነዚህ ሥጦታዎች ለምን ያህል አማኞች ነው የተሰጡት? 

በቁጥር 1 ላይ፡- «ስለመንፈሳዊ ነገርም» ሲል የቆሮንቶስ ሰዎች ከጠየቋቸው ጥያቄዎች አንዱ ይህ አንደነበር ያመለክታል። 

ቁጥር 2፡- «አህዛብ ሳላችሁ» ከማመናቸው በፊት በተለያዩ የጣዖት አምልኮዎች ያለ አእምሮ ይነዱ ነበር። ጣዖት አእምሮን ያደነዝዛል። አሁን ግን በአእምሮ መጎልመስና በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን የሕያው አምላክ ተከታዮች ሆነዋል። በጣዖት ሥር በነበሩ ጊዜ ብዙ ነገሮችን ከቁጥጥራቸው ውጭ በሰይጣን አስገዳጅነት ይፈጽሙ ነበር። አሁን ግን በመንፈስ ቅዱስ ሲመሩ አእምሮአቸውን ሳይለቁ በልባቸው መንፈስ ቅዱስ ያስተማራቸውን ረጋ ባለ መንፈስ ይናገራሉ በፈቃዳቸው ይናገራሉ፡፡ 

ጥያቄ 9. ከማመንህ በፊትና ካመንህ በኋላ በሕይወትህ ምን ዓይነት ለውጥ ታይቶአል? 

ቁጥር 3፡- ይህ እርግማን ወይም እውቀት እንዲሁ በቸልተኝነት የሚሠነዘረውን ሳይሆን ከልብ የመነጨ አነጋገርን ያመለክታል። ሰው በመንፈስ ቅዱስ ካልተመራ በስተቀር የኢየሱስን ማንነት ማወቅ አይችልም፤ (1ኛ ቆሮ.2፡6-13)። እንዲሁ ሰው በአጋንንት መንፈስ ተወስዶ ኢየሱስን ሊረገም ይችላል። 

ስለ ጸጋ ሥጦታዎች መወያየት ይጀምራል። ከቁጥር 4 እስከ 7 ድረስ ስለዚህ ነገር ያብራራል። የጸጋ ሥጦታዎች ሥላሴን ያመለክታሉ፤ ሥጦታዎችን እንደፈቃዱ ለእያንዳንዱ አማኝ የሚያድል መንፈስ ቅዱስ ነውና ብዙ ሥጦታዎች በአንዱ መንፈስ ይሰጣሉ፡፡ የሥጦታዎቹም ዓላማ ጌታ ኢየሱስን ለማክበር ስለሆነ ብዙ ቢሆኑም አንድ ዓላማ አላቸው። የሥጦታዎች አሠራር የተለያየ ቢሆንም በእግዚአብሔር አስተዳዳር ሥር ናቸው። እነዚህ ሥጦታዎች በሙሉ ዓላማቸው ቤተ ክርስቲያንን ለማሳደግና ለማነጽ ነው እንጂ ለግል ጥቅም ወይም ክብር ተብለው የሚሰጡ አይደሉም። ለዚህም ነው አንዳንድ ሥጦታዎች ለጥቂት ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሰጡት፤ (1ኛጴጥ.4፡10-11)። 

ክቁጥር 8-11 ሥጦታዎችን ይዘረዝራል፡፡ 

ጥበብ፡- በተፈጥሮ ሊታወቁ የማይቻሉትን ጥልቅና መንፈሳዊ እውቀቶች መንፈስ ቅዱስ ለተለያዩ ሰዎች ይገልጣል፡፡ ሁሉም አማኞች ክርስቶስን የማወቅ ጥበብ ተሰጥቷቸዋል፤ ይህ ጥበብ ግን የተለየ ሥጦታ ሆኖ ለቤተ ክርስቲያን አስተማሪዎች የሚሰጥ ማለት ነው። 

እውቀት፡- ይህ በመሠረቱ ከጥበብ አይለይም። 

እምነት፡- ይህም ለእያንዳንዱ አማኝ የሚሰጠውና በኢየሱስ የማመን የየደህንነት እምነት ሳይሆን በተለየ ሁኔታ በእምነት የመራመድ ሥጦታ የሚታይባቸው አማኛች አሉ ማለት ነው። 

የመፈወስ ሥጦታ፡- ይህ ሥጦታ ለምሳሌ ሐዋርያው ጴጥርስ ነበረው፤ የልብሱን ጫፍ እንኳ የነካ ይፈወስ ነበር። 

ተአምራትን ማድረግ፡- ይህ ልዩ ኃይልን የመግለጥ ሥጦታ ነበር። ለምሳሌ፡- ጴጥሮስ በተግሣጽ ሐናንያንና ሰጲራን እንደገደለ፤ ጳውሎስ አስማተኛውን በእውርነት አንደመታው ዓይነት ያላ ኃይል ነው። (የሐዋ.5፡1-11፤ 13፡6-12)። 

ትንቢት፡- የእግዚአብሔር አንደበት ሆኖ የእግዚአብሔርን ቃል ማስተላለፍ ማለት ነው። ይህ የወደፊቱን መተንበይ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ቃልም መስጠት ትንቢት ይባላል፤ (የሐዋ. 15፡32)። ደግሞም ጌታ ኢየሱስ ነቢይ ነበር፤ ግን ዋና ሥራው ማስተማር ነበር እንጂ የወደፊቱን ነገር መተንበይ ብቻ አልበረም። ነቢያት ሲተነብዩ ከአእምሮአቸው ተለይተው ዛር እንዳለበት በመንቀጥቀጥና በንግግር በመፈንዳት አልነበረም። ነገር ግን ዘና ብለው በጽሞና መንፈስ በማስተማር አቀራረብ ነበር። አንዳንድ ጊዜም በጥያቄና በመልስ በውይይት መልክ ትንቢታቸውን በትምህርት መልክ አቅርበዋል። ይህ አይሆንም ያለ የጌታን ትምህርት አሰጣጥ ከወንጌል አንብቦ ይረዳ፡፡ 

መናፍስትን መለየት፡- አማኞች በሙሉ መናፍስትን እንዲመረምሩ ታዘዋል፤ (1ኛ ዮሐ.4፡1)። ነገር ግን ይህ የተለየ የስሕተትን መንፈስ ቶሎ የመለየትና ቤተ ክርስቲያንን የማስጠንቀቅ ሥጦታ ነው። ያልበሰሉ አማኞች ብዙ ጊዜ «እኔ ለዶክትሪን ግድ የለኝም» እያሉ ሲኩራሩ ይታያሉ። ዶክትሪን በመሠረቱ ትምህርት ማለት ነው። ክርስቲያን ምን ዓይነት ትምህርት መቀበልና አለመቀበል ማወቅ ይኖርበታል። የቤተ ክርስቲያን አስተማሪዎች ሕዝባቸው ሐሰተኛ ትምህርት እንዳይቀበሉና ከክርስቶስ መንገድ ፈቀቅ እንዳይሉ መንከባከብ አለባቸው። እነዚህ ተንከባካቢዎች እንግዲህ የመለየት ሥጦታ ሊኖራቸው ይገባል ማለት ነው፤ (2ኛቆሮ. 11፡2-4፤ ገላ.1፡6-9፤ 2ኛጴጥ.2፡1-3)። 

ልሳን፡- ይህ ሥጦታ ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለው በሐዋ. ምዕራፍ 2 ላይ መንፈስ ቅዱስ በወረደ እለት ነው። በ1ኛ ቆሮንቶስ የተጠቀሰውና በሐዋርያት ሥራ ያለው የተለያዩ ናቸው የሚሉ በቂ ማስረጃ የላቸውም። ልዩነት የተባሉትን ስንመረምር ልዩነት እንዳልሆኑ እንገነዘባለን። በመሠረቱ በግሪክ ቋንቋ በሁለቱም ቦታ የተጠቀሰው ያው ልሳን የሚለው ቃል ነው። ስለዚህ ትርጉሙን ሁለት አድርገን ለመስጠት በቂ ምክንያት ሊኖረን ይገባል፤ ምክንያትም የለንም። 

ጠቅላላ ሥጦታዎቹን የእውቀትና የኃይል ሥጦታዎች በማለት በሁለት ወገን እናጠቃልላቸዋለን። የእውቀት ሥጦታዎች የተባሉት፡- ጥበብ፥ እውቀት፥ ትንቢት፥ መናፍስትን መለየት፥ ልሳን መተርጉም ሲሆኑ፤ የኃይል ሥጦታዎች ደግሞ ዕምነት፥ መፈወስ፥ ተአምእራት ማድረግ ናቸው። በሁለቱ መካከል ያለው ዝምድና ይሄ ነው። በቃሉ የተነገረው እውቀት እውነተኛ ለመሆኑ የኃይል ሥጦታዎች ማረጋገጫ ሆነው ቀርበዋል፡፡ ለዚህ ማስረጃ ዕብ.2፡3-4ን ተመልከት። ይህንን ክፍል ከኤፌ.4፡11-12፤ ከ1ኛ ጴጥ.4፡10-1፤ ከሮሜ 12፡4-8 እና ከ1ኛ ቆሮ.12፡28-30 ጋር ካነፃፀርነው ሌሎች መንፈሳዊ ሥጦታዎች እንዳሉ መገንዘብ እንችላለን። 

ጥያቄ 10. 1ኛ ቆሮ. 12፡8–10፤ 28-30ን ከኤፈ.4፡11-12፤ ከ1ኛ ጴጥ.4፡10-11 እና ከሮሜ 12፡4-8 ጋር አነፃፅር። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የተሰጡትን ሥጦታዎች በዝርዝር ጻፍ። 

ጥያቄ 11. ሀ/ የትኛው መንፈሳዊ ሥጦታ ይመስልሃል የተሰጠህ? ለ/ ይህንን ሥጦታ ያሰብከው ለምንድነው? ሐ/ አንድ ሰው መንፈሳዊ ሥጦታውን ሊያውቅ የሚችለው እንዴት ነው? መ/ ለቤተ ክርስቲያንህ ዕድገት ይህንን ሥጦታህን በምን ዓይነት መንገድ ነው የምትጠቀምበት?

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

1 thought on “1ኛ ቆሮ. 12፡ 1-11”

  1. የእግዚአብሔር ስም የተባረክ ይሁን!!
    እግዚአብሔር በልብአችሁ ይህንን ቃል አኑሮ ለሕብረተሰባችን በተለያዩ ሚዲያዎች ለመድረስ ጧትና ማታ ለሚደክሙት ወንድሞች፣አህቶች፣አባቶችና እናቶች በሙሉ እግዚአብሔር ሙሉ ጤንነታችህን፣ኢኮኖሚያችንና ሁለማችሁን ይጠብቅ!! አሜን!!
    ውድ ወንድማችሁ ሙላቱ ኢትቻ ነኝ የከጌፈርሳ ቡራዩ መሠረተ ክርስቶስ ቤ/ያን አባል
    ለበለጠ መረጃ
    Best Regards
    Mulatu Eticha Guma
    Senior Land Use and Planning Expert and GIZ SDR project Technical focal person
    Ministry of Agriculture, Natural Resource Management Directorate (NRMD) Watershed Case Team
    Telephone: 0116463080
    Mobile : 0921925018/0942429436
    E-mail: mulatueticha@gmail.com

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading