የ1ኛ ሳሙኤል አራት ዓላማዎች 

  1. የእስራኤል መንግሥት በአንድ ንጉሥ የሚተዳደርበት ሁኔታ እንዴት እንደተፈጠረ ለማሳየት ነው። 1ኛ ሳሙኤል ከተጻፈባቸው ምክንያቶች አንዱ የእስራኤል ሕዝብ ጊዜያዊ በሆኑ መሳፍንት መገዛቱ ቀርቶ በአንድ ንጉሥ የሚተዳደርበት ሁኔታ እንዴት እንደተፈጠረ ለመመዝገብ ነው።

እንደምታስታውሰው፥ መጽሐፈ መሳፍንት የሚያተኩረው የእስራኤል ሕዝብ ያለማቋረጥ የተገዙበትና ለእግዚአብሔር ሕዝብ የሥነ-ምግባር ብልሹነት አንዱ ምክንያት ንጉሥ ባለመኖሩ እንደ ነበር ለማሳየት ነው (መሳ. 21፡25)። 

1ኛ ሳሙኤል ሕዝቡ በላያቸው የሚሠለጥን ንጉሥ ማግኘት እንዴት እንደጀመሩ ያሳየናል። በተጨማሪ አንድ ንጉሥ እንደ እግዚአብሔር ልብ ካልሆነ፥ ጠላቶቹን ሊያሸንፍና የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሥነ-ምግባርና መንፈሳዊ ሕይወት ሊያሳድግ እንደማይችል ያሳየናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን እውነት የሆነው እንዴት ነው?

  1. የዳዊት ንጉሥነት ሕጋዊ እንደ ነበረና በሳኦል ላይ በተደረገ ዓመፅ፥ ወይም ዳዊት ከሳኦል ላይ የቀማው መንግሥት እንዳልሆነ ለማሳየት ነው።

የመጽሐፈ ሳሙኤል ጸሐፊ ዳዊትን ዙፋን ላይ በማስቀመጥ በእስራኤል ሁሉ እንዲነግሥ ያደረገ እግዚአብሔር እንደሆነ ለማሳየት ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጓል። የዳዊት ወደ ሥልጣን መውጣት ሳኦልን ለማስወገድ ባደረገው የትኛውም ዓይነት ጥረት አልነበረም። በ1ኛ ሳሙኤል ታሪክ እግዚአብሔር ዳዊትን እንደመረጠው በተደጋጋሚ እናነባለን። በተጨማሪም ሳኦል ሊገድለው የሚችልበት ብዙ ሁኔታ በተፈጠረ ጊዜ እንኳ፥ ዳዊት የመንግሥቱን ሥልጣን ከሳኦል በኃይል ለመውሰድ በፍጹም እንዳልፈቀደ በተደጋጋሚ እናነባለን።

  1. እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንዴት ቃል ኪዳን እንደመሠረተ ለማሳየት ነው። ይህ የ2ኛ ሳሙኤል ትኩረት ቢሆንም፥ የቃል ኪዳኑን አመሠራረት መነሻ የምናገኘው በ1ኛ ሳሙኤል ነው። እነዚህ ሁለት መጻሕፍት ቀድሞውኑ በአንድነት ያሉ፥ አንድ መጽሐፍ መሆናቸውን አስታውስ። የጋራ ትኩረታቸው እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር ባደረገው ቃል ኪዳን ላይ ሲሆን፥ ቃል ኪዳኑም ዳዊትና ዘሩን የእስራኤል ሕዝብ ሕጋዊ ነገሥታት ለመሆን የሚያበቁ እንደነበሩ የሚገልጥ ነው። 
  2. እግዚአብሔርን ያሳዘነውንና ለእግዚአብሔር ክብር ያመጣውን ሁለት ዓይነት ንግሥና ለማወዳደር ነው። መጽሐፈ ሳሙኤል የሕዝቡ እውነተኛ ንጉሥ የመሆን ሥልጣን ያለው እግዚአብሔር እንደሆነ ይናገራል (1ኛ ሳሙ. 8፡7፤ 12፡12)። እግዚአብሔር የሕዝቡ እውነተኛ መሪ ስለነበር፥ እስራኤላውያን እርሱን በመታዘዝ ሊኖሩ ይገባ ነበር። ከእውነተኛ ንጉሥ (ከእግዚአብሐር) ይልቅ፥ የሰዎችን ነገሥታት ለእርዳታ መፈለግ በእግዚአብሔር ላይ የሚደረግ ዓመፅ ነበር። ምድራዊ ንጉሥ በሰማያዊው ንጉሥ ሥር በእግዚአብሔር ሥልጣን ሥር ሊገዛ እንጂ የእግዚአብሔርን የአመራር ስፍራ ሊተካ አልተፈቀደም፤ ደግሞም አይችልም።

እግዚአብሔር ምድራዊ ንጉሥ እንዳይኖር አልከለከለም። ከብዙ ዓመታት በፊት ነገሥታት ከአብርሃም የዘር ግንድ እንደሚመጡ ተስፋ ሰጥቷል (ዘፍ. 17፡6)። ሙሴም ስለ እስራኤል ነገሥታት ግልጽ የሆኑ ትእዛዛትን ሰጥቷል (ዘዳ. 17፡14-20)። እስራኤላውያን ንጉሥ በመፈለጋቸው ሂደት ውስጥ፥ እግዚአብሔር ያልወደደላቸው የፈለጉበት ምክንያት ስሕተት ስለሆን ነበር። ሰማያዊ የሆነውን ንጉሥ ሳይታዘዙ ምድራዊው ንጉሥ ነፃ የሚያወጣቸው መስሎአቸው ነበር። እንደዚሁም ንጉሥ የፈለጉት፥ ዓለምን ለመምሰል ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም በዚህ ዘመን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሪዎች ያስፈልጋሉ የሚያስብሉት የተሳሳቱ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው? ለ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላለ አመራር በዓለም በተሳሳተ መንገድ ተጽዕኖ ሊደረግብን የሚችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር (ለምሳሌ፡- ትምህርት፥ የዘር ውርስ፥ የቤተሰብ ውርስ)።

የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ፥ ሳኦል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የተሾመ የተሳሳተ ዓይነት መሪ ወይም ንጉሥ ምሳሌ ነው። ሳኦል ጅማሬው መልካም ነበር። በእግዚአብሔር ተመርጦ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ ነበር። በእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች ላይ ድልን አግኝቶ ነበር፤ ነገር ግን በሰማያዊው ንጉሥ ትእዛዝ ስላልሄደ፥ በሌላ ንጉሥ ተተካ። አለመታዘዙም ለቤተሰቡ መፍረስ፥ ለራሱም ሞት አመጣበት።

ሁለተኛው የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት፥ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የተሾመ የመልካም መሪ ምሳሌ ነበር። ስለሆነም በ1ኛ እና 2ኛ ነገሥት በተደጋጋሚ፥ ፈለጉን መከተል የሚያስፈልግ የእስራኤል ንጉሥ እንደነበረ ተጠቅሷል (2ኛ ነገ. 14፡ 3፤ 22፡2፤ 2ኛ ዜና 13፡3፤ 28፡1 ተመልከት)። ዳዊትም የተመረጠው በእግዚአብሔር ነበር። በእግዚአብሔር ላይ የነበረው የማያቋርጥ እምነት በእግዚአብሔር ጠላቶች ላይ ታላቅ ድልን እንዲቀዳጅ አደረገው። በ2ኛ ሳሙኤል ወደፊት እንደምንመለከተው ግን፥ በኋላ በሕይወቱ በተከሰተው አለመታዘዝ ለእስራኤልና ለቤተሰቡ ታላቅ ቅጣትን አስከትሏል።

በሳኦልና በዳዊት መካከል የነበረው ዋና ልዩነት ዳዊት መታዘዙና ሳኦል አለመታዘዙ አልነበረም፤ ነገር ግን ዳዊት አለመታዘዙን በተገነዘበ ጊዜ ፈጥኖ ንስሐ መግባቱ ሲሆን፥ ሳኦል ግን ለፈጸመው ተግባር ሁልጊዜ ማመካኛ ለመስጠት መሞከሩ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ መሪዎች ኃጢአት ወይም አንድ የተሳሳተ ነገር በሚፈጽሙበት ጊዜ ለስሕተታቸው ማመካኛ ከመስጠት ይልቅ ይቅርታ ስለመጠየቃቸው አስፈላጊነት ይህ ምን ያስተምረናል?

የ1ኛ ሳሙኤል ዋና ትኩረት በሳኦል ላይ ሳይሆን በዳዊት ላይ ነበር። አብዛኛው ታሪክ በሳኦልና በዳዊት መካከል የነበረውን ተቃርኖ የሚያሳይ ነው። 2ኛ ሳሙኤል በሙሉ ስለ ዳዊት የሚናገር ነው። ከእስራኤል ነገሥታት ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ የሚናገረው ስለ ዳዊት ነው፤ ምክንያቱም ዳዊት ሌሎቹ ነገሥታት ሁሉ ምሳሌነቱን ሊከተሉት የሚገባ እግዚአብሔርን የሚፈራ መሪ ነበር። በተጨማሪ ዳዊት የእርሱ ልጅ የሆነው በፍጹም ጽድቅና ቅድስና የሚገዛው፥ ሊመጣ ያለው መሢሕ፥ የንጉሡ የኢየሱስ ክርስቶስ አምሳያ ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2 thoughts on “የ1ኛ ሳሙኤል አራት ዓላማዎች ”

  1. ሰላም ላንተ ይሁን! ፣ ከዝህ በፊት የነበሩትን የብሉይ ኪዳን ጥናቶች እንዴት ማግኘት እችላለሁ??  Sent from Yahoo Mail on Android

    1. ሰላም ለአንተ እና ለመላው ቤተሰብህ ይሁን፣

      ወንድም ፍቅሩ፣ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጽሐፎችን ጥናት ለማግኘት የሚከተለውን ሊንክ ተጫን፡-

      https://ethiopiansite.com/%e1%8b%a8%e1%89%a5%e1%88%89%e1%8b%ad-%e1%8a%aa%e1%8b%b3%e1%8a%95-%e1%88%98%e1%8c%bd%e1%88%90%e1%8d%8d-%e1%89%85%e1%8b%b1%e1%88%b5-%e1%8c%a5%e1%8a%93%e1%89%b5/

      ጌታ ኢየሱስ ይባርክህ!
      አዳነው ዲሮ
      የወንጌል በድረ ገጽ አገልግሎት አዘጋጅ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading