የ2ኛ ሳሙኤል መግቢያ

እስካሁን ድረስ የዳዊትን ሕይወት እያጠናን ነበር፤ ዳዊትም በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ውስጥ እጅግ የከበረ ከብሉይ ኪዳን ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው። በብሉይ ኪዳን ከሚገኙ ሰዎች ሁሉ በላቀ ሁኔታ (ከሙሴ፥ ከኢያሱ፥ ከአብርሃምም ሳይቀር) ስለ ዳዊት ሕይወት ብዙ ነገር እናውቃለን። 1ኛ ሳሙኤል በአብዛኛው ዳዊት የእስራኤል የመጀመሪያ ንጉሥ ከነበረው ከሳኦል ጋር ስለ ነበረው ግንኙነት ይናገራል። የዳዊት ታሪክ በ2ኛ ሳሙኤልም ይቀጥላል። በ1ኛ ዜናም ተደግሟል።

1ኛ ጥያቄ፦ 1ኛ ሳሙ. 13፡14 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ዳዊትን እንደ ልቤ የሚሆንልኝ ሲለው ምን ማለቱ ነበር? ለ) አንድ ሰው እንደ እግዚአብሔር ልብ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

እግዚአብሔር ዳዊትን «እንደ ልቤ የሆነ» ብሉ ጠራው (1ኛ ሳሙ. 13፡14)። ደግሞም «ባሪያዩ» ብሎ ጠርቶታል (2ኛ ሳሙ. 3፡18፤ 1ኛ ነገሥ. 11፡32)። እግዚአብሔር ዳዊትን በጣም የወደደው ለምንድን ነው? ከእኛ የተሻለ ስለ ነበረ ነውን? ወይስ ዳዊት ለእግዚአብሔር ጥልቅ ፍቅርና ልዩ የሆነ የጠበቀ ግንኙነት ስለ ነበረው ነው?

ዳዊት ከማናችንም የተለየ ሰው አልነበረም። ታላቅነቱ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ እግዚአብሔርን ለመውደድና ለእርሱም ለመታዘዝ ስለ መሰነ ነው። ለእግዚአብሔር የነበረው ፍቅር ታላቅ ነበር። በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ በተደጋጋሚ የዳዊት ልብ እግዚአብሔርን ለማወቅ ሲጓጓ እናያለን (መዝ. 27)። መንፈሱ ለእግዚአብሔር ሥራና በሕይወቱ ለሚፈጸም ኃጢአት ንቁ ነበር (መዝ. (51)።

ዳዊት ልዩ የሆነ መሪም ነበር። ታላቅና ብርቱ ተዋጊ ነበር። በጦርነት ሜዳ በነበረው ችሎታ ፍልስጥኤማውያንና ሌሎች በርካታ ሕዝቦችን አሸንፏል። ታላላቅ ተዋጊ የሆኑ ብርቱ ሰዎችን በዙሪያው ለማሰለፍም የሚችል ሰው ነበር። የሙዚቃ መሣሪያ በመጫወትና መዝሙሮችን በመጻፍ እጅግ የታወቀ ሰውም ነበር። ዳዊት ከጻፋቸው መዝሙራት አብዛኛዎቹ በመዝሙረ ዳዊት የተመዘገቡና ዛሬም ቢሆን ለክርስቲያኖች እጅግ ተወዳጅ የሆኑ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል ሆነዋል። ጻድቅ፥ ይቅር ባይ፥ ለጓደኞቹ ታማኝና በነገሮች ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ የሚታመን መሪ ስለ ነበር፥ ብርቅና ፍጹም መሪ ነበር። ከዳዊት በኋላ የነገሡ ነገሥታት በሙሉ ከእርሱ ጋር በንጽጽር ቀርበዋል (ለምሳሌ፡- 2ኛ ነገሥት 18፡3)። በተጨማሪም ዳዊት ሰዎችን ሁሉ የሚገዛው መሢሕ፥ የታላቁ ንጉሥ የጌታ ኢየሱስ አባት ነበር። ዳዊት በጦርነት እያሸነፈ ብዙ ምድርን ያዘ። ነገሥታትን ለራሱ አስገዛ፤ የእስራኤልን ድንበር ከግብፅ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ አሰፋ። ለቤተ መቅደሱ ሥራ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ አዘጋጀ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዳዊት ረዘም ላለ ጊዜ የሚነግረን አለምክንያት አይደለም።

ዳዊት እግዚአብሔርን እንዳስከበረ እኛም እርሱን የምናስከብር የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለመሆን ብንፈልግ፥ የእግዚአብሔር ወዳጆችና የእግዚአብሔር ሕዝብ ታላላቅ መሪዎች ለመሆን እንዴት እንደምንችል ለማወቅ የዳዊትን ሕይወት ማጥናት አለብን። ለሕይወታችን ዳዊት የሄደበትን አቅጣጫ ልናስይዘው ይገባናል።

ይህ ማለት ግን ዳዊት ፍጹም ነበረ ማለት አይደለም። ዳዊት ለእግዚአብሔር ከፍተኛ ፍቅር የነበረው ብቻ ሳይሆን ትልቅ ኃጢአትም ሠርቶአል። አመንዝራ፥ ነፍሰ ገዳይ፥ በሠራዊቱ ብዛት የሚመካ፥ ኩሩና ቤተሰቡን መቆጣጠር ያልቻለ ሰው ነበር።

የእግዚአብሔር ወዳጆችና እንደ ልቡ የምንሆን መሆን ወይም በእግዚአብሔር የተወደድን ሰዎችና እርሱ የሚጠቀምብን መሆን ማለት፥ አንዳችም ኃጢአት የማናደርግ ፍጹማን ወይም ትልቅ ኃጢአት የማንፈጽም ሰዎች ነን ማለት አይደለም። እግዚአብሔር ይጠቀምብን ዘንድ ግን መንፈሳዊ ንቃትን በሕይወታችን ልናሳድግ ለእግዚአብሔር ጥልቅ የሆነ ፍቅር ሊኖረን፥ ከእርሱ ጋር ኅብረት የማድረግ ፍላጎት ልናዳብር፥ ኃጢአትን ልንጠላና የንስሐን አስፈላጊነት ልንገነዘብ ወዘተ. ያስፈልጋል። ዳዊት የከፋ ኃጢአት ቢሠራም እንኳ ልቡ ለመንፈሳዊው ነገርና ለእግዚአብሔር ንቁ ስለነበረ እንዲሁም ንስሐ ስለሚገባ እግዚአብሔር በከፍተኛ ደረጃ ተጠቀመበት።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በመንፈሳዊ ነገር ንቁ የሆነ ልብ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ለ) መንፈሳዊ ንቃት ያለውን ልብ ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው? ሐ) ልብህን ለመንፈሳዊ ነገርና ለራሱ ንቁ ለማድረግ እግዚአብሔር በሕይወትህ እየሠራ ያለው እንዴት ነው? መ) አንተ ራስህ ለእግዚአብሔር «እንደ ልቤ» የሚባል ሰው እንድትሆን ከሕይወትህ ልታስወግዳቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው? አሁኑኑ ትናዘዝና ትተዋቸው ዘንድ ከቁርጥ ውሳኔ ድረስ። 

የውይይት ጥያቄ፥ «ዳዊት» የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልከትና ስለ ሕይወቱ አስፈላጊ የሆኑ ጥቂት ነገሮችን ዘርዝር። 

1ኛና 2ኛ ሳሙኤል በመጀመሪያ አንድ መጽሐፍ ስለነበረ፥ አብዛኛው የ1ኛ ሳሙኤል ታሪካዊ መሠረት ለ2ኛ ሳሙኤልም የሚሆን ነው። ስለ 2ኛ ሳሙኤል በጣም አስፈላጊ የሆኑ የሚከተሉትን ነገሮች አስታውስ።

  1. 1ኛና 2ኛ ሳሙኤል በመጀመሪያ አንድ መጽሐፍ ነበሩ። ጸሐፊያቸውም አንድ ሰው ነው። መጽሐፉ የተሰየመው በእስራኤል የነገሥታትን ዘመን በጀመረውና የእስራኤላውያንን የመጀመሪያ ሁለት ነገሥታት በቀባው በሳሙኤል ነው።
  2. የመጽሐፈ ሳሙኤል ጸሐፊ ማን እንደሆነ አይታወቅም። የተጻፈው የግን ከሰሎሞን ሞት በኋላ ሳይሆን አይቀርም።
  3. የእነዚህ ሁለት መጻሕፍት ማዕከላዊ ገጸ-ባሕርይ ከእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ታላቅ የነበረው ዳዊት ነው። 

የ2ኛ ሳሙኤል አስተዋጽኦ 

  1. ዳዊት በይሁዳ ላይ ነገሠ (1-4) 
  2. ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ (5፡1-5) 
  3. የንጉሥ ዳዊት ተግባራት ስኬታማነት (5፡6-9፡12)

ሀ. ዳዊት ኢየሩሳሌምንና ፍልስጥኤማውያንን አሸነፈ (5፡6-25) 

ለ. ዳዊት ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም አስመጣ (6) 

ሐ. እግዚአብሔር ለዳዊት የዘለዓለም መንግሥት ተስፋ ሰጠው (7)

መ. የዳዊት መንግሥት ስፋት (8) 

ሠ. ዳዊት ለዮናታን የገባውን ቃል ኪዳን ጠበቀ (9)

ረ. ዳዊት አሞራውያንን አሸነፈ (10) 

  1. የንጉሥ ዳዊት ውድቀት (11-20)

ሀ. የዳዊት ምንዝርናና ነፍሰ ገዳይነት (11-12)

ለ. የዳዊት ልጆች ዓመፅና ሞት (13-20) 

  1. ስለ ዳዊት አገዛዝ የመጨረሻ ትምህርቶች (21-24)

የ2ኛ ሳሙኤልና የ1ኛ ዜና መዋዕል ንጽጽር 

ብሉይ ኪዳን ታላቁ ንጉሥ የነበረውን የዳዊትን ታሪክ በሁለት የተለያዩ ነገር ግን ተደጋጋፊ በሆኑ መጻሕፍት አስፍሮአል፤ እነርሱም 1ኛና 2ኛ ሳሙኤልና 1ኛ ዜና መዋዕል ናቸው። 1ኛና 2ኛ ሳሙኤል የሚናገሩት፥ ዳዊት እንዴት ንጉሥ እንደሆን ሲሆን የ1ኛ ዜና ትኩረት ግን ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ለእስራኤል ስላበረከተው ፖለቲካዊ በተለይ ደግሞ ሃይማኖታዊ ተግባር ነው። ለምሳሌ የ1ኛ ዜና 8 ምዕራፎች አብዛኛው ክፍል የሚናገረው ዳዊት ለቤተ መቅደስ ሥራው የሚሆኑ ነገሮችን እንዴት እንዳደራጀ ነው። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: