Site icon

1ኛ ሳሙኤል 13-15

በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እጅግ አሳዛኝ ከሆኑ ታሪኮች አንዱ የሳኦል ታሪክ ነው። እግዚአብሔርን ለማክበር ታላቅ ኃይል ነበረው። በግሩም ሁኔታ ሥራውን ለእግዚአብሔር መሥራት ጀመረ፤ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ችግሮች መፈጠር ጀመሩ። በመሆኑም አንድ ቀን እግዚአብሔር ሳኦልን እውነተኛ የእስራኤል ንጉሥ እንዳይሆን ናቀው። ሳኦል ዛሬም ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሚወድቁበት ኃጢአት ወደቀ፡፡

በመጀመሪያ፥ ሳኦል በከፊል ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ኃጢአት ውስጥ ወደቀ። ማቅረብ ያልተፈቀደለትን መሥዋዕት አቀረበ። ደግሞም የአማሌቃውያን ነገሥታትና መንጎቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፋ ታዞ ሳለ ሕዝቡ የሚሉትን ሰማና አንዳንዶቹን በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ተዋቸው።

ዛሬም በተመሳሳይ ኃጢአት የሚወድቁ በርካታ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አሉ። በሕዝቡ ፊት ቆመው የእግዚአብሔርን ቃል ቢያስተምሩም እንኳ፥ በሚያስተምሩት መልክ አይኖሩም። የሚሉትና የሚኖሩት ፈጽሞ የተለያየ ነው። አሥራትን ስለማውጣት ያስተምራሉ፤ እነርሱ ግን አሥራታቸውን አይከፍሉም። ስለመመስከር ያስተምራሉ፤ ነገር ግን አይመሰክሩም። ሕይወታቸውን በእግዚአብሔር ፊት በንጽሕና አይጠብቁም። ኃይሉን ለመቀበል እግዚአብሔርን ከመፈለግና ለእርሱ ክብር ከማገልገል ይልቅ በራሳቸው ኃይል በመመራት ክብርን ለራሳቸው ይፈልጋሉ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ በቤተ ክርስቲያንህ ሲፈጸም ያየህባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

ሁለተኛ፡- የእግዚአብሔርን ሕዝብ ጠላቶች ለማሸነፍ እግዚአብሔር ዳዊትን በአስደናቂ ሁኔታ በተጠቀመበት ጊዜ ሳኦል ቀና፡፡ ሳኦል በዳዊት ላይ በመቅናቱ ምክንያት ቀሪውን የሕይወት ዘመኑን በሙሉ ዳዊትን ለመግደል በመሞከር አሳለፈ። ቅንዓት አሁንም ቢሆን ከእግዚአብሔር ሕዝብ መሪዎች ዋነኛ ጠላቶች አንዱ ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሥልጣናቸውንና ክብራቸውን እንደያዙ መቆየት ይፈልጋሉ። ከእነርሱ በተሻለ ሁኔታ የታወቀ ወይም እግዚአብሔር ከእነርሱ በበለጠ ሁኔታ የሚጠቀምበት ሰው ሲነሣ ቀናተኛች ይሆናሉ። ዋና ሥራቸው የበለጠ ስጦታ ያላቸውን ሰዎች ወደ መሪነት ሥልጣን እንዳይወጡ መከላከል እንደሆነ በማሰብ የሌሎችን መሪዎች ሥራ የሚከላከሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያን ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መቅናት እጅግ የሚቀልላቸው ለምንድን ነው? ሐ) በሚቀኑበት ጊዜ ስለ ቤተ ክርስቲያን መሪነት የሚረሱት ነገር ምንድን ነው?

በሌሎች መሪዎች ላይ መቅናት በምንጀምርበት ጊዜ፥ መሪዎች እንሆን ዘንድ የጠራን እግዚአብሔር መሆኑን ረሳን ማለት ነው። እናገለግለው ዘንድ ችሎታን የሰጠንና ሊኖረን የሚያስፈልገው ምን ዓይነት አገልግሎት እንደሆነ የሚወስነው እግዚአብሔር ራሱ ነው። ቅንዓት በውስጣችን በሚያድርበት በማንኛውም ጊዜ፥ እግዚአብሔር ተስማሚ ነው ብሎ በሚያስበው ቦታ እንድናገለግል ሊያደርግ፥ ከእኛ በሚበልጥ ሁኔታ በሌሉች ሊጠቀም መብቱ እንደሆነ ዘነጋን ማለት ነው። በምንቀናበት ጊዜ ደግሞ የምናገለግለው እግዚአብሔርን ሳይሆን ለራሳችን ክብር ነው ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ሳሙ. 13-20 አንብብ። ሀ) ሳኦል ከፍልስጥኤማውያን ጋር ከመዋጋቱ በፊት እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ምን ነገር አደረገ? ለ) ሳኦል፥ ፍልስጥኤማውያንን በሚወጋበት ጊዜ ወንድ ልጁን ሊያጠፉት በነበረ ጊዜ ምን ሞኝ ነገር አደረገ ሐ) ሳኦል በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳይሆን እግዚአብሔር እንዲንቀው ያደረገውን ምን ክፉ ነገር ሠራ? መ) መታዘዝ ከመሥዋዕት የሚበልጠው ለምንድን ነው? ሠ) ዳዊት ንጉሥ ይሆን ዘንድ በተመረጠ ጊዜ ሥራው ምን ነበር? ረ) ዳዊት ከጎልያድ ጋር በገጠመ ጊዜ እግዚአብሔርን ያከበረው እንዴት ነው? ሰ) ከቅንዓት የተነሣ ሳኦል በዳዊት ላይ ሊያደርገው የሞከረው ነገር ምን ነበር? ) በዳዊትና በዮናታን መካከል የነበረውን ግንኙነት ግለጥ።

ሳኦል፥ የእስራኤል ንጉሥ የሆነባቸው የመጀመሪያ ጊዜያት መልካም ቢሆኑም ብዙም ሳይቆይ ከጌታ ፊቱን መለሰ። ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ መረዳት እንደሌለው አሳየ። በአመራሩ ላይ የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች በጥበብ የተሞሉ አልነበሩም። የ1ኛ ሳሙኤል ጸሐፊ፥ ሳኦል ጥበብና መንፈሳዊ መረዳት የጎደለው እንደነበር ለማሳየት በርካታ ምሳሌዎችን ጠቅሷል።

  1. ሳኦል፥ ሳሙኤል እስኪመጣና መሥዋዕቱን እስኪያቀርብ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ አቃተው። በዚህ ፈንታ እግዚአብሐር ለእስራኤላውያን በፍልስጥኤማውያን ላይ ድል እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ እንስሳ ሠዋ። ሳሙኤል፥ እንደሚመጣና ለእግዚአብሔር እንደሚሠዋ ቃል ገብቶ ነበር። ሳኦል፥ የእግዚአብሔር ነቢይ የሚናገረው እግዚአብሔርን ወክሉ ስለሆነ አንዳንድ ነገሮች እርሱ እንደ ጠበቀው ባይሆኑም እንኳ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ነበረበት። 

ይህ የሳኦል ተግባር ለሳሙኤል ብቻ ሳይሆን፥ ለእግዚአብሔርም አለመታዘዝ ነበር። ውጤቱም፡- የሳኦል መንግሥት ብዙ እንደማይቆይና እግዚአብሔርም ሕዝቡን የሚመራ ሌላ ሰው እንደሚመርጥ ሳሙኤል ለሳኦል ነገረው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለዚህ አነስተኛ ያለመታዘዝ ተግባር እግዚአብሔር ሳኦልን በከፍተኛ ሁኔታ የቀጣው ለምን ይመስልሃል? ለ) ዛሬ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ሊፈጽሟቸውና እግዚአብሔርን ሊያሳዝኑ የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?

  1. ሳኦል የልጁን የዮናታንን ሕይወት ሊያጠፋ የነበረ የሞኝነት ትእዛዝ ሰጠ። ከፍልስጥኤማውያን ጋር በተደረገ ጦርነት ማንም ሰው እስከዚያ ቀን ምሽት ድረስ ምንም ነገር እንዳይበላ አዘዘ። ዮናታን ግን ትእዛዙን ስላልሰማ ማር በላ። ዮናታን በእግዚአብሔር ላይ በነበረው እምነት ምክንያት ፍልስጥኤማውያንን ለመግጠም የመጀመሪያውን እርምጃ ወሰደ። እስራኤላውያን በዚህ ጦርነት ድል ቢያገኙም እንኳ ዮናታን ለሳኦል ስላልታዘዘ ሳኦል ሊገድለው ወሰነ፤ ሌላው ሠራዊት ግን ዮናታንን ከሞት አዳነው።

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ሳሙ. 14፡6፥ 10፥ 12 አንብብ። ዮናታን በፍልስጥኤውያን ላይ ድልን ለማግኘት የተረጋገጠ እምነቱን ያደረገው በማን ላይ ነበር?

የዮናታንን መንፈሳዊ ሕይወት ከአባቱ ከሳኦል ጋር ማወዳደር በጣም አስደናቂ ነው። ዮናታን በእግዚአብሔር ላይ ተማምኖ ሲዋጋ፥ ሳኦል ግን ጦርነቱን ያደረገው በራሱ ብርታት ተመክቶ ነበር። ዮናታን ድሉ የተገኘው ከእግዚአብሔር እንደሆነ አስተዋለ። ሳኦል ግን ድሉን ያገኘው ራሱ እንደሆነ አሰበ፤ ደግሞም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ይልቅ ወደ በቀል አዘነበለ (14፡24)። 

  1. ሳኦል አማሌቃውያንና ያላቸውን ከብቶች በሙሉ እንዲያጠፉ እግዚአብሔር በሳሙኤል በኩል የሰጠውን ትእዛዝ ሳይፈጽም ቀረ። ሳኦል ከዚህ ትእዛዝ ያልፈጸመው ነገር በጣም ጥቂት ብቻ ነበር። ዳሩ ግን የአማሌቃውያንን ንጉሥና ከሁሉ የተሻሉትን እንስሳት መግደል ሲገባው አዳነ። ሳኦል እንስሳቱን ከመግደል የተዋቸው ለራሱ ፈልጎአቸው ይሁን ወይም እርሱ እንደሚለው ሕዝቡን በመስማት ብቻ እንደሆነ ግልጥ አይደለም፤ ምክንያቱም የትኛውም ይሁን ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ሳይታዘዝ ቀርቷል። በከፊል መታዘዝ እንደ አለመታዘዝ የሚቆጠር ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ጽኑ የሆነ ፍርድ ፈረደበት።

የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፡- ኢሳ. 1፡11-17፤ ሆሴዕ 6፡6፤ አሞጽ 5፡21-27። ሀ) እነዚህ ጥቅሶች ለእግዚአብሔር ስለ መታዘዝ አስፈላጊነት የሚናገሩት ነገር ምንድን ነው? ለ) እነዚህ ጥቅሶች ለዚህ ዘመን አምልኮአችን የሚያስተምሩን ነገር ምንድን ነው? 

1ኛ ሳሙ. 15፡22-23 በ1ኛ ሳሙኤል ውስጥ ከሚገኙ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ጥቅሶች ሁለቱ ናቸው። እነዚህ ጥቅሶች የቀድሞ እስራኤላውያንም ሆኑ የዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ያላቸውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ያስተካክላሉ። አይሁድ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ትኩረት በውጫዊ የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሆነ ያስባሉ። መሥዋዕት በሚያቀርቡበት ጊዜ እግዚአብሔር ስለ ልባቸው ዝንባሌና የራሳቸውን ዕለታዊ ሕይወት ስለሚኖሩበት የአኗኗር ስልት ምንም ግድ የለውም ብለው ያስቡ ነበር። ዛሬም ብዙ ክርስቲያኖች ዋናው አስፈላጊው ነገር መሰብሰባችን፥ መዝሙር መዘመራችን፥ ወዘተ. ነው ብለው ያስባሉ። ከቤተሰቦቻቸው፥ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ስላላቸው ግንኙነት፥ ወይም በሥራ ገበታቸው ላይ በሚታየው ተግባራቸውና በዝንባሌያቸው ላይ እግዚአብሔር ምንም ትኩረት የማያደርግ ይመስላቸዋል።

3 እግዚአብሔር ግን በሳሙኤልና በሌሎች ነቢያት እንደገለጠው አምልኮ የሚጀምረው አምልኮውን በሚፈጽመው ሰው ዕለታዊ ሕይወት ነው። እውነተኛ አምልኮን ለመፈጸም ትክክለኛ ዝንባሌ ያስፈልጋል። በትክክለኛ ዝንባሌ ውስጥ ለእግዚአብሔር ትእዛዝ የመግዛትና የመታዘዝ ዝንባሌ አለ። ለእግዚአብሔር ካልታዘዝን፥ ሳምንቱን በሙሉ እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ ነገር ካልተመላለስን፥ እሑድ በምናመልከው ብቻ እግዚአብሔር ደስ አይሰኝም። አምልኮ የሚጀምረው ሳምንቱን በሙሉ በምናደርገው ድርጊት ነው። እሑድ የምናደርገው ነገር ለእግዚአብሔር በመታዘዝና እርሱን በማክበር ሳምንቱን በሙሉ ያሳለፍነው ነገር ማጠቃለያ ነው።

ሳሙኤል መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል ብሏል። በተጨማሪ፥ በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም ዓመፅ፥ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝና መሰል አድራጐቶች ሁሉ የስሕተት አማልክትን የማምለክ ያህል የከፋ ናቸው ብሏል። ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ማለት ፈቃዳችንን የሕይወታችን አምላክ አድርገናል ማለት ነው፤ ስለዚህ ለእግዚአብሔር በማንታዘበት ጊዜ በስህተት ማምለክ ጀመርን ማለት ነው። የሕይወታችን አምላክ ሆንን ማለት ነው። እግዚአብሔር በሕይወታችን ላይ ሙሉ በሙሉ የሚያደርገውን የተቆጣጣሪነት መብት እኛው መሰድን ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ትእዛዛት በመጠኑ አለመታዘዝ ብዙ ጉዳት አያመጣም ብለው እንዴት እንደሚያስቡ የሚያሳዩ መግለጫዎችን ስጥ። ለ) ከዚህ ታሪክ ትንሽ ኃጢአት ስለሚያመጣው ጉዳት ምን እንማራለን?

እግዚአብሔር ለሳኦል የእስራኤል ንጉሥ እንዳይሆን የተናቀ መሆኑን ነገረው። መንግሥቱ ለልጆቹ እንደማያልፍ እግዚአብሔር ለሳኦል ከመናሩ በፊት፥ ሳኦል ራሱ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በሕይወት እያለ እንኳን የእስራኤል ንጉሥ መባሉ እንደቀረ ይነግረዋል። እርግጥ ከዚህ በኋላ ሳኦል ለብዙ ዓመታት የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ ቢቆይም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ራስ (መሪ) ሆኖ በእግዚአብሔር ተወክሎ መሥራቱ ቀርቶ ነበር። እግዚአብሔር መንፈሱን ከሳኦል ላይ ወስዶ ነበር። ሳሙኤልም ከዚያ በኋላ ተመልሶ መጥቶ የእግዚአብሔርን ቃል ነግሮት አያውቅም። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) መሪዎች እንደመሆናችን መጠን እግዚአብሔርን በሚያሳዝኑ ትናንሽ በሚመስሉ ነገሮች እንኳ ለእርሱ ለመታዘዝ ተጠንቅቀን መኖር እንዳለብን ይህ ታሪክ ምን ያስተምረናል? ለ) ያለ እግዚአብሔር ሕልውናና ኃይል በመሪነት ስለ መቀጠል ይህ ታሪክ ምን ያሳያል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version