2ኛ ሳሙኤል 1፡1-5፡5

የውይይት ጥያቄ፡- 2ኛ ሳሙኤል 1-5፥5 አንብብ። ሀ) በዮናታንና በሳኦል ሞት ምክንያት ዳዊት ስሜቱን የገለጸው እንዴት ነበር? ለ) ዳዊት በመጀመሪያ የነገሠው በየትኛው የእስራኤል ነገድ ላይ ነው? ሐ) በዳዊትና በሳኦል ቤት መካከል የተፈጸመው ነገር ምን ነበር? መ) የሳኦል ቤት የተሸነፈው እንዴት ነበር? ሠ) ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ የነገሠው እንዴት ነበር?

ከሳኦል ሞት በኋላ፥ ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ወዲያውኑ አልነበረም። ዳዊት በእስራኤል ሁሉ ላይ ለመንገሥ ከሳኦል ሞት በኋላ ሰባት ዓመት ፈጅቶበታል። ለእነዚህ ሰባት ዓመታት ዳዊት በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ዳዊትን ለማንገሥ በሚፈልጉና የሳኦል ቤተሰብ በዙፋኑ ላይ መቆየት አለበት በማለት ከሳኦል ልጆች አንዱን ለማንገሥ በሚፈልጉ መካከል የእርስ በርስ ጦርነት ተካሂዷል።

የዚህ የ2ኛ ሳሙኤል ክፍል ዋና ዓላማ በሳኦል ቤተሰብ ላይ አንዳችም የበቀል ስሜት እንዳልነበረውና እንዳልተበቀለ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ሊገድለው ይፈልግ የነበረው ሳኦል በመሞቱ እንኳ እንዳልተደሰተ ለማሳየት ነው።

ሳኦል ከሞተ በኋላ፥ ከሳኦል ጋር ይዋጉ ከነበሩ ወታደሮች አንዱ የሳኦልና የዮናታንን ሞት ለማርዳት እየሮጠ ወደ ዳዊት መጣ። ይህ አማሌቃዊ ወታደር ይዤ ስላመጣሁት ወሬ ብቻ ሳይሆን፥ ስለ ሳኦልና ስለ ዮናታን ሞት ጭምር ዳዊት ይሸልመኛል ብሎ በማሰብ፥ በእግዚአብሔር የተቀባውን መሪ ሳኦልን እንደገደለ ተናገረ። ሳኦልን ገደልኩ ስላለ ዳዊት አስገደለው። ውሸቱ ሕይወቱን እንዲያጣ አደረገው። ዳዊት በሳኦል ሞት ምክንያት አልተደሰተም፤ ነገር ግን ሳኦልና ዮናታን በመሞታቸው አዘነ፤ ከምግብ ተለይቶ በመጾም አለቀሰ። ስለ ሳኦልና ስለ ልጁ ስለ ዮናታን ሞት የኃዘን ቅኔ ተቀኝ።

ከሳኦል ሞት በኋላ በእስራኤል ምድር ብዙ መደናገር ተነሥቶ ነበር። እስራኤላውያን ከፍልስጥኤማውያን ጋር ባደረጉት ጦርነት በመሸነፋቸውና ሳኦል በመሞቱም ፍልስጥኤማውያን አብዛኛውን ማዕከላዊ የእስራኤል ግዛት ሳይቆጣጠሩ አልቀሩም። ይሁንና የይሁዳ ነገድ ወደ ዳዊት በመምጣት ዳዊትን ለንጉሥነት ቀባው። የቀሩት የእስራኤል ነገዶችና የእስራኤል ጦር አምስት ዓመታት በፍልስጥኤማውያን ተጽዕኖ ሥር ከወደቁ በኋላ፥ ኢያቡስቴ የተባለውን የሳኦልን ልጅ የእስራኤል ንጉሥ ይሆን ዘንድ ቀቡት፤ በዚህም ምክንያት ዳዊትን በተከተሉት በይሁዳ ነገድና ኢያቡስቴን በተከተሉት በቀሩት የእስራኤል ነገዶች መካከል ለሁለት ዓመታት የማያቋርጥ ጦርነት ተካሄደ። ከኢያቡስቴ ጎን የነበረው ዋና ኃይል የእስራኤል ጦር አዛዥ አበኔር ነበር። ቀስ በቀስ ዳዊትና ከጎኑ ያለው ጦር ከኢያቡስቴና ከጎኑ ካለው ጦር ይልቅ እየበረታ መጣ። ቀጥሎም የጦር አዛዥ የነበረው አበኔር ከዳዊት ጎን ለመቆም ተስማማ። ይህም የእርስ በርስ ጦርነቱን ወደ ፍጻሜ እንዲመጣ አደረገው። የዳዊት ጦር አዛዥ የነበረው ኢዮአብ ግን የወንድሙን የአሣሄልን ደም ለመበቀል አበኔርን ገደለው። በዚህ ድርጊቱ ዳዊት ኢዮአብን ለመቅጣት ቢፈልግም እንኳ በቂ ኃይል ስላልነበረው አልቻለም። ሰሎሞን በዙፋኑ ላይ እስከተቀመጠ ድረስ ኢዮአብ በድርጊቱ ሳይቀጣ ቆየ (1ኛ ነገሥት 2፡5-6፥ 29-35)።

ኢያቡስቴም የራሱ ወገን በሆኑ ሁለት ሰዎች ተገደለ። ገዳዮቹ ዳዊት ይሸልመናል ብለው ወሬውን ይዘው መጡ። ዳዊት ግን ስለዚህ ድርጊታቸው በሞት ቀጣቸው። ከዚያም የእስራኤልም መሪዎች ተሰብስበው ዳዊትን አነሡት። በዚህ ዓይነት አገሪቱ በአንድ መሪ የምትመራ አንድ አገር ስለሆነች የእርስ በርሱ ጦርነት ያበቃል።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) ዳዊት ለሳኦል ቤተሰብ ከነበረው ዝንባሌ በቀልን ስላለመፈጸምና ወደ ሕይወታችን መራርነት እንዳይገባ ስለ መከላከል ምን እንማራለን? ለ) እግዚአብሔር በመሪዎች ላይ ስላለው ቁጥጥርና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምን ያህል ጊዜ መምራት እንዳለባቸው ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: