2ኛ ሳሙኤል 13-19

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከአንድ ተራ የቤተ ክርስቲያን አባል ኃጢአት ይልቅ፥ የአንድ መሪ ኃጢአት ከፍተኛ ችግር የሚያመጣው ለምንድን ነው? ለ) ይህ ከተራ ክርስቲያን ይልቅ በመሪ ላይ ኃጢአቱን የሚያከብደው ለምንድን ነው?

ታላላቅ የእግዚአብሔር ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በከባድ ኃጢአት ይወድቃሉ። ይህም ሲሆን በንስሐ ከተመለሱ እግዚአብሔር ይቅር ይላቸዋል። ብዙ ጊዜ ግን የኃጢአታቸው ውጤት ወይም የሚያስከትለው ክፉ ነገር አይቀርም። እግዚአብሔር ለዳዊት በኃጢአቱ ምክንያት «ለዘላለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም» አለው (2ኛ ሳሙ. 12፡10)።

አንድ መሪ በኃጢአት በሚወድቅበት ጊዜ በተለይም እንደ ዳዊት ዓይነት ከባድ ኃጢአት ከሆነ፥ ብዙውን ጊዜ ውጤቱ ከተራ የቤተ ክርስቲያን አባል ኃጢአት የከፋ ነው። መሪውን የሚመለከተው በርካታ ሰው ስላለ፥ ኃጢአቱ የሚያመጣው ችግር ከሌሎች ሁሉ የላቀ ነው። በሚሰርቅበት ጊዜ ሰዎች ሁሉ በቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ የነበራቸውን እምነት ያጠፋል። ወዲያውኑ ሰዎች አሥራታቸውን መስጠት ያቆማሉ። መሪ ሲያመነዝር የእግዚአብሔርን ስም ያስነቅፋል። በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ካመነዘሩ እኔም ባመነዝር ምንም አይደለም የሚል አስተሳሰብ በሰዎች ዘንድ እንዲፈጠር ያደርጋል። ሰዎች መሪዎቻቸውን ኃጢአትን ሲያደርጉ ካዩ፥ እነርሱም ኃጢአት ያደርጋሉ። 

እግዚአብሔር በዳዊት ላይ ያመጣው ቅጣት ቤተሰቡንም የሚጨምር ነበር። ዳዊት በቤርሳቤህ ላይ የሠራውን ኃጢአት የዳዊት ልጅ መድገሙን ማየት የሚገርም ነው። አምኖን የተባለው ልጁ በከፊል እኅቱ የሆነችውን ልጃገረድ አስገድዶ ደፈራት። እንዲሁም ዳዊት ኦርዮን እንደገደለ አቤሴሎም የተባለው ሌላው ልጁም፥ ነፍስ አጠፋ።

የመሪ ኃጢአት የሚያስከትላቸውን ነገሮች ማንም ሰው ሊወስን አይችልም። ኃጢአት ለመሪ እጅግ አስከፊ ወይም ታላቅ መስሎ ላይታየው ይችላል። መሪው፥ የሠራውን ኃጢአት የመጨረሻ ውጤት ለማወቅና ለመቆጣጠር አይችልም። ኃጢአት ልጆችን እርስ በርስ በማናከስና በእግዚአብሔር ላይ እንዲያምፁ በማድረግ ቤተሰብን ያፈርሳል። ኃጢአት መከፋፈልን እንዲነሣ በማድረግም ቤተ ክርስቲያንን ሊያጠፋ ይችላል። በአጠቃላይ የአንድ አካባቢ አብያተ ክርስቲያናትን በሙሉ ሳይቀር ሊነካ ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ ሕይወት መኖር እንዳለባቸው ይህ ነገር ምን ያስተምረናል? 

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ሳሙኤል 13-19 አንብብ። ሀ) አምኖን የፈጸመው ኃጢአት ምንድን ነው? ) አቤሴሎም የፈጸመው የመጀመሪያው ኃጢአትስ ምን ነበር? ) አቤሴሎም እግዚአብሔር አስቀድሞ የተናገረውን ትንቢት ከፍጻሜ የሚያደርስ ሌላ ምን አደረገ? (2ኛ ሳሙ. 12፡10)። 

ዳዊት ኃጢአት ከሠራ ጥቂት ጊዜ በኋላ፥ በኃጢአቱ ምክንያት በእርሱና በቤተሰቡ ላይ የተሰጠው ፍርድ ተግባራዊ ይሆን ጀመር። የሚከተሉት ችግሮች እግዚአብሔር በ2ኛ ሳሙ. 12፡10 የተናገረውን ትንቢት እንዴት እንደፈጸሙ ተመልከት፡

  1. የዳዊት ታላቅ ልጅ፥ አምኖን፥ የዳዊት ልጅ የሆነችው ከፊል እኅቱን ትዕማርን አስገድዶ ደፈራት (2ኛ ሳሙ. 13፡1-22)። ትዕማር በጣም ቆንጆ ሴት ስለነበረች፥ ያመመው በማስመሰል ተኝቶ እንድታስታምመው በማድረግ አምኖንን አታለላት። በመጨረሻም አስገድዶ ደፈራት። ከደፈራት በኋላ ግን ሊያገባት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ትዕማር ድንግልናዋን ወንድሟ ስለወሰደ፥ ከእንግዲህ ሊያገባት የሚችል አንዳችም ሰው አልነበረም፤ ስለዚህ ሕይወቷ ተበላሸ። ወደ ወንድሟ ወደ አቤሴሎም ቤትም ሄደች። አቤሴሎም ይህንን ነገር ለመበቀል ሤራ ማውጠንጠን ጀመረ።
  2. አቤሴሎም የእኅቱን ነውር ለመበቀል አምኖንን ገደለ (2ኛ ሳሙ. 13፡23-39)። አቤሴሎም አምኖንን ከቤተ መንግሥቱ ራቅ ብሉ በሚገኝ ስፍራ ሊገናኘው ዐቀደ። በዕቅዱም መሠረት አምኖንን ገደለና ወደ አያቱ ቤት ወደ ጌሹር ሸሸ። አምኖንን በመግደሉ በሕይወት ከነበሩት የዳዊት ልጆች መካከል ከአምኖን ቀጥሎ ያለ እርሱ ስለነበር፥ ዙፋን የመውረስ መብቱንም አመቻቸ። 

ነቢዩ ናታን በዳዊት ላይ የተናገረው መልእክት መፈጸም ጀመረ። ትልቁ የዳዊት ልጅ አምኖን በሰይፍ ተገደለ። ይህ ክፉ ነገር የተፈጸመውና የዳዊትን ቤት ለማጥፋት ሲቀጥል የምናየው ለምንድን ነው? እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለ ተናገረ ነው? ወይስ የዳዊትም ስሕተት አለበት?

የቤተሰቡ ችግር መነሻ ማለትም ችግሩ የጀመረውና እንዲቀጥልም የሆነው፥ ዳዊት ቤተሰቡን ስላልተቆጣጠረና ልጆቹንም ባጠፉ ጊዜ ስላልቀጣቸው ይመስላል። ዳዊት አምኖን ያደረገውን ነገር ከተረዳ በኋላ ከመቅጣት ታቅቧል (2ኛ ሳሙ. 13፡2)። ደግሞም አቤሴሉም አምኖንን ከገደለ በኋላ ዳዊት አቤሴሎምን አልቀጣውም።

በቤተሰብ ውስጥ ሥነ -ሥርዓት ከሌለ፥ ልጆች ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን በመተው ወደ ሥርዓተ-አልበኝነት ያዘነብላሉ። አብዛኛዎቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሆኑ ሰዎች ልጆች ጌታን የማይከተሉበትና ሰነፎች፥ ትዕቢተኞችና ኃጢአተኞች በመሆን ምስክርነታቸውን የሚያበላሹበት አንዱ ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል። ብዙ የመሪዎች ልጆች የሚወድቁባቸው ሁለት ምክንያቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው፥ ወላጆቻቸው የጌታን ሥራ በመሥራት በጣም የተወጠሩ በመሆናቸው ተገቢ ትኩረትና ፍቅር ከወላጆቻቸው ሊያገኙ ባለመታደላቸው ነው። እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ወላጅ ልጆቹን በሚገባ እንዲይዝና በጌታ መንገድ እንዲመራቸው ኃላፊነት ሰጥቶታል። ልጆቻቸውን በእግዚአብሔር ፍርሃትና በፍቅር ሊያሳድጓቸው ካልቻሉ በአገልግሎት ላይ መቆየት እንኳ የለባቸውም (1ኛ ጢሞ. 3፡4-5 ተመልከት)። ሁለተኛው፥ ለልጆቻቸው በጣም የሚሳሱ ይሆኑና ያበላሿቸዋል። ልጆቻችንን በጌታ መንገድ ማሳደግ ፍቅርና የሥነ ሥርዓት እርምጃ የሚጠይቅ ነው። ክፉና በጎውን መለየት ከጀመሩበት ከዝቅተኛ ዕድሜያቸው አንሥቶ ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን ነገር ለማሳየት ሥነ-ሥርዓትን ማስለመድ አለብን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ልጆች ብዙ ጊዜ ደካማ ባሕርይ የሚያሳዩት እንዴት ነው? ለ) ይህ የሚሆነው ለምን ይመስልሃል? ሐ) እግዚአብሔርን በሚያስከብርና ጌታን እንዲከተሉ በሚያበረታታ መንገድ ልጆችን ለማሳደግ አንተና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እርስ በርስ ለመረዳዳት ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  1. አቤሴሎም በዳዊት ላይ ዓመፀና ዙፋኑን ለመንጠቅ ሞከረ (2ኛ ሳሙ. 14-19)። ከቤትህ አይጠፋም የተባለለት ሰይፍ፥ የዳዊትን የራሱን ሕይወት እንኳ ለማጥፋት ተፈታተነው። ይህ ነገር በእስራኤል የእርስ በርስ ጦርነት ከማስነሳቱ ሌላም ዳዊት ሕይወቱን ለማዳን ሸሽቶ እንዲደበቅና ለጊዜውም ቢሆን ዙፋኑን ለአቤሴሎም እንዲለቅ አደረገ።

ዳዊት ልጁ አቤሴሎም በቤተ መንግሥት ከእርሱ ጋር ባለመሆኑ አዝኖና አልቅሶ ነበር፤ ነገር ግን አቤሴሎምን ወደቤት ሊያስመጣውና እንደ ቀድሞ ሊያየው ፈቃደኛ አልነበረም። ከኢዮአብ ልመናና ጥረት በኋላ ይህ ነገር ተፈጸመ። አቤሴሎም ወደ ቤት ከመጣም ወዲህ ዳዊት ይቅር ሊለውና ሊያየው ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ዳዊት ሊያየው ሊያነጋግረው ፈቃደኛ ስላልሆነ አቤሴሎምም በንጉሡ ላይ አማረረ። ቀስ በቀስም የሕዝቡን ልብ ወደ ራሱ በመስረቅ፥ ዙፋን ላይ ለመውጣት ይጥር ጀመር። ይህን ለማድረግ ተሳካለትና አንድ ቀን ዳዊትን ገድሎ ዙፋን ላይ ለመውጣት ተዘጋጅቶ መጣ። ዳዊት ከመዋጋት ይልቅ፥ ከብዙ ዓመታት በፊት ከሳኦል እንደ ሸሽ፥ ከአቤሴሎምም ሸሽቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ። ይህም ነገር የዳዊት ጠላቶች የነበሩ እንደ ሳሚ ያሉ ሰዎች ሁሉ በግልጥ እንዲነሡ አደረጋቸው። እንደ ሲባ ያሉ የዮናታን ልጅ ባሪያ የነበሩ ሰዎችም ሜምፌቦስቴን በሐሰት ወንጅለው የሳኦልን ምድር ተቆጣጠሩ። ዳዊት እንዳይያዝና እንዳይገደል ያደረገው፥ የቅርብ ወዳጁና አማካሪው የነበረው አርካዊው ኩሲ ለአቤሴሎም የሰጠው የተሳሳተ ምክር ብቻ ነበር። 

በእስራኤልም ውስጥ ታላቅ የእርስ በርስ ጦርነት ተጀመረ። በመጨረሻም የዳዊት ጦር የአቤሴሎምን ጦር አሸነፈ። ረጅም ጠጉር የነበረው አቤሴሎምም በዛፍ መሐል ተንጠልጥሎ ሞተ። የንጉሡን ትእዛዝ በመጣስ ኢዮአብ አቤሴሎምን ገደለው። ዳዊት በልጁ በአቤሴሎም ሞት ምክንያት የመረረ ኃዘን አዘነ። በኢዮአብ ምክር ግን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ዙፋን ላይ ዳግመኛ ተቀመጠ። ዳዊት በዚህ አጋጣሚ ጠላቶቹን ለመበቀል አልፈለገም፤ በኋላ ግን እንዲበቀልለት ልጁን ሰሎሞንን አዝዞት ነበር (1ኛ ነገሥት 2፡8-9፡ 36-46)።

ይህ የእርስ በርስ ጦርነት በመጨረሻ በይሁዳና በቀሪው የእስራኤል ክፍል መካከል የተፈጠረውን መከፋፈል መነሻ ጠቁሟል። አሥሩ ነገዶች ዳዊትን በእስራኤል ላይ እንደ ነገሠ ንጉሥ ሳይሆን፥ እንደ ግል ንብረታችሁ ነው የምትጠብቁት ብለው የይሁዳን ነገድ ወቀሱ። የይሁዳ ሰዎች ከእስራኤል መሪዎች ጋር በዚህ በመከራከራቸው በእስራኤል መካከል መለያየትን አመጣ። ሰሎሞን ከነገሠ በኋላ ይህ ክፍፍል እውን ሆነና አሥሩ ነገዶች የራሳቸውን ንጉሥ ሲሾሙ፥ የይሁዳ ነገድም የራሱን ንጉሥ ሾመ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከእነዚህ ታሪኮች ውስጥ በዳዊት ሕይወት ከተፈጸሙት ችግሮችና ኃዘን የምንማራቸውን አንዳንድ መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) የምንማራቸው አንዳንድ መልካም ነገሮችስ የትኞቹ ናቸው? ሐ) ልንጠነቀቅባቸው የሚገቡ ነገሮችስ የትኞቹ ናቸው? መ) ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ለማስተማርና ለማስጠንቀቅ እነዚህን ምዕራፎች እንዴት መጠቀም ይቻላል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: