ክርስቲያን መሪዎችን ለመጣል ሰይጣን ብዙ ጊዜ የሚጠቀምባቸው ሦስት ዋና ዋና ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው፥ ፍትወተ ሥጋ ነው። ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ባመነዘረ ጊዜ በዚህ ኃጢአት እንዴት እንደወደቀ ተመልክተናል። የመሪን ልብ ከእግዚአብሔር ለማሸሽ ሰይጣን የሚጠቀምበት ሁለተኛው ነገር፥ ሀብት ነው። ሦስተኛው ደግሞ፥ ትዕቢት ነው። ሰይጣን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሥልጣናቸው፥ በኃይላቸው፥ በትምህርታቸው፥ ወዘተ. እንዲታበዩ ይፈታተናቸዋል። እግዚአብሔር ትዕቢተኛውን ሰው እንደሚያዋርድ ስለሚያውቅ፥ ሳይጣን አንድን መሪ ትዕቢት ሲጀምረው ሊያጠፋው እንደሚችል ያውቃል።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ሦስት ኃጢአቶች የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ሲያስቸሩ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ሰይጣን መሪዎችን በእነዚህ ሦስት ነገሮች እንዲወድቁ የሚያደርገው ለምን ይመስልሃል? ለ) ሕይወትህን መርምር። ሰይጣን በዚህ መንገድ በኃጢአት እንድትወድቅ አድርጎሃልን? ከሆነ ኃጢአትህን ተናዘዝና የተቀደሰ ሕይወት ኑር።
በዳዊትና በጠላቶቹ መካከል ሰላም በወረደና መንግሥቱ እያደገ በሄደ ጊዜ ስለ ኃያል መንግሥቱ ታበየ። ምን ያህል ታላቅ ሠራዊት እንዳለው በማወቅ ይመካና ይኮራ ዘንድ፥ በእስራኤል ውስጥ ያሉ ተዋጊ ሰዎች ሁሉ እንዲቆጠሩ በማድረግ የትዕቢተኝነት ምልክትን አሳየ። ነፍሰ ገዳይ የሆነው ኢዮአብ እንኳ ይህ ነገር ስሕተት መሆኑን አውቆ ነበር። ዳዊት ግን የግድ ቆጠራው እንዲካሄድ ስላለ በሕዝቡ ላይ ፍርድን አስከተለ (2ኛ ሳሙ. 24)።
በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት በማድረግ አመንዝራነትን ከፈጸመበት ጊዜ አንሥቶ፥ የዳዊት መንግሥት ችግሮች ይፈጠሩበት ጀመር። ዛሬ በሥልጣን ዘመኑ መጨረሻ አካባቢ ዳዊትን ስለገጠሙት የተለያዩ ችግሮች እንመለከታለን።
የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ሳሙ. 20-24 አንብብ። ሀ) የዳዊት መንግሥት መፈራረስ የጀመረው እንዴት ነው? ለ) እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የላከው ፍርድ ምን ነበር? ለምን? ሐ) የዳዊት ኃያላን የጦር ሰዎች ካደረጓቸው ታላላቅ ነገሮች አንዳንዶቹን ጥቀስ። መ) እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ፍርድን እንዲያመጣ ያደረገው ዳዊት የሠራው ኃጢአት ምንድን ነው? ሠ) ዳዊት መሠዊያን የሠራው የት ነው? ለምን?
- ከሳቤዔ ጋር የተደረገ የእርስ በርስ ጦርነት (2ኛ ሳሙ. 20)፡
ከአቤሴሎም ሞት በኋላ የዳዊት ችግሮች ቀጠሉ። በመጀመሪያ በዳዊት ልጅ በአቤሴሉም የተቀሰቀሰ ሕዝባዊ ጦርነት ነበር። ይህ ጦርነት እንዳበቃ የቢክሪ ልጅ ከሆነው ከሳቤዔ ጋር ሌላ ጦርነት ተጀመረ። ይህ ጦርነት በይሁዳና በቀረው የእስራኤል ነገድ መካከል የተካሄደ ነበር። ዳዊት ኢዮአብ ልጁን አቤሴሎምን መግደሉ አስቆጥቶት እንደነበር የምናየው የጦር አዛዥነቱን ከእርሱ ወስዶ ለአሳይ በመስጠት ሳቤዔን እንዲወጉ ለአሳይና ለአቢሳ ትእዛዝ ሲሰጣቸው ነው፤ ነገር ግን ኢዮአብ በወታደሮቹ ዘንድ እንደ ጦር አዛዥ የሚታይ ስለ ነበር ይህን በሰማ ጊዜ አሜሳይን ገደለው። በአቤል ቤትመዓካ በተባለች ከተማ ያለች አንዲት ሴት፥ ኢዮአብና ጦሩ ከተማይቱን እንዳያጠፉ ሳቤዔን መግደል እንዳለባቸው ሕዝቡን አሳመነች።
- በእስራኤል ምድር ላይ የመጣ ራብ (2ኛ ሳሙ. 21) በ2ኛ ሳሙኤል የመጨረሻ ክፍሎች ያሉት ታሪኮች ምናልባት በጊዜ ቅደም ተከተል የቀረቡ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ዳዊትን ስለገጠሙት ችግሮች የሚናገሩት ክፍሎች በሙሉ በአንድነት በመጽሐፉ መጨረሻ ሳይሰፍሩ አልቀሩም።
በዳዊት ዘመነ መንግሥት፥ በአንድ በተወሰነ ጊዜ ታላቅ ራብ ለሦስት ዓመታት ሆነ። የዚህ ራብ ምክንያት ምን እንደሆነ ዳዊት እግዚአብሔርን በሚጠይቅበት ጊዜ፥ ሳኦል የገባዖንን ሰዎች በመግደሉ ምክንያት ነው አለው።
የውይይት ጥያቄ፥ ኢያሱ 9፡15፥ 18-26 አንብብ። ሀ) የገባዖን ሰዎች እነማን ናቸው? ለ) ከእስራኤል ጋር የገቡት ቃል ኪዳን ምን ነበር?
የገባዖን ሰዎች የከነዓናውያን አንድ ነገድ ሆነው፥ በእስራኤል መካከለኛ ክፍል የሚኖሩ ነበሩ። ከ400 ዓመታት በፊት እስራኤላውያንን በማታለል አይሁድ እንዳይጎዷቸው ቃል አስገብተዋቸው ነበር። ሳኦል የገባዖንን ሰዎች የወጋው መቼ እንደሆነ አይታወቅም። ምናልባት በሳኦል በመጀመሪያዎቹ የንግሥና ዘመን ሳይሆን አይቀርም። በገባዖን ሰዎችና በእስራኤል መካከል የተደረገውን ስምምነት በመጣስ፥ ከብሔራዊ ቅንዓት ተነሥቶ የገባዖንን ሰዎች ለማጥፋት የሞከረ ይመስላል። ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ ይህንን ስምምነት በማፍረሳቸው እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ ራብ በማምጣት በሕዝቡ ላይ ፈረደ።
ዳዊትም ይህን ነገር ለመበቀል ምን እንደሚፈልጉ የገባዖንን ሰዎች በጠየቃቸው ጊዜ፥ የሳኦልን ሰባት ወንዶች ልጆች እንዲሰጣቸውና እንዲገድሉአቸው ጠየቁ። 7 ቁጥር የፍጹምነት ቁጥር ነው። የተገደሉት የገባዖን ሰዎች በርካታ ቢሆኑም የ7ቱ የሳኦል ወንድ ልጆች መገደል በሳኦል ቤት ላይ ሊደርስ የሚገባውን ፍርድ ያሟላል ማለት ነበር። እንደተባለውም 7ቱ የሳኦል ዝርያዎች ተገደሉ።
ይህ እጅግ አሳዛኝ የሆነ ታሪክ አንድ ዋና ዓላማ አለው። እግዚአብሔር ልጆቹ የገቡትን ቃል ኪዳን ይጠብቁ ዘንድ ምን ያህል እንደሚፈልግ ያሳየናል። ከ400 ዓመታት በፊት እስራኤላውያን የገባዖንን ሰዎች ላለመግደል ቃል ገብተዋል፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ቃላቸውን ይጠብቃሉ ብሉ ተስፋ አደረገ። ሰዎች ለእግዚአብሔር ቃል ሲገቡ ለመፈጸም ምንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆን፥ የገቡትን ቃል መጠበቅ አለባቸው። ቃላቸውን በማይጠብቁበት በማንኛውም ጊዜ ከእግዚአብሔር ፍርድ ሥር ይወድቃሉ።
የውይይት ጥያቄ ሀ) እግዚአብሔር የምንገባውን ቃል መጠበቃችንን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚከታተል ይህ ምን ያስተምረናል? ለ) ለእዚአብሔርም ሆነ ለሌሎች የገባነውን ቃል ኪዳን መጠበቅ ምን ያህል ከእኛ እንደሚፈለግ፥ ከዚህ ምን እንማራለን? ሐ) ሰዎች ዛሪ ደጋግመው የሚገቧቸውን ቃል ኪዳኖች በምሳሌነት ጥቀስ። መ) ለእግዚአሔር የገባሃቸውን አንዳንድ ቃል ኪዳኖች ጥቀስ። ሠ) እነዚህን ቃል ኪዳኖች ጠብቀሃል ወይስ አልጠበቅክም? ለእግዚአብሔር የገባሃቸው አንዳንድ ቃሎች ካሉ የእግዚአብሔር በረከት ወደ ሕይወትህ እንዲመጣ በዚህ ሳምንት ፈጽማቸው።
- የዳዊት ትዕቢትና የሠራው መሠዊያ (2ኛ ሳሙ. 24)፡-
በ2ኛ ሳሙኤል የሚገኘው የመጨረሻ ምዕራፍ ዳዊት የፈጸመውን አንድ ተጨማሪ ኃጢአት ይነግረናል። ይህ ኃጢአት በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ጥፋትን አስከትሏል። እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ የተቆጣው ለምን እንደሆነ አናውቅም (2ኛ ሳሙ. 24፡1 ተመልከት)። አንዳንድ ምሁራን እስራኤላውያን በዓመፃቸው ዳዊትን ትተው ከአቤሴሎም ጋር በመተባበራቸው ነው ይላሉ። 1ኛ ዜና 21፡1-7 ስንመለከት፡- ቆጠራው እንዲካሄድ ዳዊትን የፈተነው ሰይጣን እንጂ እግዚአብሔር አይደለም ይላል። እነዚህን ሁለት ታሪኮች ስናገናኛቸው፥ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በአንድ ባልታወቀ ኃጢአት ላይ ለመፍረድ ወኪላቸው የሆነውን ዳዊትን እንዲያጠቃ ለሰይጣን የፈቀደለት ይመስላል። ሰይጣንም ዳዊትን ፈተነና በትዕቢት እንዲወድቅ አደረገው። የእስራኤልን ሕዝብ በሙሉ የሚወክል ስለነበር፥ እግዚአብሔር ፍርድን በዳዊት ላይ ብቻ ሳይሆን በእስራኤል ሁሉ ላይ አመጣ።
የሠራዊቱ ቆጠራ ዓላማ ዳዊት ምን ያህል ተዋጊ ሰዎች እንዳሉት ለማወቅ ይረዳው ዘንድ ነበር። የተዋጊውን ብዛት ማወቅ የፈለገው ከመታበይ ነበር። ዳዊት በሕይወቱ ዘመን በሙሉ ሲከተለው የነበረውን ዋና ትምህርት ዘነጋ። ድልን የሚሰጥ እግዚአብሔር እንጂ ሰው እንዳልሆነ አስረግጦ ያውቅ ነበር። ሠራዊቱን በማስቆጠር ግን እስከዛሬ ድረስ ላገኘው ድል ምክንያቱ የነበረው ታላቅ ጦር እንጂ የእግዚአብሔር እርዳታ እንዳልሆነ ገለጠ። ይህ በእግዚአብሔር ላይ አለመታመንን የሚያሳይ ትልቅ ምልክት ነበር።
የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ሲሠራ እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ነገር ልናደርግና በእግዚአብሔር ዘንድ ያለንን ታማኝነት ልናጎድል የምንችለው እንዴት ነው?
ስኬታማነት (ለምሳሌ፡- በትምህርታችን፥ በንብረታችን፥ በቤተ ክርስቲያናችን ታላቅነትና ለጌታ በማረክናቸው ነፍሳት ቁጥር ወዘተ. ስንመካ) በራሳችን እንደተገኘ አድርገን ስንቆጥር ዳዊት በወደቀበት ኃጢአት ወደቅን ማለት ነው። መከናወንን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው። ያለ እርሱ አንዳችም መልካም ነገር ማድረግ አንችልም።
ለዚህ ኃጢአት ቅጣት ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ለዳዊት ከሦስት ነገሮች አንዱን ምረጥ አለው። ዳዊትም የሦስት ቀን ቸነፈርን መረጠ። በቸነፈሩም ምክንያት 70000 ሰዎች ሞቱ።
ዳዊትም ፍርዱን የፈጸመው መልአክ ሰዎችን መግደል ወደ አቆመበት ስፍራ ሄደ። ይህ ስፍራ የኢያቡሳዊው የኦርና አውድማ ነበር። ዳዊትም ይህንን አውድማ ገዛና በዚያ ስፍራ መሠሠዊያን ሠራ። ይህ ታሪክ በጣም አስፈላጊ የሆነው፥ ዳዊት መሠዊያን የሠራበት ይህ ስፍራ በኋላ የሰሎሞን ቤተ መቅደስ የተሠራበት ስፍራ ስለሆነ ነው። ይህ ማለት ቤተ መቅደሱ የተሠራው የዳዊት ቤት የንጉሣዊ ቤተሰብ ንብረት በሆነ ስፍራ ላይ ነው ማለት ነው።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)