በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ሰሎሞን በሥልጣን ላይ የነበረበት ዘመን አንዳንድ ጊዜ «ወርቃማው ዘመን» ወይም ለእስራኤል ሕዝብ ከሁሉም የተሻለው ጊዜ በመባል ይታወቃል። በሰሎሞን አመራር፥ የእስራኤል ሕዝብ በዘመኑ እጅግ የታወቁና ገናና ሕዝብ ሆኑ። በብልጽግናና በሰላም የተሞላ፥ እጅግ የሠለጠነ ሕዝብ ሆኖ ነበር፤ ነገር ግን ይህ ለእስራኤል ሕዝብ አደገኛ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፥ ዘዳ. 6፡10-13፤ 8፡7-14 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ጥቅሶች ለእስራኤላውያን የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ምን ነበር? ለ) እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች በቤተ ክርስቲያንህ የተፈጸሙት እንዴት ነው? ሐ) ስደት ሲቀርና መልካም ጊዜ ሲመጣ፥ ብዙ ክርስቲያኖች በኃጢአት የሚወድቁት ለምንድን ነው?
ሰሎሞን ከአባቱ ከዳዊት ታላቅ መንግሥትን ወረሰ። ድንበሩ ከግብፅ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ የሚዘልቅ ነበር። ከጠላቶች ጋር ሰላም ነበር። በምድሪቱ የተትረፈረፈ ነገር ነበር። ሰላምንና ብልጽግናን ለማግኘት ሰሎሞን መዋጋት አልነበረበትም። እንዲሁ ተሰጥተውት ነበር። ሰሎሞን አመራሩን የጀመረው በጥሩ ሁኔታ ነበር። በእግዚአብሔር ላይ ያለውን መደገፍ በማሳየት፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመምራት ይችል ዘንድ ጥበብን ለመነ። እግዚአብሔርም ሰሎሞንን በምድር ላይ ከኖሩ ሕዝቦች ሁሉ የላቀ ጠቢብ ሰው አደረገው። ይህ ጥበቡ በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ ተንጸባርቋል። የሰሎሞን ጥበብ ግን በመንፈሳዊ ሕይወቱ የበሰለ ሰው አላደረገውም። እንደ ዳዊት፥ እግዚአብሔርን በሙሉ ልቡ ማገልገል አልቻለም። ሴቶችን በመመኘት ወጥመድ ውስጥ ወደቀ። በርካታ ባዕዳን ሴቶችን አገባ። እነዚህም ሴቶች ወደ ክሕደትና ወደ ጣዖት አምልኮ መሩት። መጽሐፈ መክብብ ሰሎሞን እግዚአብሔርን በረሳ ጊዜ ስላሳለፈው የከንቱነት ኑሮ ይናገራል።
ሰላምና ብልጽግና ለሰሎሞን አደገኛ ሆነበት። እግዚአብሔርን ረሳ። በራሱ ጥበብና ብርታት ታመነ። ለራሱ ክብር የሚገደው ሰው ሆነ፤ ስለዚህ ለመንግሥቱ ከሁለት መከፈልና መውደቅ በተዘዋዋሪ መንገድ እርሱም ተጠያቂ ሆነ። የእስራኤል መንግሥት የተከፋፈለውና እስከ ዛሬ ድረስ ተመልሶ አንድ ሊሆን እስከማይችል ድረስ የተበተነው ከሰሎሞን ሞት በኋላ ወዲያውኑ ነው። የሰለሞን ኃጢአት በዝርያዎቹ ሁሉ ላይ ከፍተኛ ችግሮችን አምጥቷል። እርሱ የጀመረው የጣዖት አምልኮ ወዲያውኑ አገሪቱን ሁሉ ችግር ውስጥ ዘፈቃት። በመጨረሻም፥ የሰሎሞን ኃጢአት የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ወደ ምርኮ እንዲሄዱ አደረገ።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከሰሎሞን ሕይወት፥ የመሪዎች ኃጢአት በቤተ ክርስቲያን አባሎች ሁሉ ላይ ስለሚያመጣው ነገር ምን ለመማር እንችላለን? ለ) በበረከት ጊዜ ከእግዚአብሔር ስለ መራቅ ስለሚታይ አዝማሚያ ከሰሎሞን ሕይወት ታሪክ፥ የምንማረው ምንድን ነው?
ለብዙ ክርስቲያኖች፥ መንፈሳዊ ሕይወት አስቸጋሪ የሚሆነው በስደት ጊዜ ሳይሆን፥ በበረከት ጊዜ ነው። በስደት ጊዜ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ሊመለከቱና በእርሱ ሊደገፉ ይገደዳሉ። በበረከትና በሰላም ጊዜ ግን እግዚአብሔርን በመርሳት፥ ፊትን ከእርሱ መልሶ ባለመታዘዝ መኖር በጣም የተለመደ ነገር ነው። ለእግዚአብሔር ከመታዘዝ ይልቅ፥ የአኗኗር ስልታችንን የማሻሻሉ ነገር የበለጠ ትኩረት የምንሰጠው ይሆናል። የቤተ ክርስቲያን መሪም ሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ጊዜ በኃጢአት የሚወድቁት በበረከት ጊዜ ነው።
የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ነገሥት 1-11 አንብብ ሀ) ሰሎሞን በእስራኤል ላይ ንጉሥ ለመሆን የነበረበት ትግል ምንድን ነው? ለ) ሰሎሞን ያደረጋቸውን ዋና ዋና መልካም ነገሮች ዘርዝር። ሐ) ሰሎሞን ያደረጋቸውን ክፉ ተግባራት ዘርዝር። መ) በሰሎሞን አገልግሎት ውስጥ ነቢያት የነበራቸው ድርሻ ምንድን ነው?
- ሰሎሞን ንጉሥ ሆነ (1ኛ ነገሥት 1-2)
ንጉሡ ዳዊት በሸመገለ ጊዜ፥ ዙፋኑን ለልጁ ለሰሎሞን የሚያስተላልፍበት ወቅት ደረሰ። ልጇ ሰለሞን የዙፋኑ ወራሽ እንደሚሆን ዳዊት ለቤርሳቤህ ቃል ገብቶላት ነበር (1ኛ ነገ. 1፡17)። ይህ የታወቀ ነገር ይመስላል። ሰሎሞን ግን በሕይወት ያለ ትልቁ ልጅ ስላልነበረ ዙፋኑ በተለመደው መንገድ የሚገባው ለእርሱ አልነበረም። የዳዊት ትልቁ ልጅ አምኖን ሞቶ ነበር። የሚቀጥለው ትልቁ ልጅ ዶሎሕያ (2ኛ ሳሙ. 3፡3) የሞተ ይመስላል። እንዲሁም ሦስተኛው ታላቅ ልጅ አቤሴሎምም ሞቶአል። በዚህ ጊዜ በሕይወት ያለ ትልቁ ልጅ አዶንያስ ነበር፤ ስለሆነም ከውርስ መብት አኳያ በሕይወት ያለው ታላቁ ልጅ እንደመሆኑ፥ አዶንያስ መንገሥ ነበረበት። ዳዊት ንጉሥ አድርጎ እስኪመርጠውና ይህንንም ይፋ እስኪያደርግ ከመጠበቅ ይልቅ ትልቅ ወንድሙ አቤሴሎም እንዳደረገው፥ እርሱም በኃይል ለመንገሥ ሙከራ አደረገ። ታዋቂ ለመሆንና ሕዝቡ ንጉሥ ብለው እንዲጠሩት ለማድረግ ሞከረ።
ይህንን ነገር ነቢዩ ናታን፥ ጋድና የሰሎሞን እናት ቤርሳቤህ ሲሰሙ፥ ለዳዊት ነገሩትና ሰሎሞንን በግልጥ እንዲያነግሠው ገፋፉት። ዳዊትም እንዲሁ አደረገ። በመጀመሪያ በግል፥ ቀጥሉም በሕዝቡ ሁሉ ፊት ዳዊት ሰሎሞንን አነገሠው።
ዳዊት ሰሎሞንን እግዚአብሔር በሙሴ በኩል የሰጠውን ትእዛዝ በሙሉ በጥንቃቄ እንዲጠብቅ በሚገባ አስጠነቀቀው። በተጨማሪ በሕይወት ዘመኑ በደል ያደረሱበትን ኢዮአብን፥ ሳሚን ሌሎችንም እንዲቀጣለት አዘዘው። ዳዊትም ለ40 ዓመታት ከነገሠ በኋላ ሞተ።
ሰሎሞንም ወዲያውኑ መንግሥቱን ማጠናከር ጀመረ። በመጀመሪያ፥ ወንድሙን አዶኒያስን የሚገባውን ነገር አደረገ። በመካከለኛው ምሥራቅ ባሕል፥ አንድ ልጅ ንጉሥ በሚሆንበት ጊዜ፥ ዙፋኑ ይገባናል ብለው የሚገምቱ ሰዎችን በሙሉ በመንግሥቱ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ይገድላቸው ነበር። ሰሎሞን ግን ይህን አላደረገም፤ ወንድሙን ኦዶኒያስን ግን ምንም ዓይነት የዓመፅ ሙከራ ቢያደርግ ሕይወቱን ሊያጣ እንደሚችል አስጠነቀቀው። አዶኒያስ የሰሎሞንን ቁባቶች መጠየቁ የዓመፅ ምልክት ነበር። በጥንት ባሕል ሥልጣኑን ሁሉ ከአባቱ ለመውረሱ ምልክት ይሆን ዘንድ፥ አዲሱ ንጉሥ የቀድሞውን ንጉስ (የአባቱን) ቁባቶች ሁሉ ይወስድ ነበር፤ ስለዚህ አዶኒያስ የአባቱን ቁባቶች ሲጠይቅ ጥያቄው በዙፋኑ ላይ የመቀመጥ ጥያቄ መሆኑን ተገንዝቦ ሰሎሞን አዶኒያስን ገደለው።
በሁለተኛ ደረጃ፥ ሰሎሞን በዳዊት ላይ ዓምፆ የነበረውን ሊቀ ካህኑን አቢያታርን አስወገደ። ይህ ከብዙ ዓመታት በፊት ሊቀ ካህን የመሆኑ መብት ከቤተሰቡ እንደሚወሰድ ለዔሊ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜ መሆኑ ነው (1ኛ ሳሙ. 2:27-37፤ 1ኛ ነገ. 2፡26-27)።
ሦስተኛ፥ ሰሎሞን ኢዮዓብን ለሠራው ወንጀል አስገደለው።
አራተኛ፥ ሳሚ ተገደለ።
የሰሎሞን ታላቅነት ማስረጃዎች (1ኛ ነገሥት 2-10)
ከዳዊት ጋር ካወዳደርነው፥ የ1ኛ ነገሥት ጸሐፊ ስለ ሰሎሞን በመናገር ያጠፋው ጊዜ በጣም አነስተኛ ነው። በእርግጥ አብዛኛው የሰሎሞን ታሪክ ከቤተ መቅደስ ሥራው ጋር የተያያዘ ነው። በጸሐፊው ዓይን ሰሎሞንን ታላቅ ያደረገው ጥበቡና ሌላው ተግባሩ ሳይሆን፥ የቤተ መቅደስ ሥራው ነው። ሰሎሞን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 20 ዓመት አካባቢ ሳይሆን አይቀርም፤ ስለዚህ ይህንን ታላቅ ሕዝብ ለመምራት ችሎታ እንደሌለው ተገነዘበና ዋስትና የማጣት ስሜት ተሰማው። ምን እንደሚፈልግ እግዚአብሔር በጠየቀው ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚመራበትን ጥበብ ጠየቀ (1ኛ ነገ. 3)። እግዚአብሔርም ጥበብን፥ በተጨማሪም ሀብትንና ኃይልን ሰጠው። ሰሎሞንም በምድር ላይ ከነገሡ ነገሥታት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ መሪ ሆነ። ከማንም የላቀ ጠቢብ ነበር። ከዳዊት ጋር ስናወዳድረው ግን በመንፈሳዊ ሕይወቱ ያነሰ ነበር። ሰሎሞን ከእግዚአብሔር ጥበብ ተሰጠው። ይህንንም ጥበብ በተለያየ መንገድ ተጠቀመበት፡-
ሀ. ክፉና ደጉን ለመለየት የሚችል ስለነበረ በጽድቅ ገዛ (1ኛ ነገ. 3፡16-28)።
ለ. መንግሥቱን በሚገባ አደራጀ። ከዚህ ጊዜ በፊት ከነበረው የነገድ «አገዛዝ (አከፋፈል) ዘዴ በተለየ ሁኔታ አገሪቱን በ12 የአስተዳደር ክልሎች ከፋፈላት (1ኛ ነገሥት 4)።
ሐ. ቤተ መቅደሱን በማሠራት ረገድ 7 ዓመታት አሳለፈ (1ኛ ነገሥት 5-6)።
ከ1ኛ ነገሥት ጸሐፊ አመለካከት፥ ሰሎሞን የሠራው ከፍተኛው ነገር የቤተ መቅደሱ ሥራ ነው። የሰሎሞን ቤተ መቅደስ፥ ለብዙ መቶ ዓመታት የቆየና በመጨረሻም በ586 ዓ.ዓ. በባቢሎናውያን የተደመሰሰ ነው። በ520 ዓ.ዓ. ሌላ ቤተ መቅደስ የተሠራ ሲሆን፥ በ70 ዓ.ዓ. ተደምስሶአል። ከዚያ በኋላ እስካሁን ድረስ እንደገና አልተሠራም። ቤተ መቅደሱ በነበረበት ስፍራ ዛሬ እጅግ የተቀደሰው ከሚባሉት መስጊዶች 2ኛ የሆኝው የዓለቱ ክብ ጣራ በመባል የሚታወቀው መስጊድ ይገኛል። ለአይሁድ ይህ ስፍራ በምድር ላይ ከሚገኙ ስፍራዎች ሁሉ እጅግ የተቀደሰ ሲሆን፥ ሙስሊሞችም ደግሞ ያከብሩታል። አይሁድ ቤተ ወመቅደሳቸውን በዚያ ስፍራ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን፥ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይህ ቤተ መቅደስ ጌታ ኢየሱስ በምድር ላይ ለመግዛት ከመምጣቱ በፊት ይሠራል ብለው ያምናሉ።
የቤተ መቅደሱ መጠን ከ500 ዓመታት በፊት ከተሠራው ከመገናኛው ድንኳን በሁለት ዕጥፍ የሚበልጥ ነበር፡፡ የከርሰ-ምድር አጥኚዎች በጥንት ጊዜ ከነበሩ ሰባት አስደናቂ ነገሮች፥ አንዱ ቤተ መቅደሱ እንደነበር ስለሚናገሩ በጣም ትልቅና ያማረ ነበር። የቤተ መቅደሱ ሕንጻ 27 ሜትር ርዝመት፥ 9 ሜትር ስፋት፥13.5 ሜትር ከፍታ ነበረው። በሚከተሉት ክፍሎች የተከፋፈለም ነበር፡
- ቅድስት፡- 9 ሜትር ስፋት፥18 ሜትር ርዝመትና 13.5 ሜትር ከፍታ ነበረው። በውስጡ አምስት የኅብስት ማቅረቢያ የወርቅ ገበታዎች ነበሩት የመገናኛው ድንኳን አንድ ገበታ ብቻ ነበረው፤ አምስት የወርቅ መቅረዞች- (የመገናኛው ድንኳን አንድ መቅረዝ ብቻ ነበረው)፤ እና 1 የዕጣን መሠዊያ ነበር።
- ቅድስተ ቅዱሳን፡- 9 ሜትር ስፋት፥ 9 ሜትር ከፍታና 9 ሜትር የጎን ርዝመት ነበረው። በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ በምድረ በዳ የተሠራውና ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም ያስመጣው የመጀመሪያው የቃል ኪዳን ታቦት ነበር። ክንፎቻቸውን ከግድግዳ ጫፍ እስከ ጫፍ የዘረጉ የሁለት ኪሩቦች ምስል የሚታይ ሲሆን፥ ታቦቱ ከክንፎቻቸው በታች በመሀል ነበር።
- የካህናት አደባባይ፡- ከቤተ መቅደሱ ሕንጻ ወጣ ብሎ የሚገኝ ነበር። 45 ሜትር ስፋትና 90 ሜትር ርዝመት ነበረው። በዚህ ክልል ውስጥ ስፋቱ 9 ካሬ ሜትር ሆኖ 4.5 ሜትር ከፍታ ያለው የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረቢያ ነበር። በተጨማሪ 2.5 ሜትር ከፍታና ዙሪያው 5 ሜትር የሆነ አንድ ትልቅ የነሐስ መታጠቢያ እንዲሁም ሁለት ሜትር ከፍታ ያላቸው 10 ትናንሽ ተንቀሳቃሽ የነሐስ መታጠቢያዎች ነበሩ፤ ደግሞም ንጉሡ ለሕዝቡ ንግግር የሚያደርግበት አንድ ትልቅ የነሐስ መድረክ ነበር።
- የውጪው አደባባይ፡- ይህ አደባባይ ማንኛውም ተራ ሕዝብ ለአምልኮ የሚሰባሰብበት ቦታ ነበር። 90 ሜትር ስፋትና 180 ሜትር ርዝመት ነበረው። ይህ ክፍል አራት በሮች ባሉት የግንብ አጥር የታጠረ ነበር።
ቤተ መቅደሱን የሠሩት ዋናዎቹ የሕንጻ መሐንዲሶች በፎኔሺያ ከምትገኘው በዓለም አቀፍ የባሕር ንግድና ጥበብዋ ከታወቀችው ከጢሮስ ስለነበሩ፥ የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በፍኔሽያ ከሚገኙ ቤተ መቅደሶች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ በርካታ ምሁራን ይስማማሉ።
የቤተ መቅደሱ ሥራ እንዳለቀ፥ እግዚአብሔር ሥራውን መቀበሉንና መቅደሱን ማደሪያው ለማድረግ መስማማቱን ለማረጋገጥ፥ ቤተ መቅደሱን በከብሩ ደመና ሞላው።
የሰሎሞን ጸሎት የእግዚአብሔርን ባሕርይ በጥልቀት መረዳቱን ያሳያል። በሰሎሞን ዘመን ሰዎች አማልክት በአንድ በተወሰነ ስፍራ (ቤተ መቅደስ) የሚገኙ ናቸው ብለው ያምኑ ነበር፤ ሰሎሞን ግን እግዚአብሔር ከቤተ መቅደስ የላቀ መሆኑን ያውቅ ነበር። በእርግጥ ከሰማያትም ሁሉ የላቀ ነበር (1ኛ ነገ. 8፡27)። እግዚአብሔር እንደ እኛ በቦታ የተወሰነ አይደለም። እርሱ በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ መገኘት ይችላል፤ ነገር ግን በአንድ በተወሰነ መንገድ እግዚአብሔር በልዩ ሁኔታ በቤተ መቅደስ እንደሚሆንም ያምን ነበር። የሰሎሞን ጸሎት የእግዚአብሔርን ይቅርታና ጸጋ ለኃጢአተኛው ሕዝብ የጠየቀበት አስደናቂ ጸሎት ነበር።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ዛሬም እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ውስጥ ይኖራል ብለው የሚያስቡት እንዴት ነው? ለ) ዛሬ በተለየ መንገድ እግዚአብሔር ማደሪያ ያደረገው ምንን ነው? (1ኛ ቆሮ. 6፡19 ተመልከት)
አንዳንድ ከርስቲያኖች ዛሬ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን የሚያየው እንደ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ ነው በማለት የተሳሳተ አሳብ ያቀርባሉ። እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚኖር፥ ስፍራው ከሌሎች ስፍራዎች ይልቅ የተቀደሰ ነው ብለው ያስባሉ። ይህ የቤተ ክርስቲያንን ምንነት በተሳሳተ መንገድ መረዳት ነው። ዛሬ እግዚአብሔር የሚያድረው በሕንጻዎች ውስጥ ሳይሆን በሰዎች ውስጥ ነው (1ኛ ቆሮ. 6፡19)። እውነተኛዎቹ ቤተ ክርስቲያኖች ሰዎች ናቸው እንጂ ሕንጻው አይደለም። በአዲስ ኪዳን፥ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል በኢየሱስ ለሚያምኑ ሰዎች ኅብረት እንጂ አንድም ጊዜ እንኳ ለሕንጻ አልተሰጠም። እግዚአብሔር ቤተ መቅደሴ ሕንጻ ሳይሆን በሰዎች ልብ ነው ብሏል።
በቤተ መቅደሱ ሥራ ታሪክ መካከል፥ ሰሎሞን ለራሱ ስለሠራው የቤተ መንግሥት ሕንጻ ሥራ ጥቂት ነገር ተጠቅሷል። የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ሰሎሞን ለራሱ ስለሠራው ቤተ መንግሥት በቀጥታ ባያወግዘውም እንኳ፥ ብዙ እንዳልተደሰተበት ግልጽ ነው። ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የወሰደበት ጊዜ 7 ዓመት ሲሆን፥ የራሱን ቤተ መንግሥት ለመሥራት ግን 13 ዓመት አጥፍቷል። ይህም ሰሎሞን ቅድሚያ የሰጠው ነገር የተሳሳተ እንደነበር ያሳየናል። ከእግዚአብሔር መኖሪያ ይልቅ ለራሱ መኖሪያ ገዶት ነበር።
የውይይት ጥያቄ፥ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ክርስቲያኖችም ይህንኑ በሚመለከት የተሳሳተ ቅድሚያ የሚሰጡት እንዴት ነው?
ከጸሎቱ በኋላ እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገለጠና ባረከው፤ ነገር ግን ከትእዛዛቱ ፈቀቅ እንዳይልም አስጠነቀቀው። አለበለዚያ እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱንም እንደማይቀበልና እንደሚያጠፋው ነገረው። በኋላ የተፈጸመው ነገር ልክ እንደዚሁ ነበር። በሕዝቅኤል ዘመን የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱን ለቅቆ ሄደ (ሕዝ.10)። እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ስላልታዘዙ፥ ባቢሎናውያን ቤተ መቅደሱን ደመሰሱት።
መ. የንግሥተ ሳባ ጉብኝት የሳልሞን ታላቅነት ምልክት (1ኛ ነገ. 10) ኢትዮጵያውያን ስለ ንግሥት ሳባና ስለ ምኒልክ አስደናቂ የሆነ ታሪክ ቢኖራቸውም፥ ሳባውያን በአሁኒቱ ኢትዮጵያ የነበሩ ሰዎች ለመሆናቸው ታሪካዊም ሆነ የከርሰ ምድር መረጃው በጣም ጥቂት ነው። በተጨማሪም የንግሥተ ሳባና የሰሎሞን ልጅ የኢትዮጵያ ንጉሥ ስለመሆኑና የቃል ኪዳኑን ታቦት ሰርቆ ስለማምጣቱ የሚቀርብ መረጃ የለም። ይልቁንም በርካታ የከርሰ ምድር አጥኚዎች ሳባ በደቡብ ምዕራብ ዓረቢያ በየመን አካባቢ የምትገኝ አገር ናት ብለው ያምናሉ።
የንግሥት ሳባ ታሪክ ዓላማ፥ የሰሎሞን ዝና በዓለም ሁሉ እንዴት ተሰራጭቶ እንደ ነበር ለማሳየት ነው። ሰሎሞን በጥበቡ፥ ለእስራኤል ባስገኘው ብልጽግናና ከፍተኛ ሕንጻዎችን በመገንባቱ ዝናን አትርፎ ነበር።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)