የ1ኛና የ2ኛ ነገሥት የጊዜ ቅደም ተከተል

የነገሥታት ዘመን በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች መከፈሉን ቀደም ሲል አይተናል። የመጀመሪያው ደረጃ ሳኦል፥ ዳዊትና ሰሎሞን በየተራ የነገሡበት የተባበረው የእስራኤል መንግሥት ሲሆን፥ ይህ ጊዜ ከ1050 እስከ 931 ዓ.ዓ. ድረስ የቆየ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፥ የተከፋፈለው መንግሥት የቆየበት ጊዜ ሲሆን በሦስቱ ነገሥታት ዘመን በአንድነት የቆየችው አገር ለሁለት ተከፍላ፡- በሰሜን እስራኤል፡ በደቡብ ይሁዳ የሚል መንግሥት ተቋቁሞ ነበር። ይህ ዘመን ከ931-586 ዓ.ዓ. ድረስ ቆይቷል።

1ኛ ነገሥት በተባበረው መንግሥትና ለሁለት በተከፈለው መንግሥት መካከል ስለ ነበረው የሽግግር ጊዜ የሚገልጥ ነው። በአንድነት በቆየው መንግሥት የነገሠው የመጨረሻው ሰው የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ነበር። የ1ኛ ነገሥት ታሪክ የተቀረጸበት ጊዜ ዳዊት ከሞተበት ከ970 ዓ.ዓ. እስከ 853 ዓ.ዓ. ድረስ ነበር።

አንድ በነበረው በእስራኤል መንግሥት ላይ የነገሡት ነገሥታት እያንዳንዳቸው 40 ዓመታት ገዝተዋል። አንዳንድ ምሁራን ሳኦል፥ ዳዊትና ሰሎሞን የነገሡበትን ጊዞእ በሚከተለው ሁኔታ ይገልጻሉ፡-

ሳኦል – 1050-1010 ዓ.ዓ. 

ዳዊት – 1010-970 ዓ.ዓ. 

ሰሎሞን – 970-931 ዓ.ዓ.

ለሁለት በተከፈለው የእስራኤል መንግሥት ልናስታውሳቸው የሚገቡን ጊዚያት የሚከተሉት ናቸው፡-

 1. የሰሎሞን ሞትና የመንግሥቱ ለሁለት መከፈል 931 ዓ.ዓ. 
 2. የሰሜኑ መንግሥት ምርኮ 722 ዓ.ዓ. 
 3. የደቡብ መንግሥት ምርኮ 586 ዓ.ዓ.

የሚከተሉትን ነገሮች ልብ በል፡-

 1. በደቡብና በሰሜኑ መንግሥታት ውስጥ የነገሥታት ቁጥር እኩል ነበር።

እያንዳንዳቸው 20 ነገሥታት ነበራቸው። የሰሜኑ መንግሥት አንድ ንጉሥ በሥልጣን ላይ የቆየበት ማዕከላዊ ጊዜ 10 ዓመት ሲሆን፥ የደቡብ ግን 17 ዓመት ነበር። 

 1. የሰሜኑ መንግሥታት ከ930-722 ዓ.ዓ. ድረስ (208 ዓመታት) የቆየ ሲሆን፥ የደቡብ መንግሥት 931-586 (345 ዓመታት) ቆይቷል። 
 2. የሰሜኑ ነገሥታት በቀዳማዊ ኢዮርብዓም 1ኛ የተጀመረውን የጣዖት አምልኮ ማምለክ የቀጠሉ ሁሉም ክፉ የነበሩ ናቸው፤ ነገር ግን ከደቡብ ነገሥታት መካከል ስምንቱ መልካም ሲሆኑ፥ የቀሩት እንደ ዳዊት ስላልነበሩና ለእግዚአብሔር ስላልታዘዙ ክፉ ተብለው ተጠርተዋል። ይልቁንም እነርሱ ጣዖት አምላኪዎች ስለሆኑ ሕዝቡን ወደ ኃጢአት መሩት። 
 3. 2ኛ ዜና በሰሜኑ ሳይሆን በደቡብ መንግሥት ላይ ያተኮረ ነው። 
 4. የአንዳንዶቹ ነገሥታት ዘመናት ተደራራቢ ናቸው። (ለምሳሌ፡- ሕዝቅያስና ምናሴ የኖሩባቸውን ዘመናት ተመልከት)። ይህ የሚሆነው አባቱ በነገሠበት ጊዜ ልጁም የአባቱን የተወሰነ ክልል ይገዛ ስለነበር ነው። እነዚህን የነገሥታት ዘመናት ከሌሎች መጻሕፍት ጋር ብታወዳድር ትንሽ ልዩነት ታያለህ። ይህም የሆነው ምሁራን ስለእነዚህ ዘመናት ፍጹም በእርግጠኝነት መወሰን ስላልቻሉ ነው።

የደቡብ መንግሥት በሙሉ የተገዙት በዳዊት ዝርያ ነው። የሰሜኑ መንግሥት ግን ዘጠኝ የተለያዩ የንጉሣውያን ቤተሰብ ነበራቸው። ቀጥሎ እራቱ ንጉሣውያን ቤተሰብ ተዘርዝረዋል፡-

 1. የኢዮርብዓም ሥርወ-መንግሥት 930-908 ዓ.ዓ. 
 2. የበአሳ ሥርወ-መንግሥት 908-885 ዓ.ዓ. 
 3. የዘንበሪ ሥርወ-መንግሥት 885-841 ዓ.ዓ. 
 4. የኢዩ ሥርወ-መንግሥት 841-752 ዓ.ዓ. 
 5. የመጨረሻዎቹ ነገሥታት 752-722 ዓ.ዓ. 

ከሰሜኑ መንግሥት ሰባት ነገሥታት በሰው እጅ ሲገደሉ፥ አንድ ንጉሥ ራሱን ገሏል፤ አንድ ሌላ ንጉሥ በእግዚአብሔር የተገደለ ሲሆን፥ እንድ ንጉሥ በምርኮ ወደ አሦር መንግሥት ተወስዷል።

በደቡብ መንግሥት አምስት ነገሥታት በሰው እጅ ሲገደሉ፥ ሁለት በእግዚአብሔር መቅሠፍት ተመትተዋል ሦስት ደግሞ ወደ ባዕድ ምድር በምርኮ ተወስደዋል።

በ1ኛ ነገሥት ታሪክ ውስጥ የነበሩ ኃያላን መንግሥታት 

 1. ከ1000-931 ዓ.ዓ. በመካከለኛው ምሥራቅ የነበረ ኃያል መንግሥት የእስራኤል መንግሥት ነበር። ግብፅ በጣም ደካማ ስለነበረች በሰሜን በኩል ከነዓንን የሚፈታተን ጠንካራ መንግሥት አልነበረም። በዳዊት አመራር፥ የእስራኤል መንግሥት በደቡብ እስከ ግብፅ ድረስ፥ በሰሜን ደግሞ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ተስፋፋ። በተጨማሪም ዳዊት የሞዓብን፥ የኤዶምና የኦምንን ወዘተ. መንግሥታት ተቆጣጠረ። እነዚህ መንግሥታት በዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ በኩል የሚገኙ ነበሩ። ሰሎሞን ይህንን ታላቅ መንግሥት ከአባቱ ከዳዊት የተረከበ ሲሆን፥ አብዛኛውን ክፍል እስከ ሞተበት እስከ 931 ዓ.ዓ. ሊያቆየው ችሏል። ከሰሎሞን ሞት በኋላ መንግሥቱ ለሁለት ስለተከፈለች፥ የእስራኤል ኃይል በመዳከሙ፥ ሌሎች መንግሥታት አይለው ተነሡ። በሰሜንና በደቡብ መንግሥታት መካከል የተደረገው የእርስ በርስ ጦርነትም፥ ሁለቱ መንግሥታት በጣም ደካሞች እንዲሆኑ አደረገ። 
 2. ግብፅ፡- በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ግብፅና እስራኤል ይተባበሩ ነበር። ሰሎሞን የግብፁን የፈርዖንን ልጅ ያገባው በዚህ ምክንያት ነው፤ ነገር ግን በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት መጨረሻ አካባቢ ግብፅ የሰሎሞንን መንግሥት የሚቃወሙ ዓመፀኞችን መደገፍ ጀመረች (ለምሳሌ፡- ቀዳማዊ ኢዮርብዓም)። መንግሥቱም ለሁለት እንደተከፈለ፥ የግብፅ ንጉሥ የከነዓንን ደቡባዊ ክፍል አጥቅቶ ከይሁዳ መንግሥት ላይ ወሰደ። የኢየሩሳሌምን ከተማ አጥቅቶ ምርኮ ወሰደ። በ1ኛ ነገሥት ታሪክ ውስጥ በሙሉ ግን የግብፅ መንግሥት እስራኤልን ወይም ይሁዳን የሚፈታተን ጠንካራ ኃይል አልነበረም። 
 3. ሶርያ፡- በእነዚህ ዓመታት በእስራኤል መንግሥት ላይ ችግር ሲፈጥር የነበረ የአሕዛብ ዋና መንግሥት፥ የሶርያ መንግሥት በዚያን ዘመን አረማውያን በመባል ይታወቅ ነበር። ዋና ከተማቸው ደማስቆ ነበር። ከሮብዓም ዘመን (732 ዓ.ዓ.) ጀምሮ ደማስቆ በአሶር መንግሥት እስከተደመሰሰችበት ጊዜ ድረስ፥ የሶርያ መንግሥት ለእስራኤል የማያቋርጥ፥ ለይሁዳ ደግሞ የአንዳንድ ጊዜ ፈተና ነበር (ለምሳሌ፡- ኢሳ. 7)። 
 4. አሶር፡- በ1ኛ ነገሥት ታሪክ መጨረሻ ገደማ፥ የአሶር መንግሥት በኃይል ማደግ ጀመረ። ከ892-648 ዓ.ዓ. ባለው ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ ጠንካራ መንግሥት ሆኖ ቆየ። መጽሐፍ ቅዱስ ባይገልጸውም እንኳ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ የአሦርን መስፋፋት ለመግታት በ853 ዓ.ዓ.፥ ከሌላ መንግሥት ጋር በመተባበር ተዋግቶ ነበር። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑ ዓለማዊ ታሪኮች አክዓብ ከሶርያ ጋር በትብብር ለመዋጋት 2000 ሰረገሎችንና 10000 ወታደሮችን ሰጥቶ እንደነበር ይናገራሉ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: