2ኛ ነገሥት 13-17

ሕይወትንና ቤተ ክርስቲያንን በሚመለከት አንዱ አስደናቂ ነገር የሰው ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ ከሕይወት ወደ ሞት መሆኑ ነው። በሰው አነጋገር፣ እኛ የምንጓዘው ከሕይወት ወደ ሞት ነው። ቤተ ክርስቲያንም እንዲሁ ከሕይወት ወደ ሞት ለማዝገም ትሻለች። ለመከላከል አስቸጋሪ የሆነ የመፈራረስ ሂደት አለ። በመንፈሳዊ አባባል ደግሞ ይህ ሂደት ለእግዚአብሔር ካለን ፍቅር ወደ ሥርዓታዊ የሃይማኖት ልማድ፥ በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያን ሙት ወደምትሆንበት ሁኔታ ያደርሳል። ይህ ሂደት ብዙ ዓመታት የሚወስድ ቢሆንም እንኳ ለማቆም ግን አስቸጋሪ ነው። ይህ ዝንባሌ ያለማቋረጥ ልንዋጋውና ልንታገለው እንደሚገባ ኃይለኛ የስበት ኃይል እንዳለው ማግኔት ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ለእግዚአብሔር የነበረንን የመጀመሪያ ግላዊ ፍቅር ልንጠብቅና እንደ ቤተ ክርስቲያን ያለማቋረጥ ልናድግ እና ለእግዚአብሔር ክብር ልሠራ የምንችለው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በሕይወትህ ይህንን ወደ መንፈሳዊ ሞት የሚወስደውን ዝንባሌ እንዴት ተመለከትከው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ይህን ዝንባሌ የምታየው እንዴት ነው?

የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታትን በምንመለከትበት ጥናታችን፥ በመበላሸትና በመፈራረስ ወደ መንፈሳዊ ሞት የሚወስደውን ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ መመልከት እንችላለን። ምንም እንኳ እግዚአብሔርን የሚፈሩ መሪዎች ሕዝቡን ወደተገቢውና በእግዚአብሔር ላይ ወዳለው ትክክለኛ አምልኮ ለመምራት ቢሞክሩም፥ ሕዝቡ ወደ ጣዖት አምልኮ ለመመለስ ብዙ ጊዜ አይወስድባቸውም ነበር። በኃጢአት መውደቅና ከጌታ መራቅ ቀላል ነገር ነው። መንፈሳዊ መሠረታችንን እንደገና መገንባት ግን ብዙ ጊዜ በጣም አስቸጋሪ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ነገሥት 13-17 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ቁጥሮች የተጠቀሱትን ነገሥታት ዘርዝር። ለ) ስለ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ሥዕላዊ መግለጫ ስጥ። ሐ) በነገሡበት ዘመን ሰለተፈጸሙ ዋና ዋና ነገሮች ጥቀስ። መ) እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ በመፍረድ አይሁድን ወደ ምርኮ እንዲሄዱ ያደረገበት ምክንያት ምንድን ነው? 

  1. የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአካዝ፡- (814-798 ዓ.ዓ.)

የኢዮአካዝ ዘመን ለእስራኤል በጣም አስቸጋሪ ነበር። አዛሄል የተባለው የሶርያ ንጉሥ ያለማቋረጥ እነርሱን የጨቆነበትና በሰሜኑ መንግሥት ክልል ውስጥ ከፊሉን መሬት የወረረበት ጊዜ ነበር። እንደ ኤዶም፥ አሞንና ፍልስጥኤም ያሉ ሕዝቦች እስራኤልን ያጠቁበትም ጊዜ ነበር።

በመጨረሻም ኢዮአካዝ እጅግ ተስፋ ቆርጦ ፊቱን ወደ እግዚአብሔር መለሰና ከእርሱ እርዳታን ጠየቀ። እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ረዳውና የእስራኤልን ምድር በእንግዳ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ከመወሰድ ጠበቀው።

ኢዮአካዝ እግዚአብሔር ቢረዳውም እንኳ ሙሉ ለሙሉ እርሱን አልተከተለም። ይልቁንም ከብዙ ዓመታት በፊት በቀዳማዊ ኢዮርብዓም የተጀመረውን የጣዖት አምልኮ ቀጠለ። 

  1. የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ፡- (798-782 ዓ.ዓ.) 

በዮአስ ዘመነ መንግሥት፥ የሶርያ ንጉሥ የነበረው አዛሄል ስለ ሞተ፥ እስራኤላውያን ከሶርያውያን ይደርስባቸው የነበረው ጭቆና ቀነሰ። ኤልሳዕ ብርቱ ደዌ ታሞ ከሞት አፋፍ ላይ ደርሶ በነበረበት ጊዜ ዮአስ ወደ እርሱ መጣ። ንጉሥ ዮአስ እግዚአብሔርን የማይከተል መሪ ቢሆንም እንኳ፥ የእግዚአብሔር ኃይላት በሙሉ ከእርሱ ጎን እንደሆኑና ኤልሳዕ የእግዚአብሔር ሰው እንደሆነ የተገነዘበ መሪ ነበር። ለዚህ ነው ኤልሳዕን «የእስራኤል ሰረገላና ፈረሰኞች» ብሎ የጠራው። እውነተኛው የእስራኤል ጦር እግዚአብሔር ነበር እንጂ ሌላ ሥጋዊ ጦር አልነበረም። ኤልሳዕ የሶርያን ጦር ሽንፈት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። እስራኤልም ሶርያን ለማሽንፍና ከሰሜኑ የእስራኤል ክፍል የወሰደችውን ግዛት ሁሉ ለማስመለስ ችላ ነበር፤ በተጨማሪ ዮአስ ኤዶምንም ለማሸነፍ ችሉ ነበር።

በዮአስ ዘመነ መንግሥት በይሁዳ ንጉሥ ከነበረው ከአሜስያስ ጋር ጦርነት ተደርጎ ነበር። የእስራኤል ጦር ይሁዳን ለማሸነፍና የኢየሩሳሌምን ቅጥር የተወሰነ ክፍል ለመደምሰስ ችሎ ነበር።

ዮአስ እንደቀሩት የእስራኤል ነገሥታት ሁሉ የጣዖት አምልኮውን ቀጠለ። እግዚአብሔርን ለመፍራትና ለእርሱ ለመታዘዝም አልቻለም።

  1. የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ (796-767 ዓ.ዓ.)

አሜስያስ በይሁዳ ላይ ለብዙ ዓመታት የነገሠ ቢሆንም፥ አብዛኛውን የሥልጣን ዘመኑን ያጠፋው ከልጁ ከታዝያን ጋር ነበር። በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት ይሁዳ በጣም ብርቱ ነበረች። ኤዶምንም ለማሸነፍ ችለው ነበር። ኤዶምን ካሸነፉ በኋላ ግን አሜስያስ ከኤዶም ጣዖትን አስመጣና በኢየሩሳሌም በማቆም አመለከው። ስላገኘው ድል ለእግዚአብሔር ክብርን ከመስጠት ይልቅ ጣዖትን አከበረ።

ቆይቶም አሜስያስ ባለማስተዋል ከእስራኤል ጋር ጦርነት ጀመረና ተሸነፈ (791-790 ዓ.ዓ.)። በዚህ ጊዜ አሜስያስ እስረኛ የነበረና የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዮአስ እስኪሞት ድረስ እንደገና ወደ ሥልጣኑ ለመመለስ ያልቻለ ይመስላል። በእርሱ ምትክ ግን ልጁ ዖዝያን ነግሦ ነበር። በኋላ ግን አሜስያስ ከእስሩ ተለቀቀና ወደ ይሁዳ ተመለሰ። ሕዝቡ ግን ጠልተውት ስለ ነበር ሊገድሉት አሴሩበት። አሜስያስ በዚህ ምክንያት ሸሽቶ ወደ ላኪሽ ከተማ ቢሄድም፥ ያሴሩበት ሰዎች ተከታትለው ገደሉት።

አሜስያስ የጣዖት አምልኮን የሚከተል ክፉ ንጉሥ ነበር። 

  1. የእስራኤል ንጉሥ ዳግማዊ ኢዮርብዓም (793-753 ዓ.ዓ.)

ከዓለም ታሪክ አመለካከት፥ ዳግማዊ ኢዮርብዓም በሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ከነበሩት ታላላቅ ነገሥታት አንዱ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን ስለ እርሱ የተነገረው ነገር በጣም ጥቂት ነው። ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ፍላጎት መንፈሳዊ ታላቅነትን መግለጽ እንጂ የፖለቲካ ዝናን ወይም ችሎታን ማሳወቅ አይደለም። ዳግማዊ ኢዮርብዓም የእግዚአብሔር ሰው ስላልነበረ፥ መጽሐፍ ቅዱስ አያመሰግነውም። በእስራኤል ላይ ለመንገሥ የመጀመሪያው በነበረው በቀዳማዊ ኢዮርብዓም የተጀመረውን የጣዖት አምልኮ ማካሄዱን ቀጠለ።

ከዳዊትና ከሰሎሞን ዘመነ መንግሥት በኋላ እጅግ ሰላምና ብልጽግና የሞላበት፥ ለእስራኤል መልካም የነበረ ጊዜ የዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ነበር። በሰሜን በኩል አንዳችም ኃያል መንግሥት ስላልነበረ ኢዮርብዓም ፖለቲካዊ ተጽዕኖውን እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ለማስፋፋት ችሎ ነበር። እስራኤልም እጅግ ባለጠጋ መንግሥት ሆና ነበር። ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ ያለውን የሶርያን ምድርም ወሰደች።

ሆሴዕና አሞጽ የተባሉት ነቢያት ያገለገሉት በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ነበር። በምድሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ብልጽግና የነበረ ቢሆንም፥ በሀብታምና በድሀ መካከል ከፍተኛ የሆነ የፍርድ አድልዎ ነበር። የሕዝቡ ሥነ-ምግባርም በእጅጉ ድቀት ይታይበት ነበር። ለእግዚአብሔር ባላቸው አምልኮም ግድ የለሾች ነበሩ።

የውይይት ጥያቄ፥ ብልጽግና፥ ወደ ፍርድ መዛባት፥ ወደ ሥነ-ምግባር ድቀት በእግዚአብሔር ላይ ወዳለ የአምልኮ ግድየለሽነት የሚያመራው እንዴት ነው?

  1. የይሁዳ ንጉሥ አዛርያ (ዖዝያን) (791-740 ዓ.ዓ.) 

ከዳዊትና ከሰሎሞን ዘመነ መንግሥት በኋላ፥ በይሁዳ ከነገሡ ታላላቅ ነገሥታት አንዱ ዖዝያን ወይም አዛርያ ነው። ጥሩ የፖለቲካ መሪ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔርን የሚፈራና የሚያመልክም ነበር። ዖዝያን በትረ መንግሥቱን በጨበጠ ጊዜ፥ የይሁዳ መንግሥት – በጣም ደካማ ነበር። ለእስራኤልና ለሶርያ አገልጋይ ነበር። ከዮአስ ሞት በኋላ ግን ይሁዳ ከእስራኤል ጋር መልካም ግንኙነት ነበራት። ዖዝያን የይሁዳን ጦር እንደገና መመሥረት ችሎ ነበር። እንደዚሁም ፍልስጥኤማውያን፥ ዓረቦችንና አሞናውያንን ለማሸነፍም ችሎ ነበር። ከዚህ ቀደም በሰሎሞን ጊዜ ብቻ እንደሆነው፥ ሕዝቡን ባለጸጋና በዚህም ተደስተው የሚኖሩ አደረጋቸው።

በዘመነ መንግሥቱ መጀመሪያ አካባቢ ዖዝያን እግዚአብሔርን አጥብቆ ተከተለ። እጅግ ባለጸጋ የሆነውም እግዚአብሔርን ስለተከተለና የእርሱን ትእዛዛት ስለ ጠበቀ ነበር (2ኛ ዜና 26፡5-7)።

በሥልጣንና በዝና እጅግ ከፍ ባለ ጊዜ ግን ታበየ። ካህናቱ ቢከለክሉትም እንኳ እምቢ ብሎ ወደ ቤተ መቅደስ በመግባት፥ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ዕጣን በመሠዊያው ላይ የማጠን ሥርዓትን ፈጸመ። ይህ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ የማመፅና ትዕቢትን የማሳየት ግልጥ ድርጊት ነበር። የእግዚአብሔር ፍርድ በዚህ ድርጊቱ ምክንያት ፈጣንና ኃይለኛ ቅጣትን መላክ ነበር። ዖዝያን ወዲያውኑ በለምጽ ተመታ። ይህም በሕይወቱ ላይ ዐበይት ውጤቶችን አስከተለ። ሞትን ባይሞትም እንኳ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር እንዳይገናኝ ተገለለ። በቤተ መንግሥቱ ውስጥም ለመኖር አይችልም ነበር። ወደ ቤተ መቅደሱ ለአምልኮ እንደገና መሄድ ጨርሶ አይችልም ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ልጁ ኢዮአታም በይሁዳ ላይ ተባባሪ ገዥ የሆነው። በዖዝያን ዘመነ መንግሥት መጨረሻ አካባቢ የአሦር መንግሥት በኃይሉ እጅግ ገናና እየሆነ ሄደ። ከአሦር ጋር ለመዋጋትና ለማሸነፍ ቢሞክርም አልሆነለትም። ተሸነፈ። ከዖዝያን ሞት በኋላም የይሁዳ መንግሥት ብርታት በፍጥነት እየቀነሰ መጣ። 

ዖዝያን ለ52 ዓመታት የነገሠ ቢሆንም፥ ብቻውን በንጉሥነት ሥልጣን ላይ የቆየው ግን ለ17 ዓመታት ብቻ ነበር። ከዚህ ቀጥሎ ከይሁዳ ታላላቅ ነገሥታት አንዱ የነበረው የዖዝያን ዘመነ- መንግሥት ዋና ዋና ዓመታት ተጠቅሰዋል፡-

797 ዓ.ዓ. አሜስያስ መንገሥ ጀመረ።

791 ዓ.ዓ. ፆዝያን ከአሜስያስ ጋር ይገዛ ጀመር። 

768 ዓ.ዓ. ዖዝያን ለብቻው መንገሥ ጀመረ። 

750 ዓ.ዓ. ዖዝያን በለምጽ ስለተመታ ኢዮአታም ከእርሱ ጋር መንገሥ ጀመረ። 

740 ዓ.ዓ. ዖዝያን ሞተ።

የውይይት ጥያቄ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሚሰምርላቸው ጊዜ በትዕቢት የመውደቅ አደጋ ከፊታቸው እንዳለ፥ ከዖዝያን ሕይወት ምን ለመማር እንችላለን? 

  1. የእስራኤል ንጉሥ ዘካርያስ (753 ዓ.ዓ.)

ዘካርያስ በእስራኤል ላይ ለረጅም ጊዜ ለመንገሥ አልቻለም። ለስድስት ወራት ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ በሻሎም ተገደለ። 

  1. የእስራኤል ንጉሥ ሻሎም (752 ዓ.ዓ.)

የዳግማዊ ኢዮርብዓም ልጅ የነበረውን ዘካርያስን ገድሉ በሥልጣን ላይ ከወጣ ከአንድ ወር በኋላ በምናሔም ተገደለ። 

  1. የእስራኤል ንጉሥ ምናሔም (752-741 ዓ.ዓ.)

ምናሔም በእስራኤል ላይ ለ10 ዓመታት ለመንገሥ ቢችልም፥ ዘመነ መንግሥቱ በጣም አስቸጋሪ ከነበሩት ጊዜያት አንዱ ነው። በዚህ ጊዜ የአሦር ኃይል ስለ ጨመረ፥ ጥቃት እንዳይደርስበት ከፈለገ ለአሦር ንጉሥ ቀረጥ የመክፈል ግዴታ ነበረበት።

  1. የእስራኤል ንጉሥ ፈቃሕያ (741-739 ዓ.ዓ.)

የምናሔም ልጅ የነበረው ፈቃሕያ የመንግሥት ሥልጣን በያዘ ጊዜ፥ የእስራኤል መንግሥት በአሦር መንግሥት ቁጥጥር ሥር ሆኖ አገልጋዩ ነበር። ስለዚህ ፈቃሕያ ብዙ ኃይል አልነበረውም። በእነዚህ ጊዜያት በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ከነበሩት ሰዎች አንዳንዶቹ በአሦር መንግሥት ቁጥጥር መሆናቸውን አይወዱትም ነበር። ከእንደነዚህ ዓይነት ሰዎች አንዱ ፋቁሔ እንደነበር የማያጠራጥር ነው። ፋቁሔ ፈቃሕያን ገደለና የሚቀጥለው የእስራኤል ንጉሥ ሆነ። 

  1. የእስራኤል ንጉሥ ፋቁሔ (739-731 ዓ.ዓ.)

በፋቁሔ ዘመነ መንግሥት ሶርያ ዋናዋ ኃያል መንግሥትና ለእስራኤል መንግሥት ፈተና ነበረች። የሶርያ ኃያል መሆን ለፋቁሔ የፀረ አሦር አቋም ትልቅ እርዳታ ሆኖት ነበር። ረአሶን የተባለው የሶርያ ንጉሥም አሦርን ለመውጋት ከእስራኤልና ከይሁዳ ሕዝቦች ጋር የጦር ቃል ኪዳን ትብብር ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ይሁዳ ይህን ትብብር (ፌዴሬሽን) ለመቀበል ሳትፈቅድ ስትቀር፥ ሶርያና እስራኤል በመተባበር ይሁዳን ወጉ። በዚህም ጦርነት ከኢየሩሳሌም በቀር ሌላው የይሁዳ ግዛት በሙሉ በእነርሱ እጅ ወደቀ። በመጨረሻም አካዝ የአሦርን እርዳታ በጠየቀ ጊዜ የሶርያና የእስራኤል ኃይሉች ወደ ግዛታቸው መመለስ ግድ ሆነባቸው።

ኢየሩሳሌም ሙሉ በሙሉ ያልተጠቃችበት ሁለት ምክንያቶች ነበሩ፡- 

  1. እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እንደሚፈርድ አንድ ነቢይ የእስራኤልን ንጉሥ አስጠነቀቀው።
  2. የይሁዳ ንጉሥ የነበረው አካዝ የአሦርን እርዳታ ለመነ፤ ስለዚህ የአሦር ንጉሥ የነበረው ቴልጌልቴልፌልሶር ሶርያን አጠቃ። በ732 ዓ.ዓ. የሶርያ ዋና ከተማ የነበረችው ደማስቆ ተደመሰሰችና አሥር ሶርያን ተቆጣጠረች።

በዚህ ጊዜ የአሦር መንግሥት እስከ እስራኤል ድንበር ድረስ ምድሪቱን ስለ ተቆጣጠረና የእስራኤልን መንግሥት ለማጥቃት የተዘጋጀ ስለ መሰለ፥ በመንግሥቱም ውስጥ የፀረ አሦር አስተዳደር ማካሄድ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም ነበር። ስለዚህ ፋቁሑ በሆሴዕ መሪነት ተገደለ።

እስራኤል የምትጠፋበት ጊዜ የቀረበ ቢሆንም የእግዚአብሔር ሕዝብ ግን ወደ እርሱ አልተመለሱም ነበር፤ ይልቁንም እስከመጨረሻው ድረስ የጣዖት አምልኮአቸውን ቀጠሉ።

  1. የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ኢዮአታም (750-732 ዓ.ዓ.)

ኢዮአታም መንገሥ የጀመረው ከአባቱ ጋር በአንድነት ሲሆን፥ ጠቅላላ አመራሩን ለብቻው የወሰደው ግን በ740 ዓ.ዓ. ነበር። ኢዮአታም የአባቱን የዖዝያንን የአመራር ፈለጎች (ፖሊሲዎች) የተከተለ ቢሆንም ለብቻው ለመግዛት የቻለው ግን ለ4 ዓመታት ብቻ ነበር። በቤተ መቅደስ ይካሄድ የነበረውን አምልኮ ደገፈ። ቀደም ሲል በይሁዳ የነበሩትን ጣዖታት ለማጥፋት ግን ቆራጥ አልነበረም።

ኢዮአታም አሦርን ለመደገፍ አልፈለገም። የይሁዳ መሪዎች ግን የአሦርን ኃይል መዳበር እየፈሩ ሲመጡ፥ ከአሶር ጋር በሰላም ለመኖር ፈለጉና ልጁን አካዝን የኢዮአታም ተባባሪ መሪ አደረጉት። በዘመነ መንግሥቱ መጨረሻ አካባቢም ከእስራኤልና ከሶርያ በኩል ችግር ገጥሞት ነበር። 

  1. የይሁዳ ንጉሥ አካዝ (735-716 ዓ.ዓ.)

አካዝ አባቱ በሥልጣን ላይ በነበረ ጊዜ እርሱም ወደ መንግሥት ሥልጣን የመጣው የአሦር ደጋፊ ስለነበረ ነው። አሦርን ለመውጋት ሶርያና እስራኤል እንዲተባበራቸው በጠየቁት ጊዜ እምቢ በማለቱ፥ እስራኤልና ሶርያ ይሁዳን አጠቁና ከይሁዳ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ምርኮ ወሰዱ። ስለዚህ እርዳታ ለመጠየቅ ተወካዮን ወደ አሦር ላከ። አሦርም ሶርያን አጠቃችና ደማስቆን አጠፋች። እስራኤላውያንም ከይሁዳ እንዲወጡ አደረጉ። አካዝም ለአሦር መንግሥት ለመገበር ተገደደ።

አካዝ የአባቱን መመሪያዎች ተቃረነ። ጣዖት አምላኪና በይሁዳ ከነገሡት እጅግ ክፉ ነገሥታት አንዱ ነበር። አካዝ ልጁን እንኳ ለጣዖት አምልኮ የሠዋ ሰው እንደሆነ ተጽፏል። አካዝ የአሦርን ንጉሥ ለመገናኘት ወደ ደማስቆ ሄደ። እዚያ እያለ አንድ ትልቅ የጣዖት መሠዊያ ያያል። የዚህን የጣዖት መሠዊያ ተመሳሳይ ያሠራና በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ ያኖረዋል። ከዚህ በኋላም ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለሌሎች የውሸት አማልክት በዚህ መሠዊያ ላይ መሥዋዕትን ያቀርቡ ዘንድ ሕዝቡን ያበረታታቸዋል።

የሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ወደ ምርኮ የተወሰደው አካዝ በይሁዳ ላይ ሥልጣን በነበረው ጊዜ ነበር። አካዝ እግዚአብሔርን ብቻ ያመልክ ዘንድ ለእርሱም ይታዘዝ ዘንድ ከእስራኤል ውድቀት አልተማረም። ነቢዩ ኢሳይያስ ያገለገለውና በእግዚአብሔር ላይ ይታመን ዘንድ አካዝን ለማበረታታት የሞከረው በዚህ ሰው ዘመነ መንግሥት ነበር። አንዳንዶቹ ትላልቅ የኢሳይያስ ትንቢቶች የተሰጡትም በዚህ ዘመን ነበር (ለምሳሌ፡- ኢሳ. 7፡14፤ 9፡6-7)። 

  1. የእስራኤል ንጉሥ ሆሴዕ (731-722 ዓ.ዓ.) 

ሆሴዕ ሥልጣን የያዘው የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን ፋቁሑን በመግደል ነበር። ሆሴዕ ሥልጣን በያዘ ጊዜ ደማስቆ በአሥር እጅ የወደቀች ሲሆን፥ እስራኤልም የአሦር አገልጋይ ሆና ነበር። ከጥቂት የእስራኤል ግዛት በስተቀር አብዛኛው የእስራኤል ግዛት በአሦር ቁጥጥር ሥር ሆኖ ነበር። 

በ727 ዓ.ዓ. የአሦር ንጉሥ ሞተ። ይህንንም ሆሴዕ፥ የአሦር መንግሥት በእስራኤል ላይ የነበረውን የበላይነት ለማስወገድ ጥሩ ዕድል አድርጎ ቆጠረው፤ ስለዚህም ከግብፅ መንግሥት ጋር ተባበረ። በ725 ዓ.ዓ. ግን የአሦር መንግሥት የእስራኤል ዋና ከተማ የነበረችውን ሰማርያን አጠቃች። ለሦስት ዓመታት ከተማዋን ለመከላከል ቢችሉም፥ በ722 ዓ.ዓ. ግን የሰማርያ ከተማ ተደመሰሰች። ከ28000 የሚበልጡ ሰዎች ተገደሉ። የቀሩት እስራኤላውያንም በምርኮ ተግዘው በአሦር ግዛት በሙሉ፥ በተለይም በፋርስ ተበተኑ። በባቢሎን የነበሩ ሌሎች ሕዝቦች ደግሞ ወደ እስራኤል እንዲመጡና እንዲኖሩ ተደረገ። የሰሜኑ የእስራኤል ሕዝብ ከሌሎች ጋር በጋብቻ የተሳሰሩትና የተቀላቀሉት በዚህ ጊዜ ነበር። ስለዚህም እውነተኛ እስራኤላውያንም ሆነ ሙሉ አሕዛብ መሆናቸው ቀረ። እምነታቸውም ሙሉ በሙሉ ጣዖትን ማምለክ ወይም እውነተኛውን እግዚአብሔርን ማምለክ አልነበረም። ይልቁንም የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን አምልኮ ከአሕዛብ አምልኮ ጋር ቀላቀሉት። ዝርያዎቻቸውም በአዲስ ኪዳን ዘመን ሳምራውያን በመባል ይታወቁ የነበሩት ሲሆኑ፥ በአይሁዶችም የተጠሉትም የእግዚአብሔርን እውነተኛ አምልኮ ስላበላሹ ነበር።

እግዚአብሔር ሕዝቡ ወደ ምርኮ እንዲሄዱ የፈቀደው ለምን ነበር? የመጽሐፉ ጸሐፊ በ2ኛ ነገ. 17፡7-23 ለመመለስ የሚሞክረው ይህንን ጥያቄ ነው። እነዚህ ጥቅሶች እስራኤል በነገሥታት ዘመን የነበራትን ታሪክ በአጭሩ የሚያቀርቡና ከእግዚአብሔር ጋር የነበራትን ግንኙነት የሚናገሩ ናቸው። በአጭሩ የመጽሐፈ ነገሥት ጸሐፊ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ፥ አይሁድ በማያቋርጥ ሁኔታ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዙ እግዚአብሔር ቀጣቸው የሚል ነው። ትኩረት የተደገረበት ዋናው ኃጢአትም የጣዖት አምልኮና የውሸት አምልኮ ነው።

በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ያለውን የእስራኤልን የውድቀት ማሽቆልቆል መገንዘብ በጣም የሚያስገርም ነው። በመጀመሪያ፡- ጸሐፊው በሕዝቡ የተሳሳተ አምልኮ ላይ ያተኩራል። ጣዖታትን ያለማቋረጥ አመለኩ። 

ሁለተኛ፡- ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ፈቃደኞች አልነበሩም። እግዚአብሔር ሕዝቡን ያለማቋረጥ ወደ እርሱ መመለስ እንዳለባቸው ወይም ፍርዱን እንደሚቀበሉ በነቢያት ያስጠነቅቃቸው ነበር። ሦስተኛ፡- በአምልኮ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር፥ አይሁድ በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ መሰሉ። ልጆችን እንደ መሥዋዕት ይሠዉ ጀመር። በሥነ – ምግባር የወደቁና ጣዖት አምላኪ ሆኑ። አራተኛ፡- እግዚአብሔር ወደ ራሱ ሊመልሳቸው ይችል ዘንድ ጊዚያዊ ቅጣትን ቀጣቸው። ጭቆና ይደርስባቸው ዘንድ ለተለያዩ ሕዝቦች አሳልፎ ሰጣቸው። ይህም ሆኖ ግን ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር አልተመለሱም። አምስተኛ፡- እግዚአብሔር ወደ ምርኮ ይጓዙ ዘንድ ተዋቸው። 

እግዚአብሔር በነገሥታት ዘመን ያደረገውን ተመሳሳይ ሂደት ዛሬም ይጠቀማል። ሕዝቡ ከእውነት እየራቁ ሲሄዱ፥ አምላክነቱን ሲገፋና አምልኮአቸውን ሲያበላሹ፥ በመጀመሪያ እግዚአብሔር የተመረጡ ሰዎችን ወደ እነርሱ በመላክ በግልጥ እንዲያስጠነቅቋቸውና ይህ እውነተኛ አምልኮ እንዳልሆነ፥ በእግዚአብሔር ፊትም ተቀባይነት እንደሌለው እንዲነግሯቸው ያደርጋል። ሕዝቡም ካልተመለሱ እግዚአብሔር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲያልፉ ያደርጋል። ይህም ራብ፥ ስደት፥ ወይም ሌሎች ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። የእግዚአብሔር ሕዝቦች በዚህም ሁኔታ ሊመለሱ ካልፈቀዱ፥ እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ ይተዋቸዋል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ክፍል በዘመናችን ላሉ አብያተ ክርስቲያናትም ጠንካራ ማስጠንቀቂያ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ይህ ነገር ባለፈው ጊዜ እንዴት እንደተፈጸመ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ሐ) እኛ በግላችንም ሆነ አብያተ ክርስቲያኖቻችን ይህንን ወደ ጥፋትና ምርኮ የሚወስደውን ማሽቆልቆል አለመጀመራችንን ለማረጋገጥ ምን ማድረግ እንችላለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d