2ኛ ነገሥት 8፡16-12፡21

አንድ የተሳሳተ ውሳኔ፥ ወይም ዓለምን ለማስደሰት ሲባል የሚወስድ እርምጃ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጥፋትን ሊያመጣ ይችላል። ኢዮሳፍጥ በልጁና የእስራኤል ንጉሥ በነበረው በአክዓብ ሴት ልጅ መካከል ጋብቻ እንዲፈጸም በማድረግ፥ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ሰላምን ብቻ የፈጠረ መስሉት ነበር። ይህ ተግባር በእስራኤል ያደረጋቸውን ሃይማኖታዊ ተሐድሶዎች በሙሉ እንደሚያጠፋ አልተረዳም ነበር። ልጆቹን ሁሉ ለምት የሚዳርግ ነገር እንደሆነ አላስተዋለም ነበር። የዳዊትን ዘር በሙሉ ሊያጠፋ የሚችል ነገር እንደነበረም አላወቀም። 

የውይይት ጥያቄ፥ በዚህም ዘመን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያደርጉት ተመሳሳይ ውሳኔ እንዴት በከፍተኛ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያን መፍረስን ሊያስከትል እንደሚችል ምሳሌዎችን ጥቀስ።

ምንም እንኳ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች፥ ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የማያስከትሉ ቢሆንም፥ ሆኖም ግን በርካታ መልካም ነገሮችን ወይም ጉዳቶችን ሊያመጡ ይችላሉ። ለምሳሌ፡- አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የዓለም አቀፍ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ተብሎ በሚጠራው ኅብረት ውስጥ፥ ለክርስትና አንድነት ስንል መግባት አለብን ብለው ይወስናሉ። ቤተ ክርስቲያናቸው ምስክርነቷንና መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ የተቀበለችውን እምነት እንድታጣ ያደርጋሉ። ይህን መሰሉ እርምጃ ብዙ ክርስቲያኖች ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያደርሱ መንገዶች በርካታ ናቸው፤ በኢየሱስ ላይ ያለ እምነት ብቻ አይደለም ወደሚል እምነት እንዲያመሩ አድርጎአቸዋል። ይህም ማለት ዛሬ ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው የሚጠሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ኢየሱስን የማያውቁና ያልዳኑ ሰዎች ናቸው። አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከትርፍ ገንዘብ ለራሳቸው ጥቅምን ያገኙ ዘንድ የልማት ሥራን ለመጀመር ፈጥነው መወሰናቸው፥ ወደ ቤተ ክርስቲያን ክፍፍል፥ የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ምን እንደሆነ ወደ አለመረዳት፥ በአንዳንድ ሁኔታዎች ለእግዚአብሒር ያላቸውን ፍቅር ሁሉ ወደ መቀነስ አድርሶአቸዋል። የልማት ሥራ ወንጌልን ለማስፋፋት መሣሪያ ሊሆን ቢችልም፥ በሚገባ ካልተያዘ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ፥ ወይም የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ኃላፊነቷ ከሆነው ከወንጌል ሥራና ከማስተማር አገልግሎት ፈቀቅ እንድትል ዋና የሰይጣን መሣሪያ ሊሆን ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ነገ. 8፡16-12:21 አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል የተጠቀሱ የተለያዩ ነገሥታትን ዘርዝር። ለ) የእያንዳንዱን ንጉሥ ባሕርይ ዘርዝር። ሐ) እያንዳንዱ ንጉሥ በነገሠበት ጊዜ ስለ ተፈጸሙት ዋና ዋና ጉዳዮች ግለጥ። መ) የኢዮሳፍጥ ውሳኔ የይሁዳን መንግሥት ሊያጠፋ የነበረው እንዴት ነው? 

  1. ኢዮራም፡- የይሁዳ ንጉሥ (848-841 ዓ.ዓ.)

ኢዮራም ከአባቱ ከኢዮሳፍጥ ጋር ተባባሪ መሪ ሆኖ የሠራ ቢሆንም፥ ሥልጣን ሙሉ ለሙሉ ለመጨበጥ የበቃው ግን አባቱ ከሞተ በኋላ ነው። ኢዮሳፍጥ ሲሞት፥ ኢዮራም ከአባቱ የመንግሥት አስተዳደር መመሪያ ዞር በማለትና ስድስት ወንድሞቹን በመግደል መንግሥቱን ደም በማፍሰስ ጀምሯል። ሕዝቡም ወደ ጣዖት አምልኮ እንዲመለሱ አድርጓል። እንደምታስታውሰው፥ ይህ ሰው ያገባው የበአልን አምልኮ ወደ እስራኤል ያመጡትን የአክዓብንና የኤልዛቤልን ሴት ልጅ ነበር። በሚስቱ በጎቶልያና በአባቱ በአክዓብ ተጽዕኖ የበአልን አምልኮ ወደ ይሁዳ አስገባ፤ እንዲሁም በይሁዳ ከተሞች ዙሪያ የነበሩትን የጣዖት ማምለኪያ ስፍራዎች አደሰ።

በኢዮራም ዘመነ መንግሥት፥ የይሁዳ መንግሥት መዳከም ጀመረ። ኤዶማውያን በይሁዳ ላይ ዓመፁ። ፍልስጥኤማውያንና ዓረቦችም ኢየሩሳሌምን በማጥቃት ብዙ ብዝበዛ ከማድረጋቸውም በላይ በርካታ የንጉሣውያን ቤተሰብ አባሎችን ማርከው ወሰዱ። ኢዮራም በክፉ ደዌ ተመትቶ ሞተ። ሕዝቡ ግን እጅግ ስለጠላው፥ በይሁዳ ነገሥታት መቃብር አልተቀበረም። 

  1. የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ (841 ዓ.ዓ.) 

ከማንኛውም የይሁዳ ንጉሥ ያነሰ አጭር ጊዜ የገዛው አካዝያስ ነበር። በሥልጣን ላይ የቆየው ለአንድ ዓመት ብቻ ነበር። በእናቱ በጎቶልያ ተጽዕኖ አባቱ በጀመረው መንገድ የጣዖትና የበአልን አምልኮ ለማካሄድ ሳይገደድ አልቀረም። እንዲሁም የእስራኤል ንጉሥ በነበረው በአጎቱ በኢዮራም ማበረታቻና ምክር ሶርያን ለመውጋት ከእስራኤል ጋር ተባበረ። አካዝያስ ኢዮራምን ለመጎብኘትና ከእርሱ ጋር በመተባበር ለመዋጋት ሊሄድ፥ ኤልዛቤልንም ሆነ ኢዮራምን በመግደል ሥልጣን ከያዘው ከኢዩ ጋር ተገናኙ። ኢዩም አካዝያስንና በርካታ የይሁዳ ገዥዎችን ገደለ (2ኛ ዜና 22፡7-9)።

  1. የእስራኤል ንጉሥ ኢዩ (841-753 ዓ.ዓ.)

በሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ለረጅም ጊዜ የቆየው፥ የኢዩ ሥርወ መንግሥት ነበር። ኢዩ ሥልጣንን በያዘ ጊዜ፥ የእስራኤል መንግሥት በጣም የተዳከመ ቢሆንም በከፊል እንደገና ሊያጠናክረው ችሎ ነበር። ኢዩ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንደሚሆንና የአክዓብን ቤት እንደሚያጠፋ በነቢዩ ኤልሳዕ ተነግሮት ነበር። ኢዩ የጦሩ አዛዥ ስለ ነበር፥ ኢዮራምንና ኤልዛቤልን ከሥልጣናቸው ለማስወገድ ቻለ። ይህ ሰው በጣም ደም የተጠማ ሰው ነበር። የአክዓብን 70 ልጆች ገድሏል። የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን ኢዮራምን፥ የእስራኤልን ንግሥት ኤልዛቤልና የይሁዳን ንጉሥ አካዝያስን ገደለ። ይህን በማድረጉ የኤልሳዕ ትንቢት እንዲፈጸም አደረገ። በተጨማሪ የበአል ነቢያትንም ገደለ። ከብዙዎቹ የእስራኤል ነገሥታት የተሻለ ቢሆንም እንኳ በእስራኤል ምድር የነበረውን የጣዖት አምልኮ ስላላጠፋ፥ እርሱም ክፉ መሪ ነበር። 

በኢዩ ዘመነ መንግሥት በአሦርና በሶርያ መካከል ጦርነት ነበር። ኢዩ ለአሦር ግብር ሰጠ። በኋላ ግን ሶርያ በአሦር ላይ የበላይነቱን ልታገኝና አንዳንዱን የእስራኤል ምድር ወርራ ለመያዝ ችላ ነበር። 

  1. የይሁዳ ንግሥት የነበረችው ጎተልያ (841-835 ዓ.ዓ.) 

በእስራኤልም ሆነ በይሁዳ ለመግዛት የቻለች ብቸኛ ሴት ንግሥት ጎቶልያ ነበረች። እርሷ የአክዓብና የኤልዛቤል ልጅ ነበረች። አካዝያስ በኢዩ እጅ በተገደለ ጊዜ የይሁዳን መንግሥት ለማስተዳደር የቀሩ ንጉሣውያን ቤተሰቦች በጣም ጥቂት ነበሩ፤ ስለዚህ ጎተልያ ዙፋኑን ወረሰችና ለ6 ዓመታት ገዛች። የእርሷ አስተዳደር ብዙ ደም የፈሰሰበት ነበር። በይሁዳ ዙፋኑ ይገባኛል የሚል ማንኛውንም ሰው በመግደል የዳዊትን ዝርያዎውን ለማጥፋት ሞከረች። በኢዮሳፍጥ የተደረገውን ተሐድሶ የተመለከተው ካህኑ ዮዳሄ ግን የአካዝያስን ከሁሉም ታናሽ የሆነውን ልጅ ኢዮአስን በቤተ መቅደስ ሸሸገው። ስድስት ዓመት ከሸሽገው በኋላም የጦሩን አዛዥ ጠርቶ ገና የሰባት ዓመት ልጅ ቢሆንም እንኳ በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆኖአል ብለው በአንድነት አወጁ። ጎቶልያ በሕዝቡ ዘንድ የተጠላች ስለነበረች የጦሩ አዛዦች ኢዮአስ ንጉሥ እንዲሆን በመስማማት ጎቶልያን ገደሏት። 

  1. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአስ (835-796 ዓ.ዓ.)

ኢዮአስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ ገና የሰባት ዓመት ልጅ ነበር። ኢዮአስን በቤተ መቅደስ ያሳደገው ሊቀ ካህኑ ዮዳሄ የቅርብ አማካሪው ነበር፤ ስለዚህ ኢዮአስ ከይሁዳ ምድር የበአል አምልኮንና ሌሎች የጣዖት አምልኮዎችን ሁሉ እንዲያስወግድ ዮዳሄ አበረታታው። በአብዛኛው የሥልጣን ዘመኑ ኢዮአስ እግዚአብሔርን ተከተለ። 

በዮዳሄ አመራር የይሁዳ ሕዝብ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ ያላቸውን ፈቃደኝነት አረጋገጡ። ቃል ኪዳንቸውንም ከእግዚአብሔር ጋር አደሱ። ኢዮአስ ቤተ መቅደሱንም ማደስ ጀመረ። እግዚአብሔርን በማይፈሩ መሪዎች ዘመን ለመጠገን አስቸጋሪ እስኪሆን ድረስ ፈራርሶ የነበረው ቤተ መቅደስ እንዲሠራ ሕዝቡ ገንዘብ ማዋጣት ጀመሩ። 

ሆኖም ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ባደሱት ቃል ኪዳን ብዙ አልቆዩም። የሚያሳዝነው ነገር ኢዮአስ ለመንፈሳዊ አመራር በዮዳሄ ላይ ተደገፈ እንጂ፥ እርሱ ራሱ በእምነቱ ጠንካራ አልነበረም፤ ስለዚህ ዮዳሄ እንደሞተ ወዲያውኑ ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፁና ወደ ጣኦት አምልኮ ተመለሱ። ኢዮአስ ራሱም ጣዖት ማምለክ ጀመረ። በቤተ መቅደስ ኢዮአስን ያሳደገው የካህኑ የዮዳሄ ልጅ የነበረው ዘካርያስም፥ ኢዮአስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መተላለፍ መልካም እንደማይሆን በማመልከት እንደገና አስጠነቀቃቸው። ኢዮአስ ግን በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ተወግሮ እንዲገደል አስደረገ (2ኛ ዜና 24፡17-22)።

ኢዮአስ እግዚአብሔርን ስለተወ፥ በሕይወቱ ላይ መከራን አመጣ። ለሶርያ መንግሥት ግብር ለመክፈል ተገደደ። በኋላም ግብሩን መክፈል ሊያቆም፡ የሶርያ ኃይል በጉልበት ወደ ኢየሩሳሌም በመግባት ከኢዮአስ ጋር ተዋጋ። ኢዮአስ በውጊያው ቆስሉ በተኛ ጊዜም የገዛ አገልጋዮች ተማምለውበት በአልጋው ላይ ሳለ ገደሉት። ይህም በዘካርያስ ላይ የፈጸመውን በደል ለመበቀል ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚኖር መንፈሳዊ መሪነት ከእነዚህ ቁጥሮች ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: