የዜና መዋዕል አስተዋጽኦ እና አወቃቀር

የዜና መዋዕል አስተዋጽኦ

  1. ከፍጥረት ጀምሮ አይሁድ ከባቢሎን ምርኮ እስከ ተመለሱበት ጊዜ ድረስ ያለውን እምነት የሚመለከት የትውልዶች ታሪክ የዘር ሐረግ (1ኛ ዜና 1-9)
  2. የተባበረው የእስራኤል መንግሥት

ሀ. የዳዊት ታሪክ (1ኛ ዜና 10-29)

ለ. የሰሎሞን ታሪክ (2ኛ ዜና 1-9) 

  1. የይሁዳ መንግሥት ታሪክ (2ኛ ዜና 10-36፡16) 
  2. የይሁዳ መንግሥት መማረክ (2ኛ ዜና 36፡17-23)

የመጽሐፈ ዜና መዋዕል አወቃቀር 

1ኛ እና 2ኛ ዜና መዋዕልን በአራት ዋና ዋና ክፍሎች መክፈል ይቻላል። .

  1. የመጀመሪያው ክፍል በተለይ የሚያተኩረው የዘር ሐረግ (ትውልድ) ላይ ነው (1ኛ ዜና 1-9)። ይህ ዝርዝር የዘር ሐረግ ለእኛ ምንም የሚጠቅመን ባይመስለንም፥ ለአይሁድና ለመጽሐፈ ዜና መዋዕል በጣም አስፈላጊ ነበር። ጸሐፊው ከአዳም ጀምሮ እስከ ይሁዳ መታደስ ድረስ የዘለቀውን የዘር ሐረግ የጠቀሰበት ሦስት ታላላቅ ምክንያቶች ነበሩት፡- 

የመጀመሪያው፥ ጸሐፊው ከአዳም ጀምሮ ከምርኮ በኋላ እስካሉት አይሁድ ድረስ የነበረውን የእምነት መስመር (የዘር ሐረግ) ለመናገር ፈልጎ ነው። ይህ የእምነት መስመር አይሁድ ከእስራኤልም ሆነ ከይሁዳ ቢሆኑ አንድ ሕዝብ እንደሆኑ የሚያሳይ ነበር። የዘር ግንዳቸው ከአንድ አባት ከአብርሃምና ከአንድ ሰው ከአዳም እንደሆነ የሚያሳይ ነበር።

ሁለተኛው፥ የዘር ግንዱ (ሐረጉ) የሚያተኩረው በሌዊና በይሁዳ ነገድ ላይ ነበር። እነዚህ ሁለት ነገዶች የካህናትና የነገሥታት ነገዶች ስለሆኑ በጣም አስፈላጊዎች ነበሩ። ጸሐፊው እነዚህ ሁለት ነገዶች አሁንም ቢሆን የሕዝቡ ትክክለኛ መሪዎች እንደሆኑና የዘር ሐረጋቸውም እንዴት እንደ ቀጠለ ለማሳየት ፈልጎ ነበር። የሌዊ ነገዶች የሃይማኖት መሪዎች ነበሩ። በመጽሐፈ ነህምያ እንደምንመለከተው፥ የዘር ሐረጋቸው ዞሮ ዞሮ ወደ አሮን የማይደርስ በቤተ መቅደስ ውስጥ እንደ ካህናት ማገልገል አይችሉም ነበር (ነህ. 7፡64-65)። መጽሐፈ ዘና መዋዕል በተጻፈበት ጊዜ ነገሥታት ባይኖሩም፥ የይሁዳ ነገድ መኖር ብቻ እንኳን ከዳዊት ዘር የሆነ ንጉሥ እስራኤልን እንደሚገዛ እግዚአብሔር ለዳዊት የገባው ቃል ኪዳን ማረጋገጥ ነበር።

ሦስተኛ፥ ይህ የዘር ሐረግ ዝርዝር ሕጋዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለመስጠት የሚረዳ ነበር። ይህ የዘር ሐረግ በኩር የሆኑ የወንዶች ስም ስለሚዘረዝር፥ የቤተሰብ ውርስ፥ የፖለቲካ ሥልጣንና የመሬት ባለመብትነት መስመርን የሚያሳይ ነበር።

በዜና መዋዕል ያለውን የዘር ሐረግ ዝርዝር በኦሪት ዘፍጥረትና በማቴዎስ ወንጌል ካለው ጋር ስናወዳድር አንዳንድ ልዩነቶችን እንመለከታለን። ይህንን ልዩነት የምናብራራበት የተለመደው መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ብዙ ጊዜ የዘር ሐረጎችን ለማሳጠር ከመሀል አንዳንዶቹን ስሞች መተዋቸው ነው። በዕብራይስጥ «ልጅ» የሚለው ቃል «ዘር» ማለትም ስለሚሆን፥ በአንዳንድ ሁኔታዎች የዘሩን ሐረግ በማሳየት ረገድ በርካታ ትውልዶች ይዘለላሉ። 

  1. ዳዊትና የሰሎሞን ዘመነ መንግሥት፡- የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ጸሐፊ አብዛኛውን የ1ኛና የ2ኛ ሳሙኤል ክፍል እንደገና ቢተርክም፥ በዜና መዋዕል ውስጥ የተሰጠው ትኩረት ለየት ያለ ነው። የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ያተኮረው ዳዊት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ልዩ ግንኙነት ከቃል ኪዳኑ ታቦትና ከቤተ መቅደሱ ጋር በነበረው ግንኙነት እንዴት እንደገለጠው በማሳየት ነው። የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል የእግዚአብሔርን ታቦት ተወና እርሱንም እግዚአብሔር ንቆ ተወው። ዳዊት ግን የእግዚአብሔርን ታቦት አከበረና ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ዳዊትን ቤተ መቅደሱን ይሠራ ዘንድ ባይፈቅድለትም እንኳ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመሥራት የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ አዘጋጀ፤ የቃል ኪዳኑ ታቦትም መኖር የነበረበት በዚያ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት በጣም ያሳሰበውና ትኩረቱን በእርሱ ላይ ያደረገው ለምን ይመስልሃል?

አይሁድ እግዚአብሔር በሰማይ የሚኖርና ከሰማይ ሆኖ የሚገዛ መሆኑን የሚያውቁ ቢሆንም እንኳ የቃል ኪዳኑን ታቦት የእግዚአብሔር ሕልውና ቁሳዊ አምሳያ አድርገው ይመለከቱት ነበር። በእርግጥ እግዚአብሔርን በታቦቱ አይወስኑትም ነበር። ታቦቱ ግን የእግዚአብሔርን ሰማያዊ ዙፋን በምድር ላይ የሚወክል ምድራዊ ዙፋን ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በመካከላቸው ለመሆኑ ቁሳዊ የሆነ ተወካይ እንጂ የሚመለክ ነገር አልነበረም። በዳዊት ዓይን ይህን የእግዚአብሔር ሕልውና ምልክት የሆነው የእግዚአብሔር ታቦት ጊዜያዊ በሆነ ሕንጻ ወይም በድንኳን መኖሩ ትክክል አልነበረም። ዳዊት ለእግዚአብሔር ወይም ለታቦቱ የሚሆን ቤት ማለትም ቤተ መቅደስ ለመሥራት መፈለጉ ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅር መግለጫ ነበር። ይህን እንዲያደርግ እግዚአብሔር ለዳዊት ባይፈቅድለትም እንኳ የዳዊት ልጅ የአባቱን ምኞት ፈጽሞአል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለእግዚአብሖር ያለንን ፍቅር ለማረጋገጥ ዛሬ ልናደርጋቸው የምንችል አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) እግዚአብሔር ዛሬ የሚኖረው የት ነው? (1ኛ ቆሮ. 6፡19)። ሐ) ዳዊት በብሉይ ኪዳን ታቦቱንና ቤተ መቅደሱን ባከበረ ጊዜ ለእግዚአብሔር የሰጠውን ዓይነት ክብር እንዴት ለእግዚአብሔር መስጠት እንችላለን?

መጽሐፈ ዜና መዋዕል በሰሎሞን ላይም አተኩሮአል። ሰሎሞን ታላቅ የሆነው ስለ ጥበቡና ስለ ታላቁ ቤተ መንግሥቱ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር የሚመለክበት ትልቅ ቤተ መቅደስ በመሥራቱ ነበር።

የመጽሐፈ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ስለ ዳዊትም ሆነ ስለ ሰሎሞን አንዳችም ክፉ ነገር አለመጨመሩን ማየት የሚያስገርም ነው። ይህን ያላደረገው የእነዚህን ሁለት ሰዎች ኃጢአትና ችግር ባለማወቁ አልነበረም፤ ነገር ግን በዳዊትና ሰሎሞን ሕይወት ታሪክ ላይ ያተኮረው ሁለት ዓላማዎች ስለነበሩት ነው። በመጀመሪያ፥ ዳዊትንና ሰሎሞንን ሌሎች ነገሥታትና የእግዚአብሔር ሕዝብ መሪዎች ሁሉ ሊከተሏቸው የሚገቡ መልካም ምሳሌነት ያላቸው መሪዎች እንደሆኑ ለማመልከት ነበር። እግዚአብሔርን ስለሚወዱትና ስለሚያከብሩት እርሱም በተራው አከበራቸው። እንደ ጸሐፊው አመላካከት ፍጹም መሪዎች እንደመሆናቸው፥ ለመጨረሻው ታላቅ ንጉሥ ተምሳሌቶች ነበሩ፤ ያም ንጉሥ እንደ ዳዊት የሚነግሥ መሢሕ ሲሆን ከኃጢአት ግን የራቀ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ፣ ጸሐፊው ዳዊትና ሰሎሞን እንዴት የሙሴና የኢያሱ ምሳሌዎች እንደ ነበሩ አሳይቶአል። ዳዊት እንደ ሙሴ ነበር። ሁለቱም በእግዚአብሔር የተወደዱ ነበሩ። ሁለቱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ መሪዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ሁለቱም የተመኙት ነገር አልሆነላቸውም፡፡ ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር መግባት አልቻለም፤ ዳዊት ደግሞ ቤተ መቅደሱን መሥራት አልቻለም። የሁለቱም ግብ በእነርሱ ቦታ በተተኩ ሰዎች ከፍጻሜ ሊደርስ ቻለ።

ሰሎሞን እንደ ኢያሱ ነበር። የእግዚአብሔርን ሕዝብ ወደ ዕረፍትና ወደ ብልጽግና ለማድረስ በሁለቱም እግዚአብሔር ተጠቅሞባቸዋል (1ኛ ዜና 22፡8-9 እና ኢያሱ 11፡23፤ 21፡44)። ዳዊትና እግዚአብሔር ለሰሎሞን የሰጡት የማበረታቻ ቃላት በአብዛኛው ለኢያሱ ከተሰጡት ጋር ተመሳሳይ ነበሩ። (1ኛ ዜና 22፡11-13፥ 16፤ 28፡7-10፥ 20፤ 2ኛ ዜና 1፡1ን ከዘጻ. 31፡5-8፥ 23፤ ኢያሱ 1፡5-9 ጋር አወዳድር)።

  1. የይሁዳ ነገሥታት፡- መጽሐፈ ዜና መዋዕል ሁሉንም የይሁዳ ነገሥታት ባይጠቅስም እንኳ «መልካም» ለሆኑና እግዚአብሔርን ለሚፈሩ መሪዎች ጸሐፊው በተለይ ትኩረት የሰጠው ነው። እንደ ዳዊትና ሰሎሞን በነበሩና ቤተ መቅደሱን በማንጻት፥ ንጹሕ የሆነ የእግዚአብሔር አምልኮ እንደገና በመጀመር፥ እንዲሁም የጣዖት አምልኮ በማጥፋት እግዚአብሔርን ባከበሩ መሪዎች ላይ አትኩሮአል።
  2. መጽሐፈ ዜና መዋዕል የሚደመደመው በምርኮ ነው። ጸሐፊው ትኩረት ያደረገው፥ ነቢያት ሕዝቡ ወደ ምርኮ እንደሚወሰዱና ይሁዳ እንደምትጠፋ፥ እንደምትታደስም በተናገሩት ላይ ነው። የእግዚአብሔርን ቅጣት ያስከተለው የእግዚአብሔር ሕዝብ ዓመፅ ነበር። ይህ ቅጣት የዳዊት ሥርወ መንግሥት መጥፋትንና የቤተ መቅደሱን መደምሰስ አስከተለ። የዳዊት ሥርወ መንግሥት ሊታደስ ባይችልም ቤተ መቅደሱ ግን እንደገና ተሠርቶአል። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: