ዕዝራ 1-6

የውይይት ጥያቄ፥ ኤር. 25፡7-12፤ 29፡10፤ ኢሳ. 43፡1-7 አንብብ። ወደ ምርኮ ከመሄዳቸው በፊት፥ እግዚአብሔር ለይሁዳ ሕዝብ የሰጣቸውን ቃል ኪዳኖች ጥቀስ።

የክርስቲያን ሕይወት ተስፋ የተመሠረተው በእግዚአብሔር ላይ ባለ ጠንካራ እምነት ነው። ልንሞት በተቃረብንበት ሰዓት ወይም በከፍተኛ ስደት ውስጥ እንኳ ተስፋ ያለን፥ እግዚአብሔር ቃሉን እንደሚያከብርና የተስፋ ቃሉን እንደሚጠብቅ ስለምናምን ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬም ቢሆን አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታዎች ውስጥ ልንጨብጣቸው የምንችል አንዳንድ የተስፋ ቃሎችን ጥቀስ።

የይሁዳ ሕዝብ ተማርከው ከመሄዳቸው በፊት፥ ከ70 ዓመታት ምርኮ በኋላ እንዲመለሱ እግዚአብሔር ነግሮአቸው ነበር። ከምርኮ እንዲመለሱ ያደርግ ዘንድ የሚጠቀምበትን ንጉሥ ስም እንኳ በኢሳይያስ በኩል ነግሮአቸው ነበር። የዚህ ንጉሥ ስም ቂሮስ ነበር (ኢሳ. 45፡1)። አይሁድ ለ70 ዓመታት የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ጠበቁ። ወዲያውኑ የፋርስ ንጉሥ የነበረው ቂሮስ ሜዶንን መውጋት ጀመረና የባቢሎንን ከተማ ወሰደ። አይሁዶች ቂሮስ የባቢሎንን ከተማ መማረኩን በተመለከቱ ጊዜ በመካከላቸው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እየተፈጸመ እንደሆነ በማሰብ እንዴት ደስ እንደተሰኙ መገመት ትችላለህ።

የክርስትና መሠረት በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ማመን ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ብናምን በተሰጠን የተስፋ ቃል መሰረት የዘላለም ሕይወት ይኖረናል። የማይገቡንን ነገሮች እንኳ ለመልካም እንደሚያደርግልን (ሮሜ 8፡28) በሰጠን የተስፋ ቃል ላይ እንተማመናለን። እንዲሁም እግዚአብሔር ከሙታን እንደሚያስነሣንና ከእርሱም ጋር ለዘላለም በሕይወት እንደሚያኖረን በተሰጠን የቃል ኪዳን ተስፋ እናምናለን (1ኛ ቆሮ. 15)። የእነዚህን ተስፋዎች አንዳንድ ውጤቶች በምድር እንለማመዳለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከሰጠን የተስፋ ቃሉች አብዛኛዎቹን በሙላት የምንለማመዳቸው ወደ መንግሥተ ሰማያት ከደረስን በኋላ ነው። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለነበሩ አይሁድ የገባውን የተስፋ ቃል አስደናቂ በሆነ መንገድ ማክበሩ በማይዋሸውና ቃል ኪዳኑን ሁልጊዜ በሚፈጽመው አምላክ ላይ እምነታችንን እንድንጥል ያበረታታናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ እውነት ዛሬም ክርስቲያኖችን የሚያበረታታው እንዴት ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ዕዝራ 1-6 አንብብ። ሀ) ቂሮስ ያሟላው ትንቢት ምንድን ነው? ለ) እግዚአብሔር ፈቃዱን ለመፈጸም ቂሮስን የተጠቀመበት እንዴት ነው? ሐ) ወደ ይሁዳ የተመለሱት ሕዝብ ቁጥር በአጠቃላይ ስንት ነው? መ) ሌላስ የተመለሰ ነገር ምንድን ነው? (ዕዝራ 1፡7)። ሠ) ሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም እንደደረሱ በቅድሚያ የሠሩት ነገር ምን ነበር? ረ) የቤተ መቅደሱን ሥራ የተቃወመው ማን ነበር? ሰ) ቤተ መቅደሱ በመጨረሻ የተሠራው በማን ዘመነ መንግሥት ነበር?

በዕዝራ 1-6 የተፈጸሙ ድርጊቶች የተጀመሩት በ538 ዓ.ዓ. ነበር። ቂሮስ ባቢሎንን በወጋና በባቢሎን ተማርከው በግዞት የመጡ የተለያዩ ሕዝቦች ወደ የአገራቸው እንዲመለሱ በፈቀደ ጊዜ፥ ከእነዚህ ሕዝቦች አንደኛው ከይሁዳ የመጡ የአይሁድ ሕዝብ ነበሩ። በቅድሚያ ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁድ ግን በአጠቃላይ 50000 ያህል ብቻ ነበሩ፤ የቀሩት ግን በባቢሎን የነበራቸው ሕይወት ተመችቶአቸው ስለነበር በዚያ ቆዩ። በዚህ በመጽሐፈ ዕዝራ የመጀመሪያ ክፍል መጨረሻ ላይ የተጠቀሰው ድርጊት ከ20 ዓመታት በኋላ በ516 ዓ.ዓ. የተፈጸመው የቤተ መቅደሱ ሥራ ነበር።

እግዚአብሔር የአሕዛብ ንጉሥ በሆነው በቂሮስ ልብ ውስጥ በመሥራት፥ ከእርሱ ቀደም የነበሩትን የአሦርንና የባቢሎንን ነገሥታት መመሪያ እንዲቀይር ማድረጉ፥ ጸሐፊውን እንዳስደነቀው እንመለከታለን። እንዲያውም ጸሐፊው አይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የታዘዙትን ሕጋዊ ሰነድ ሁለት ጊዜ ጠቅሶታል። በመጀመሪያ፥ በምዕ. 1፡2-4 ሕጋዊ የሆነው የፈቃድ ትእዛዝ በዕብራይስጥ ቋንቋ ተተርጉሞ እንመለከተዋለን። ይህም ለአይሁድ የተደረገ የትርጉም ቅጂ ሳይሆን አይቀርም። ጸሐፊው የመንግሥቱ የመግባቢያ ቋንቋ በነበረው በአራማይክ ቋንቋ የቀረበውን ጽሑፍ በምዕ. 6፡3-5 እንደገና አቅርቦታል። ቂሮስ አይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መፍቀድ ብቻ ሳይሆን ባቢሎናውያን ከቤተ መቅደሳቸው የወሰዱባቸውን የአምልኮ ዕቃዎቻቸውንም መለሰላቸው።

ሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም በሚመለስበት ጊዜ የመጀመሪያውን ቡድን የመራው ሰው የይሁዳ አለቃ የነበረው ሼሽባደር ነበር፤ ስለዚህ ሰው ማንነት ምሁራን የተለያዩ አሳቦች አሏቸው። በዚህ አንጻር ሁለት ዋና ዋና አመለካከቶች ይቀርባሉ፡- በመጀመሪያ፥ አንዳንዶች ሼሽባደር ሺናአሰር በመባል የሚታወቅ ወደ ግዛት ተወስደው ከነበሩት የኢዮአኪን ልጆች አንዱ ነበር ይላሉ (1ኛ ዜና 3፡18)፡፡ ይህ ሰው ሽማግሌ ቢሆንም፥ አይሁድ በሚመለሱበት ጊዜ ሕጋዊ የሆነና የታወቀ መሪ ነበር። ምናልባትም በሰማርያ ከሰማርያ ገዢ በታች ሆኖ ይሁዳን ያስተዳድር የነበረ ሰው ሳይሆን አይቀርም ይላሉ። የቤተ መቅደሱን ግንባታ ሥራ የጀመረ ቢሆንም፥ ስለ ሞተ ወይም ሥራውን ለመምራት እስከማይችል ድረስ ስለ ሸመገለ አመራሩን ዘሩባቤል ከእርሱ ተረከበ። ይህንን አመለካከት ከተቀበልን፥ ዘሩባቤል የሼሽባደር የወንድም ልጅ ነው ማለት ነው። ሕጋዊ የሆነውን የታወቀው መሪ ሼሽባደር ሲሆን፥ ዝነኛ የሆነና ከሕዝቡ ጋር ግንኙነት የነበረው መሪ ግን ዘሩባቤል ነው ይላሉ።

ሁለተኛ፥ ሌሎች ምሁራን ደግሞ ሼሽባደር የዘሩባቤል ሌላው ስም ነው ይላሉ። እነዚህ ሁለት ሰዎች ስለ አንድ ሰው የተነገሩ እንደሆኑ ያስባሉ። ሼሽባደር የዘሩባቤል ባቢሎናዊ ስሙ ነው ይላሉ። ሁለቱም ሰዎች አለቆች ወይም ሹማምንት ነበሩ (ዕዝራ 5፡14፤ ሐጌ 1፡1)፤ ሁለቱም የቤተ መቅደሱን መሠረት ጥለዋል (ዕዝራ 3፡2-8፤ 5፡16፤ ሐጌ 1፡14-15)። ሌሉችም የታሪክ መጻሕፍት ሁለቱ ስሞች የአንድ ሰው ናቸው ይላሉ፤ ስለዚህ ሼሽባዳርና ዘሩባቤል የአንድ ሰው ሁለት ስሞች ሳይሆኑ አይቀሩም።

አይሁድ ከ4 ወራት ጉዞ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርሱ፥ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት የሚያቀርቡበት መሠዊያ መሥራት፡ ቅድሚያ የሰጡት ተግባር ነው። አይሁድ በምርኮ በነበሩባቸው 70 ዓመታት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረብ አልቻሉም ነበር፡፡ የዳስ በዓል በማክበርም እግዚአብሔርን አመለኩ።

ለ50 ዓመታት ያህል ቤተ መቅደሱ የተበላሸና ለአምልኮ አገልግሎት ያልዋለ ነበር (586-538 ዓ.ዓ.)፤ ስለዚህ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ሕዝብ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበትን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመሩ። ገና መሠረቱን እንደጣሉ ተቃውሞ ገጠማቸው። በሰሜን እስራኤል ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣት የቤተ መቅደሱን ሥራ ለማገዝ ፈለጉ። የአሕዛብና የአይሁድ ቅይጥ እንጂ ሙሉ ለሙሉ አይሁድ ስላልነበሩ፥ የብሉይ ኪዳን ሕግም አሕዛብ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲገቡ ስለማይፈቅድ፥ ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩና ከእነርሱ ጋር እንዲያመልኩ ለማድረግ አይሁድ ሳይፈቅዱ ቀሩ። የእግዚአብሔር አምልኮ ይበላሽና እንደገና የእግዚአብሔር ፍርድ ያጋጥመናል ብለው ፈሩ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የማያምኑ ሰዎች ለእግዚአብሔር ያለንን ንጹሕ አምልኮና የተቀደሰ አኗኗራችንን እንዲያበላሹ የምንፈቅድባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያንህ ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው? የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የእግዚአብሔር አምልኮ ንጽሕና እንዲጠበቅና ሌሎችም በአኗኗራቸው ዓለምን እንዳይመስሉ ለማበረታታት ምን ማድረግ ይችላሉ?

ሳምራውያን የቤተ መቅደሱን ሥራ ማገዝ እንደማይችሉ ሲነገራቸው፥ አይሁድ የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲያቆሙ እንዲያደርግ የፋርስን መንግሥት ጠየቁ። አይሁድ የቤተ መቅደሱን ሥራ እንደገና በ538 ዓ.ዓ ጀመሩ፤ ነገር ግን ሥራውን እንዲያቆሙ ስለተገደዱ እስከ 520 ዓ.ዓ. ድረስ እንደገና ሊጀምሩ አልቻሉም። ይኸውም ከ18 ዓመታት በኋላ ማለት ነው።

ዕዝራ 4 አይሁድ በሰማርያ ሕዝብ አማካይነት የደረሰባቸውን የተለያየ የቤተ መቀደስ ሥራ ማደናቀፊያ መንገድ የተገለጠበት ክፍል ነው። የተቃውሞው ዓይነት የተዘረዘረው በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ቀጥሉ አይሁድ የደረሱባቸውን ሦስት የተለያዩ ዓይነት ተቃውሞዎች እንመለከታለን።

አንደኛ፣ ቤተ መቅደሱን የመሥራት ተግባር እንደቆመና እስከ ዳርዮስ ዘመን ድረስ ሊቀጥል እንዳልቻለ እንመለከታለን (ዕዝራ 4፡5)።

ሁለተኛ፥ በኋላ የአስቴር ባል በነበረው በንጉሥ አርጤክስስ ዘመነ መንግሥት በአይሁድ ላይ ስለ ቀረበው ክስ እንመለከታለን። ይህም የሆነው ከ485-465 ዓ.ዓ. በነበረው ጊዜ ነው።

ሦስተኛ፥ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደገና በመሥራት ረገድ ስለ ደረሰው ተቃውሞ እንመለከታለን (ዕዝራ 4፡7-23)። አርጤክስስ የነገሠው በ464 ዓ.ዓ. ስለነበር፥ ይህ ክስ የቀረበው እርሱ በነገሠበት ዘመን አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። በኋላ ዕዝራና ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱና የኢየሩሳሌም ቅጥሮችም እንዲሠሩ የፈቀደው እርሱ ነበር። ይህ ክፍል የሚናገረው ስለ ቤተ መቅደሱ ሥራ ስለ ከተማይቱ መሠራት ነው፤ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ የቤተ መቅደሱ ሥራ ተጠናቅቆ ነበር።

የዕዝራ 5 ና 6 ታሪክ በ520 ዓ.ዓ. ወደ ተፈጸመው የዳርዮስ ዘመን ይመልሰናል። ሐጌና ዘካርያስ የተባሉት ነቢያት ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን ይሠሩ ዘንድ እንዴት እንዳበረታቱ የሚናገር ነው። ቤተ መቅደሱን መሥራት በጀመሩበት ጊዜ የሰማርያው ገዢ አይሁድ ይህን ነገር ለማድረግ ፈቃድ አላቸው ወይ? ብሎ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለፋርስ መንግሥት ጻፈ። ይህንንም ለማረጋገጥ በተደረገው ፍለጋ፥ አይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ቤተ መቅደሱን እንዲሠሩ የተፈቀደበት ሰነድ ቅጂ ተገኘ። አይሁድ ሥራቸውን ቀጠሉ። ቤተ መቅደሱን ሠርተው ለማጠናቀቅ አራት ዓመታት ፈጀባቸው። የቤተ መቅደሱም ሥራ በ516 ዓ.ዓ. ተጠናቀቀ። ኢየሱስ ከመወለዱ ጥቂት፥ ቀደም ብሎ የሄሮድስ ቤተ መቅደስ እስኪሠራ ድረስ ለአይሁድ ዋናው የአምልኮ ማዕከላቸው ይህ ቤተ መቅደስ ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእግዚአብሔር ሰዎች ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለማድረግ በሚሠሩበት ጊዜ ሁሉ፥ በአብዛኛው ተቃውሞ የሚኖረው ለምን ይመስልሃል? ለ) ይህንን ነገር በቤተ ክርስቲያንህ ያየኸው እንዴት ነው? ሐ) ዮሐ. 15፡18-21፤ 17፡11-16 አንብብ። ዓለምን እየመሰሉ ለማይኖሩ ክርስቲያኖች የተሰጠው ተስፋ ምንድን ነው? መ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሕዝባቸው ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕይወት ለመኖር የሚፈልግ ከሆነ ለተቃውሞ እንዴት ሊያዘጋጁት ይገባል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: