ዕዝራ 7-10

ውጫዊ የሆነው የአምልኮ ስፍራ የሚደመሰስበት ጊዜ ቢኖርም እንኳ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያጋጥማቸው ከዚህ የባሰ ከፍተኛ ችግር አለ። ይህም የእግዚአብሔር ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት እንደገና መሠራት የሚያሻው ሆኖ ሲገኝ ነው። ተፈጥሮአዊ የሆነው ዝንባሌ የእግዚአብሔር ሕዝብ የመጀመሪያ ፍቅራቸውን በመተው ከእምነታቸው ፈቀቅ ማለታቸው ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አባላቱ በእግዚአብሔር ፊት በቅድስና የመመላለስ ፍላጎታቸው ቀስ በቀስ እየጠፋ ይሄዳል፤ እንዲሁም ለማያምኑ ሰዎች ጠንካራ ምስክሮች መሆናቸው ይቀራል። አምልኮ ልማዳዊ ብቻ ሊሆን ይችላል፥ በኋላም በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት ይተዋሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህን ዝንባሌ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ እንዴት ነው ያየኸው? ለ) መሪ እንደመሆንህ መጠን በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉ ሰዎች ፍቅራቸውን እንዳይተዉ፥ ንጽሕናቸውን እንዳያጓድሉና እግዚአብሔርን የማምለክ ፍላጎታቸው እንዳይቀንስ ልታደርጋቸው የምትችልባቸውን ነገሮች ዝርዝር።

የመጽሐፈ ዕዝራ የመጨረሻው ክፍል አጋማሽ የሚነግረን፥ የሕዝባችንን መንፈሳዊ ሕይወት ንጹሕና ለእግዚአብሔር ታዛዥ እንዲሆን አድርገን እንዴት እንደምናድሰው ነው። የካህኑ ዕዝራ ታሪክ ኃጢአትን የሚጠላና ሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት በቅድስና እንዲኖሩ የሚፈልግ መሪ ጥሩ ምሳሌ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዕዝራ 7-10 አንብብ። ሀ) ወደ ይሁዳ እንዲመለስ ለዕዝራ የፈቀደለት ንጉሥ የትኛው ነው? ለ) ዕዝራ በምዕ. 7፡6፥10 የተገለጸው እንዴት ነው? ዛሬም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይከተሉት ዘንድ ይህ መልካም ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው? ሐ) ከዕዝራ ጋር የተመለሱት ሰዎች ብዛት ምን ያህል ነበር? መ) ዕዝራ ሕዝቡ ከአሕዛብ ጋር በጋብቻ የመጣመርን ኃጢአት እንደሠሩ ሲሰማ ምን አደረገ? ሠ) በእግዚአብሔር ፊት ሕዝቡን ወደ ተቀደሰ አካሄድ ለመመለስ ዕዝራ ምን አደረገ? ረ) በእነዚህ ምዕራፎች «የእግዚአብሔር ሕግ» የሚለው ቃል የተጠቀሰው ስንት ጊዜ ነው?

በመጽሐፈ ዕዝራ ምዕራፍ 6 እና 7 በምናገኛቸው ክስተቶች መካከል የብዙ ዓመታት ልዩነት አለ። የመጽሐፈ አስቴር ጠቅላላ ታሪክ የተፈጸመው በዚህ ጊዜ ነው። የምዕ. 6 ታሪክ የተፈጸመው በ516 ዓ.ዓ. ሲሆን፥ ከዕዝራ 7-10 ያለው ታሪክ የተፈጸመው ደግሞ በ458 ዓ.ዓ. በአንድ ዓመት ውስጥ ነበር። ይህም ማለት በምዕ. 6 ና 7 መካከል 57 ዓመታት አሉ ማለት ነው።

ዕዝራ የዘር ግንዱ ከአሮን ወገን የሆነ ካህን ነበር። ወላጆቹ ከዘሩባቤል ጋር ከምርኮ ስላልተመለሱ፥ የተወለደው በምርኮ ምድር ነበር፤ ነገር ግን ዕዝራ ለእግዚአብሔርና ለቃሉ ከፍተኛ ፍቅርን አጎለበተ። ዕዝራ በአይሁድ ዘንድ የታወቀና በፋርስ መንግሥት በምርኮ ላይ ሳሉ እንኳ ሳይወክላቸው አልቀረም። ዕዝራ የእግዚአብሔርን ቃል ያውቅ ነበር። ያለማቋረጥ ያጠናው፥ ትምህርቱን ሁሉ ይከተልና በውስጡ ያለውን እውነት በሙሉ ለሕዝቡ ለማስተማር በሚገባ ይተጋ ነበር (ዕዝራ 7፡6፥ 10)። የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ሥራ ምን እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገባ ከሚገልጹት ክፍሎች አንዱ ይህ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ እግዚአብሔርን ማወቅ አለበት። እግዚአብሔርን ማወቅ ማለት ቃሉን ማወቅ ማለት ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ለማወቅ የብዙ ዓመታት ጥናት ይጠይቃል። አስተማሪ የተጻፈውን የእግዚአብሔርን ቃል ማወቅ ብቻ ሳይሆን፥ በውስጡ ያሉትን እውነቶች ለሌሎች ማስተማርና በመታዘዝም መመላለስ ይገባዋል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት በጣም ጥቂት ጊዜ ብቻ የሚሰጡት ለምንድን ነው? ) ስለ እግዚአብሔር ቃል እውቀታቸውና ለቃሉ ባላቸው መታዘዝ የታወቁ የቤተ ክርስቲያንህ ሰዎችን ስም ዘርዝር። ሐ) እነዚህ ሰዎች ሌሎችን ለማስተማር እግዚአብሔር የተጠቀመባቸው እንዴት ነው?

ዕዝራ ወደ ይሁዳ ለመመለስ ስለፈለገ ንጉሥ አርጤክስስን ፈቃድ ጠየቀው። እግዚአብሔርም የአርጤክስስን ልብ ከፈተና ለዕዝራ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን ገንዘብም እንዲሰጠው አደረገ፡፡ ዕዝራም ወደ ይሁዳ ለመመለስ የሚፈልጉ አይሁዳውያንን ሰበሰበ። ከእነዚህ መካከል ግን የእግዚአብሔርን ቃል ለማወቅና ሌሎችን ለማስተማር፥ ለእግዚአብሔር የሚደረገውን አምልኮ መምራት የሚጠበቅባቸው ሌዋውያን ጥቂት መሆናቸውን አየ። ስለዚህ አብረውት እንዲሄዱ በተለይ ሌዋውያንን ጠየቃቸው። በመጨረሻም 1800 ወንዶችና ቤተሰቦቻቸውም ከዕዝራ ጋር ከምርኮ ተመለሱ። ይህም ከምርኮ፤ የተመለሰው ሁለተኛው ቡድን ነበር። ጉዞው ከ1400 ኪሉ ሜትር በላይ ስለነበር፥ ዕዝራና ሕዝቡ 3 ወር ተኩል ፈጀባቸው። 

ዕዝራ ወደ ይሁዳ በደረሰ ጊዜ በቀጥታ ከሕዝቡ ኃጢአት ጋር ተፋጠጠ። ሕዝቡ በይሁዳ ለ80 ዓመታት የቆዩ ሲሆን፥ ለእግዚአብሔር የነበራቸው ፍቅር እየቀዘቀዘ ሄዶ ነበር። ኃጢአትም ወደ አምልኮአቸው ገብቷል። በትንቢተ ሚልክያስ ውስጥ የሕዝቡ መንፈሳዊ ችግር ምን እንደሆነ እንመለከታለን፤ ነገር ግን ዕዝራ የተዋጋው ኃጢአት በአይሁዳና በአሕዛብ መካከል የተደረገ ቅይጥ ጋብቻ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ነገር ዕዝራን በጣም ያሳሰበው ይመስልሃል? ለ) አንድ ክርስቲያን የማታምን ሴት ሲያገባ መንፈሳዊ ሕይወቱ እየቀዘቀዘ ሲሄድ ያየኸው እንዴት ነው? 

ሰሎሞን ወደ ኃጢአት ካመራባቸው መንገዶች አንዱ ከአሕዛብ ሴቶች ጋር ጋብቻ መመሥረቱ እንደሆነ ዕዝራ ከመጽሐፍ ቅዱስ፥ በተለይ ደግሞ ከሰሎሞን ታሪክ ያውቅ ነበር። ባዕዳን የሆኑት የሰሎሞን ሚስቶች ሰሎሞን እውነተኛውን አምላክ ትቶ የተሳሳቱ አማልክትን እንዲያመልክ አደረጉት። ይህ ነገር በአይሁድም ላይ እንዳይፈጸም ዕዝራ ሰግቶ ነበር። ዛሬ በርካታ ክርስቲያኖች የማያምን ሰው በማግባት ይህንን ሰው በኋላ አማኝ አደርገዋለሁ ይላሉ፤ ይህ ግን ብዙ ጊዜ አይሆንም። ይልቁንም ቀስ በቀስ ወደ ዓለም በመግባት ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅርና ለሌሎች የነበራቸውን ምስክርነት ያጣሉ።

ስለዚህ ዕዝራ ይህን ኃጢአት በሚመለከት ፈጣን ምላሽ ሰጠ። በሕዝቡ መካከል ልብሱን ቀደደ፤ አመድ በራሱ ላይ ነሰነሰ፤ ጠጉሩን ነጨ፤ በመሬት ላይ ተቀምጦ በእግዚአብሔር ፊት ያለቅስ ጀመር። ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ከእግዚአብሔር ዘንድ በግልጽ ይቅርታን ጠየቀ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዕዝራ ስለ አይሁድ ሕዝብ ኃጢአት ከሰጠው ምላሽ በኃጢአት ላይ የነበረውን ጥላቻ እንዴት እናያለን? ለ) በቤተ ክርስቲያን መሪነታችን በእግዚአብሔር ሕዝብ ዘንድ ኃጢአት ስናይ ማድረግ ስላለብን ነገር ከዕዝራ ምላሽ ምን እንማራለን?

ሕዝቡ ዕዝራ ያደረጋቸውን ነገሮች በተመለከቱ ጊዜ፥ አንድ ስሕተት እንዳለ ወዲያውኑ አወቁ። በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኝነታቸውን በማወቅ ንስሐ መግባት ጀመሩ። ከዚያም ዕዝራ ለእግዚአብሔር ሕግ ለመታዘዝና አይሁድ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ጋብቻን ላለመፈጸም ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን እንዲገቡ አደረገ። ሕዝቡም ይህንን ነገር በመታዘዝ ባዕዳን ሚስቶቻቸውን አሰናበቱ። ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ ቃል ኪዳን ገቡ። የሚያሳዝነው ግን ይህ ቃል ኪዳን ለረጅም ጊዜ አለመቆየቱ ነው፤ ምክንያቱም በነህምያ ዘመን ሕዝቡ በተመሳሳይ ኃጢአት ወድቀው እናገኛቸዋለን።

ኃጢአት ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ሲገባ መሪዎች ወዲያውኑ እርምጃ መውሰድ አለባቸው። በእግዚአብሔር ፊት ራሳቸውን ትሑታን ሊያደርጉና ስለ ሕዝቡም ሆነ ስለ ራሳቸው ኃጢአት ንስሐ ሊገቡ ያስፈልጋል። ሕዝቡንም ስለ ኃጢአታቸው በመውቀስ ንስሐ እንዲገቡ ንጹሕ ሕይወትን በእግዚአብሔር ፊት እንዲኖሩ ለማድረግ መቻል አለባቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ አሁን የራስህንና የቤተ ክርስቲያንህን ሕይወት መርምር። ሀ) አንተና ሌሎች ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት የምትመላለሱት በንጽሕና ነውን? ለ) በአንተና በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ችግር የፈጠሩ አንዳንድ ኃጢአቶችን ጥቀስ። ሐ) አሁን እግዚአብሔር አንተንና ቤተ ክርስቲያህን ንጹሕ እንዲያደርግ ለመለመን የጸሎት ጊዜ ይኑርህ። መ) ስለ ኃጢአታቸው በፍቅር ልትወቅሳቸውና ወደ ንስሐ እንዲመጡ ልታደርጋቸው የምትችላቸው ሰዎች ካሉ፥ በዚህ ሳምንት አነጋግራቸው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: