የመጽሐፈ ዕዝራ ዋና ዋና ትምህርቶች 

  1. መጽሐፈ ዕዝራ እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን በመጠበቅ ረገድ ታማኝ እንደሆነ ያስተምረናል። 

እግዚአብሔር የአይሁድን ሕዝብ ከማስማረኩ በፊት፥ እንደሚመልሳቸው ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበር (ኢሳ. 43፡1-7፤ ኤር. 29፡10 ተመለክት)። ኢየሩሳሌም ከተደመሰሰች ከ50 ዓመታት በኋላ እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ለመፈጸም በአንድ አረማዊ ንጉሥ ተጠቀመ። እግዚአብሔር ሕዝቡ ታማኝ ባልነበሩበት ሰዓት እንኳ ታማኝ ነበረና፥ ዛሪም በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ብንሠራም እንኳ፥ ሙሉ ለሙሉ እንደማይጥለን ዋስትና ሊኖረን ይችላል። እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን ለእኛ በመፈጸም እጅግ የዘገየ ቢመስልም፥ ሰራሱ ጊዜና ፍቅር በተሞላ መንገድ እንደሚፈጽምልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ነገር ግን እግዚአብሔር ሊባርካቸው የሚፈቅደው፥ ወደ እርሱ በንስሐ ለመመለስ የሚፈቅዱትን ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ ከኃጢአታቸው ተመልሰው ንስሐ በሚገቡበት ጊዜ እግዚአብሔር ለእነርሱ ሊሰጣቸው የሚፈልገውን በረከት ይመልስላቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የእግዚአብሔርን ታማኝነት በሕይወትህ የተለማመድከው እንዴት ነው? ምሳሌዎችን ጥቀስ። ለ) ስለዚህ ጉዳይ እርሱን ለማመስገን ጊዜ ወስን። 

  1. እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የፈረሱትን ነገሮች እንደገና ለማነጽና ለማደስ እንዴት እንደሚሠራ መጽሐፈ ዕዝራ ያስተምረናል። መጽሐፈ ዕዝራ ስለ ቤተ መቅደሱና ስለ እግዚአብሔር ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት እንደገና መታነጽ ያስተምረናል። የእግዚአብሔር ሕዝብ በመታዘዝ ለመኖር እግዚአብሔር በኃይል እንዲጠቀምባቸው በሚፈልግበት ጊዜ ሰይጣን ይህንን ነገር የማስቆም ሙከራ ለማድረግ ሁለት ነገሮችን ይጠቀማል። የመጀመሪያው፥ ተቃውሞ ወይም ስደት ነው። ሰይጣን የቤተ መቅደሱን ሥራ ለ20 ዓመታት ለማስተጓጎል የሰማርያ ሰዎችን ተቃውሞ ተጠቀመ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁልጊዜ ታማኝ ከሆኑ፥ በሚቃወሟቸው ሁሉ ላይ ድልን ይቀዳጃሉ። ሁለተኛ፥ ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሥራ ለማስቆም የእግዚአብሔር ሰዎች ለእርሱ ያላቸውን ፍቅር እንዲያጡና ባለመታዘዝ እንዲኖሩ ለማድረግ ይጥራል። ሰይጣን የእግዚአብሔር ሕዝብ ከእርሱ ተለይተው በኃጢአት እንዲወድቁ የሚያደርገው፥ ጥረት ከፍተኛ ነው። እግዚአብሔር ለሥራው ያልነጹ ዕቃዎችን አይጠቀምም። ይልቁንም ኃጢአት የእግዚአብሔርን ፍርድ ያመጣል። የመጽሐፈ ዕዝራ ጸሐፊ በሁለት ነገሮች ላይ አትኩሯል። የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ሕዝብ አለመታዘዝ ሌላ ምርኮ እንዳያመጣባቸው ከመሥጋቱ ላይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የማያምኑ ሰዎችን በማግባትና እንደ ዓለም በመኖር የራሳቸውን ማንነት የማጣታቸው ነገር ያሳስበዋል። ዛሬም ቢሆን እነዚህን ሁለት አደጋዎች ፊት ለፊት እንጋፈጣለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ትምህርቶች ዛሬ ለክርስቲያኖች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ለ) መጽሐፈ ዕዝራን ለቤተ ክርስቲያንህ የምታስተምርባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

መጽሐፈ ዕዝራ ከአዲስ ኪዳን ጋር ያለው ግንኙነት በአዲስ ኪዳን ፈሪሳውያንና ጸሐፍት የሚባሉ የሕግ መምህራንና የሃይማኖት መሪዎች ቡድን እናያለን። እነዚህ የጌታ ኢየሱስ ዋና ጠላቶች የነበሩና በመስቀል ላይ እንዲሞትም ያደረጉ ናቸው። ለወጋቸው ከሚገባ በላይ ትኩረት በመስጠት የእግዚአብሔርን ሕግ ስለጣሱ፥ ኢየሱስ ግብዞች ናችሁ በማለት ብዙ ጊዜ ሲወቅሳቸው እንመለከታለን (ማቴ. 15፡1-9 እና 23፡13-35 ተመልከት)። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ከየት መጡ? ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የአዲስ ኪዳን ፈሪሳውያን ወይም የሕግ መምህራን ይህን በሚመለከት የመጀመሪያው ጸሐፊ የነበረውን የዕዝራን ባሕል የተከተሉ ናቸው ብለው ያስባሉ፤ ነገር ግን ዕዝራ ከእነርሱ በተለየ ሁኔታ ለእግዚአብሔር ሕግ ባለው ታዛዥነት፥ ራሱን ዝቅ በማድረግ፥ በትሕትናው፥ ደግሞም ለውስጥ ንጽሕና በሚሰጠው ትኩረት የታወቀ ነበር። ሆኖም በመጽሐፈ ዕዝራ ውስጥ እነዚህ ፈሪሳውያንና የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች የሆኑ ሰዎች ኢየሱስ በምድር ከኖረበት ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የነበረውን ሥረ መሠረታቸውን እንመለከታለን። በመጽሐፈ ዕዝራ የሚከተሉትን ነገሮች መመልከት እንጀምራለን፡-

  1. የሕዝቡ ዋና መሪዎች:- የፖለቲካ አመራሩን የያዙት ነገሥታት ወይም ገዥዎችና አስተዳዳሪዎች ሳይሆኑ፥ መንፈሳዊ መሪዎች ነበሩ። እነርሱም ካህናትና ሌዋውያን ነበሩ። ካህናቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኃይላቸውና ተሰሚነታቸው እየጨመረ ስለመጣ፥ በኋላ የፖለቲካ አመራሩንም ጠቅልለው ያዙ፤ ስለዚህም ካህናቱ ከመንፈሳዊ ነገር ይልቅ፥ በፖለቲካ ጉዳዮች ማተኰር ጀመሩ። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ የአይሁዳ መሪዎች የሃይማኖት መሪዎች ሲሆኑ፥ የአይሁድ ሕዝብ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነው የካህናት አለቆች ሸንጎ አባላት ነበሩ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ እጅግ ጠለቅ ብለው በሚገቡበት ጊዜ ችግር የሚመጣው ለምንድን ነው? 

  1. የእግዚአብሔርን ሕግ ማጥናትና መተርጎም ብቸኛ ኃላፊነታቸው የሆነ ጸሐፍት የሚባሉ ባለሙያዎች አገልግሎት መጀመር (ዕዝራ 7፡10):- እንደነዚህ ዓይነት መሪዎች ተፈላጊ ነበሩ፤ ነገር ግን አደገኛም ሊሆኑ ይችላሉ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ አባላት በታወቁ መሪዎች ትምህርት ላይ ብቻ ከተደገፉና የእግዚአብሔርን ቃል ለራሳቸው ማጥናት ካቆሙ እነርሱም ሆኑ ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት እየደከሙ ይሄዳሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ እጅግ አስፈላጊ ትምህርቶች አንዱ ክርስቲያኖች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ካህናት ስለሆኑ (1ኛ ጴጥ. 2፡9)፣ እኛ ሁላችን የእግዚአብሔርን ቃል የማጥናትና የመተርጎም ኃላፊነት አለብን የሚል ነው።
  2. ለእግዚአብሔር ቃል ሙሉ በሙሉ በመታዘዝ ጉዳይ ላይ በማተኮር፡- እነዚህ በሙያው የተካኑ ጸሐፍት ወዲያውኑ ወደ ክፋት የተለወጠ አንድ ነገር ማድረግ ጀመሩ። ግን ሕዝቡ መታዘዝ እንዳለባቸው አድርገው ተጨማሪ ሕግጋትን መስጠት ጀመሩ። ግን ይህንን ያደረጉት ለመልካም ነበር? የታወቁ የእግዚአብሔር ሕግጋትን እንዳይጥሱ ተጨማሪ ጥበቃ ማድረጋቸውስ አስፈላጊ ነበር? ለመሆኑ እግዚአብሔር ሕዝቡን ያስማረከው የእግዚአብሔርን ሕግ ስለ ጣሱ አይደለምን? እነርሱ ግን ተጨማሪ ሕግጋት ቢያወጡ ሕዝቡ በጽሑፍ ያለውን የእግዚአብሔርን ሕግ ለመጣስ ብዙ ዕድል አይኖረውም ብለው አሰቡ። ብዙም ሳይቆዩ ከእግዚአብሔር ሕግ ይልቅ በዚህ መልክ በተሰጡ ሕጎች (ወግና ልማዶች) ላይ ማተኮር ጀመሩ፥ (ማለትም፡- ምሕረት፥ ቅን ፍርድና፥ እምነትን ለመሳሰለው) ከሁሉ ይልቅ አስፈላጊ ለሆነው ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዛቸውን ከማረጋገጥ ይልቅ፥ ሕዝቡ እነርሱ ላወጡት ሕግ መታዘዝ አለመታዘዛቸውን በማጣራት ላይ ትኩረት አደረጉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ተመሳሳይ ነገር በአብያተ ክርስቲያኖቻችን እንዴት ሊፈጸም ይችላል? ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጨመሩ ቤተ ክርስቲያንህ የምታስተምራቸው ሕጎች የትኞቹ ናቸው? ሐ) እነዚህ ሕግጋት ለክርስቲያን የማሰናከያ ዓለት የሆኑት እንዴት ነው? 

አንዲት ቤተ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ሕግጋት ላይ ሌሎች ተጨማሪ ሕግጋትን ስትጨምር፥ አንድ አደገኛ ነገር መከሰት ይጀምራል። ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ይልቅ የሰዎችን ሕግ መከተል ይጀምራሉ። (ማቴ. 23፡23፤ ማር. 7፡1-9)። ወዲያውኑ የሰዎችን ሕግ ከጠበቁ መንፈሳዊ እንደሆኑ ያስባሉ። በመቀጠልም አምልኮአቸው እግዚአብሔርን ከልብ ከማምለክ ይልቅ ሕግን መጠበቅ ወደ መሞከር ይለወጣል። የግል እምነት አስፈላጊነት ለመዳን ሕግን መጠበቅ ያሻል በሚለው ተተክቶአል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሕጋዊነት ብሎ ሲጠራው፥ ሐዋርያው ጳውሎስ የሮሜንና የገላትያን መልእክቶች የጻፈው ይህንን አቋም በሚፃረር መንገድ ነው። 

  1. ከዓለም የመለየት አስፈላጊነት:- ወዲያውኑ አይሁድ የዓለምን ሕዝብ እንዲጠሉና ከአሕዛብ ጋር ምንም ግንኙነት ሊያደርጉ እንደማይገባ እንዲወስኑ አደረጋቸው። ዕዝራና ነህምያ በግልጥ እንዳስተማሩት የእግዚአብሔር ሕዝብ ከአሕዛብ ጋር የጋብቻ ኅብረት ማድረግ የለባቸውም። ነገር ግን ከአሕዛብ ጋር ከሚደረግ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንዲርቁ አላስተማሩም። በኋላ የተነሡት የአይሁድ መሪዎች ግን ከአሕዛብ ጋር ከሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ግንኙነት መራቅ እንዳለባቸው ሕዝቡን አስተማሩ። መሪዎቹ በንጽሕና በመቆየት ላይ ትኩረት ስላደረጉ ከአሕዛብ ጋር መብላት ወይም ኅብረት ማድረግ እንደሚያረክሳቸው ገመቱ። እግዚአብሔር እነርሱን የመረጠበት አንዱ ምክንያት ለአሕዛብ ብርሃን እንዲሆኑ መሆኑን ረሱ (ኢሳ. 42፡6 ተመልከት)። 

የውይይት ጥያቄ፥ የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ነገር ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ሊፈጸም የሚችለው እንዴት ነው?

ብዙ ጊዜ በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ከሚፈጸሙት አሳዛኝ ነገሮች አንዱ፥ ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ያለንን ማንኛውንም ግንኙነት ቀስ በቀስ ማቋረጣችን ነው። በዓለም ተጽዕኖ እንዳይደረግብን ከሚገባ በላይ በመሥጋት ክርስቲያን ያልሆኑ ጓደኞች እንዲኖሩን እንኳ አንፈቅድም። ከክርስቲያኖች ጋር ብቻ እንኖራለን፤ ቢመቸን ጊዜያችንን ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማሳለፍ እንሞክራለን ወዘተ። እግዚአብሔር ግን ለዓለም ብርሃንና ጨው እንድንሆን ጠርቶናል (ማቴ. 5፡13-16)። ይህንን ነገር መፈጸም የምንችለው ከማያምኑ ሰዎች ጋር ኅብረት ሲኖረን ብቻ ነው። ኢየሱስ የጸለየው ከዓለም ክፉ ነገሮች እንድንጠበቅ እንጂ፥ ከዓለም እንድንወጣ አይደለም (ዮሐ. 17፡9-16፥18 ተመልከት)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አባሎቻቸው ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ግንኙነት በማድረግ ወንጌልን እንዲያካፍሏቸው ለማበረታታት ምን ማድረግ ይችላሉ? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አባሎቻቸው ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ከሚገባ በላይ አዘውትረው ጊዜያቸውን በማሳለፍ ለማያምኑ ሰዎች ሊመሰክሩ እስከማይችሉ ድረስ እንዳይሆኑ ምን ማድረግ ይችላሉ? ሐ) የምትገናኛቸው ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ዘርዝር። መ) ስለ ኢየሱስ የመሰከርክላቸው መቼ ነበር? ሠ) በዚህ ሳምንት ለምታውቀው ለአንድ ለማያምን ሰው ፍቅር በተሞላው መንገድ ስለ ክርስቶስ ልትነግረው ቀጠሮ ያዝ። (ለምሳሌ፡- ሻይ ወይም ምሳ ጋብዘው)። ይህን ለማድረግ የምታውቀው ክርስቲያን ያልሆነ ሰው ከሌለ፥ እግዚአብሔር አንድ ሰው እንዲሰጥህና በዚህ ሳምንት ልትመሰክርለት እንድትችል ጸልይ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: