ነህምያ 5-10

ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን መሪ በተጋለጠ ስፍራ ላይ ያለ ነው። ሰይጣን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኘውን ማንኛውንም አባል የሚያጠቃ ቢሆንም፥ በተለይ በቀጥታ የሚያነጣጥረው በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ላይ ነው። ጥቃቱን የሚያደርገው በሦስት ዋና ዋና ፈተናዎች ነው። አንደኛ፥ በትዕቢት ይፈትናቸዋል። ሰይጣን መሪዎችን በኃይላቸው፥ በችሎታቸውና በውጤታማነታቸው እንዲታበዩ ይፈትናቸዋል፤ በዚህ ዓይነት በእግዚአብሔር ላይ መታመናቸውን ስለሚያቆሙ ያለ ውጤት ይቀራሉ። በሁለተኛ ደረጃ የገንዘብ ፍቅር ያጠቃቸዋል። በዚህም ሕዝቡ በአደራ የሰጡአቸውን ገንዘብ ያለ አግባብ ይጠቀሙበታል። በሦስተኛ ደረጃ፥ መሪዎች በፍትወተ ሥጋ እንዲወድቁ ያደርጋል።

የውይይት ጥያቄ፥ መሪዎች በእነዚህ ሦስት ፈተናዎች ሲወድቁ ያየኸው እንዴት ነው?

ሰይጣን ሕዝቡን ተስፋ በማስቆረጥ፥ በስደትና በማስፈራራት ሊያሸንፋቸው ስላልቻለ፥ እስራኤላውያንን በሌላ መንገድ ማጥቃት ጀመረ። ጥቃቱንም በተለይ የሕዝቡ መሪ በነበረው በነህምያ ላይ አነጣጠረ።

የውይይት ጥያቄ፥ ነህምያ 5-10 አንብብ። ሀ) ሰይጣን በእስራኤላውያን መካከል የአሳብ መከፋፈል እንዲመጣ ያደረገው እንዴት ነበር? ለ) ሰይጣን ነህምያን ለማጥፋት የሞከረው እንዴት ነበር? ሐ) የኢየሩሳሌምን ቅጥር ለመሥራት የፈጀው ጊዜ ምን ያህል ነበር? መ) የእግዚአብሔርን ቃል የማንበብ ውጤትስ ምን ነበር?

የእግዚአብሔር ሕዝብ በዓላማቸው አንድ ሲሆኑ፥ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ሲኖሩና ለእርሱ ለመሥራትም ሲስማሙ ሰይጣን ይፈራል። አንድ ሰው ለብቻው ተነጥሉ መሥራቱ አያስፈራውም። ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የታጠቁ ክርስቲያኖች በአንድነት ሆነው በቡድን የእግዚአሔርን ሥራ ከፍጻሜ ለማድረስ መሥራት ሲጀምሩ ይፈራል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እንድትሠራ የጠየቃትንና በግል ከሚሠሩ ይልቅ በቡድን ቢከናወኑ የበለጠ በጥሩ ሁኔታ ሊሠሩ የሚችሉ ነገሮችን ዘርዝር። ለ) በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ የሚሳተፉት የቤተ ክርስቲያናችን አባሎች ጥቂቶች የሆኑት ለምንድን ነው? ሐ) ብዙ አባላትን ማሳተፍ የምንችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር (ኤፌ. 4፡11-13 ተመልከት)።

ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥር የሚሠሩ ሰዎችን ሲያደራጅ ተቃውሞ ተነሣበት። በቅድሚያ ተቃውሞው የመጣው የእግዚአብሔርን ሕዝብ ተስፋ ለማስቆረጥና ስደትን እንዲፈሩ በማድረግ ነበር። ይህ ዘዴ ውጤት ሳያስገኝ ሲቀር፥ ሰይጣን ሌሎች መንገዶችን ሞከረ።

በመጀመሪያ፥ ሰይጣን በአይሁድ መካከል መከፋፈልን ሊያመጣ ሞከረ (ነህ. 5)። በነህምያ ዘመን በእስራኤል ምድር ራብ ነበር። በተጨማሪ የፋርስ መንግሥት የሚጠይቀው ግብር ለሕዝቡ ሸክም ሆነ፤ ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች ግብር ለመከፈልና የሚበሉትን ለማግኘት ሲሉ መሬታቸውን ለሀብታሞች መሽጥ ነበረባቸው። ሌሎች ደግሞ ልጆቻቸውን ለባርነት አሳልፈው መስጠት ነበረባቸው። የሚያሳዝነው ነገር ሀብታም የሆኑ አይሁድ ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም መሞከራቸው ነው። ገንዘባቸውን ከድሆች አይሁዳውያን ላይ በርካሽ ዋጋ መሬት ለመግዛት ተጠቀሙበት፤ እንዲሁም የገዛ ሕዝባቸውንም በባርነት ያዙ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም በኢትዮጵያ ይህ እንዴት ሊፈጸም ይችላል? ለ) በእንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ጊዜያት ሀብታም ክርስቲያኖች ማድረግ ያለባቸው ነገር ምንድን ነው? ሐ) መዝ. (35)፡10፤ (140)፡12 አንብብ። እግዚአብሔር ወደ ድሆች የሚመለከተው እንዴት ነው?

ነህምያ የአይሁድን መሪዎች በተለይም ገንዘባቸውን ያለ አግባብ በመጠቀማቸውና ለወንድሞቻቸው ምሕረት ባለማሳየታቸው ሀብታሞቹን ገሠጻቸው። ይህ ጉዳይ መከፋፈልን ሊያመጣና የተጀመረው ሥራ እንዲቆም ሊያደርግ ይችል ነበር፤ ነገር ግን ነህምያ በፍጥነት ስብሰባ በመጥራቱና ለችግሩ መፍትሔ በመፈለጉ፥ የመከፋፈል ነገር ቀረና የቅጥሩ ሥራ ቀጠለ።

ሁለተኛ፥ ጦቢያና ሰንባላጥ ነህምያን ማጥቃት በመጀመር ሥራውን እንዲተው ለማድረግ ሞከሩ። እነዚህ ሰዎች መሪው ከሥራው ከተለየ ሥራው እንደሚቆም ያውቁ ነበር። መሪው በቅርቡ የማይከታተለው ከሆነ ወይም ብዙ ጊዜ በሥራው ላይ ከሌለ ሥራው ሊሠራ አይችልም። ጦቢያና ሰንባላጥ ለነህምያ መልካም የሚመስለውን አሳባቸውን አቀረቡለት። ስለ አሳባቸው ለመመካከርና ሰላምን በአንድነት ለማምጣት ስለሚቻልበት መንገድ በመሰባሰብ እንዲወያዩበት አሳብ አቀረቡለት። ኦኖ ከኢየሩሳሌም 30 ኪሎ ሜትር ርቆ በይሁዳ ጫፍ የሚገኝ ስፍራ ነበር። ነህምያ ግን ሥራውን ትቶ ወደዚያ መሄድ እምቢ አለ። እግዚአብሔር ቅጥሩን ይሠራ ዘንድ እንደጠራው ያውቅ ነበር፤ ስለዚህ ሥራው እስኪጠናቀቅ ድረስ በዚያ ሥራ ላይ መቆየትን መረጠ። 

የውይይት ጥያቄ፥ አንድ መሪ እግዚአብሔር ከሰጠው ሥራዎች እጅግ ሊርቅ የሚችልበትንና በዚህ ምክንያት ሥራው እየተዳከመ ሊሄድ የሚችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

ሦስተኛ፥ ጠላቶቻቸው በሕዝቡ ፊት የነህምያን መልካም ምስክርነት ለማበላሸት ሞከሩ። ለነህምያ ግልጽ ደብዳቤ ላኩለት። የደብዳቤው አሳብ በንጉሡ ላይ ለማመፅ መሞከርህ ተሰምቶአልና ይህንን ማረጋገጫ ወደ ንጉሡ ከመላካችን በፊት ናና እንማከር የሚል ነበር።

ለአንድ መሪ ምስክርነቱን መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ሕዝቡ መሪውን የማያምነው ከሆነ፥ ወይም መጥፎ ምስክርነት ካለው ወዲያውኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት እርሱን መከተል ያቆማሉ። የነህምያ ምላሽ ግን የሚያስፋፉት ወሬ ውሸት መሆኑን በሕዝቡ ሁሉ ፊት ማሳወቅ ነበር። ነህምያ በእነዚህ ሁሉ ተቃውሞዎች ውስጥ ሥራውን እንዲቀጥል ከእግዚአብሔር ዘንድ ብርታትን ጠየቀ። አንድን መሪ እጅግ ተስፋ ሊያስቆርጡት ከሚችሉት ነገሮች አንዱ፥ የሚፈጽመውን ተግባር ሌሉች ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሲረዱትና በሐሰት ሲወነጅሉት ነው። ሕዝቡ ሁሉ እውነትን ያውቁና ይረዱ ዘንድ የተፈጸሙትን ተግባራት ለመግለጥ መሞከር አስፈላጊ ቢሆንም፥ መሪዎች በእንደዚህ ዓይነት የሐሰት ውንጀላ ሊረቱ አይገባም።

አራተኛ፥ ጠላቶች ነህምያ ስለ ሕይወቱ እንዲሠጋና ሕይወቱን ለማዳን ወደ ቤተ መቅደስ ሸሽቶ ካልተሸሸገ እንደሚገደል በመናገር አስፈራሩት። ይህም የነህምያን ምስክርነት ለማበላሸት የተደረገ ሙከራ ነበር። ነህምያ በጣም ቢፈራና ሕይወቱን ለማዳን ብሎ ቢደበቅ ኖሮ፥ ሕዝቡም ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚያስፈልጋቸው አውቀው ሥራውን ሊያቆሙ ይችሉ ነበር። መሪዎች ከሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባላት ሁሉ በተሻለና በበለጠ ሁኔታ በስደት ጊዜ ራሳቸውን ለመሸሽግና ለመከላከል መሞከር ጨርሶ የለባቸውም። ስደትን ለመጋፈጥ፥ አስፈላጊ ከሆነ ለወንጌል ለመሞት እንኳ፥ የመጀመሪያዎቹ መሆን አለባቸው። መሪዎች ደፋሮች ሲሆኑና ተቃውሞን ሲጋፈጡ፥ ሕዝቡ ድፍረትን ያገኛሉ። መሪዎች ግን ሕይወታቸውን ለመጠበቅና ለመሸሸግ ከሞከሩ፥ ሕዝቡም ለወንጌል ከመኖር ይልቅ ሕይወታቸውን በመጠበቅ ላይ ያተኩራሉ።

ነህምያና ሕዝቡ በጠላቶቻቸው ሙከራ ለመሸነፍ ፈቃደኞች ባለመሆናቸውና በአንድ አሳብ አብረው ስለሠሩ የቅጥሩ ሥራ በ52 ቀናት ውስጥ ተጠናቀቀ።

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያን አመራር ከነህምያ ሕይወትና ከቅጥሩ መሠራት ምን ለመማር እንችላለን?

የውይይት ጥያቄ፥ በነህምያ 8-10 እንደተጻፈው በሕዝቡ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል እውቀት ምን ድርሻ ነበረው?

በምዕ. 7 ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱ ሰዎች ስም ከተዘረዘረ በኋላ፥ በዕዝራና በነህምያ መሪነት በእስራኤል ስለ ተካሄደው መንፈሳዊ መነቃቃት (ተሐድሶ) እናነባለን። አንዳንድ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቁሳቁሳዊ የሆኑ ሌሎች ነገሮችን መገንባት በጣም ቀላል ነው፤ ነገር ግን የሰዎችን መንፈሳዊ ሕይወት መገንባት በጣም አስቸጋሪ ነው። ነህ. 8-10 በእስራኤል የቅጥሩ ሥራ ከተፈጸመ በኋላ ስለተካሄደው መንፈሳዊ መነቃቃት ይገልጣል። ስለ መንፈሳዊ መነቃቃት የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡

  1. መንፈሳዊ መነቃቃት የተጀመረው ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብና ማጥናት በጀመሩበት ጊዜ ነው፤ (ነህ. 8፡4-9)። ዕዝራ ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል በሚያነብበት ጊዜ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ቃል እየታዘዙ እንዳልኖሩ ተገነዘበ። ብዙ ሰዎች የዕብራይስጥን ቋንቋ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተጻፈበትን ቋንቋ የማይረዱ ስለነበሩ፥ ነህምያ ሕዝቡ መልእክቱን እንዲረዱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ወደ አራማይክ ቋንቋ በቃል ይተረጉምላቸው ነበር። 
  2. የእግዚአብሔር ቃል በእንባ የተረጋገጠ የግል ንስሐን ወደ ሰዎቹ ሕይወት አመጣ፤ (ነህ. 8፡9)። ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል በሰሙ ጊዜ እያንዳንዱ ሰው በኃጢአት እንደሚኖር ተገነዘበ። ይህም ጥልቅ ኀዘን፥ ልቅሶና በእግዚአብሔር ፊት የግል ንስሐን አስከተለ። 
  3. የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብና መረዳት ሕዝቡን ለእግዚአብሔር ወደ መታዘዝ መራቸው። ሕዝቡ ከ800 ዓመታት በፊት ከኢያሱ ዘመን ወዲህ ከተከበሩት በዓላት ሁሉ በላቀ ሁኔታ የዳስ በዓል አከበሩ።
  4. የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብ በሕዝብ ፊት በግልጽ መናዘዝንና ንስሐን አመጣ። ሕዝቡ በግል ስለ ኃጢአታቸው ማወቅ ብቻ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔር ጉባኤ እንደ መሆናቸው መጠን ስለ ኃጢአታቸው በአንድነት በግልጽ ከተናዘዙ በኋላ ንስሐ ገቡ።
  5. . ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ መወሰናቸውን ለማሳየት በመሪዎቻቸው በኩል ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ቃል ኪዳን አደሱ። እንዲሁም ለሙሴ ሕግጋት እንደሚታዘዙ በጽሑፍ ለእግዚአብሔር ቃል ሰጡ። በተለይ ከአሕዛብ ጋር ላለመጋባት መወሰናቸውን፥ በሰንበት መግዛትና መሽጥ እንደሚያቆሙ፥ አሥራትና ምጽዋት በመስጠት የቤተ መቅደሱን አገልግሉትና የአምልኮ መሪዎች የሆኑትን ሌዋውያኑን እንደሚደግፉ ቃል መግባታቸው ተገልጿል።  

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) መንፈሳዊ መነቃቃት (ተሐድሶ) በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ስለሚያስከትለው ውጤት፥ በእስራኤል ሁሉ ላይ በኃይልና በፍጥነት ከተስፋፋው ከዚህ መንፈሳዊ መነቃቃት ምን እንማራለን? ለ) የዚህ ዓይነቱ መንፈሳዊ መነቃቃት ለቤተ ክርስቲያናችን ያስፈልጋል ብለህ ታስባለህን? ምክንያትህን ግለጥ። ሐ) የዚህ ዓይነቱ መንፈሳዊ መነቃቃት እንዲኖር የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሊያደርጉት የሚገባ ነው ብለህ የምታስበውን ነገር ተናገር። መ) የዚህ ዓይነት መንፈሳዊ መነቃቃት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈጥኖ እንዲመጣ ጸልይ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: