Site icon

አስቴር 1-6

ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር በዓለም ላይ ለሕዝቡ ያለውን ዕቅድ ለመፈጸም የሚሠራው እንዴት ነው? ብዙ ጊዜ ቀይ ባሕርን እንደመክፈል ያሉ ታላላቅ ተአምራትን ይሠራልን? ብዙ ጊዜ እኛ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ይህንን የመሳሰሉ ታላላቅ ተአምራትን እንዲሠራ እንፈልጋለን። በመሆኑም በልሳን መናገርና ፈውስን ወደ መሳሰሉ አስደናቂ ተግባራት እንሳባለን። አዎን እግዚአብሔር ዛሬም ቢሆን በመካከላችን በታላላቅ መንገዶች ይሠራል፤ ነገር ግን ለአስደናቂ ነገሮች ብቻ ትኩረት በመስጠታችን፥ እግዚአብሒር በተለመዱ ጥቃቅን ነገሮችም ውስጥ እንደሚሠራ እንዘነጋለን። እግዚአብሔር የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ውሳኔ በመቆጣጠር ይሠራል። እግዚአብሔር ለወንጌል ሥራ ከፍተኛ ጥቅም ሊሰጡ በሚችሉበት ትክክለኛ ስፍራ ልጆቹን በማስቀመጥ ይሠራል። እግዚአብሔር ልናስባቸው በማንችል በሕይወታችን በሚፈጸሙ ጥቃቅን ነገሮች ውስጥ እንኳ ሲሠራ እናገኘዋለን። ለምሳሌ፥ በየቀኑ ሊጎበኙን የሚመጡ ሰዎችን የሚቆጣጠር እግዚአብሔር ነው። በመንገድም ሆነ በቢሮ የሚመጡትንና የሚገናኙንን ሰዎች የሚቆጣጠር እግዚአብሔር ነው። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን በአስደናቂ ነገሮች ላይ ብቻ የምናተኩር መሆን የለብንም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በሚያደርጋቸው ዕለታዊ የተለመዱ ነገሮችም ላይ ማተኮር ያስፈልገናል። በሕይወታችን የሚፈጸሙ ነገሮች በሙሉ በእግዚአብሔር መሪነት የሚከናወኑ ናቸው። እነዚህ ለእኛ በጣም ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮች ልናስተውላቸው እስከማንችል ድረስ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚያተኩሩባቸውን የእግዚአብሔርን ኃይል የሚያሳዩ አስደናቂ ሁኔታዎች የሚገልጹ ነገሮችን ዘርዝር ለ) እግዚአብሔር በሥራ ላይ እንደሆነ የሚያሳዩ ብዙ ሰዎች የማይገነዘቡአቸውን ተራና የተለምዶ የሚመስሉ ነገሮችን ዘርዝር። ሐ) ተአምራታዊ ከሆኑ መንገዶች ይልቅ በእነዚህ የተለመዱ ነገሮች ላይ የእግዚአብሔር እጅ እንዳለ ሌሎች የበለጠ እንዲገነዘቡ ለማድረግ ልብ ልትላቸው የምትችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። 

የውይይት ጥያቄ፥ አስቴር 1-6 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የተገለጹትን ዋና ዋና ድርጊቶች ዘርዝር። ለ) ለአይሁድ ሕዝብ ጥቅም ሲል እግዚአብሔር እንዴት በሥራ ላይ እንደሆነ የሚያሳዩ የተለያዩ ጥቃቅን ነገሮችን ዘርዝር።

አስቴር 1-6 የአስቴርን ታሪክ የተለያዩ ደረጃዎች ያሳያል። በፋርስ ቤተ መንግሥት ውስጥ የተፈጸሙ ጨርሶ የማይገናኙ የሚመስሉ ነገሮችን ይዟል። እነዚህ ታሪኮች ሲነገሩንም ለዋናው ታሪክ ያላቸው አስፈላጊነት አልተጠቀሰም። ለታሪኩ መሠረት የሆነው ዋናው ነገር በሓማ በተመሰለው በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤላዊያን ጠላትና በአስቴርና በመርዶክዮስ በተመሰለው በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ያለውን ትግል ነው። ቀጥሎ ይህንን ትግልና በባዕድ ምድር ሕዝቡን ለመታደግ በመሥራት ላይ የነበረውን የእግዚአብሔርን እጅ የሚያሳዩትን ነገሮች አስተውል። 

  1. ንግሥት አስጢን ከንግሥትነት ሥልጣንዋ ተወግዳ አንዲት የማትታወቅ አስቴር የተባለች ሴት የምትቀጥለዋ የፋርስ ንግሥት ሆና ተመረጠች። ይህ በጣም አስፈላጊ የነበረው በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግና የአይሁድን ሕዝብ ከጠቅላላ ጥፋት ለማዳን የቻለች ንግሥት አስቴር ስለነበረች ነው። እግዚአብሔር በአንድ የአሕዛብ ግብዣ ተጠቅሞ አንዲት ንግሥት እንድትወገድና ሕዝቧን ለማዳን እንድትችል አስቴር ንግሥት እንድትሆን አደረገ። 
  2. የአስቴር አጎት የነበረው መርዶክዮስ ንጉሡን ለመግደል የተደረገውን ሴራ ሰማና ይህንን ለንጉሡ ነገረ። መርዶክዮስ ይህን ሴራ በማክሸፉ ረገድ ያበረከተው በቤተ መንግሥቱ መዛግብት ውስጥ ተጻፈ። ይህ መረጃ የአይሁድ ሕዝብ ጠላት የነበረው ሐማ የሚጠላውን መርዶክዮስን ለማክበር በተገደደበት ጊዜ አስፈላጊ ሆነ። የንጉሡ የግል አማካሪ የነበረውን የሐማ ስፍራ የወሰደም መርዶክዮስ ነበር። በዚህም ውስጥ የእግዚአብሔርን እጅ እናያለን። እግዚአብሔር ንጉሡ እንዳይገደል አደረገ፤ ቢገደልም ኖሮ አስቴር በአዲሱ ንጉሥ ላይ ተጽዕኖ ማድረግ አትችልም ነበር። እግዚአብሔር ሴራውን ሊያከሽፍ በሚችልበት ትክክለኛ ስፍራ ላይ መርዶክዮስን አስቀመጠው። በኋላም የመርዶክዮስን ሥራ እግዚአብሔር ለንጉሥ አስታወሰና በፋርስ መንግሥት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ በሆነ ስፍራ በማስቀመጥ እንዲያከብረው አደረገ።
  3. አጋጋዊው ሐማ ያለ ምንም ምክንያት የጠላቸውን የአይሁድን ሕዝብ ለማጥፋት ሴራ አሴረ። እንደምታስታውሰው፥ አጋግ ከአማሌቃውያን ነገሥታት አንዱ ነበር (1ኛ ሳሙ. 15፡20)፤ ስለዚህ ሐማም አማሌቃዊ መሆኑን መገመት ትክክል ነው። ሐማ በምድሪቱ ያሉትን አይሁድ በሙሉ ለማጥፋት ከአርጤክስስ ፈቃድ አገኘ። 
  4. መርዶክዮስ አይሁድን ለማዳን የምትችለውን ሁሉ ማድረግ እንዳለባት አስቴርን አሳመናት፡ አስቴር 4፣14 በመጽሐፉ ውስጥ ያለ ቁልፍ ጥቅስ ነው። ስለ ሕይወቷ ለፈራችው ለአስቴር መርዶክዮስ እንዲህ አላት፡- «አንቺ፡- በንጉሥ ቤት ሰለሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። በዚህ ጊዜ ቸል ብትይ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደሆነ ማን ያውቃል?» በዚህ ንግግር ውስጥ ሁለት እውነቶችን እናያለን። የመጀመሪያው፥ ከአይሁድ ሕዝብ ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን ያደረገው እግዚአብሔር የአይሁድ ሕዝብ እንዳሉ እንዲጠፉ እንደማይፈቅድ መርዶክዮስ ያውቅ እንደ ነበር ነው። ብዙ ሰዎች ቢሞቱም እንኳ፥ እግዚአብሔር አይሁድን ሙሉ ለሙሉ ከመጥፋት ሁልጊዜ ይጠብቃቸዋል።

ሁለተኛው ነገር እግዚአብሔር የራሱን ዓላማ ለመፈጸም ግለሰቦችን በልዩ የኃላፊነት ስፍራ በማስቀመጥ እንደሚጠቀምባቸው መርዶክዮስ ተገንዝቦ ነበር። መርዶክዮስ አስቴር ንግሥት የሆነችው በዕድል እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። አስቴርን የፋርስ ንግሥት በማድረግ አይሁድን ለማዳን ሊጠቀምባት የወደደው እግዚአብሔር እንደሆነ መረዳት አለብን።

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር ጠቃሚ የሆኑ ክርስቲያኖችን ትክክለኛ በሆነ የአመራር ስፍራ በማስቀመጥ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት እንዴት እንደተጠቀመባቸው የሚያሳይ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመ ተመሳሳይ ሁኔታ ስጥ። 

  1. አስቴር ወደ ንጉሡ በመሄድ ወደ አዘጋጀችው ግብዣ እንዲመጣ ጠየቀችው። በፋርስ ባሕል ማንም ሰው ንግሥቲቱም ብትሆን እንኳ ያለ ንጉሡ ጥሪ እርሱ ወዳለበት መግባት አይችልም ነበር። አስቴር ወደ ንጉሡ በመግባቷ በትረ መንግሥቱን የምታመለክተውን በትር ወደ እርሷ ካልዘረጋላት ሕይወቷን እንኳ ልታጣ እንደምትችል ታውቅ ነበር፤ ነገር ግን የእርሷ ሕይወት ከወገኖች ሁሉ ሕይወት እንደማይበልጥ ተገነዘበች። ስለዚህ በፈቃዴ ወደ ንጉሡ ገባች። ይህንን ከማድረጓ በፊት ግን እግዚአብሔር በሥራዋ የተዋጣለት ያደርጋት ዘንድ አይሁድ ሁሉ እንዲጾሙና እንዲጸልዩ ጠይቃ ነበር። አስቴር፥ በንጉሡ ፊት ሞገስ እንድታገኝ ሊያደርግ የሚችል እግዚአብሔር እንደሆነ ታውቅ ነበር! ስለዚህ አይሁድ ሁሉ እንዲጸልዩላት ጠየቀች። እግዚአብሔር ጸሎቷን አከበረ። እንዲሁም በእግዚአብሔር ጥበቃ ላይ የነበራትን እምነት ሕይወቷን እንኳ ለመሠዋት ፈቃደኛ መሆኗን በንጉሡ ፊት ሞገስ በመስጠት አከበረላት።
  2. ለእርሱ ክብር ለመስጠት መርዶክዮስ ባለመስገዱ ሐማ ተቆጣ። ስለዚህ ለመርዶክዮስ የመስቀያ ግንድ አዘጋጀ፤ ነገር ግን መርዶክዮስን ለመስቀል ከንጉሥ ፈቃድ ከመጠየቁ በፊት፥ እግዚአብሔር ለንጉሡ እንቅልፍ በመከልከል መርዶክዮስ ሕይወቱን ማዳኑን እንዲያስታውስ አደረገው። በዚያን ጊዜ ሐማ፥ የሚጠላውን መርዶክዮስን ለማክበር ተገደደ፤ ስለዚህ ጸሐፊው የማያምኑ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕዝብ ቢጠሉም እንኳ አንድ ቀን ሊያከብሯቸው እንደሚገደዱ ያስተምረናል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ፊልጵ. 2፡9-11 አንብብ። የኢየሱስ ጠላቶች አንድ ቀን እርሱን እንዲያከብሩት የሚገደዱት እንዴት ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከዚህ የመጽሐፈ አስቴር ክፍል የምንማራቸውን አንዳንድ ጠቃሚ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ እውነቶች ለቤተ ክርስቲያንህ የምታስተምርባቸውን መንገዶች በሚመለከት ዕቅድ አውጣ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version