የታሪክ መጻሕፍት ክለሳ

እስካሁን ድረስ ባካሄድነው ጥናታችን ሁለት ዋና ዋና የብሉይ ኪዳን ክፍሎችን ተመልክተናል። በመጀመሪያ ፔንታቱክ በሚል ስም የታወቁትን በሙሴ የተጻፉትን አምስቱን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ተመልክተናል። በሁለተኛ ደረጃ፣ አሥራ ሁለቱን የታሪክ መጻሕፍትን ተመልክተናል። እነዚህ የታሪክ መጻሕፍት የተጻፉት በተለያዩ ያልታወቁ ጸሐፊዎች ነበር። የሚናገሩትም በብሉይ ኪዳን ያሉትን የቀሩትን የእግዚአብሔር ሕዝብ ታሪክ ነው። ታሪኩም ከ1400 እስከ 400 ዓ.ዓ. ድረስ ያለውን ዘመን የሚሸፍን ነው። እነዚህ 12 መጻሕፍት የ1000 ዓመታት ታሪክ ይሸፍናሉ። ታዲያ ሁሉም የታሪክ መጻሕፍት ቢሆንም በትምህርት ቤት እንደምንማራቸው የታሪክ መጻሕፍት የተጻፉ አይደሉም። ይልቁንም እያንዳንዱ መጽሐፍ የተጻፈው መንፈሳዊ እውነትን ለእግዚአብሔር ሕዝብ ለማስተማር ነው። ከእነዚህ መጻሕፍት በምናነብበት፥ በምናጠናበትና በምንሰብክበት ጊዜ በውስጣቸው ያለው መንፈሳዊ እውነት ምን እንደሆነ ልንረዳና ለቤተ ክርስቲያን አባሎቻችን ልናስተምር ይገባናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) 12ቱን የታሪክ መጻሕፍት ዘርዝር። ለ) እያንዳንዱን መጽሐፍ በሚመለከት መጽሐፉ የሚናገራቸውን ዋና ዋና የታሪክ ወቅቶች ዘርዝር። ) በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ገጸ ባሕርያትን ግለጥ፡ መ) በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና ትምህርቶች ዘርዝር።

የሚከተሉትን መጻሕፍት ዝርዝር ተመልከት 

  1. ኢያሱ፡- እንደምታስታውሰው ኢያሱ ሙሴ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ መሪ ነበር። ሕዝቡን ወደ ከነዓን ለመምራትና በዚያ የሚኖሩ ጠላቶቻቸውን ሁሉ ለማሸነፍ እግዚአብሔር የተጠቀመበት ሰው ነበር። ኢያሱ በእግዚአብሔር ጠላቶች ላይ ስለሚገኝ ድል የሚናገር መጽሐፍ ነው። በኢያሱ ዘመን የተገኘው ድል አብዛኛው በምድራዊ ጠላቶች ላይ ነበር፤ ለእኛ ግን በመንፈሳዊ ጠላቶቻችን ላይ ስለሚገኝ ድል የሚያስተምረን ነው። 
  2. መሳፍንትና ሩት፡- ዘመነ መሳፍንት ኢያሱ ከሞተ አንሥቶ እስከ መጀመሪያው የእስራኤል ሕዝብ ንጉሥ እስከ ሳኦል ዘመን ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን ወደ 400 ዓመታት ይጠጋል። የመጽሐፈ መሳፍንት ዋና አሳብ «ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር» (መሳ. 17፡6፤ 21፡25) በሚለው ጥቅስ ውስጥ ይገኛል። አይሁድ እግዚአብሔርን በመካድ የሐሰት አማልክትን (ጣዖታትን) የተከተሉበት የክሕደት ጊዜ ነበር። መጽሐፈ መሳፍንት አይሁድ ያለፉበትን የውድቀት ሂደት ይናገራል። በመጀመሪያ፣ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠሩ። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው በከነዓናውያን እጅ አሳልፎ በመስጠት ቀጣቸው። ሦስተኛ፥ ለተወሰነ ጊዜ በባርነት ቀንበር ሥር ቆዩ። አራተኛ፥ እግዚአብሔር ከጠላቶቻቸው እጅ ነፃ እንዲያወጣቸው ወደ እርሱ ጮኹ። አምስተኛ፥ እግዚአብሔር ፈራጅ የሆነ መስፍንን ወይም የጦር መሪን በማስነሣት ጠላቶቻቸውን እንዲያሸንፉና እንደገና ኃጢአት ሠርተው እስኪፈረድባቸው ድረስ የነፃነት ዘመን ሰጣቸው። በዚህ ዘመን የተነሡ ዋና ዋና መሳፍንት ናትናኤል፥ ናዖድ፥ ዲቦራና ባርቅ፥ ጌዴዎን፥ ዮፍታሔና ሶምሶን ነበሩ። የመጽሐፈ ሩት ታሪክ የተፈጸመው በዘመነ መሳፍንት ሲሆን፥ አብዛኛው ሕዝብ እንዴት እግዚአብሔርን እንዳላከበረና በዚህ ዓይነት ጨለማ ውስጥ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ጥቂት ሰዎች እንደነበሩ የሚያሳይ ነው። 
  3. 1ኛ ሳሙኤል፡- 1ኛ ሳሙኤል እስራኤል ከዘመነ መሳፍንት በአንድ ንጉሥ ሥር አንድ መንግሥት ሆና ትተዳደር ወደነበረችበት ወደ ነገሥታት ዘመን ስላደረገችው የሽግግር ጊዜ የሚናገር መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ የእስራኤል የመጨረሻ መሳፍንት ስለሆኑት ስለ ዔሊና ስለ ሳሙኤል ይገልጣል። በተጨማሪ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ስለሆነው ስለ ሳኦልም ይናገራል። ስለ ሳኦል ውድቀትና ተከታዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን እግዚአብሔር ዳዊትን እንዴት እንደመረጠው ይናገራል። የ1ኛ ሳሙኤል አብዛኛው ታሪክ የሚናገረው ስለ ዳዊት ዝና አጀማመርና ሳኦልም ዳዊትን ለመግደል ስላደረጋቸው የተለያዩ ሙከራዎች ነው።
  4. 2ኛ ሳሙኤልና 1ኛ ዜና መዋዕል፡- እነዚህ ሁለት መጻሕፍት የሚሸፍኑት ተመሳሳይ ጊዜያትን ነው። የሚናገሩትም በእስራኤል ተወዳዳሪ ስላልተገኘለት ስለ ታላቁ ንጉሥ ነው። እግዚአብሔር ለዳዊት የዘላለም ቃል ኪዳንን በመግባት በእስራኤል ሁሉ ላይ ገዥ የመሆን መብትን ለዘሩ እንደ ሰጠ እንመለከታለን። ይህንን ቃል ኪዳን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደሚፈጽመው አይተናል። እነዚህ መጻሕፍት በዳዊት ሕይወት ስለታየው መንፈሳዊ ታላቅነትና ወታደራዊ ኃይል ይናገራሉ። 2ኛ ሳሙኤል በዳዊት ወታደራዊ ታላቅነትና ኃጢአት ላይ ሲያተኩር፥ 1ኛ ዜና የሚያተኩረው ደግሞ በዳዊት መንፈሳዊ ሕይወትና ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም በመውሰድና ለቤተ መቅደሱ ሥራ ዝግጅት በማድረግ እግዚአብሔርን እንዴት እንዳከበረ በመናገር ላይ ነው። 
  5. 1ኛ ነገሥትና 2ኛ ዜና መዋዕል 1-18፡- እነዚህ መጻሕፍት ከተባበረው የእስራኤል መንግሥት ወደ ተከፋፈለው መንግሥት የተደረገውን የሽግግር ዘመን የሚናገሩ ናቸው። የሁለቱም መጻሕፍት የመጀመሪያ ክፍሎች የሚናገሩት ጠቢብ ስለነበረው ስለ ዳዊት ልጅ ስለ ሰሎሞን ነው። 1ኛ ነገሥት እስራኤልን ወደ ክሕደት በመምራት የእስራኤልን መንግሥት በሁለት ስለከፈለው ስለ ሰሎሞን ኃጢአት ይናገራል። 2ኛ ዜና መዋዕል ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንዴት እንደሠራ ይናገራል። ቀጥሉ እነዚህ መጻሕፍት የሚናገሩት አንድ የነበረው የእስራኤል መንግሥት እንዴት ለሁለት እንደተከፈለ ነው። በስተ ሰሜን የሚገኙት አሥሩ ነገዶች እስራኤል ተብለው የተጠሩ ሲሆን፥ ዋና ከተማቸውም ሰማርያ ነበረች። የብንያምና የይሁዳን ነገዶች የያዙት ሁለቱ ነገዶች ዋና ከተማቸውን ኢየሩሳሌም በማድረግ የይሁዳን መንግሥት መሠረቱ። 1ኛ ነገሥት የሰሜኑንና የደቡቡን መንግሥታት የተለያዩ ነገሥታት በአጭር በአጭሩ ሲያቀርብ፥ 2ኛ ዜና ደግሞ ያተኮረው በደቡብ መንግሥት ነገሥታት ላይ ነው። እንደዚሁም 1ኛ ነገሥት በነቢያት ሥራ ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ 2ኛ ዜና የሚያተኩረው ግን በሌዋውያን ሥራ ላይ ነው። 
  6. 2ኛ ነገሥትና 2ኛ ዜና መዋዕል 19-36፡- እነዚህ መጻሕፍት የሰሜኑ መንግሥት እስራኤል በ722 ዓ.ዓ. በአሦር መንግሥት መደምሰሱንና የይሁዳ መንግሥት የሚባለው የደቡብ መንግሥት ደግሞ በ586 በባቢሎናውያን መማረኩን ይናገራሉ። 2ኛ ነገሥት የሚናገረው ስለ ሰሜኑና ላለ ደቡቡ መንግሥት ሲሆን 2ኛ ዜና የሚያተኩረው ግን በደቡቡ መንግሥት ላይ ሆኖ በተለይ ደግሞ በይሁዳ እውነተኛ አምልኮን ለመመለስ የተሐድሶ ሥራ በሠሩ እግዚአብሔርን በሚፈሩ መሪዎች ታሪክ ላይ ነው። 2ኛ ነገሥት በነቢያት ሥራ ላይ ማተኮሩን ሲቀጥል፥ 2ኛ ዜና ግን ስለ ሌዋውያን ሥራ ይናገራል። 
  7. መጽሐፈ ዕዝራ፥ ነህምያና አስቴር፡- እነዚህ ሦስት መጻሕፍት የሚናገሩት ከኢየሩሳሌም መደምሰስ በኋላና አይሁድ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከተመለሱ በኋላ ስላለው ጊዜ ነው። ዕዝራና ነህምያ የሚያተኩሩት ከምርኮ ወደ ይሁዳ በተመለሱት አይሁድ ላይ ነው። መጽሐፈ ዕዝራ በዕዝራና በዘሩባቤል መሪነት የተመለሱትን የመጀመሪያዎቹን ሁለት የእስራኤል ቡድኖች የሚገልጽ ሲሆን፥ በተጨማሪ ስለ ሁለተኛው ቤተ መቅደስ መሠራትና ዕዝራ በይሁዳ ስለመራው መንፈሳዊ መነቃቃት ይናገራል። መጽሐፈ ነህምያ ደግሞ ስለ ኢየሩሳሌም ቅጥር መሠራትና ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል በሰሙ ጊዜ በመካከላቸው ስለተፈጸመው መንፈሳዊ መነቃቃት ይናገራል። መጽሐፈ አስቴር የሚያተኩረው በምርኮ ምድር በነበሩ አይሁድ ላይ ነው። መጽሐፉ እዚአብሔር ሕዝቡን በቸርነቱ የፋርስ ንግሥት አድርጎ ባስቀመጣት በአስቴር አማካይነት ከመደምሰስ እንዴት እንደጠበቃቸውና የሐማን ዕቅድ እንዳከሸፈ ይናገራል። የብሉይ ኪዳን ጥናት የመጀመሪያ ክፍል የሆነውን የዚህን መጽሐፍ ጥናት የመጨረሻውን ፈተና ለመውሰድ ተዘጋጅ። የቀሩትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በሚቀጥለው ጥናት እንመለከታለን።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: