“አማኝ ኃጢአት አያደርግም” ማለት ምን ማለት ነው? (1 ዮሐ. 3:6 ፤ 5:18)?

በመጀመሪያው መልዕክቱ ላይ ሐዋሪያው ዮሐንስ አማኝ ስላለው ድነት (ደኅንነት) ማረጋገጫ የሚሰጥ መልዕክት ያስተላልፋል “የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ።” (1 ዮሐ 5:13)፡፡ አንባቢዎቹ የዘላለም ሕይወት እንዳላቸው “እንዲገነዘቡ” ስለሚፈልግ፣ ዮሐንስ በእውነት የዳንን መሆናችንን ወይም አለመሆናችንን ለመመርመር የምንጠቀምበትን የእምነት መፈተሻም ያቀርባል፡፡

በ 1 ዮሐንስ ውስጥ የእውነተኛ አማኝ መገለጫዎች በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ አንድ ሰው ክርስቶስን ካወቀ እና በጸጋው እያደገ ከሄደ በአጠቃላይ የሚከተሉት ባህሪዎች ሊታዩበት ይገባል፡-

  1. አማኝ ከክርስቶስ እና ከተቤዣቸው ህዝቡ ጋር ህብረት ያደርጋል (1 ዮሐ. 1፡3)።
  2. አማኝ በጨለማ ሳይሆን በብርሃን ውስጥ ይራመዳል (1 ዮሐንስ 1፡6-7)።
  3. አማኝ ኃጢአቱን አምኖ ይናዘዛል (1 ዮሐንስ 1፡8)
  4. አማኝ የእግዚአብሔርን ቃል ይታዘዛል (1 ዮሐ. 2፡3-5)።
  5. አማኝ ከዓለም ይልቅ እግዚአብሔርን ይወዳል (1 ዮሐ. 2፡15)።
  6. የአማኝ ሕይወት ባሕርይ “ትክክል የሆነውን በማድረግ” ይገለጣል (1 ዮሐ. 2፡29)።
  7. አማኝ ንፁህ ህይወት ጠብቆ ለመኖር ይፈልጋል (1 ዮሐ. 3፡3)።
  8. አማኝ በሕይወቱ ውስጥ የኃጢአት ተግባራት እየቀነሱ የመሄዳቸውን ሁኔታ ይመለከታል (1 ዮሐንስ 3፡5-6፣ 5፡18)።
  9. አማኝ ለሌሎች ክርስቲያኖች ፍቅርን ያሳያል (1 ዮሐንስ 3፡14)።
  10. አማኝ “የቃል” ሳይሆን “የተግባር” ሰው ነው (1 ዮሐንስ 3 ፥ 18-19)።
  11. አማኝ ንጹህ ህሊናን ይይዛል (1 ዮሐንስ 3:21)።
  12. አማኝ በክርስቲያናዊ ጉዞው ድልን ይለማመዳል (1 ዮሐንስ 5:4)።

ከላይ በተዘረዘረው ዝርዝር ተራ ቁጥር 8 ላይ አማኙ በሕይወቱ የኃጢያት ልምምድን እየቀነሰ እንደሚሄድ ያሳያል፡፡ ዮሐንስ በምዕራፍ 3 እና 5 ላይ እንዲህ ይላል፣ “በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም።”(1 ዮሐ. 3፡6) “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንዳያደርግ፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተወለደው ራሱን እንዲጠብቅ ክፉውም እንዳይነካው እናውቃለን።” (1 ዮሐንስ 5፡18)

አንዳንዶች እነዚህን ጥቅሶች “ክርስቲያኖች ኃጢአት የሌለበትን ፍጹም ሕይወት መምራት ይችላሉ” በማለት በተሳሳተ መንገድ ይተረጉማሉ፡፡ በዮሐንስ “በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤” (1 ዮሐ. 3፡6) እና “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እያደርግም፥” (5፡18) በሚሉት ጥቅሶች ላይ በመመስረት ክርስቲያኖች ፍጹማን ስለሆኑ ክርስቲያን ነኝ እያለ ሃጢአትን የሚያደርግ ሰው ተግባሩ አለመዳኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው ይላሉ፡፡ ዮሐንስ ግን የሚያስተምረው ይህን አይደለም፡፡

ዮሐንስ ይህን ሲል አማኞች በኃጢአት ጸንተው እንደማይቀጥሉ ለማሳየት እንጂ ሃጢአት አልባ ሕይወት እንደማይኖሩ ለመናገር ፈልጎ እንዳልሆነ በዚሁ መልዕክቱ ውስጥ በሌላ ስፍራ በተናገረው ሃሳብ ለመረዳት እንችላለን፡፡ “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።” (1ኛ ዮሐንስ 1፡8)፡፡ ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን፤ ከዳንን በኋላም እንኳን ከኃጢአት ጋር መታገላችንን እንቀጥላለን፡፡ ከጌታ ጋር በክብር መኖር እስክንጀምር ድረስ ከሃጢአት ጋር የምናደርገው ትግል ይቀጥላል፡፡ “…እርሱን እንድንመስል እናውቃለን” (1 ዮሐ. 3፡2)።

ዮሐንስ ኃጢአት ስለሌለበት ፍጹም ሕይወት የማይናገር ከሆነ አማኞች ኃጢያት አያደርጉም ማለቱ ምን ማለቱ ነው? ይህ ማለት በቀላሉ፣ ሃጢአት የአማኞች የዘወትር ተግባር ወይም መገለጫቸው አይደለም ማለቱ ነው፡፡ ከክርስቶስ በፊት በነበራቸው አሮጌ ሕይወትና ከክርስቶስ በኋላ ባላቸው አዲስ ሕይወት መካከል ልዩነት እንዳለ መታየት ይገባዋል፡፡ በስርቆት ይታወቅ የነበረ ሰው ከእንግዲህ በዚያ ሕይወቱ ሊታወቅ አይገባውም፡፡ በሥነ ምግባር ብልሹነቱ ተለይቶ ይታወቅ የነበረው ዘማዊ ደግሞ ከዚህ ወዲያ ያ መታወቂያው ሊሆን አይገባም ማለት ነው፡፡ ቀድሞ ሌባ የነበረው የእግዚአብሔር ልጅ አሁንም ከስግብግብነት ፈተና ጋር ይታገላል፤ ዳሩ ግን በስርቆት ሕይወት ጸንቶ አይኖርም፡፡ ቀድሞ አመንዝራ የነበረው የእግዚአብሔር ልጅ አሁንም ከሥጋዊ ፍላጎቱ ጋር ይታገላል፤ ዳሩ ግን ከሃጢአት ሃይል ነጻ ስለሆነ የተለየ ሕይወት ለመኖር አቅም አለው፡፡ “በእርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል።” (1 ዮሐንስ 3፡3)።

በእርሱ የሚኖር (ከእርሱ ጋር የጠበቀ ሕብረት ያለው) ስራዬ ብሎ እና አዘውትሮ በሃጢአት ልምምድ ውስጥ አይኖርም፡፡ ከእግዚአብሔር የተወለደ ሃጢአትን በመስራት ጸንቶ አይኖርምና፡፡ የሃጢአት ልምምድ የሕይወቱ መገለጫ አይሆንም፡፡ ሃጢአት አልፎ አልፎ የሚሳብበት እና የሚታለልበት እንቅፋቱ እንጂ የሚኖርበት ጎጆው አይሆንም፡፡  

አማኝ ከኃጢያት ጋር ይታገላል፤ አንዳንዴም ይሸነፋል፡፡ ሆኖም በሃጢአት ጸንቶ መኖር የሕይወት ዘይቤው ሊሆን አይችልም፡፡ በጸጋ እና በጌታ እውቀት እያደግን ስንሄድ (2 ጴጥሮስ 3፡18) እየተቀደስን እንሄዳለን፡፡ አብዝተን በመንፈስ ቅዱስ በተመራን ቁጥር የበለጠ ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዥ በመሆን እንራመዳለን፡፡ ያለንስሃ ሕይወት በሃጢአት ጸንቶ መኖር በክርስቶስ ካለው አዲስ ሕይወት ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ያለመዳን ምልክት ነው፡፡  

ዮሐንስ አማኞች በኃጢአት ጸንተው የማይኖሩበትን ምክንያት ነግሮናል፣ “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም (በሃጢአት ጸንቶ አይኖርም)፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም (በሃጢአት ጸንቶ ሊኖር አይችልም)።” (1 ዮሐ. 3 9)። እውነተኛ ክርስቲያን “ስራዬ ብሎ እና አዘውትሮ” ኃጢአት አይሠራም፡፡ ይህ ልምምድ በእርሱ “መንፈሳዊ ዲ ኤን ኤ” ውስጥ አይገኝና።

ምንጭ፣ https://www.gotquestions.org/

ትርጉም፣ አዳነው ዲሮ ዳባ

Leave a Reply

%d bloggers like this: