ፔንታቱክ፣ የብሉይ ኪዳን የክፍል አንድ ጥናት ክለሳ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተመደቡባቸውን አራት የተለያዩ ክፍሎች ጥቀስ። ለ) በእነዚህ አራት የተለያዩ ክፍሎች የሚመደቡትን መጻሕፍት ዘርዝር።

ሠላሳ ዘጠኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ ነው። የመጀመሪያው መጽሐፍ ኦሪት ዘፍጥረት በሙሴ በ1400 ዓ.ዓ. ተጻፈ። የመጨረሻው መጽሐፍ ትንቢተ ሚልክያስ ደግሞ በ400 ዓ.ዓ. አካባቢ ተጻፈ።

ብሉይ ኪዳን በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ሊከፈል ይችላል፡-

  1. ፔንታቱክ ወይም የሙሴ መጻሕፍት፡- ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ኦሪት ዘዳግም ያሉት የመጀመሪያ አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በሙሴ ነው ተብሎ ይታመናል። አይሁድ እነዚህን አምስት መጻሕፍት እንደ አንድ ክፍል ያዩዋቸዋል። እነዚህ መጻሕፍት ለቀሪው የብሉይ ኪዳን ክፍል መሠረት ስለሚጥሉ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ የብሉይ ኪዳን መጻሕት መካከል ነበሩ፡
  2. የታሪክ መጻሕፍት፡- የሚቀጥሉት አሥራ ሁለቱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ የደቡቡ የይሁዳ መንግሥት ከምርኮ በመመለስ ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እስከሠራበት ጊዜ ያለውን የእስራኤልን ታሪክ የሚናገሩ ናቸው (ኢያሱ – ዕዝራና ነህምያ)። በመጀመሪያው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ጥናታችን ውስጥ እነዚህን ሁለት ክፍሉች ተመልክተናል። 
  3. የግጥምና የቅኔ ወይም የጥበብ መጻሕፍት፡- ሦስተኛው የብሉይ ኪዳን ክፍል ሁለት ዐበይት መጠሪያዎች አሉት። አንዳንዶች የግጥምና የቅኔ መጻሕፍት ብለው ሲጠሩት፥ ሌሎች ደግሞ የጥበብ መጻሕፍት በማለት ይጠሩታል። ይህ ክፍል ከኢዮብ እስከ መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን ያሉትን አምስት መጻሕፍት ይይዛል። 
  4. ነቢያት፡- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የመጨረሻ ዐቢይ ክፍል አሥራ ሰባት የነቢያት መጻሕፍትን ይዟል። እነዚህ አሥራ ሰባት የነቢያት መጻሕፍት በተጨማሪ በሁለት ክፍሎች ይከፈላሉ። የመጀመሪያው ክፍል አምስት ትልልቅ የነቢያት መጻሕፍትን የያዘ ሲሆን እነዚህ መጻሕፍት ከኢሳይያስ እስከ ዳንኤል ያሉት ናቸው። ትልልቅ የነቢያት መጻሕፍት የተባሉበት ምክንያት ረጃጅም ስለሆኑና መልእክታቸው ከሌሉች የነቢያት መጻሕፍት ይልቅ ጥልቀት ያለው ስለሆነ ነው። ሁለተኛው የነቢያት መጻሕፍት ክፍል ደግሞ ታናናሽ የነቢያት መጻሕፍት የሚባል ሲሆን፥ ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ያሉ አሥራ ሁለት መጻሕፍትን የያዘ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የፔንታቱክን አምስት መጻሕፍት ዘርዝር። ለ) የእነዚህ መጻሕፍት ጸሐፊ ማን ነበር? ሐ) በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ዋና ታሪክ ወይም ትምህርት ምንድን ነው?

ፔንታቱክ 

ፔንታቱክ ወይም የመጀመሪያዎቹ አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በሙሴ እንደሆነ ይታመናል። እነዚህ መጻሕፍት የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ ከመጀመሪያው ከአብርሃም አንሥቶ፥ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ፍጻሜ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት እስከተዘጋጁበት ጊዜ ድረስ ያለውን የሚያጠቃልሉ ናቸው።

ኦሪት ዘፍጥረት፡- ኦሪት ዘፍጥረት ስለ ነገሮች ጅማሬ የሚናገር መጽሐፍ ነው። ኦሪት ዘፍጥረት የአብዛኛዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች የሚያስተዋውቀን መጽሐፍ በመሆኑ፥ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረት የሚጥል መጽሐፍ ነው። ዓለም እንዴት በእግዚአብሔር እንደተፈጠረ፥ ኃጢአት ወደ ዓለም እንዴት እንደገባ፥ የተለያዩ ነገዶች የተገኙት እንዴት እንደሆነ ይገልጥልናል። ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር ምርጥ የሆነው የእስራኤል ሕዝብ ጅማሬ እንዴት እንደነበር ይገልጻል። የእስራኤል ሕዝብ አባትና የክርስቲያኖች መንፈሳዊ አባት ስለሆነው ስለ አብርሃም ይናገራል። እንዲሁም ስለ ሌሉቹ የእስራኤል ሕዝብ አባቶች ማለትም ስለ ይስሐቅና ያዕቆብ ይነግረናል። ያዕቆብ የአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች አባት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ከሚገኙ ዐበይት መንፈሳዊ ትምህርቶች አንዳንዶቹን ጥቀስ።

ኦሪት ዘጸአት፡- የኦሪት ዘጸአት መጽሐፍ የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ሲናገር የቆየውን የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ ከ400 ዓመታት ልዩነት በኋላ በመቀጠል ይተርካል። በግብፅ ስለነበረባቸው የባርነት ቀንበር፥ እግዚአብሔር ከባርነት እንዴት ነፃ እንዳወጣቸውና በሲና ተራራ ከእነርሱ ጋር በመገናኘት ቃል ኪዳንን እንዳደረገ ይናገራል። የኦሪት ዘጸአት ታሪክ ለእስራኤላውያን እጅግ ጠቃሚ ነበር። ስለሆነም የግጥምና የቅኔ እንዲሁም የነቢያት መጻሕፍት ጸሐፊዎች በተደጋጋሚ ከኦሪት ዘጸአት ይጠቅሱ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ፥ እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት በእግዚአብሔር የመዋጀታቸው ታሪክ እግዚአብሔር እንዴት ሕዝቡን ያለማቋረጥ ከመከራቸው እንደሚያድናቸው ለአይሁድ የሚያሳይ ምሳሌ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት አሥር ተአምራትን የተጠቀመበት መንገድ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ አስደናቂ ተአምራትን በማድረግ ከጎናቸው እንደሚቆም ዋስትና ነበር። በሦስተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር ታላቅነቱን ያሳየበትና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን የጀመረበት የሲና ተራራ ገጠመኝ፥ እስራኤላውያንን የእግዚአብሔር ልዩ ሕዝብ እንደሆኑ በማሳየት አበረታትቶቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ከላይ የተመለከትናቸው ሦስቱ እውነቶች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለክርስቲያኖች የሚታዩት እንዴት ነው?

ኦሪት ዘሌዋውያን፡- ኦሪት ዘሌዋውያን ስለ አምልኮና ስለተቀደሰ አኗኗር ሕግጋት የሚናገር ነው። የኦሪት ዘሌዋውያን አብዛኛው ክፍል የሕግጋትን ዝርዝር የያዘ ነው። እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለማምለክ ማቅረብ ስለነበረባቸው የተለያዩ መሥዋዕቶች ይገልጻል። የአምልኮውን ሥርዓት ለመምራት ስለተመረጡት ካህናትና ሌዋውያን ይገልጻል። በመጨረሻም የእግዚአብሔር ሕዝብ በዙሪያው ከሚኖሩ ሕዝብ የሚለይባቸውን በርካታ የተለያዩ ሕግጋት ይሰጣል። እነዚህ ሕግጋት የእግዚአብሔርን ቅድስናና ሕዝቡም ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ እንደሚፈልግ ያሳያሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ጴጥሮስ 1፡15-16 ኣንብብ። ሀ) በዚህ ስፍራ ከኦሪት ዘሌዋውያን ትምህርት ጋር ተመሳሳይ ሆኖ የተሰጠው ትእዛዝ ምንድን ነው? ለ) በዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ቅዱሳን እንደሆኑ የሚያሳዩባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

ኦሪት ዘኁልቁ፡- ኦሪት ዘኁልቁ እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ መንከራተታቸውን ይገልጻል። የእስራኤልን ሕዝብ ዓመፀኛነት በሚያመለክቱ አሳዛኝ ታሪኮች የተሞላ ነው። እግዚአብሔር የሚቀጥለው የእስራኤል ትውልድ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገባ ከመፍቀዱ በፊት፥ የመጀመሪያው ትውልድ በሙሉ በምድረ-በዳ እንዳለቀ የሚናገር ታሪክ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ የክርስትና ሕይወትህ ብዙ ጊዜ የኦሪት ዘኁልቁን ታሪክ የሚመስለው እንዴት ነው?

ኦሪት ዘዳግም፡- ኦሪት ዘዳግም በሲና ተራራ ለአይሁዳውያን የተሰጣቸው ሕግ በክለሳ መልክ የቀረበበት ነው። ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ለተዘጋጀው ለአዲሱ ትውልድ ሕጉን ደግሞ ተናገረ። ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ ካልታዘዙና እግዚአብሔርን ካላወቁት፥ እግዚአብሔር እንደሚቀጣቸውና የገባላቸውን የተስፋ ቃል እንደሚያጡ ሙሴ ያውቅ ስለነበር የእግዚአብሔርን ሕግ ማወቃቸውን ለማረጋገጥ ፈለገ።

የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያኖችም እግዚአብሔርን ካልታዘዙ በረከትን ሊያጡ የሚችሉት እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: